Saturday, 07 May 2022 15:00

ቀጠሮዬ

Written by  አድሃኖም ምትኩ
Rate this item
(1 Vote)

 እርግጠኛ ነኝ ወደ መስታወቱ እንድሄድ  እግሬን አላዘዝኩትም፤ ቢሆንም ግን ራሴን መስታወት ፊት አገኘሁት። ፊቴን አየሁት፣ ገመገምኩት፤ ምንም አልልም።
ከክት ልብሶቼ ውስጥ ያደመቀኝን ቢጫ ቲ-ሸርት፣ በደማቅ ኦሞ ከለር ጅንሴ ለበስኩ፤ ነጭ  ወንፊታም ስኒከሬን ተጫምቼ  ሽቶም ተቀባሁ፡፡
 ምን ነካኝ?
እንደዚህ መቼ ነው ሰው ለማግኘት ተሽሞንሙኜ የማውቀው፤ መቼም በጣም ለፈለግነው ነገር ውስጣችን  ይዳክራል።
ኤላድን ለማግኘት ነው እንዲህ የምሽሞነሞነው ብዬ ማመን አልፈለኩም፤ ለምን ለራሴ ግልፅ ሆኜ አልነገርኩትም?
ሰው ከራሱ ለምን ይደበቃል፤ ከራስ መደበቅ ይቻላል? እኛ ስንት ነን ግን? ራስን ማታለል ይቻላል? ቢቻልስ የትኛው አካላችን የትኛውን ነው የሚያታልለው?
ለራሴ ኤላድ እንድትወደኝ አምሬ ለመገኘት ሽር ጉድ እያልኩ ነው ብሎ ለራሴ ለመናገር ታበይኩኝ።
  ከቀጠሮዬ አንድ ሰዓት ከአርባ ሁለት ደቂቃ ቀድሜ ከቤቴ ወጣሁ፤ ከመውጣቴ በፊት መፅሐፍ ያዝኩ፤ ቀድሜ ለመገኘት ሳይሆን ቀጠሮ ቦታ ለማንበብ ምቹ ስለሆነ ነው  አልኩኝ።
ለማታለል የሞከርኩት እኔ፣ ሊያታልለኝ የሞከረው እኔነቴን ያሽሟጠጠው ይመስለኛል።
ቀጠሮ ስፍራ  ደረስኩ።
ጥበቃ መሃል በሌላ ነገር የሚመሰጡ የተባረኩ ናቸው፤ ጊዜው እንደሌላ ቀን አይደለም ተጎተተ።
 ስታረፍድ ራሴን ሳፅናናው "ሴቶች ሲኳኳሉ፣ ሲሽሞነሞኑ ማርፈዳቸው ልማድ ነው" አልኩት።
ብዙ አርፍዳ መጣች።
ስትመጣ መላምቴና መፅናኛዬ ላይ ውሃ ከለሰችበት፤ ከመላምቴ ስነቃ፤ ራሴን ያፅናናሁበት መንገድ ስህተት መሆኑ ገባኝ።
ኤላድ በቤት ቱታ ፀጉሯን እርግብግቢቷ ላይ ጉብ አድርጋው፤ ከቆዳ በተሰራ ክፍት ጫማ እየተጎተተች መጣች ።
 እንዴት እንዳዘንኩ፤ ግዙፍ ስፍራ የሰጠኋት ልጅ ከምንም እንደማትቆጥረኝ ሁነኛ  ማሳያ ነው፤ ምን አለ አትዘንጥ ቢያንስ እንደ’ኔም የክት ልብስ አታማርጥ፤ ምን አለ የአዘቦት ልብሷን ብትለብስ?
አንደበቴ አልላቀቅ አለኝ፤ ደሞ ፈገግ ትላለች። አለመውደዷን፣ አለመፈለጓን የምታሳየው በአድራጎት ነው ኣ?! ድሮስ ትክክለኛ አሸናፊ ፈገግታ አይለየውም፤ እኔ ላኩርፍ እንጂ።
የልብ ትርታችንን እያወቁ ቁርጡን የማይነግሩን ተፈቃሪያን፣ በመላምት እልፍ አእላፍ እንድንባትል ምክንያት ናቸው።
“ቆየሽ እኮ!” አልኳት።
“ይቅርታ ባለፈው ፈልጌ ፈልጌ አጣሁት ያልከኝን “the queen” የሚለውን  መፅሐፍ ላመጣልህ ኤልሲ ጋ ሄጄ ታክሲ አጥቼ ነው፤ ማርያምን” አለችኝ።
 በቃ ትወደኛለች፤ ባትወደኝ ያን ሁላ መንገድ  ለእኔ ብላ ምን አስኬዳት?


Read 1201 times