Monday, 09 May 2022 00:00

60 አገራት ነጻ ኢንተርኔትን ለማስፋፋት ተማምለዋል

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  ባለፉት 3 ወራት አፕሊኬሽኖች 37 ቢሊዮን ጊዜ ዳውሎድ ተደርገዋል አለማቀፉ የአፕሊኬሽኖች ዳውንሎድ 8.6 ቢሊዮን ደርሷል

             አሜሪካ፣ ሁሉም የአውሮፓ ህብረት አገራትና የህብረቱ አባላት ያልሆኑ ሌሎች 32 የአለማችን አገራት የተካተቱበት አንድ የ60 አገራት ቡድን፤ ነጻ፣ አስተማማኝና ደህንነቱ የተጠበቀ የኢንተርኔት አገልግሎት በአለማቀፍ ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ ባለፈው ሳምንት የጋራ ስምምነት መፈጸማቸው ተነግሯል፡፡
አገራቱ መንግስታት የኢንተርኔት አገልግሎትን ከማፈን ይልቅ ሃሳብን በነጻነት ለማንሸራሸርና ለዲሞክራሲ ግንባታ የሚውል ገንቢ የቴክኖሎጂ ውጤት መሆኑን አምነው ለዘርፉ ልማት ያላቸውን ድጋፍ ለማሳየት ሲሉ የፈጸሙት ነው በተባለው በዚህ ስምምነት፣ አገልግሎቱን ማግኘት ላልቻሉ በመላ አለም የሚገኙ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች አለማቀፍና ነጻ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ለማከናወን መስማማታቸውን ነው ቢዝነስ ስታንዳርድ የዘገበው፡፡
ስምምነቱን ከፈጸሙት ሌሎች አገራት መካከል አልባኒያ፣ ካናዳ፣ አርጀንቲና፣ ኬንያ፣ ኒጀር፣ ታይዋን፣ ዩክሬንና ኡራጓይ እንደሚገኙበት የጠቆመው ዘገባው፤ የኢንተርኔት አገልግሎቱን ለመዘርጋት የተስማሙት 60 አገራት ቢሆኑም፣ በቀጣይ ሳምንታት ሌሎች ተጨማሪ አገራት የቡድኑ አባል የሆናሉ ተብሎ እንደሚጠበቅና ቻይና፣ ህንድና ሩስያ በስምምነቱ ውስጥ እንዳልተካተቱም አመልክቷል፡፡
በሌላ ተያያዥ ዜና ደግሞ፤ በፈረንጆች አመት 2022 የመጀመሪያዎቹ 3 ወራት ብቻ ከአፕል ስቶርና ጎግል ፕሌይ የተለያዩ አፕሊኬሽኖች 37 ቢሊዮን ጊዜ ዳውሎድ እንደተደረጉና አጠቃላዩ አለማቀፍ የአፕሊኬሽኖች ዳውንሎድ መጠን 8.6 ቢሊዮን መድረሱ ተዘግቧል፡፡
ሴንሰር ታወር የተባለው ተቋም ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ እንዳለው፤ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ብዛት ያላቸው አፕሊኬሽኖች ዳውንሎድ የተደረጉት ከጎግል ፕሌይ ሲሆን ከድረገጹ 28.3 ቢሊዮን ጊዜ ዳውንሎድ ተደርጓል፡፡ ቲክቶክ የተባለው የቪዲዮ ማጋሪያ አፕልኬሽን በብዛት ዳውንሎድ በመደረግ ቀዳሚነቱን የያዘ ሲሆን፣ አፕሌኬሽኑ ይፋ ከተደረገበት 2018 መጀመሪያ አንስቶ በድምሩ ከ3.5 ቢሊዮን ጊዜ በላይ ዳውንሎድ መደረጉ ተነግሯል፡፡
ከቲክ ቶክ በመቀጠል በብዛት ዳውንሎድ በመደረግ የሚከተሉት አፕሊኬሽኖች ኢንስታግራም፣ ፌስቡክ፣ ዋትሳፕና ቴሌግራም መሆናቸውም ተቋሙ ያወጣው መረጃ ያሳያል፡፡


Read 2739 times