Saturday, 07 May 2022 14:12

ዩክሬን ከጦርነቱ ወዲህ 4.5 ቢ. ዶላር ድጋፍ አግኝታለች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   ጦርነቱ 3ሺህ 153 ንጹሃን ዩክሬናውያንን ለሞት ዳርጓል ተብሏል

               ከሩስያ ጋር ጦርነት ውስጥ ከገባች ከ70 ቀናት በላይ ያስቆጠረችው ዩክሬን፤ ከጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ ከአለማቀፉ ህብረተሰብ በጥሬ ገንዘብ ብቻ 4.5 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ድጋፍ ማግኘቷ ተነግሯል፡፡
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴኒስ ሻምያልን ጠቅሶ ቢዝነስ ስታንዳርድ እንደዘገበው፣ አለማቀፉ ማህበረሰብ ለዩክሬን ያሳየው ድጋፍ ትልቅ ትርጉም ያለውና ምስጋና የሚቸረው ነው፡፡ የገንዘብ ድጋፉ የተሟላ የማህበራዊ ዋስትና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አገሪቱ ሌሎች አዳዲስ የድጋፍ አገልግሎት ፕሮግራሞችን ለመጀመር ማቀዷንም ተናግረዋል፡፡
የአገሪቱ መንግስት ለድህረ ግጭት የመልሶ ግንባታ ስራዎች የሚውል ገንዘብ የማሰባሰቢያ መድረክ መፍጠሩን እንደገለጹ የጠቆመው ዘገባው፣ ዩክሬን ባለፈው ሳምንት ብቻ ከአለም ባንክ የ500 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ማግኘቷንም አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ ለሞት የተዳረጉት ንጹሃን ዩክሬናውያን ቁጥር 3ሺህ 153 መድረሱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ከሰሞኑ አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ ባለፈው ሰኞ ባወጣው መረጃ እንዳለው፣ በዩክሬን ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ለሞት ከተዳረጉት 3ሺህ 315 ሰዎች መካከል 722 ያህሉ ሴቶች ሲሆኑ 154 ያህሉ ደግሞ ህጻናትና ልጃገረዶች ናቸው፡፡
በአገሪቱ በጦርነቱ ሳቢያ ለሞት ከተዳረጉት ዜጎች በተጨማሪ 3 ሺህ 316 ንጹሃን ዜጎች ለመቁሰል አደጋ መጋለጣቸውንና ከእነዚህም ውስጥ 324 ሴቶች፣ 349 ያህሉ ደግሞ ልጃገረዶችና ህጻናት መሆናቸውን ለማረጋገጥ መቻሉንም የኮሚሽኑ ሪፖርት ያሳያል፡፡

Read 1799 times