Saturday, 07 May 2022 14:42

COVID-19 ክትባት

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

     የአለም የጤና ድርጅት(WHO) እ.ኤ.አ16 March 2022 ስለ ኮሮና ቫይረስ ሕመም እና ስለክትባቱ አንድ የጥያቄና መልስ አምድ በድረገጹ ለንባብ አቅርቦአል፡፡ ወደ ጥያቄና መልሱ ከመግባታችን በፊት ግን በቅርቡ ማለትም እ.ኤ.አ May 1/2022 ባወጣው መረጃ በኮሮና ምክንያት መወሰድ ያለበት ክትባት በኢትዮጵያ እና በአለም ያለበትን ደረጃ እናስነብባችሁ፡፡
በኢትዮጵያ
በአጠቃላይ የተሰጠው ክትባት ልክ 46.4 ሚሊዮን (46,400,000)
ሙሉ በሙሉ ክትባቱን የወሰዱ 21.3 ሚሊዮን (21,300,000)
ሙሉ በሙሉ የተከተቡ ሰዎች በመቶኛ ሲሰላ 18.5%
በአለም
የተሰጠው ክትባት ልክ 11.6 ቢሊዮን (11,600,000,000)
ሙሉ በሙሉ የተከተቡት 4,66 ቢሊዮን (4,660,000,000)
ሙሉ በሙሉ የተከተቡት በመቶኛ ሲሰላ 59.8%
ከላይ የተጠቀሰው ልክ በአለም እንዲሁም በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ እስከ May 1/2022 የወጣው መረጃ ምን ያህል ሰዎች ክትባቱን እንደወሰዱ እና ክትባቱን በተለያየ መንገድ ያልወሰዱ መኖራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ በዚህ እትም ልናስነብባችሁ የወደድነው በክትባቱ ዙሪያ በየጊዜው ለሚነሱ ጥያቄዎች የተሰጠውን መልስ ይሆናል፡፡ መረጃውን ያገኘነው ከአለም የጤና ድርጅት ድረገጽ ነው፡፡
እስከአሁን ድረስ ኮቪድ 19ን ለመከላከል የተዘጋጁት ክትባቶች የትኞቹ ናቸው?
የኮቪድ 19 ሕመም ከተከሰተ በሁዋላ ኮቪድን ለመከላከል ሲባል የተለያዩ ክትባቶች በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች እውን በመሆናቸው የአለም የጤና ድርጅትም እውቅና የሰጣቸውና በስራ ላይ እንዲውሉ የተፈቀደላቸው በግልጽ የትኞቹ እንደሆኑ በመታወቁ በአለማችን በተለያዩ ሀገራት በስራ ላይ መዋላቸው እውን ነው፡፡ የመጀመሪያው የክትባት ፕሮግራም የጀመረውም እ.ኤ.አ December 2020 ሲሆን መወሰድ የሚገባው የክትባት መጠን ግን በየጊዜው እየተወሰነ እየተሻሻለ የሄደ መሆኑን መረጃው ይገልጻል፡፡  
የአለም የጤና ድርጅት የአስቸኳይ ጊዜ አሰራር የተጠቀመባቸው አመዘጋገቦች የክትባቱ አይነት እና ሁኔታው በተመቻቸባቸው ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ደህንነቱና ጥራቱ በተጠበቀ መንገድ እና በተመቻቸ ሁኔታ እንዲሰጥ የሚሉ ወቅታዊ መረጃዎች በየጊዜው ሲወጡ ስለነበር ይኼው ተግባራዊ እንዲሆን በሀገራት ዘንድ ጥረት ተደርጎአል። ክትባቶች ተቀባይነት እንዲኖራቸው የጥራት ደረጃቸው፤ ለደህንነት ምቹ መሆናቸው እና ኮሮናን በመከላከል ረገድ ብቃት ያላቸው መሆኑን በህክምና ተቋማት እንዲረጋገጥ የሚያስችል እውነታ እንዲኖራቸው በሚመረቱባቸው ቦታዎች ሁሉ ክትትልና የቁጥጥር ፍተሻ ተደርጎባቸዋል፡፡
ይህን ተንተርሶ ሀገራት ባላቸው ብሔራዊ ህግና አፈጻጸሙ መሰረት ለየትኛውም ክትባቱን ለሚያመርት ድርጅት ወይንም ሀገራት ለአስቸኳይ ድጋፍ ሲሉ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ክትባትን ለመጠቀም እንዲችሉ የመወሰን፤ የመጠየቅ ፤የመጠቀም መብት እና ወደሀገራቸ ውም የማስገባት ስልጣን አላቸው። ለዚህም የአለም የጤና ድርጅትን ፈቃድ መጠየቅ አይገባቸውም ይላል መረጃው፡፡
እ.ኤ.አ 12 January 2022 በወጣው የአለም የጤና ድርጅት መረጃ የሚከተሉት ክትባቶች በአለም ላይ በጥናት ተደግፈው ከተመረቱ በሁዋላ ለጠቀሜታ ይፋ ሆነዋል፡፡ የተወሰኑት በስማቸውም አዲስ አይደሉም፡፡ ለማንኛውም ሳይንሳዊ ስማቸውን ወደ አማርኛ መመለስ አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ ለአጠቃቀምም አሳሳች እንዳይሆን ስንል እንዳለ እንግሊዝኛውን ለንባብ ብለነዋል፡፡  
The Pfizer/BioNTech Comirnaty vaccine, 31 December 2020.
The SII/COVISHIELD and AstraZeneca/AZD1222 vaccines, 16 February 2021.
The Janssen/Ad26.COV 2.S vaccine developed by Johnson & Johnson, 12 March 2021.
The Moderna COVID-19 vaccine (mRNA 1273), 30 April 2021.
The Sinopharm COVID-19 vaccine, 7 May 2021.
The Sinovac-CoronaVac vaccine, 1 June 2021.
The Bharat Biotech BBV152 COVAXIN vaccine, 3 November 2021.
The Covovax (NVX-CoV2373) vaccine, 17 December 2021.
The Nuvaxovid (NVX-CoV2373) vaccine, 20 December 2021
ክትባቶቹን መውሰድ የሚያስገኘው ጥቅም ምንድነው?
በመጀመሪየ ደረጃ የመከተብ ጥቅሙ ህይወትን ማዳን ነው፡፡ የኮቪድ 19 ክትባቶች አንድን ታማሚ በከፋ ሁኔታ ከመታመም፤ ሆስፒታል ከመተኛትና ከመሞት ያድናሉ። አልፎ አል ፎም የኮቪድ 19 ክትባትን የተከተቡ ሰዎች ቫይረሱ ቢይዛቸው እንኩዋን ለሌሎች ሰዎች ማስተላለፋቸው እንደሚቀንስ አንዳንድ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ በሌላ አባባል ክትባቱን ለመውሰድ መወሰን ሌሎችን ለማዳን መወሰንም ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በእርግጥ አንዳንድ ሰዎች ክትባቱን ከወሰዱም በሁዋላ በቫይረሱ ምክንያት እንደሚታመሙ ቢታወቅም በአ ብዛኛው ግን ክትባቱን የወሰዱ ሰዎች እራሳቸውን ለመጠበቅ መከላከያ እንደወሰዱ እና ይሄ ደግሞ ለራሳቸው ብቻም ሳይሆን ለቤተሰባቸው፤ ለጉዋደኞቻቸው፤ እና ለማንኛውም ለሚያ ገኙት ሰው ሁሉ መድህን መሆኑ እሙን ነው፡፡
ከላይ የተገለጸው እንዳለ ሆኖ አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ክትባት ቢከተቡም ለቫይረሱ ከተጋለጡ መያዛቸው እንደማይቀርና በአቅራቢያ ክትባቱን ያልወሰዱ ሰዎች ቢገኙ ቫይረሱን የማስተላለፍ እድል እንደሚኖራቸው መዘንጋት የለበትም፡፡ ስለሆነም እራስንም ለመጠበቅ ሆነ ሌሎችን ለመከላከል በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የተሰጡትን የጥንቃቄ እርምጃዎች መከተል የግድ ይሆናል፡፡ ክትባቱን ወስደናል በሚል እርቀትን አለመጠበቅ፤ እጅን በደንብ አለመታጠብ እና ንክኪ በቀላሉ መፍጠር፤ አፍንጫና አፍን አለመሸፈን… ወዘተ. ለተለያዩ ምክንያቶች በሚንቀሳቀሱባቸው ወይንም በሚሰሩበት እና በሚኖሩበት አካባቢ መጋለጥን ማስወገድ ይገባል፡፡ ስለሆነም ክትባቱን መውሰድ ጥንቃቄ ከማድረግ ሊያዘናጋ አይገባም፡፡
መከተብ ያለበት ማነው?
በአለም የጤና ድርጅት መመሪያ መሰረት የክትባቱ አቅርቦት ውስን በነበረበት ወቅት ቅድ ሚያ ተሰጥቶአቸው መከተብ የሚገባቸው ሰዎች እንዲከተቡ ተደርጎአል፡፡ ይህ ውሳኔ የተላፈውም ሌሎች ተጉዋዳኝ በሽታዎች ያሉባቸው (ሰኩዋር፤ የደም ግፊት፤የልብ ሕመም… ወዘተ) በእድሜአቸው የገፉ ሰዎች፤ በሙያቸው ምክንያት ለቫይረሱ የተጋለጡ ሰዎች (የጤና ባለሙያ ዎች….ወዘተ) በእርግዝና ላይ ያሉ እና በተለይም በቫይረሱ ቢያዙ ለጤናቸው ብሎም ልጃቸውን በሰላም ለመገላገል እንዳይችሉ የሚያደርጋቸው ውስብስብ ችግር ያለባቸው ከሆኑ ቅድሚያ ተሰጥቶአቸው መከተብ ካለባቸው ሰዎች መካከል የተመደቡ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ክትባቱ እንደልብ በሚገኝባቸው ሀገራት የሚኖሩ ሰዎች ቅድሚያ የሚሰጣቸው የሚባል ምደባ ስለማይኖር ሁሉም ሰዎች መከተብ ይኖርባቸዋል፡፡
የአለም የጤና ድርጅት እውቅና የሰጣቸው የኮቪድ 19 ክትባቶች ከ18 አመት እና ከዚያ በላይ ላሉ ሰዎች ደህንነትን በማረጋገጥ የታመኑ ሲሆኑ በተለይም አንዳንድ ሕመም ላለባቸው ማለትም የደም ግፊት፤ ስኩዋር፤ አስም፤ ጉበትና ኩላሊት እንዲሁም አደገኛ ኢንፌክሽን ለያዛቸው ሰዎች ቫይረሱ እንዳይጎዳቸው ለማድረግ ጠቃሚ ናቸው፡፡
ህጻናትን በሚመለከት ከ5 አመት ጀምሮ Pfizer የተባለው ክትባት ምቹ ሲሆን ሁለቱም ማለትም Moderna እና Pfizer የተባሉት ክትባቶችን ከ12 አመት ጀምሮ ላሉት ህጻናት መስጠት ይቻላል፡፡ ኮቪድ 19ን ለመከላከል የተዘጋጁት ክትባቶች ለህጻናቱም ሆነ ለአዋቂዎች በተገቢው መንገድ እየተሰጡ ነው፡፡ የተለየ መመሪያ ወይም የፖሊሲ ለውጥ የሚያስፈልገው ከሆነ ግን የአለም የጤና ድርጅት በበቂ መረጃ ላይ ተመስርቶ አዲስ አሰራርን ይፋ ያደርጋል የሚል ተስፋ አለ፡፡   
ማንነው የኮቪድ 19 ክትባትን መውሰድ የሌለበት?
በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ሰው ክትባቱን መውሰድ አለበት?…ወዘተ የሚሉትን እና ሌሎች ጥያቄዎችን በቀጣይ እንመለከታለን፡፡


Read 12627 times