Saturday, 30 April 2022 12:51

ሁሉም ወገኖች ግጭት ከሚያባብስ ተግባር እንዲቆጠቡ መንግስት አስጠነቀቀ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(4 votes)

  • በግጭቱ እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩ 370 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል
     • የጎንደር ከተማን ግጭት ተከትሎ በሌሎች አካባቢዎች በሚገኙ የሃይማኖት ተቋማት ላይ ውድመት ደርሷል
     • በአዲስ አበባ አንዋር መስጊድ የጎንደሩን ግጭት የሚቃወም ሰልፍ ተካሂዷል
     • ከተቃዋሚ ፓርቲዎች እስከ የሃይማኖት ተቋማትና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ድረስ ድርጊቱን አውግዘዋል

             ሰሞኑን በጎንደር ከተማ የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ፣ በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጸሙ ያሉትን ግጭት አባባሽ ድርጊቶች እንደማይታገስና በአጥፊዎቹ ላይ ጥብቅ እርምጃ እንደሚወስድ መንግስት አስጠንቅቋል። ወንጀልን በወንጀል ለማካካስ የሚደረግ ማንኛውም ጥረት፣ ከወንጀል ፈጻሚነት ተለይቶ እንደማይታይም  የፌደራል የደህንነትና የፀጥታ የጋራ ግብረ ሃይል ገልጿል። በግጭቱ እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩ 370 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ታውቋል፡፡
ማክሰኞ ሚያዚያ 18 ቀን 2014 ዓ.ም በጎንደር ከተማ ውስጥ ነዋሪ የነበሩ ሼህ ከማል ለጋስ የተባሉ ግለሰብ የቀብር ስነ-ስርዓት፣ ለማስፈጸም በተለምዶ አዲስ አለም የሙስሊሞች መካነ መቃብር  በተሰባሰቡ የእምነቱ ተከታዮችና በመካነ መቃብሩ አዋሳኝ ላይ በሚገኘው የአበራ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን በነበሩ የክርስትና እምነት ተከታይ ወገኖች መካከል በተነሳ አለመግባባት የተቀሰቀሰውን ግጭት ተባብሶ፣ ሃያ የሚደርሱ ዜጎችን ለሞት የዳረገ ሲሆን በርካታ ንብረት እንዲወድም ምክንያት መሆኑን የአማራ ክልል እስልምና ምክር ቤት አስታውቋል። ግጭቱ እንዲስፋፋ በሚፈልጉ ወገኖች እየተባባሰ የሄደው የጎንደር ከተማው ግጭት በደባርቅና ወራቤ ከተሞች ላይም የከፋ ጉዳት አድርሷል ተብሏል።
በጎንደር ከተማ በተቀሰቀሰው ግጭት ሳቢያ የሁለቱም ሃይማኖት ተከታይ የሆኑ 20 የሚደርሱ ሰዎች መሞታቸውንና ከ160 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን ምንጮች ጠቁመዋል።
ግጭቱ በተቀሰቀሰበት አዲስ አለም የሙስሊም መካነ መቃር አጠገብ በሚገኘው የአበራ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን መካከል ቀደም ሲል  የይዞታ ይገባኛል ክርክር እንደነበር የሚገልጹት ምንጮች፤ በለቱም የቀብር ስርዓቱ ሊፈጸም ከታሰበበት ሰዓት ቀደም ብሎ አለመግባባት እንደተጀመረና ቀስ በቀስም ሁኔታው እየተባባሰ ሄዶ ግጭቱ መነሳቱን ጠቁመዋል።
“ችግሩ ለከፋ ጉዳት ሊዳርግ የሚችል አልነበረም። ተራ አለመግባባት ነው። ከሁለቱም ወገኖች አስተዋይና ግጭት እንዳይፈጠር የሚፈልጉ አባቶች ቢኖሩ ኖሮ፣ ሁለቱንም ወገኖች በማስማማትና ሁኔታው በሰላም እንዲፈታ በማድረግ ችግሩን ለማስቀረት ይችሉ ነበር።” ብለዋል የዓይን እማኞች።
“ነገር ግን ከሁለቱም ወገን ይህንን ከማድረግ ይልቅ ´እኛ´ እና ´እነሱ´ እያሉ ችግሩ እንዲባባስ የሚያደርጉ ሰዎች ስለበዙ ተራው አለመግባባት ለዚህ ደረጃ ደርሶ የሰው ህይወት ከመጥፋቱም ባሻገር፣ ከአካባቢው በራቁና ስለጉዳቱ ምንም በማያውቁ ሰዎች መካከል ግጭት እንዲቀሰቀስ በማድረግ የሃይማኖት ተቋማት እንዲወድሙና ንብረት እንዲጠፋ ምክንያት ሆኗል ብለዋል-ምንጮች። “ይህ ሁኔታ አሁንም ሃይ ባይ ካላገኘና ከሁለቱም ወገኖች በኩል ችግሩን ለማብረድ የሚችሉ አባቶች ወጥተው ነገሩን ካላስተካከሉት የከፋ ጉዳት ማድረሱ አይቀሬ ነው”  ብለዋል።  የአካባቢው ነዋሪዎች ስጋታቸውን ገልጸዋል።
እንዲህ አይነት የሃይማኖት ግጭት በከተማችን ተከስቶ አያውቅም የሚሉት ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የጎንደር ከተማ ነዋሪ ችግሩን፤ ያባባሱት ሆነ ብለው ከተማዋን ለመረበሽና ግጭት ለመፍጠር የተዘጋጁ ወገኖች ናቸው ብለዋል። “በዕለቱ የቀብር ስነስርዓታቸው ሊፈጸም የነበረው አባት በከተማችን ትልቅና የሚከበሩ አባት ሲሆኑ በአገር በቀል የህክምና ዘርፍ ለከተማው ህዝብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ አባት ነበሩ። እኔ የክርስትና እምነት ተከታይ ብሆንም፣ እኚህን ታላቅ አባት በክብር ለማሳረፍና በቀብር ስነስርዓታቸው ላይ ለመገኘት ወደ ቦታው ሄጄ ነበር። እኔን የመሰሉ በርካታ የክርስቲያን ወንድሞቼም በቀብር ስፍራው ሄደዋል።
“ግጭቱ በክርስቲያኖችና በሙስሊም ወገኖች መካከል የተፈጠረ ትልቅ ችግር አድርገው ያባባሱት ቀደም ሲል እደገለጽኩት፣ ከግጭቱ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የፈለጉ ወገኖች ናቸው። እነዚህ ወገኖች በሰዎች ደምና ህይወት እየቆመሩ እስከመቼ እንደሚዘልቁ አይገባኝም” ሲሉም ጠይቀዋል።
በከተማዋ የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ፣ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች እየተቀሰቀሱና የሃይማኖት ተቋማት ላይ ጥቃት እየደረሰ ሲሆን መንግስት ይህንን እንደማይታገስ በመግለጽ፣ ሁሉም ወገኖች ግጭት ከሚያባብሱ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ አስጠንቅቋል። ጥፋትን በሌላ ጥፋት ለማካካስ የሚደረግ ማንኛውም ጥረት ከወንጀል ፈጻሚነት ተለይቶ እንደማታይም ያስገነዘበው መንግስት፤ ሁሉም ወገን ከአፍራሽ ድርጊት ሊታቀብ ይገባል ብሏል።
የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገስ ቱሉ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ በደረሰው ጉዳት እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ትናንት ባወጣው መግለጫ፤ ሃይማኖትን ሽፋን አድርገው የሚነሱ ግጭቶች በቂ ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አሳስቧል። የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ለችግሩ የሰጠው ፈጣን ምለሽ አለመኖሩን ያመለከተው የጉባኤው መግለጫ መንግስት እንደ መንግስት ችግሩ ከቁጥጥር ውጪ ከመሆኑ በፊት  የመፍታት ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ብሏል። መንግስት የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች የማህረሰብ አንቂዎች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማህበራትና ህብረተሰቡ ከቅርብ ጊዜ  ወዲህ በሃይማኖት ሽፋን እየተነሱ ያሉ ግጭቶችንና እያደረሱ ያሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን በመፍታቱ ረገድ የበኩላቸውን እንዲወጡ ኢሰመጉ ጥሪ አቅርቧል።
ከሰሞኑ በጎንደር ከተማ የተቀሰቀሰውን የግጭት ከተቃዋሚ ፓርቲዎች እስከ የሃይማኖት ተቋማትና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ድረስ ክፉኛ አውግዘውታል። የአማራ  ክልላዊ አስተዳደር፣ የአማራ ክልል የእስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፣ ኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና ባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ድርጊቱን አውግዘው መግለጫ አውጥተዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር ኢድሪስ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጡት መግለጫ፤ “በጎንደር በተፈጠረው ችግር የሰው ሕይወት እስከሚጠፋ፣ የእምነት ቦታ እስከሚወድምና ንብረት እስከሚቃጠል ድረስ የአካባቢው አስተዳደርና የክልሉ መንግስት የጸጥታ አካላት ተግባራቸውን አልተወጡም” ሲሉ ወቅሰዋል። “ኃላፊነት ላይ ያሉ ሰዎች ከላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ችግሩ እልባት እንዲያገኝ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን” ብለዋል።
“በክልሉ ያሉ ሁሉም የመንግስት ኃላፊዎች፣ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ክልሉ አስተዳደር ድረስ መጀመሪያ ችግሩ ሲፈጠር ማስቆም እየቻሉ ኃላፊነታቸውን ባለመወጣት አላስቆሙትም ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።
“ማንኛውም ሃይማኖት ተገዳደሉ፣ እርስ በርሳችሁ ተጣሉ፣ የንፁሃንን ደም አፍስሱ አይልም። ተከባበሩ፣ ተዋደዱ፣ ተመካከሩ ተረዳዱ ነው የሚለው። የሃይማኖት መሪዎችም እንደ ሃይማኖት አባትነታችን ህዝቡን ስለ ሰላም ማስተማር ይኖርብናል” ብለዋል ሀጂ ሙፍቲ መግለጫቸው።
ኢዜማ ድርጊቱን አውግዞ ባወጣው መግለጫ፤ “ሀገር የሁላችን ናት። ኢትዮጵያውያን ያለምንም ቅድመ ሁኔታና ከልካይ ምክንያት በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች መብታቸው ተከብሮ ሊኖሩ ይገባል። ነገር ግን ኢትዮጵያ አሁንም ክቡሩ የሰው ህይወት እንደ ዘበት የሚቀጠፍባት ሀገር እንደሆነች ቀጥላለች ብሏል።
መንግስት ጉዳዩን በፍጥነት አጣርቶ አጥፊዎቹን ለፍርድ እንዲያቀርብና ችግሩ እንዳይስፋፋና የበለጠ ችግር እንዳያመጣ ሊቆጣጠር ይገባል ብሏል- በመግለጫው።
ባልደራስ በበኩሉ ባወጣው መግለጫ፤ የችግሩ መነሻ ምንም ይሁን ምን የተፈጸመው ነገር በፍጹም ሊወገዝ የሚገባው እንደሆነ አመልክቶ፤ ግጭቱ እንዳይስፋፋና የፀረ ኢትዮጵያ ሃይሎች መጠቀሚያ እንዳይሆን የሚመለከታቸው የክልሉ የፍትህ አካላት፣ የእምነት አባቶችና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች በሙሉ በአስቸኳይ የከተማውን ጸጥታ ለማስከበር መረባረብ አለባቸው ብሏል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ድርጊቱን ባወገዘበት መግለጫው፤ የክልሉ ህዝብ የሃይማኖት አጥር ሳይገድበው ተዋልዶ፣ ተጋብቶና ተዋዶ የኖረ ህዝብ መሆኑን ጠቁሞ፤ ይህን የሕዝቡን ሰላማዊና ታሪካዊ መስተጋብር የማይፈልጉ ውጫዊ ሃይሎች ችግሮችን በማጋጋል ሃይማኖትን ሰበብ ያደረጉ ግጭችን ለመፍጠር እንቅስቃሴ እንደሚያደርጉ ተገንዝበን- አላማቸው እንዳይሳካ ሁላችንም የበኩላችንን ጥረት ልናደርግ ይገባል ብሏል።
“ማንኛውንም ችግር በሃይማኖት አባቶችና በአማራ የሽምግልና  ባህል መሰረት የመቅረፍ የኖረ ባህልን አጠናክረህ እንድትቀጥል” ሲልም ፓርቲው ጥሪ አስተላልፈዋል።
በጎንደር ከተማ የተፈጠረውን ግጭት ተከትሎ፣ በአንዳንድ አካባቢዎችም ግጭቶች የተከሰቱ ሲሆን ከትላንት በስቲያ በስልጤ ዞን በሚገኙ የወራቤ ቅዱስ ሩፋኤል እና በሳንኩራ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስያናት ላይ ጥቃት  መፈጸሙ ተገልጿል።
ሁኔታው እየተባባሰ እንዳይድና በሌሎችም አካባቢዎች እንዳይስፋፋ ለማድረግ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ጥረት ማድረግ ይባቸዋል ተብሏል።
በጎንደር ከተማ በተቀሰቀሰው ግጭት ሳቢያ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች የቀብር ስነ-ስርዓት መፈጸሙንም የአካባቢው ምንጮቻችን ጠቁመዋል።
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጉዳዩን በትዊተር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ “ማንንም ለማጥፋት ኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረግ ጥቃት በሁላችን ላይ የሚደረግ ነው። አጥፊውን አውግዘን ከተጠቂው ጋር እንቆማን እንጂ ጥፋቱን በሌላ ጥቃት ለማባባስ መሞከር የለብንም” ብለዋል።


Read 11607 times Last modified on Saturday, 30 April 2022 13:24