Saturday, 14 May 2022 00:00

ክትባቱን መውሰድ የሌለበት ሰው አለ?

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

የኮሮና ቫይረስን ወረርሽኝ ለመከላከላ እንዲቻል በአለም ላይ ያሉ ሳይንቲስቶች በየፊናቸው ክትባቱን ለማምረት የቻሉትን ጥረት አድርገዋል፡፡ ክትባቱ ተገኝቶአል… ክትባቱን ተከተቡ የሚለው መግለጫ ሲወጣ ግን በተቃራኒው የቆሙ ሰዎች ቁጥር ቀላል አልነ በረም፡፡ ዛሬም ድረስ ቢሆን በተለያዩ ምክንያቶች ክትባቱን ላለመውሰድ ጸንተው የቆሙ አሉ፡፡ ስለዚህ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ይቻል ዘንድ የአለም የጤና ድርጅት WHO በሰዎች መካከል የሚመላለሱ ጥያቄዎችንና መልሶችን በድረገጹ ለንባብ ብሎአል፡፡ ይህ አምድም አንባቢዎችን እንዲያውቁት ለማድረግ ለህትመት ያለው ሲሆን ሁለተኛው እትም የሚጀ ምርበት ጥያቄ ለርእስነት የመረጥነው ነው፡፡
የCOVID-19 ክትባትን መውሰድ የሌለበት ሰው አለ?
ክትባቱን ላለመከተብ ምክንያት የሚሆኑ የተወሰኑ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ስለዚህም ላለመከተብ ምክንያት ይሆናሉ ተብለው በተጠቀሱ ምክንያቶች ለጊዜውም ቢሆን እርስዎም ላይከተቡ ይችላሉ እንጂ በደፈናው መከተብ የሌለበት ሰው አለ የሚል ድምደሜ የለም፡፡
የኮቪድ-19 ክትባትን ለመስራት ጥቅም ላይ የዋሉ ድብልቆች በሕይወት ዘመን ተጠቃሽ ወይንም አስቸጋሪ ከሆነ የአለርጂክ በሽታ ጋር የሚገናኝ ከሆነ ተጨማሪ ችግር እንዳይመጣ ለመከላከል ከህምና ባለሙያዎች ጋር ሳይመክሩ ክትባቱን መውሰድ አይመከርም፡፡
ክትባት በሚወስዱበት ቀን ትኩሳቱ ከ38.5 ዲግሪ ሴንትግሬድ በላይ በሆነ ትኩሳት ተይዘው ከሆነ ህመሙ እስኪቀንስ ክትባቱን ማስተላለፍ ይገባል፡፡
በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ሰው ክትባቱን መውሰድ አለበት?
በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ሰው ቫይረሱ በሰውነት ውስጥ መኖሩ ከተጠረጠረ ቫይረሱ ከሰውነት ውስጥ እስኪወጣ መቆየትና ለመከተብ ብቁ መሆንን በህክምና ማረጋገጥ ይገባል፡፡ የሚከተበውን ሰው ጤንነት በሚገባ ፈትሾ ብቃትን የሚያረጋግጥ ባለሙያ ባልተሳተፈበት በግል ፈቃድ ክትባቱን መውሰድ አይገባም፡፡
በእርግጥ በኮሮና ቫይረስ ከተያዙ ክትባቱን ሊወስዱ ይችላሉ ወይንም አይችሉም የሚል መደምደሚያ የለም፡፡ አንድ ሰው በኮሮና ቫይረስ ተይዞ የነበረ ከሆነ ክትባቱን ሊወስድ ይችላል ወይ ለሚለው መልሱ አዎ፡፡ ይችላል ፡፡ የሚል ነው ፡፡ ነገር ግን ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ሁሉም ሰው አንድ አይነት አቅም ያለው ስላልሆነ በምን ሁኔታ የሚለውን ለመወሰን ከሰው ሰው ይለያያል፡፡ ስለሆነም በቫይረሱ ከተያዙ በሁዋላ ይህን ያህል ጊዜ መቆየት ይገባል ለሚለውም ግልጽ የሆነ የተቀመጠ ማሳያ የለም፡፡ ስለሆነም ሰዎች በሚደረግላቸው የምርመራ ውጤት በሚገኘው የኮቪድ-19 ኢንፌክሽን ምክንያት ክትባቱ እስከ 6 ወር እንዲዘገይ ሊደረግ ይችላል፡፡ ለማንኛውም የህክምና ባለሙያን ማማከር ተገቢ ይሆናል፡፡  
የኮሮና ቫይረስ ክትባቶች በተለይም በሕክምናው ዘርፍ የደም ማቅጠኛ ለሚወስዱ ሰዎች ምንም ችግር አያስከትሉም፡፡ ማንኛውም ተከታቢ ክትባቱን ከመውሰዱ በፊት ያለበትን የህክምና ባህርይና የሚወስደውን መድሀኒት አይነት ለሐኪሙ አስቀድሞ መናገር አለበት፡፡ ከላይ የተጠቀሰው እንዳለ ሆኖ ማንኛውም የክትባት አይነት ከሚከተበው ሰው ጤና ጋር በተያያዘ የራሱ የሆነ መግለጫ ወይንም ማብራሪያ እንዳለው መዘንጋት የለበትም፡፡ ዋናው ነገር በግልጽ ከሐኪሙ ጋር መነጋገር ወይንም መመካር ነው፡፡
በእርግዝና ላይ እያሉ የኮቪድ-19ን ክትባት መውሰድ ይቻላል?
አዎን፡፡ በእርግዝና ላይ እያሉ የኮሮና ክትባትን መውሰድ ይቻላል፡፡በእርግዝና ላይ ያሉ ሴቶች በቫይረሱ የመያዝና በከፍተኛ ሁኔታ የመታመም እድል አላቸው፡፡ በተጨማሪም በቫይረሱ ከተያዙ ልጅን ካለእድሜው የመውለድ ሁኔታ ያጋጥማል። ክትባቱን በመውሰዱ ረገድ በእርግዝና ላይ ካሉት ውስጥ ብዙ ባይመዘገቡም ነገር ግን ክትባቱ በእርግዝና ላይ ላሉት ምንም ችግር እንደማያስከትልና ይልቁንም ከቫይረሱ የሚከላከላቸው መሆኑ የተረ ጋገጠ መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች በየጊዜው እየጨመሩ ነው ይላል የአለም የጤና ድር ጅት መረጃ፡፡ በተለይም የኮቪድ ቫይረስ በስፋት በሚሰራጭባቸው ሀገራት ወይንም አንዲት እርጉዝ ሴት በምትኖርበት ወይንም በምትሰራበት...ወዘተ በመሳሰሉት ቦታዎች ለኮሮና ቫይረስ የመጋለጥ እድሉ የሰፋ ስለሆነ ክትባቱን የወሰዱ እርጉዝ ሴቶች ለከፋ ችግር መጋለጣቸው መቀነሱን የተለያዩ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡  አንዳንዶች በተሳሳተ መንገድ የኮቪድ-19 ከትባት በራሱ ቫይረሱን እንደሚያስይዝ የሚናገሩ ሲሆን በምንም አይነት ከክትባቱ የሚሰራጭ ቫይረስ አለመኖሩን እርግጠኛ መሆን ይገባል፡፡ በተጨማሪም ማንኛው ንም የጤና መረጃ ከትክክለኛው የህክምና ባለሙያ ወይንም ተቋም ካልሆነ በስተቀር ከማይ መለከታቸው ሰዎች መሰብሰብ አደጋ አለው ይላል መረጃው፡፡
ወደፊት ልጅ እወልዳለሁ ብለው የሚያስቡ ክትባቱን ቢወስዱ ችግር የለውምን?
ምንም ችግር የለውም፡፡ ወደፊት እርግዝና እንዲኖርና ልጅ እንዲወለድ የሚፈልጉ ከሆነ ክትባቱን ከመውሰድ የሚያግድ ምንም ነገር የለም፡፡ እስከአሁን ድረስ የኮቪድ-19 ክትባት ልጅ ከመውለድ አለመውለድ ጋር በተያያዘ የሚያመጣው ችግር አለ የሚል ምንም መረጃ የለም፡፡ እስከአሁን ድረስ ክትባቱን ከወሰዱ ሰዎች ጋር በተያያዘ በእርግዝና በክትትል ወቅት የታየ ምንም አይነት መረጃ የለም፡፡ በስነተዋልዶ ጤና አካላት ላይም ክትባቱ የሚያደርሰው ምንም ጉዳት የለም፡፡ የኮሮና ቫይረስ ክትባትን መውሰድ ለራስ ጤንነትም ሆነ ወደፊት ሊወ ልዱት ለሚፈልጉት ልጅ ጤንነት ጠቃሚ እንጂ ጎጂ አይደለም፡፡
ጡት በማጥባት ላይ ያለች እናት የ COVID-19ን ክትባት መውሰድ ትችላለችን?
ጡት የምታጠባ ሴት መከተብ በምትችልበት ወቅት ኮሮናን ለመከላከል ክትባቱን መውሰድ ትችላለች፡፡በመሰጠት ላይ ያሉት የትኞቹም ክትባቶች ህይወት ያለው ቫይረስ በውስጣቸው የለም፡፡ ስለሆነም ኮሮና ቫይረስን ከእናት ወደልጅ በጡት ወተት አማካኝነት የሚያስተላልፍ ምንም መንገድ የለም፡፡ ይልቁንም ከክትባቱ የሚገኘው ቫይረሱን የሚከላከለው antibodies በጡት ወተት አማካኝነት ጡት ወደ ሚጠባው ህጻን ስለሚተላለፍ ልጁን ከቫይረሱ ለመጠ በቅ ይረዳል፡፡
በወር አበባ ወቅት የኮቪድ-19ን ክትባት መውሰድ ይቻላል?
በወር አበባ ወቅት የኮቪድ-19ን ክትባትን መውሰድ ይቻላል፡፡ ምናልባትም ለክትባት ቀጠሮ የያዙበት ቀን የወር አበባው በሚመጣበት ቀን ቢሆን እና የተለያየ ምክንያት ቢኖርዎት እንኩዋን ቀደም ብሎም ቢሆን ክትባቱን መውሰድ ይቻላል፡፡ የወር አበባ የህመም ወይንም ከህክምና ጋር የተያያዘ ሳይሆን ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ተፈጥሮአዊው ነገር ችግር ከገጠመው ብቻ ነው ከህክምና ጋር የሚያያዘው፡፡ ስለሆነም የኮሮና ቫይረስ ክትባትን ከመውሰድ አለመ ውሰድ ጋር ምንም የሚያገናኘው ምንም ነገር የለም። ለማንኛውም በዚህ ጉዳይ ጥያቄ ወይንም ጥርጣሬ ካለዎት የህክምና ባለሙያን ከማነጋገር ወደሁዋላ አይበሉ፡፡  
የኮሮና ቫይረስ ክትባት የወር አበባ ሂደትን ሊረብሽ ወይንም ሊያዛባ ይችላልን?
አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት አንዳንድ ሴቶች የኮሮና ቫይረስን ክትባት ከወሰዱ በሁዋላ የወር አበባ ኡደት እንደተዛባባቸው የሚያሳይ ሪፖርት ለሐኪሞቻቸው አቅርበዋል የሚል መረጃ አለ፡፡ እስከአሁን ድረስ ግን በትክክል የኮሮና ክትባትን በመውሰድ ምክንያት የወር አበባ መዛባት ሊከሰት ይችላል የሚል ማረጋገጫ ስለሌለ በወር አበባ መዛባት እና በክትባቱ መካከል ምንም ግንኙነት እንደሌለ ይታመናል፡፡ በእርግጥ በከፍተኛ ደረጃ የተያዙ አንዳንድ ጥናቶች የክትባት ውጤት ከወር አበባ መዛባት ጋር ይገናኛል ወይንስ? የሚለውን ለማረጋገጥ እንዲቻል በመሰራት ላይ ናቸው፡፡ መረጃው ሲገኝ ይፋ እንደሚደረግ የአለም የጤና ድርጅት ያረጋግጣል፡፡ በተደጋጋሚ እንደሚነገረው ማንኛውንም አይነት ጥርጣሬ ወይንም ጥያቄ ለሕክምና ባለሙያ ከማማከር አይዘናጉ፡፡
የCOVID-19 ክትባት በምን ያህል ፍጥነት ወረርሽኙን ይከላከላል?
የኮቪድ-19 ክትባት ወረርሽኝን የመከላከል ኃላፊነት ከተለያዩ ነገሮች ጋር ይያያዛል፡፡ የክት ባቱ ውጤታማነት፤ በምን ያል ፍጥነት ይመረታል፤በምን ያህል ጊዜ ለሚፈልጉት ሀገራት ይዳረሳል፤በስራ ላይስ በምን ሁኔታ ይውላሉ የሚለው እና ምን ያህል ሰዎች ክትባቱን በመውሰድ ላይ ናቸው የሚለው ይወስነዋል፡፡
ለማንኛውም ወረርሽኙን ለመከላከል ማኛውም ሰው ማለትም ክትባቱን የወሰደም ያልወሰደም የጥንቃቄ እርምጃዎችን ምንም ሳያዛቡ ከተገበሩ ከክትባቱ ጋር ተዳምሮ ወረርሽኙ እንደሚቀንስ ምንም ጥርጥር አይኖርም፡፡

Read 12794 times