Saturday, 30 April 2022 14:39

ጥበበኛ ጓዘ ቀላል ነው!

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(1 Vote)

     ቁም
ጥበበኛ ጓዙን ይጥል ዘንድ ተደንግጓል። ጓዙን  ሊጥል ሲሰናዳ፣ ቅጥ ያጣውን ግርግር በአርምሞ ይገረምማል፡፡  ከመንጋው በመነጠል፣ ሀሞቱን ኮስተር አድርጎ ምናቡን ይሰነዝራል፡፡ የጉዞው መዳረሻ አድማስ ነው። ሲጠጉት የሚሸሽ፡፡ ጥበበኛ ነገ አስጨንቆት አያውቅም፡፡ ግጥሙ ከዛሬ ጸሐይ ጋር ነው። ይኽንን የባለቅኔውን እንጉርጉሮ እያነከትክ ተከተለኝ፤
ከሰው መንጋ እንነጠል፣
ለአንድ አፍታ እንኳን እንገለል፣
በእፎይታ ጥላ እንጠለል፣
ዝም ብለን አብረን ዝም እንበል፣
(ፀ.ገ)
የጥበብ ካራማ
የጥበብ ካራማ ደርሳ ባገኘችው በድን ላይ አትሳፈርም፡፡ ሲበዛ መራጭ ናት፡፡ በዐይኗ የሚሞላ ጓዘ ቀላል ብጹዕ ሰብእናን ታማትራለች። ታጥቦ ታጥኖ ለሚጠብቃት ብእረኛ፣ ገመናዋን ትከፍታለች፡፡ ግብዙ ገላ፣ ቢሰባ ቢኮሰምን፤ ግጥሟ አይደለም፡፡ ልቧን የሚያሸፍታት የፋፋ ምናብ ነው፡፡
ሥራ-ፈት አእምሮ የካራማዋ ማደሪያ ነው። ናላ ሲሰንፍ ጥበብ በብርቱ ታንሰራራለች፡፡ የምናብ ሐድራ ሲጫጫስ፣ ሁሉም ነገር ጥረት አልባ ሆኖ ይከወናል፡፡ ሂንዱዎች “be  like  a hollow bamboo” የሚሉት ለዚህም ሳይሆን አይቀርም፡፡
ቀርከሃ ጥዑም ዜማ ያፈልቅ ዘንድ፤ ውስጡ ኦና መሆን አለበት፡፡ ኦና ሲሆን ዜመኛው እስትንፋሱን ለማንሸራሸር እክል አይገጥመውም፡፡ እስትንፋሱን በቀርከሃው ሆድ ዕቃ ሲያንጀረጀርው፤ ለጆሮ የሚጥም ዜማ በእዛው ልክ ይንቆረቆራል፡፡
ጥበበኛ እንደቀርከሃው ምናቡን ሲያራቁት፤ መጠበቡ እንደ መተንፈስ ይቀለዋል፡፡ ጥበብ ትምነሸነሽ ዘንድ የአእምሮ ጓዝ ከሥፍራው መፈናቀል ይኖርበታል። “በእብሪት መቀመቅ ከቃበዝክ፣ ዕድሜ ልክህን ብትማስን እንኳን፣ ወደ አንተ የምትቀርብ እግር የጣላት ጥበብ አትኖርም” የሚለው መርህ የጥበብ ቀኖና ነው፡፡
ከስምህ ፊት እንደ ኒሻን የተደረደሩት ተቀጥላዎች፣ የጥበብን ልብ ያሞቃል ብለህ ካሰብክ፣ ተላላ ነህ፡፡ ጥበበኛ አንዳንዴ  ከትውልዱ ጋር ባይገጥም አይግረምህ፡፡ የምናቡ አብራክ ፍሬ ከዘመኑ ቀድሞ ሊሄድ ይችላል፡፡ "አደፍርስ;ን የሚረዳ ትውልድ እስኪመጣ ስንት ክረምት አለፈ፤ ጎበዝ!
ጥበበኛ ግቡ የውስጡን ቅታቴ ለዐይነ ሥጋ ማብቃት ነው፡፡ ለአደባባይ ሙገሳ አይባትትም። ትርፍ፣ ኪሳራ ላይ ዳተኛ ነው፡፡ ጭብጨባ፣ አጀብ ከያዘው የምናኔ ጉዞ አያደነቃቅፈውም፡፡
የጥበብ ሥር ቁማርተኞች
የጥበብ ሥር ቁማርተኞች በሰው ሰራሽ አበባ ይመሰላሉ፡፡ ከዐይን ሲርቁ የለመለሙ ይመስላሉ፡፡  ነውራቸውን  ለመቃረም ብዙም መድከም አይጠበቅብህም፡፡ ጥቂት ጋት ቀረብ ብለህ ሰልላቸው፡፡ በዚህን ጊዜ፣ ዋጋ እንደመታው ሰብል ከፍሬ መራቆታቸው ገሀድ ይሆንልሃል፡፡
ጥበብ አሻሻጮች ልክ እንደ ግሪክ  ሶፊስቶች ናቸው፡፡ ሽንፈት ይመራቸዋል። እውነትን ሰውተው ኒሻንን ቢሸለሙ ይመርጣሉ፡፡  
የአደባባይ ድግስ ያለ እነርሱ አይደምቅም። የደመነፍስ ባለሟልነታቸውን ተመክተው ብእር ሲያነሱ፤ ለመንጋው ስሜት አብዝተው እየቃበዙ ነው፡፡ እንደ ፈሪሳዊያን እብሪት ጌጣቸው ነው፤ ምድር ያፈራችውን ማእረግ በሙሉ ብታሸክማቸው ከአንጀታቸው አይደርስም፡፡
የጥበብ ቁማርተኞች ምናብ አይረጋም፤ በየአፍታው ሾተላይ ይመተዋል፤ ሥንዝር በተራመዱ ቁጥር እንደ ሎጥ ሚስት ኋላቸውን ይሰልላሉ፡፡ እነርሱ በጥበብ ፊት እስትንፋሳቸውን የተነጠቁ፣ የጨው አምድ ናቸው፡፡
ታዋቂው ጣሊያናዊ ጥበበኛ ማይክል አንጅሎ፣ ያነጸውን ግሩም ሀውልት፣ አንድ ክልፍልፍ ወፈፌ ዶግ አመድ ለማድረግ ቅጽበት ነበር የወሰደበት፡፡ ወፈፌው ይህን ለምን እንደ አደረገ ሲጠየቅ፤
”ከዚህ ቀደም የተቀኘኋቸውን ግጥሞች የሕትመት ብርሃን ሊለግሳቸው የፈቀደ አንድም አካል አላጋጠመኝም፡፡ ጭራሽ ከእነ መፈጠሬም ነበር የተዘነጋሁት፡፡ አሁን ግን ይኸው ይህንን ሀውልት በማፍረሴ፣ የሀገር ምድሩ መነጋገሪያ ሆንኩኝ፤ ጋዜጦች፣ መጽሔቶች የእኔን ፎቶ ከፊት ገጻቸው ላይ ለመለጠፍ ተሽቀዳደሙ፡፡” ብሎ አረፈ፡፡
የቁማርተኞቹ ግብር፣ ከወፈፌው ጋር ኩታ-ገጠም ነው፡፡ መዳፋቸው ጥበብን አፈር ድሜ የሚያበላ መዶሻ እንጂ፤ ነፍስን የሚያለመልም ብዕር አልጨበጠም። አሻሻጮቹን ፊት የሚነሳ ትውልድ ካልተፈጠረ፣ ክሽፈት ቀኖና ሆኖ ይቀጥላል። ሴራ ጥሎ ማለፍ ያሾማል፤ ያሸልማል፡፡ በዚህም የጥበብ አድባር ቅያሜ ገብቷት፣ ገመናዋን ሸሽጋ፣ ከነፍስ ጋር ዐይንና ናጫ ሆና ትኖራለች፡፡
መቋጫ
 በሁለት ገሀነሞች መካከል ገነት አለ፤ ይላሉ የሩቅ ምሥራቅ አበው፡፡ ሁለት የገሀነም ጠርዞች ላይ እልፍ አእላፍ ጓዝ ተከምሯል፡፡ አፍቅሮተ ነዋይ፣ አድርባይነት፣ ግብዝነት፣ እብሪት፣ ዝና ያረከሰው  ማንነት፣ ሂሳብ እያሰላ የሚራመድ ክሽፍ ሰብእና…. ትከሻ የሚያጎብጡ ሸክሞች ናቸው፡፡
ይኽን ሁሉ ጓዝ ተሸክመህ ወደ ጥበብ ለመቅረብ ከሞከርክ፤ ቅዱሱን ሥፍራ በጫማህ እንዳረከስክ ይቆጠራል፡፡ የጥበብ ሥፍራው ጓዝ አልባው ወርቃማው አማካዩ ነው፡፡ በአንዱ ገሀነም ጫፍ ትዕቢት ቢሰየም፤ በሌላው ገሀነም ጫፍ አሽከርነት ይኖራል፡፡ አማካዩ፣ ወርቃማው ሰብእና ትህትና ነው። ይህንን ትሁት ሰው፣ ጓዝ አልባውን፤ጥበብ በብርቱ ብትከጅለው ሊደንቀህ አይገባም፡፡


Read 1585 times