Print this page
Saturday, 14 May 2022 00:00

የነዳጅ ዋጋ ንረቱ ያልተጠበቀ ማህበራዊ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል ተባለ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

 • “የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው በኑሮ ውድነቱ ላይ ቤንዚን ማርከፍከፍ ነው”
      • የነዳጅ እጥረቱ የተከሰተው በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚገባው ነዳጅ በኮንትሮባንድ እየተቸበቸበ በመሆኑ ነው
      • የነዳጅ ድጎማው ሲነሳ የአንድ ሊትር ቤንዚን ዋጋ 66 ብር ከ78 ሳንቲም፤ የአንድ ሊትር ናፍጣ ዋጋ 73 ብር ይደርሳል
               
           ታህሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም በተካሄደው ሶስተኛው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ የፀደቀውና የነዳጅ ድጎማን በሂደት የሚቀንስና የሚያስቀር ውሳኔን ተከትሎ፣ በነዳጅ ዋጋ ላይ እየተደረገ ያለው ጭማሪ ያልተጠበቀ ማህበራዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል የምጣኔ ሃብት ምሁራን ተናገሩ፡፡ ምሁራኑ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት መንግስት ለነዳጅ የሚያደርገውን የ82% ድጎማ ባላነሳበት ሁኔታ በነዳጅ ችርቻሮ ዋጋ ላይ እያደረገ ያለው የዋጋ ጭማሪ በጥናት ያልተደገፈና የሚያመጣው ችግር ያልተጤነ ነው ብለውታል፡፡
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶ/ር ይታገስ ሙሉቀን እንደሚናገሩት፤ መንግስት በነዳጅ ዋጋ ላይ የሚያደርገውን የ82% ድጎማ በመጪው ሐምሌ ወር  እንደሚጀምርና ድጎማው ለግሉ ዘርፍ በየሶስት ወሩ 25 በመቶ እየተነሳ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ እንዲያልቅ፣ ለመንግስት ተሽከርካሪዎች  ደግሞ 10 በመቶ በየስድስት ወሩ እየተነሳ በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ሙሉ  በሙሉ ከድጎማ እንዲወጡ እንደሚያደርግ ገልፆ የነበረ ቢሆንም፤ የተገለጸው የድጎማ ማንሻ ጊዜ ሳይደርስ በነዳጅ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋ ላይ ተደጋጋሚ ጭማሪ እያደረገ ይገኛል፡፡ መንግስት ይህ ጭማሪ በማህበረሰቡ ላይ እያስከተለ  ያለውን የኑሮ ጫና በሚገባ ሊመለከትና ሊያጤነው ይገባል ያሉት ምሁሩ፤ ይህ ካልሆነ ግን ያልተጠበቀ ማህበራዊ ቀውስ ማስከተሉ አይቀሬ ነው ብለዋል፡፡
መንግስት ለነዳጅ ዋጋ ድጎማው መነሳት ምክንያት ናቸው ከሚላቸው ጉዳዮች መካከል ዋነኞቹ በከፍተኛ የውጭ  ምንዛሬ እየተገዛ ወደ አገር ውሰጥ የሚገባው ነዳጅ በኮንትሮባንድ ወደ ጎረቤት አገራት እየተወሰደ በከፍተኛ ዋጋ እየተቸበቸበ መሆኑና ለነዳጅ ድጎማ የሚወጣው ከፍተኛ ወጪ በመንግስት ላይ ጫና መፍጠሩ እንደሆነ የተናገሩት ዶ/ር ይታገስ፤ ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ድጎማን ለማንሳት መሮጡ ዋጋ ያስከፍላል ብለዋል፡፡
በኮንትሮባንድ ነዳጅ ወደ ጎረቤት አገራት እያሸሹ የሚሸጡ ህገወጦችን መቆጣጠርና በኬላዎች አካባቢ ያለውን ቁጥጥር በማጥበቅ ህገ ወጥነትን ከመከላከል ይልቅ የኮቪድ 19 የተፈጥሮ አደጋዎችና የጦርነቱ መዘዝ ባስከተለው የኑሮ ውድነት ሳቢያ ናላው የዞረ ህዝብ ላይ ተጨማሪ ጫና  የሚፈጥር ውሳኔ ማሳለፉ ለወንጀልና ስርዓት አልበኝት በር የሚከፍት አደገኛ ውሳኔ ነው ብለዋል፡፡
የነዳጅ ድጎማ መነሳት እንደ አገራችን ላሉ በርካታ ዕለታዊ ሸቀጦቻቸውን ከውጭ አገር እያስገቡ ለሚጠቀሙና የተለያዩ የመጓጓዣ መንገዶችን ለሚጠቀሙ አገራት በትራንስፖርት ዋጋ ላይ ጭማሪ እንዲፈጠር በማድረግ የሸቀጦች ዋጋ ንረትን ያስከትላል ያሉት ምሁሩ፤ ይህ ደግሞ መንግስትን በቀላሉ ሊወጣው የማይችለው ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ ያስገባዋል ብለዋል፡፡
ወቅቱ አገሪቱ ከጦርነት መከራ ውስጥ ገና ያልወጣችበት፣ ኢኮኖሚዋ በተለያዩ ምክንያቶች ክፉኛ የተጎዳበት የዋጋ ንረቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ  እያሻቀበ የሄደበትና የዜጎች የመግዛት አቅም በከፍተኛ ሁኔታ የተዳከመበት  በመሆኑ ቢያንስ ይህ ሁኔታ እስከሚሻሻልና ገበያው እስከሚረጋጋ ድረስ በመንግስት በኩል የሚደረጉ ተጨማሪ ጫናዎችና የዋጋ ጭማሪዎች ቢቆዩና የነዳጅ ዋጋ ድጎማ የማንሳቱ ውሳኔ እንዲዘገይ ቢደረግ የተሻለ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
መንግስት በአሁኑ ወቅት በምግብና ምግብ ነክ የፍጆታ ሸቀጦች ላይ የሚታው ከልክ ያለፈ የዋጋ ጭማሪን ለማስተካከል የተለያዩ የመፍትሄ እርምጃዎችን መውሰድ ሲገባው፤ በኑሮ ውድነቱ ላይ ተጨማሪ ቤንዚን  የማርከፍከፍ ተግባር እየፈፀመ መሆኑ የማይወጣው አጣብቂኝ ውስጥ ይከተዋል ብለዋ-ዶ/ር ይታገስ፡፡
ባሳለፍነው የሚያዝያ ወር የምግብ ነክ ሸቀጦች ዋጋ ግሽበት 42.9 በመቶ የደረሰ ሲሆን ይህ አሃዝ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር፣ የ36.6 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን የብሔራዊ ስታቲስቲክ አገልግሎት መረጃ ያመለክታል፡፡
የኢትዮጵያ የነዳጅ ምርቶች ፍላጎት በየጊዜው እየጨመረ የመጣ ሲሆን የብሔራዊ ባንክ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ ከ10 ዓመት በፊት በ2004 አገሪቱ ለነዳጅ ግዚ አውጥታ የነበረው ገንዘብ 22.8 ቢሊዮን ብር ነበር፤ ይህ ቁጥር ባለፈው ዓመት ወደ 62.05 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡
የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ አገሪቱ በቀን 2.5 ሚሊዮን ሊትር ቤንዚን እና 8 ሚሊዮን ሊትር ናፍጣ ትጠቀማለች፡፡ በኢትዮጵያ ከታህሳስ እስከ ግንቦት ባሉት የበጋ ወራት  ከሌላው ጊዜ በበለጠ ከፍተኛ መጠን ያለው የነዳጅ ምርት ጥቅም ላይ የሚውል ሲሆን ይህም የኮንስትራክሽን ስራዎች በስፋት የሚከናወንበት ወቅት ከመሆኑ ጋር የሚያያዝ መሆኑንም መረጃው አመልክቷል፡፡
የነዳጅ ዋጋ ጭማሪው በዓለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ መጠን እያሻቀበ የሄደ ሲሆን ባለፉት አራት ወራት ብቻ በአለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ላይ የ27 በመቶ ጭማሪ ታይቷል። በታህሳስ ወር በሜትሪክ ቶን 870 ዶላር ይሸጥ የነበረው ቤንዚን፤ ባሳለፍነው የሚያዝያ ወር ወደ 1028  ዶላር አሻቅቧል፡፡ ኢትዮጵያ የነዳጅ ምርቶችን ከሳውዲ አረቢያና ከኩዌት የምታስገባ ሲሆን የነዳጅ ምርቱ ወደ አገር ውስጥ የሚገባበት ብቸኛው መንገድ ደግሞ የጅቡቲ ወደብ ነው። ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ መንግስት ለነዳጅ  የሚያደርገውን ድጎማ ቢያቆም በአዲስ አበባ የአንድ ሊትር ቤንዚን ዋጋ 66 ብር  ከ78 ሳንቲም እንዲሁም የአንድ ሊትር ናፍጣ ዋጋ 73 ብር ይደርሳል፡፡


Read 9469 times
Administrator

Latest from Administrator