Saturday, 14 May 2022 00:00

ብራዚል የእግር ኳስ ተጫዋቾችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ 1ኛ ሆናለች

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ብራዚል ከአለማችን አገራት መካከል በርካታ የእግር ኳስ ተጫቾቿ በውጭ አገራት የእግር ኳስ ሊጎች የሚጫወቱባት ቀዳሚዋ አገር መሆኗንና ባለፉት አምስት አመታት 1 ሺህ 219 ብራዚላውያን የእግር ኳስ ተጫዋቾች በተለያዩ ሊጎች እንደተጫወቱ ሰሞኑን የወጣ ሪፖርት አመልክቷል፡፡
ከእነዚህ ብራዚላውያን የእግር ኳስ ተጫዋቾች መካከል 65 በመቶ ያህሉ በአውሮፓ አገራት ሊጎች ውስጥ እንደሚጫወቱና፣ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት በፖርቹጋል ሊጎች ውስጥ የሚጫወቱ 221 ብራዚላውያን ኳስ ተጫዋቾች መሆናቸውም ተነግሯል፡፡
ተቀማጭነቱ በስዊዘርላንድ የሆነው ኢንተርናሽናል ኢንስቲቲዩት ፎር ስፖርትስ ስተዲስ የተባለው አለማቀፍ ተቋም ባለፉት አምስት አመታት በአለም ዙሪያ በሚገኙ 135 ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ሊጎች ውስጥ ከተካተቱ 2 ሺህ 198 የእግር ኳስ ቡድኖች ያሰባሰበውን መረጃ መሰረት አድርጎ ባወጣው መረጃ እንደሚለው፣ ፈረንሳይ በ978 ተጨዋቾች የሁለተኛነት ደረጃን ይዛለች፡፡ 815 የእግር ኳስ ተጫዋቾቿ በተለያዩ የውጭ አገራት ሊጎች ውስጥ የሚጫወቱባት አርጀንቲና ሶስተኛ ደረጃን ስትይዝ፣ እንግሊዝ በ525፣ ጀርመን በ441 አራተኛና አምስተኛ ደረጃን መያዛቸውን መረጃው ያሳያል፡፡
ኮሎምቢያ በ425፣ ስፔን በ409፣ ክሮሺያ በ400፣ ሰርቢያ በ379 እና ሆላንድ በ367 የውጭ አገራት ሊግ ተጫዋቾች ብዛት እንደ ቅደም ተከተላቸው ከስድስተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙ የአለማችን አገራት መሆናቸውም ተነግሯል፡፡

Read 3023 times