Saturday, 07 May 2022 13:55

“አንቺን ደግሞ ምን አደረጉሽ?”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(0 votes)

  እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሀ፡- ሥራ እንዴት ነው፡፡
ለ፡- እሱን ተዪኝ እባክሽ፡፡ ይልቅ ሌላ፣ ሌላ ነገር እናውራ፡፡
ሀ፡- ምንም ሌላ ብሎ ነገር የለም፡፡ ሥራ ቦታሽ አንቺን ደግሞ ምን አድርገውሽ ነው እንዲህ የሚያነጫንጭሽ? (አጠያየቋን አያችሁልኝ! ጓደኛዋ ሥራ ቦታ ላይ የሆነ ነገር እንደገጠማት እርግጠኛ ነች፡፡ የችግሩን አይነት ብቻ ነው ማወቅ የምትፈልገው። ጊዜው ነዋ! ይሄ ተደነጋግሮ እያደነጋገረን ያለ ጊዜ ነዋ! የቅርብ ሰዋችን ገጽታው...አለ አይደል... የነሀሴ ደመናን መስሎ ስናየው፣ ጥያቄያችን እንደ ወትሮው “አሞሀል እንዴ?” ምናምን አይነት ሳይሆን “እንዲህ ቅዝዝ ያልከው ምን ገጥሞህ ነው?” አይነት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር “ደግሞ አንተን ምን አደረጉህ?” እንደማለት፡፡)
ለ፡- ብለፈልፍ፣ ስጮህ ብውል የእኔ ጨጓራ ጭራሽኑ ወንፊት ይሆናል እንጂ አንቺ ምን ያደርግልሻል?
ሀ፡- ሁሉም ነገር ያደርግልኛል፣ ለምን አያደርግልኝም! አንዲትም ነገር ሳይቀር ማወቅ አለብኝ፡፡ ነገ ትንሽ ነካ አድርጎሽ በየመንገዱ መዘባረቅ ስትጀምሪ “ምን ሆና ነው?” “ይቺን የመሰለች ልጅ ማን መድሀኒት አቅምሷት ይሆን?” ሲባል ምን እንደሆንሽ የሚያብራራ ሰው ያስፈልጋላ!
ለ፡- አንቺ ምን ታደርጊ የደላሽ፡፡ ውይ! ውይ! ውይ! በእናትሽ እንደው እንዴት አድርጌ ነው ከዚህ መሥሪያ ቤት ንቅል ብዬ የምወጣው!
ሀ፡- እስከዚህ ድረስ አማረውሻል ማለት ነው?
ለ፡- የሚገርምሽ’ኮ አዳዲስ ከሚሾመው አንዳንዱ መሥሪያ ቤት ሊመራ ይምጣ፣ እነሱን ጨርቃቸውን እስኪጥሉ ድረስ  አሳብዳቸው ተብሎ ይምጣ ግራ ግብት ነው የሚልሽ፡፡ ደግሞልሽ የመጣው ሁሉ ገና የተቀመጠበት ወንበር ሞቅ ሳይል የራሱን ዘመድ አዝማድ፣ የሀገር ልጅ የሚለውን እየሰበሰበ እዚህም ቡድን፣ እዛም ቡድን...እኛ ለእለት እንጀራ የገባነው፣ ቡድን የሌለንና የማንፈለግ ምስኪኖች ፍጥጥ!
ሀ፡- አገላለጽሽ የደራሲ ነፍስ እንዳለሽ የሚያሳይ...
ለ፡- እንግዲህ ጀመረሽ...
ሀ፡- እሺ! እሺ! ተረጋጊ!
እናላችሁ... ዘንድሮ “ሥራ እንዴት ነው?” “የሥራ ቦታ እንዴት ነው?” ምናምን ስንባባል የምናወራው ስለደሞዝ ጭማሪ፣ ስለሚጢጢዬዋ እርከን፣ ከምክትል ወደ ዋና ስለመሸጋገር መሆኑ እየቀረ ነው፡፡ ስለ ሥራ ወይም ስለ ሥራ ቦታ ስንጠያየቅ በአጭሩ “ሁሉም ነገር ሰላም ነው ወይ?”  “እስካሁን ምንም አልደረሰብሽም/ህም?; ማለት ነው። እኔ የምለው ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...እንዴት ነው ብዙ ነገሮች በአጭር ጊዜ እንዲህ ደስ የማይሉበትና የማይመቹበት ደረጃ የደረሱት አያስብላችሁም?
አንድ ሰሞን “ከእንግዲህ ሻማ ለልደት ብቻ ነው፣” ነገር ስንባል እውነት መስሎን ነበር... ሲያምራችሁ ይቅር አይነት ነገር ሆነብን እንጂ!
20/80፣ 40/60 ባለ አንድ መኝታ፣ ባለ ሦስት መኝታ፣ ስቱድዮ ምናምን ሲባል ህዝቤ በሦስትና ሦስት ዓመታት ውስጥ የቤት ችግር ደህና ሁን የሚባል መስሎት ነበር... “ሲያምርህ ይቅር!” ሆኖበት ቀረ እንጂ፡፡
የሪል ስቴት የዋጋውን ሠላሳ፣ አርባ በመቶ ከከፈልክ ቤትህ በዓመት፣ በዓመት ተኩል ያልቅልሀል ሲባል እውነት ሁሉም ቃላቸውን ይጠብቃሉ መስሎት “እህ!” ብሎ አምጦ ያጠራቀማትን ፍራንክ መስጠት.... “ሲያምርህ ይቅር!” ሆኖበት ቀረ እንጂ፡፡
ስሙኝማ...ጨዋታም አይደል... አንድ ሰሞን አንዳንዶቻችን የ“አይቅርብን፣” አይነት ‘ፈረንጅ፣ ፈረንጅ’ ነገር አሰኝቶን ነበር እኮ፣ “አይ ፔይ ማይ ታክስስ...; ማለት ጀማምሮን፡፡ “ታክሴን እስከከፈልኩ ድረስ አገልግሎት ማግኘት ችሮታ ሳይሆን መብቴ ነው፣” አይነት ነገር እዚህም እዛም ብልጭ ብላ ነበር፡፡ የምር ግን እሷ ነገር ከመቼው እንደተሰወረች አይገርማችሁም! እናላችሁ...ለምሳሌ የሆነ አገልግሎት መስጫ ገብታችሁ ያው እዚህ ሀገር ባህልም፣ ልምድም እንደሆነው ሲያጉላሏችሁ፤ “እዚህ ተቀምጣችሁ ደሞዝ የምትነጩት እኮ እኔ በምከፍለው ታክስ ነው፣” አይነት መብት ጥየቃ ብትጀምሩ... አለ አይደል...ሰበር ዜና ይሆናል፡፡ ልክ ነዋ... አንደኛ ነገር “ፍሬንድስ እየሰማችሁ ነው፣ ፈረንጅ የሚያደርገው ሀበሻ መጥቶላችኋል፣” እያሉ ‘በታክሳችሁ ደሞዝ የሚነጩት አገልጋዮች በወጣቶቹ አነጋገር ‘ሙድ’ ይይዙባችኋል። ወይ ደግሞ አዛኝ የሆኑ ሴቶች ደንግጠው “ኸረ እናንተ ሰውየው አሞት ሳይሆን አይቀርም! ሳይብስበት አምቡላንስ ይጠራ እንጂ!” ሊሉ ይችላሉ! እንደውም በወሬ፣ ወሬ እንደምንሰማው አንዳንድ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች መጉላላት ሲደርስባችሁ “ሄጄ ለበላይ አካል አሳውቃለሁ፣” ስትሉ ምን ይሆናል አሉ መሰላችሁ... መጀመሪያ ይሳቅባችኋል አሉ፡፡ (ሚስተር ቢን በሙያዬ ገቡ ብሎ እንዳይቆጣ ለማብራራት ያህል...ሳቁ እናንተ እንደ ኮሜዲያን አሳቃችኋቸው ማለት ሳይሆን፣ እንደሚሳቅበት እንደ ቶም ኤንድ ጄሪ አይነት ነገር እናንተ ላይ ሳቁባችሁ ለማለት ነው፡፡ አንዲት ጠንከር ያለ ነፋስ ቢያገኛት ‘ጧ’ የምትል የምትመስል ክር መዝዞ፣ ኑ ካምፕን የሚያክል የነገር ጨርቅ የሚተበተብበት ሀገርና ዘመን ስለሆነ ነው!) ቀጥሎ ደግሞ ምን ይከተላል...የሆነ ስም ይጠሩና፤ “ከፈለግህ ሄደህ ለምን ለእንትና አትነግረውም!” ይባላል አሉ፡፡ እናም እኛ ምስኪኖች እነኚህ የሠማይ ስባሪ የሚያካክሉ ባለወንበሮች ላይ እንዲህ ደፍሮ በአደባባይ ከፎከረ ሰው አለው ማለት ነው እንልና፣ የሀሪ ኬን ሽያጭ ነገር ምን እንደደረሰ ለማወቅ ኢንተርኔት ካፌ እንሄዳለን፡፡
እኔ የምለው... ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ... በቀደም አርሴ ማንቼን ሲያሸንፈው ከተማችን አንዳንድ ቦታዎች ላይ በፊት ጊዜ እንደነበረው ‘ፍስፍስ’ ቢጤ ሊጀመር ዳር ዳር ሲባል ነበር አሉ፡፡  ታጥቦ ምናምን እንደሚባለው ተመልሶ እዛው!
እናላችሁ... ጥቂት በማይባሉ የሥራ ቦታዎች በትንሽ ትልቁ የሥራ መንፈስ እየተበላሸ ነው ይባላል፡፡ የምር እኮ...አለ አይደል... እዚህ ሀገር ነገር እየተቆፈረ አንዱ አንዱን ለማሳጣት መከራውን እንደሚበላው፣ ያኛው ወገንም እኮ በምላሹ ነገር ልምዘዝ ቢል ትርክቱ በሙሉ በአፍ ጢሙ ይደፋ ነበር፡፡
ሚስት ሆዬ አንድ እለት የሆነ ነገር በይ፣ በይ ይላትና ትጠይቀዋለች፡፡
“እኔን ከማግባትህ በፊት ገርልፍሬንዶች ነበሩህ እንዴ?”
(ምን የሚሉት ጥያቄ ነው! አሁን እሷስ ብትሆን ያለ ‘ኤክስፒሪየንስ’ ድጋፍ በባዶ ሜዳ የተገኘች መሰላት እንዴ! ቂ...ቂ...ቂ...)
አቶ ባል ሆዬ፤ አንዲትም ነገር ሳይል በተቀመጠበት ይቆያል፡፡ ሚስት እንደገና ትጠይቃለች...
“ምን ይዘጋሀል፣ አትመልስልኝም እንዴ?”  እናማ፣ መልስ ይሰጣል...
“ምን ያጣድፍሻል፣ ረጋ በያ!”
“አሁን ይቺን ለመመለስ ይህን ሁሉ ጊዜ ይወስዳል?”
ምን ቢላት ጥሩ ነው...
“ምናለበት ቆጥሬ እስክጨርስ ብትጠብቂኝ?” ‘እርፍ በይ!’ የሚባለው በዚህ ጊዜ ነው፣ አይደል?
ጉድ እኮ ነው...ሰው ከዓመት ዓመት ስለትላንትናና ስለትላንት ወዲያ እየተጨቃጨቀና እየተናቆረ ይኖራል! ያውም አብዛኞቻችን ለራሳችን እንደሚመቸን አድርገን በምንፈጥረው ታሪክ!
ለክፉም ለደጉም ይቺን ቀልድ ስሙና ትንሽ ዘና በሉማ...ታካሚ ከአእምሮ ሀኪሙ ጋር እየተነጋገረ ነው፡፡
ሀኪም፡- በእውነቱ ደስተኛ ልትሆን ይገባል፡፡
ታካሚ፡- ዶክተር ምን ሆንኩ ብዬ ነው ደስ የሚለኝ?
ሀኪም፡- ፈጣን መሻሻል እያሳየህ ነዋ! አስተሳሰብህ ሁሉ እየተሻሻለ ነው፡፡
ታካሚ፡- ዶክተር እንደእኔ ከሆነ ምንም መሻሻል የለብኝም፡፡ እንደውም ብሶብኛል፡፡
ሀኪም፡- እንዴት እንዲህ ልትል ቻልክ?
ታካሚ፡- ዶክተር ከስድስት ወር በፊት አንተ ዘንድ ስመጣ ናፖሌኦን እንደሆንኩ ነበር የሚሰማኝ፡፡ አሁን ግን ምንም ያልሆንኩ ተራ ሰው ነኝ፡፡
በነገራችን ላይ እንደ ናፖሌኦንነት የሚሰማችሁ ወገኖች ካላችሁ...ይቅርባችሁ። አይ...ሌላ ሳይሆን የአቅማችንን እንበል ብለን ነው፡፡ ምንም ያልሆነ ተራ ሰውነት ስሜት ሊሰማችሁ ሲጀምር የአእምሮ ጫናውን አትችሉትም፡፡
“አንቺን ደግሞ ምን አደረጉሽ?” “አንተን ደግሞ ምን አደረጉህ?” ከምናባባልበት ዘመን በፍጥነት ያውጣንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 635 times