Saturday, 14 May 2022 00:00

ልማት ባንክ ለ34 ሺህ ሰልጣኞች 20 ቢሊዮን ብር ብድር አፅድቋል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(4 votes)

ስልጠናው በመላው አገሪቱ በ20 ከተሞችና በ32 የስልጠና ማዕከላት ለ5 ቀን ተካሂዷል
                         የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ብድር ወስደው  ወደ ስራ  እንዲገቡ ለማድረግ ላለፉት 5 ቀናት የዘለቀ ሥልጠና ለ34 ሺ ሰልጣኞች የሰጠ ሲሆን ለእነዚህ ሰልጣኞች 20 ቢሊዮን ብር  ብድር ማዘጋጀቱን ባንኩ አስታውቋል። ባንኩ ባፉት ሁለት ዙሮች 5 ሺ 100 ያህል የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሽ ሰልጣኞችን ማሰልጠን መቻሉን ያስታወሱት የልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር)፤ከእነዚህ ውስጥ 1ሺህ 200 ያህሉ የሚገባውን መስፈርት  አሟልተውና ብድር ፀድቆላቸው ወደ ስራ የሚገቡበት ሁኔታ መመቻቸቱንና 14 ቢሊዮን ብር ብድር መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡
የባንኩ ፕሬዚዳንት ይህን የገለፁት ባለፈው ሰኞ ግንቦት 1 ቀን 2014 ዓ.ም ረፋድ ላይ 3ኛውን ዙር የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ስልጠና መከፈት ምክንትያ በማድረግ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ ነው፡፡ እስከ ትላንት ግንቦት 5 ቀን 2014 ዓ.ም ለተከታታይ አምስት ቀናት በዘለቀው የ3ኛው ዙር ስልጠና በመላው አገሪቱ 34 ሺህ ሰልጣኞች ተሳትፈውበታል። ከዓለም ባንክ ጋር በመተባበር የተዘጋጀው ስልጠና በ20 ከተሞችና በ32   የስልጠና ማዕከላት እስከ ትላንት ድረስ መሰጠቱ ታውቋል።
የሶስተኛውን ዙር ስልጠና ከቀደሙት ሁለት ዙር ስልጠናዎች ለየት የሚያደርገው ከታችኛው የትምህርት ደረጃ እስከ ከፍተኛው የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ድረስ ያላቸው ሰልጣኞች መሳተፋቸው እንደሆነ የገለፁት ዶ/ር ዩሐንስ፤ ለሰልጣኞች 20 ቢሊዮን ብር ብድር መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
ሶስተኛው ዙር ስልጠና በአዲስ አበባ ጌት ፋም ሆቴል ባለፈው ሰኞ በይፋ በተከፈተበት ወቅት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር እና   የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የዳሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ ተገኝ ወርቅ ጌጡ (ዶ/ር) እና የባንኩ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ዮሐንስ አያሌው ለሰልጣኞች መልዕክት አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አሁን በጀመረው የለውጥ ጎዳናና ትጉህ አሰራር ባንኩ የነበረበትን 40 በመቶ የተበላሸ ብድር ወደ 26 በመቶ ማውረድ መቻሉን የጠቆሙት ፕሬዝዳንቱ በቀጣይ ሁለት ዓመታት የባንኩን የተበላሸ ብድር አሁን ካለበት 26 በመቶ ወደ 10 በመቶ ለማውረድ፤ በመጨረሻም ወደ 5 በመቶ ዝቅ ለማድረግ ተግቶ እየሰራ መሆኑን የባንኩ ፕሬዚዳንት ዮሀንስ አያሌው (ዶ/ር) ጠቁመው፤ “መቶ በመቶ የተበላሸ ብድሩን እናጠፋለን ማለት አይቻልም፤ ምክንያቱም የባንክ ስራ አንዱ ሪስክ መውሰድ ነውና” ብለዋል፡፡
ባንኩ በቀጣይ ፊልምና ሌሎች የኪነ-ጥበብ ስራዎችን ጨምሮ የፈጠራ ሀሳብ ያላቸውን ሁሉ እየተቀበለ ብድር በመስጠት (idea financing) እንደሚሰራ የገለፁ ፕሬዚዳንቱ፤ ለሀገር የሚጠቅምና ትልቅ ፋይዳ ያለው ፈጠራና ሀሳብ ይዘው ኮላተራል በማጣት እጃቸውን አጣጥፈው የተቀመጡትን ሀሳባቸውን (ፈጠራቸውን ራሱን) በማስያዣነት በመቀበል ህልማቸውን እውን እንዲያደርጉ የፋይናንስ አቅርቦት ከማመቻቸት እስክ ቴክኒካል ድጋፍ ድረስ ባንኩ ትብብር እንደሚያደርግ ዮሀንስ አያሌው (ዶ/ር) አብራርተዋል።

Read 10077 times