Saturday, 07 May 2022 14:29

ሚያዝያ 27 እና እንግሊዞች

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(1 Vote)

      የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ለአምስት ዓመት መራራ ትግል አድርጎ በአርበኞች  ኃይል፣  በንጉሠ ነገሥቱ መሪነት፣ በእንግሊዞች ድጋፍ ወራሪውን የኢጣሊያንን ጦር አሸንፎ ነጻነቱን ያስከበረበትን፣ የሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ ም 81ኛ የድል ቀን እያከበርን  ነው፡፡
እንኳን  አደረሳችሁ፡፡
‹‹ንጉሠ ነገሥታችን በአገራችን  በኢትዮጵያ ላይ የፋሽሽት ጦር የሚፈጽመውን ግፍ ለዓለም መንግሥታት ማኅበር ለማመልከት ወደ አውሮፓ ሲሄዱ፣ እኛም አገልጋዮቻቼው አዲስ አበባን ለቀን በየጫካው በየገደሉ በመሰማራት ከጠላታችን ጋር ስንዋጋ አምስት አመት አሳልፈናል፡፡ ዛሬ የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆኖ፣ የወዳጅ አገር የእንግሊዝ መንግሥት እርዳታ ተጨምሮበት፣ ንጉሠ ነገሥታችን የነጻነትን ችቦ እያበሩ ወደ መናገሻ ከተማቸው እያመሩ፣ እኛ ተነጥለን እዚህ እንጦጦ እንድንቆይ የምንጠየቀውን አንቀበልም፡፡ አሁን የቆምነው ነጻ በሆነች አገራችን መሬት ላይ ነው፡፡ ዛሬም ለመጓዝ  የተዘጋጀነው ነጻ ወደ ሆነችው አዲስ አበባ ከተማችን ነው፡፡ ምን አልባት የአዲስ አበባ ጸጥታ አስግቷችሁ እንደሆን እኛ በቂ የሆነ የሰው ኃይል ስለአለን በቶሎ ደርሰን እንጋፈጥላችኋለን ከዚህ ሌላ ባታስቸግሩን ይሻላል፡፡ እኛ ውለታችሁን ማሰብ፣ እናንተም ምስጋናችሁን መቀበል የተገባ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ የምንጠይቃችሁ ነገር የለም››
ራስ አበበ አረጋይ
ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም፤ ለኮሎኔል ዊንጌት  የተናገሩት፤ እመለስበታለሁ፡፡
ሐምሌ 22 ቀን 1875 ዓ ም በሰሜን፣ጣሊያን ኮስታ በተባለ ወረዳ ከአናጺ ቤተሰብ የተወለደው ቬኒቶ አሜልካር አንድሬል መሶለኒ፣ መስከረም 20 ቀን 1915 ዓ ም በፋሽሽት ፓርቲ መሪነቱ  የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆነ፡፡ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ባገሩ ማምረት የቻለውን እያመረተ፣ ያልቻለውን የጦር መሳሪያ እየገዛ ኢትዮጵያን ለመውረር ተዘጋጀ፡፡ በይፋ በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ያወጀውና በሰሜን ግንባር ወረራ የጀመረው መስከረም 21 ቀን 1928 ዓ ም ነው፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ አጼ ኃይለ ሥላሴ መስከረም 22 ቀን 1928 ዓ ም የክተት አዋጅ አወጁ። ከመስከረም 25 ቀን ጀምሮ ያካባቢው ሕዝብ የመከላከል ጦርነት ሲያደርግ ቆየ። የመሀል አገሩ ጦር በቦታው ከደረሰ በኋላ በሽሬ ግንባር በራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ፣ በተምቤን ግንባር በራስ ካሳ ኃይሉና በራስ ሥዩም መንገሻ፣ በአምባራዶም በራስ ሙሉጌታ፣ በደቡብ በራስ ደስታ የሚመራው ጦር ከፍተኛ ተጋድሎ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
የመጨረሻው የመከላከል ጦርነት የተካሄደው መጋቢት 22 ቀን 1928 ዓ.ም ማይጨው ላይ ነው፡፡ ጦርነቱ  ሃምሳ አንድ ሺህ የሚሆን ሠራዊት የተሰለፈበት ነው። የደጀኑን ጦር ንጉሠ ነገሥቱ፣ የግራውን ራስ ጌታቸው፣ የመሐሉን ልዑል ራስ ካሣ፣ የቀኙን ልዑል ራስ ሥዩም መንገሻ እንዲመሩት ተደርጓል፡፡ ጦርነቱ ለሊት አስር ሰዓት ላይ የተጀመረ ሲሆን የኢትዮጵያ ጦር ከፍተኛ የማጥቃት ሥራ እየሠራ፣ በርካታ ምሽግ እያስለቀቀ ነበር፡፡ ጣሊያኖች የሚመኩበትን ፑስቴሪያ የተባለውን ጦራቸውን እያርበደበደውም  ነበር፡፡ ረፋድ ላይ ሰባ ቦምብ ጣይ አይሮፕላን አምጥተው  ቢደበድቡትም የሚበገርላቸው አልሆንም፡፡ አንደኛው በሌላኛው ሬሳ ላይ እየተረማመደ ወደ ምሽጋቸው እየገባ እያስጨነቃቸው ነበር፡፡ የክብር ዘበኛ ጦር የሠራውን የጀግንነት ሥራ፣ ጣሊያኖች ራሳቸው ‹‹ከጠዋቱ አምስት ሰዓት ላይ 10ኛው ባታሊዮን ባዶ በመሆኑ አዛዡ ሌተናል ኮለኔል ዙሬቲ ለጠቅላይ ሰፈሩ ከበድ የጠላት ኃይል ገጥሞናል፡፡ እኛ ያለንበትን አካባቢ በምደፍ ደብድቡልን” ሲል ጠየቀ። ይህን ባለ በጥቂት ደቂቃ ውስጥ እሱና ኮሎኔል ሬጄሮ ተገደሉ›› በማለት ሲመሰክሩ እናገኛቸዋለን፡፡
የጠላቱን የመሳሪያ የበላይነት ከምንም ሳይቆጥር ሕይወቱን ለሞት ሰጥቶ ወደፊት እያጠቃ፣ ለድል እየተቀረበ እያለ፣ ለጣሊያን ያደሩ የአካባቢው ሰዎች ጦሩን ከጀርባ ገብተው ወጉት፡፡ ከእጁ ሊያስገባው የነበረውን ድል አድረጊነት አስነጠቁት። ተሸናፊ እንደ አደረጉት አዶልፍ ፓርለሳክ “የአበሻ ጀብዱ” ተብሎ ወደ አማርኛ በተተረጎመው መጽሐፉ፣ በምሬት ገልጦአል። ጦርነቱ መጋቢት 23 ቀጥሎ ቢውልም የተገኘ ለውጥ አልነበረም፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ ተለምነው ከአካባቢው እንዲወጡ ተደረገ፡፡ የጦር መሪዎች እንደ ወልዲያ ባሉ ወታደራዊ ቦታዎችን ይዘው የመከለከሉን ጦርነት እንዲያደርጉ ንጉሡ ቢያዝዙም፣ የተተገበረ አልነበረም፡፡ መጋቢት 25 ቀን 1928 ዓ ም አንድ ስብሰባ ተደረገ፡፡ ጥያቄው እያፈገፈግን እንዋጋ ወይስ እንመለስ የሚል ነበር፡፡ በዘህ ስብሰባ ሻለቃ መስፍን ስለሺ፣ ልጅ ገሠሠ ጅማ፣ ደጃዝማች ወንድ ወስን ካሳና ሌሎችም ተገኝተዋል፡፡ እየተወጋን “እናፈግፍግ” የሚሉት አምስት ሲሆኑ ቀሪዎቹ “እንመልሰ” ሲሉ መወሰናቸውን “የማይጨው ዘመቻና የጉዞ ታሪክ” ጸሐፊ ገብረ ወልድ እንግዳ መዝግበውት ይገኛል፡፡
ተመላሹ ጦር ስርዓት ያለው የመልስ ጉዞ ለማድረግ አለመቻሉን  ደጃዝማች ከበደ ተሰማ የ“ታሪክ ማስታወሻ” በተበለው መጽሐፋቸቸው ሲገልፁ  ‹‹ከዚህ በኋላ ያው የተገኘው ጦርየባታዋዮን ዋሻ ለቆ መመለስ  ግድ ሆነበት፡፡ ፊቱን ወደ ኮረም አምርቶ ሌሊቱን ጉዞ ተጀመረ፡፡ ጠላት በሰላዮች ደርሶብት ኖሮ ለሊቱን ሲገሰግስ አድሮ አሼንጌ ላይ የደፈጣ አደጋ ጣለ፡፡ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር የነበረው ደፈጣውን ተከላክሎ ለማለፍ ሲታኮስ ነግቶ ነበርና የጠላት አይሮፕላን፣ ጦሩን አሼንጌ ሜዳ ላይ ፈጀው›› ብለዋል፡፡
ንጉሠ ነገሥቱ  በወረ ኢሉ፣ በለገ ሂዳ  አድርገው የጃማን ወንዝ በመሻግር ፍቼ ደረሱ፡፡ከፍቼ አዲስ አበባ ገቡ፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ በቆዩባቸው ቀናት ንጉሡ   ‹‹በዚያ አጣብቂኝ ውስጥ እያሉ አስደናቂ መረጋጋትና ልበ ሙሉነት አልተለያቸውም›› ሲል ጃፍ ፐርሰ ይገልፀዋል፡፡
ንጉሡ እንደተመለሱ በቤተ መንግሥት አንድ ስብሰባ ተደረገ፡፡ በሰብሰባው ላይ ጦር ሜዳ የነበሩትም ከተማ ሲጠብቁ የቆዩትም ባለሥልጣነት ተሳትፈዋል፡፡ አጀንዳው የመንግሥቱን መቀመጫ ወደ ጎሬ ማዛወርና በሽፍትነት ለነጻነት የሚደረገውን ትግል ስለመቀጠል ነበር፡፡ ውሳኔ ሳይሰጥበት አደረ። በነጋው ውይይቱ ሲቀጥል፤ የመጀመሪያው ተረስቶ ንጉሠ ነገሥቱ ወደ ዓለም ማኅበር ሄደው አቤት እንዲሉ፣ የመንግሥቱ መቀመጫ ወደ ጎሬ እንዲዛወርና ወራሪውን በሽፍተነት የመከላከሉ ተግባር እንዲቀጥል ተወሰነ፡፡ እሳቸውና  በተሰባቸው ሚያዝያ 24 ቀን 1928 ዓ ም ወደ አውሮፓ ተጓዙ፡፡
እነዚህ ውሳኔዎች የማይጨው ጦርነት ሽንፈት ውጤቶች መሆናቸው ልብ ሊባል ይገባል፡፡ የንጉሡ ስደት የአገር መሪነታቸውና ማዕከልነታቸው እንደተጠበቀ እንዲቆይ ያደረገው ሲሆን  የጦሩ ወደ ሽፍትነት መገባቱም የጦርነቱን መልክ እንዲለወጥ በኋላ አርበኛ እያልን የምንጠራው ኃይል እንዲፈጠር በማድረግ ማገልገሉ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
ከሞት የተረፈው ዘማች በየአካባቢው ከቆየው ወጣትና ጎልማሳ ጋር እየተሰበሰበ ከመካከሉ የጎበዝ አለቃ እየመረጠ፤ በጣሊያን አገዛዝ ላይ ሸፈተ፡፡ አልሰለፍም ያለ እሳት የሚያስጭረው፣ ቢሞት የሚቀብረው እንዲያጣ እምብዳዴ ተጣለበት፡፡ ማሩኝ እያለ እንዲመለስ ሆነ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥም በአስር ሺህ የሚቆጠሩ የጦር መሪዎች ተፈጠሩ፡፡ በዚያው ልክ የጦር ሜዳው በመላው ኢትዮጵያ ተስፋፋ ፡፡ በጠላት ላይ የሚሰነዘረው ጥቃት በትንሽ  የሰው ኃይል ባልተጠበቀ ቦታ በመሆኑ ጠላት ታንክ፣ መድፍና አይሮፕላን መጠቀም የማይችልበት ሁኔታ ተከሰተ፡፡
ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ ም አቡነ ጴጥሮስ “ለጣሊያን መንግሥት አልገዛም፤ ሕዝቡም እንዲገዛ አልሰብክም” ብለው በጥይት ተደብድበው ተገደሉ፡፡ የጎሬው አቡነ ሚካኤልም በተመሳሳይ ምክንያት ሕይወታቸውን እንዲያጡ ተደረገ፡፡ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም  አብርሀም ደቦጭና ሞገስ አስጎዶ ቦምብ ወርውረው ጀኔራል ግራዚያኒንና ሌሎች የጦር መኮንኖችን አቆሰሉ፡፡ በዚህ የተበሳጩት ጣሊያኖች፣ የአዲሰ አበባ ሕዝብ ለተከታታይ ሶስት ቀን በተገኘበት እንዲገደል፣ ቤት ተዘግቶበት እንዲቃጠል አደረጉ፡፡ ከ30ሺ በላይ ሰው  ጨፈጨፉ፡፡ ደበረ ሊባኖስ ገዳም ውስጥም 350፣ ዝቋላ 150 መነኮሰትን ገደሉ፡፡ ይህ ግፍ የአርበኝነት ትግሉን ይበልጥ እንዲጠናከር አደረገው፡
ሰኔ 23 ቀን 1929 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥቱ ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ በጄኔቭ በመንግሥታቱ ማኅበር አዳራሽ የተሰየሙት ዕለት ነበር፡፡
‹‹ማኅበሩ የተመሠረተው ሰላም በሕግ እንዲጠበቅ ስለሆነ ተጠቂ፣ በአጥቂ እግር ስር እንዲወድቅ ባደረገ ጊዜ እራሱን እንደገደለ ይወቅ፡፡ ጥያቄዬ መልስ ባያገኝ  እውነተኛ ፍትሕ እስከሚገኝ ድረስ ጣሊያን ላይ የምናደርገው ጦርነት የማያቋርጥ መሆኑን እገልጣለሁ፡፡ አንድ የተፈረመ ውል የሚረጋው ፈራሚዎችን መንግሥታት እስከጠቀመ ጊዜ ነውን? እግዚአብሔርና ታሪክ ፍርዳችሁን ሲያሰታውሱ ይኖራሉ›› ሲሉም ንገግር አደረጉ፡፡ ሰሚ ጆሮ ባያገኝም።
የኢጣሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቬንቶ ሞሶለኔ ከጀርመኑ መሪ ሒልተር  ጋር የጦር ጓደኛ መሆኑን ሰኔ 3 ቀን 1932 ዓ ም ገለፀ፡፡ ለታላቋ ብሪታንያ የኬኒያ፣ የሱዳን፣ የእንግሊዝ ሱማሌ ላንድ የቅኝ ግዛትዋ አደጋ ላይ መሆኑን ተረደች፡፡ የጣሊያን የቅኝ ግዛት አገር አድርጋ ስትቆጥራት የነበረችውን ኢትዮጵያን  ለጦር ጓደኝነት ፈለገቻት። የኢትዮጵያ የጦር ጓደኛ በመሆንም በጀኔራል ዊሊያም ፕላት መሪነት፤ ከከሰላ ወደ ኤርትራ፣ በጀኔራል ኪንግሐም መሪነት፤ ከኬኒያ ወደ አዲስ አበባ እና በንጉሠ ነገሥቱ የሚመራና ጀኔራል ዊንጊት የሚገኙበት ከሱዳን በኦሜድላ በኩል ወደ አዲስ አበባ በሶስት አቅጣጫ በጣሊያን ላይ ጥቃት ተከፈተ፡፡
ሱዳን ላይ ብዙ መጉላላት የደረሰባቸው ንጉሠ ነገሥቱ፣ ጥር 12 ቀን 1933 ዓ.ም ኦሜድላ ገብተው የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ሰቀሉ፡፡ የጎጃም አርበኛ የጠላትን ምሽግ እያፈረሰና የጠላትን ጦር እየደመሰሰ፣ የንጉሠ ነገሥቱን መልእክት አንዱ ለሌላው እያደረሰ፣ ጠላት በያቅጣጫው ተሳደደ። የማሰደዱ ሥራ ወደ ጎንደርና ሌሎች አካባቢዎች ተስፋፋ፡፡  ንጉሡ መጋቢት 22 ቀን 1933 ዓ.ም ደብረ ማርቆስ ገቡ፡፡ በዚሁ ቀን በጀኔራል ኪኒግሐም የሚመራው የእንግሊዝ ጦር አዲስ አበባ በመግባት በገነተ ለዑል ቤተ መንግሥት (አሁን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያለበት)  የእንግሊዝን ሰንደቅ ዓላማ ሰቀለ፡፡ የሕዝብን ቁጣ በማየት ከሰአት የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ታላቁ ቤተ መንግሥት ሰቀሉ። ጀኔራል ኪንገሃም ለደኅንነት ሲባል የሚል ምክንያት ሰጥቶ ንጉሡ ደብረ ማርቆስ ለአንድ ወር እንዲቆዩ በማድረግ፣ ኢትዮጵያን “ከጠላት የተለቀቀች አገር” በማለት በሊቢያ እንዳደረጉት የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዙን ዘረጋ። ጊዜውንም ጣሊያን ትቶት የሔደውን ንብረት ወደ ኬኒያ ለማጋዝ ተጠቀመበት፡፡
ሚያዝያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም ንጉሠ ነገሥቱ በድል አድራጊነት እንጦጦ ደረሱ። አስር ሺህ የሚሆነው የራስ አበበ ጦር ተቀበላቸው። ኪንግሃም ጦሩ ንጉሡን ተከትሎ እንዳይገባ ከለከለ፡፡ ራስ አበበ ‹‹ ባታስቸግሩን ይሻላል›› ብለው ጦራቸውን ይዘው፣ ንጉሡን አጅበው አዲስ አበባ ገቡ። በእንግሊዞች ላይ እንቢታ በዚህ ጀመረ፡፡
ከአምስት ቀን በኋላ ጀኝሆይ ሰባት ሚኒስትሮችን ሾሙ፡፡ የእንግሊዙ የፖለቲካ ሹም ጀኔራል ሞርስ ላሽ “ማን ፈቀደልዎ?” ብሎ ተቆጣ፡፡ የታላቋ ብሪታኒያ የጦር ካቢኔ፤ ‹‹ኢትዮጵያ የጠላታችን የፋሽሽት መንግሥት ቅኝ ግዛት በመሆኗ ድል አድርጋ ስለያዘቻት በወታደረዊ አስተዳደር ስር ትቆያለች” ብሎ ወስኗል›› ሲል ለንጉሡ ነገራቸው፡፡
ንጉሡ “በወዳጃችን በእንግሊዝ መንግሥት እንዲህ ያለ በደል ይፈጸምብናል ብለን አልጠበቅንም” በማለት ውሳኔውን ተቃወሙ፡፡ “ዳኛ መሾሙ፣ ታክስ መጣሉ፣ ግብር መሰብሰቡ ወዘተ የእኛ” ነው ብለው እንግሊዞች ቀጠሉ፡፡ ኢትዮጵያ ወደ አዲስ የዲፕሎማሲ ትግል ገባች፡፡
ለዓለም እርሻና ምግብ ጉባኤ ወደ አሜሪካ ያቀኑት ምክትል ሚኒስትር ይልማ ደሬሳ እንዲዘረጉት በተደረገው የኢትዮጵያና የአሜሪካ ግንኙነት፣ የካቲት 5 ቀን 1937 ዓም  ግርማዊ ንጉሠ ነገሥትና የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ሩዝቬልት ስዊዝ ካናል ውስጥ በአንድ መርከብ ላይ ተገናኝተው መከሩ፡፡ ይህን የሰሙትና የተደናገጡት እንግሊዞች፤ ከንጉሡ ጋር ለመነጋገር ጥያቄ አቅርበው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዊንስተን ቸርችልና ንጉሡ  የካቲት 9 ቀን 1937 ዓ.ም ተገናኝተው መወያየታቸውንና ከዚህ ጊዜ ጀምሮም የእንግሊዝ የእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ መሰበሩን የታሪክ ልሂቁ ዘውዴ ረታ “የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት” በሚለው መጽሐፋቸው አስፍረዋል፡፡
ኢትዮጵያ አገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ፡፡
የሚለውን የአርበኞችን የምሬት ግጥም እናስታውስ፡፡ ንጉሡ እንዲፈጽሙ የጣዘዙትን ቢፈጽሙ ኖሮ፤ ታጥቦ ጭቃ የሆኑት እንግሊዞችና ባንዳዎች ኢትዮጵያን ምን ያደርጓት ነበር? መልሱን ለአንባቢ ትቼዋለሁ፡፡
ለመሆኑ 900 ሺ ባንዳ ለጣሊያን ያገለግሉ መሆኑን ያውቃሉ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይጠብቅ!!!



Read 1585 times