Saturday, 21 May 2022 10:53

ያልተነገረው የትግራይ ወጣቶችና ቤተሰቦቻቸው ሰቆቃ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(4 votes)

ከፍተኛ የጦርነት ዝግጅት ላይ  የሚገኘው የህውሓት ቡድን፣ የትግራይ ወጣቶችን በግዳጅ  ለጦርነት እየቀሰቀሰና እየመለመለ መሆኑን የተለያዩ አለማቀፍ ተቋማትና ሚዲያዎች  ያጋለጡ ሲሆን ሕውሓትም ድርጊቱን አላስተባበለም።
ሮይተርስ የዜና ወኪል ከየካቲት እስከ ግንቦት 2014 ዓ.ም በትግራይ ባደረገው ቅኝትና የምርመራ ሪፖርት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ወጣቶች በግዳጅ ለጦርነት እየተመለመሉ መሆኑን አረጋግጧል። በግዳጅ ምልመላው ወቅት ልጆቹን የደበቀ ወይም ወደ ስልጠና ያልላከ ቤተሰብ፣ እስርና የከፋ ስቃይ እንደሚደርስበትም የምርመራ ሪፖርቱ ያስረዳል።ወደ ግዳጅ ዘመቻው አንሄድም ብለው የተደበቁ ወጣቶች ቤተሰቦችን በማሰር፣ በማስፈራራትና  በማገት ወጣቶቹ ሳይወዱ በግድ የቤተሰቦቻቸውን ደህንነት ለመጠበቅ ሲሉ ወደ ስልጠና እንደሚገቡ ተጠቁሟል።
ሮይተርስ ከየካቲት እስከ ያዝነው ግንቦት ወር ድረስ በርካታ ሰዎችን በጉዳዩ ላይ ማነጋገሩን ጠቅሶ፣ያነጋገራቸው ወጣቶችና ቤተሰቦችም የግዳጅ ዘመቻውን አስከፊ ገጽታዎች እንደሚያስረዱ አመልክቷል።
በሌላ በኩል፤ ከዚህ በፊት በራሳቸው ፈቃደኝነት ለመዋጋት ስልጠና ወስደው የነበሩ እንዲሁም  በግዳጅ ላይ ያሉ ወጣቶችም የተኩስ አቁም ከተደረገ በኋላ በድጋሚ ወደ ጦርነት የመግባት ፍላጎቱ እንደሌላቸውም ሪፖርቱ ይጠቁማል። ሮይተርስ ያነጋገራቸው በውጊያ ላይ ያሉ ወጣቶችም በሁኔታው መሰላቸታቸውንና ወደ መደበኛ ህይወት የሚመለሱበት ጊዜ እንደናፈቃቸው፣ ከእንግዲህም የመዋጋት ፍላጎት እንደሌላቸውና ሞራላቸው መላሸቁን ገልጸዋል።
በግዳጅ እንዲዘምቱ ከተደረጉ ወጣቶች አንዱ የሆነው የ18 ዓመቱ ወጣት አልዩ፣ እንዳባጉና በሚገኝ የወላጆቹ ቤት ሳለ፣ የአካባቢው ባለስልጣናትና ሌሎች ሰዎች መጥተው፣ ቤተሰቦቹን አስፈራርተውና  አዋክበው እንደወሰዱት ይገልጻል።
“በወቅቱ እናቴን እንደሚያስሯት ቤተሰቦቼም ከ10 ሺህ እስከ 20 ሺህ ብር የሚደርስ መቀጫ እንደሚጠበቅባቸው ሲነገረኝ ዘመቻውን ተቀላቀልኩ” የሚለው አሊዩ፤ ለትንሽ ቀን ስልጠና ከወሰደ በኋላ በአፋር ግንባር እንዲሰለፍ ግዳጅ ተሰጥቶት ሳለ፣ ጭፍራ ላይ በተደረገ ጦርነት እግሩ ላይ በከባድ መሳሪያ አረር መመታቱን ያስረዳል። በአሁኑ ወቅትም በአፋር ዱብቲ ሪፈራል ሆስፒታል በህክምና ላይ እንደሚገኝ ሪፖርቱ ያመለክታል፡፡
ከአልዩ ጋር በዱብቲ ሆስፒታል ተኝተው የሚታከሙ በርካታ የትግራይ ወጣቶችም ተመሳሳይ ታሪኮችን ለሮይተርስ ዘጋቢዎች አጋርተዋል።“እኔ በህይወት እያለሁ እናቴ ስትሰቃይና እስር ቤት ስትገባ ማየት አልፈልግም” የሚለው የ18 ዓመቱ ሌላኛው የግዳጅ ዘማች ፊሊሞን፣ የሚኖርበት መቀሌ ከተማ ባለስልጣናት ወደ መኖሪያ መንደራቸው መጥተው ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ለስብስባ መቀመጣቸውን ያስታውሳል።
በስብሰባው ወቅትም እያንዳንዱ አባወራ ከቤቱ ለዘመቻው አንድ ልጅ የመስጠት ግዴታ  እንደተጣለበት፣ ይህን በማያደርጉት ላይም ከባድ ቅጣት እንደሚጣልባቸው እንደተነገራቸው ያስረዳል- ፊሊሞን።
“በዚህ ማስጠንቀቂያ መሰረት እናቴ ወደ እስር ቤት እንድትገባ ፈጽሞ ስላልፈለኩ ተመዝግቤ ዘመቻውን ልቀላቀል ችያለሁ” ያለው ወጣቱ፤ በጦርነት መሃልም የግራ እግሩን ሙሉ በሙሉ ማጣቱን ተናግሯል።
በከባድ መሳሪያ ተመትቶ ቆስሎ በነበረበት ወቅት ለዘጠኝ ቀናት በኪሱ የያዘውን ብስኩት እየተመገበና የወንዝ ውሃ እየጠጣ ነፍሱን ማቆየቱን፣ በኋላ ተመቶ በወደቀበት አካባቢ ያሉ አርሶ አደሮች አስጠግተውት፣ ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት እንዳስረከቡት ፊሊሞን ገልጿል።
በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ስር ሆኖም በሆስፒታል ተገቢውን የህክምና ክትትል ማድረጉን የተናገረው ወጣቱ፤ “ጦርነት እጅግ  መጥፎ ነው፤ የጓደኞቼን አስክሬን ጥንብ አንሳ አሞራ ሲበላው በአይኔ አይቻለሁ። ይህም የአእምሮ እረፍት ይነሳኛል” ብሏል።
ሮይተርስ ከመቀሌና አካባቢው ያነጋገራቸው በአሁን ወቅት በስልጠና ላይ የሚገኙ ልጆች ያሏቸው ቤተሰቦች በበኩላቸው፤ ከጥር ወር ጀምሮ ከየቤቱ በግዳጅ ታዳጊ ልጆችና ወጣቶች መወሰዳቸውን፣ ልጆቻቸውን የደበቁ ቤተሰቦች እስርን ጨምሮ የከፋ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ሲፈጸምባቸው እንደቆየ አስረድተዋል።
በአሁን ወቅትም በተመሳሳይ የሕወሓት እኩይ ድርጊት መቀጠሉን፣ ይህም ህብረተሰቡን ለከፋ ምሬት መዳረጉን  ሪፖርቱ ያመለክታል።
የየአካባቢው ባለስልጣናት ነዋሪዎችን በግድ እየሰበሰቡ፤ “ያለ ምንም ማመንታት ወታደራዊ ስልጠና  ወስዳችሁ እናት ሃገራችሁን (ትግራይ) ከጠላት መከላከል አለባችሁ።” እንደሚሉም  ሪፖርቱ ያመለክታል።
ይህ መልእክትም በስብሰባ መሃል እንደ መልዕክት ከመተላለፉ ባለፈም እ.ኤ.አ ጃንዋሪ 9 ቀን 2022 ተጽፎ፣ የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስትና የመቀሌ ከተማ አስተዳደር የሚሉ ማህተሞች አርፈውበት፣ በበራሪ ወረቀት ሲሰራጭ እንደነበር የሮይተርስ የምርመራ ዘገባ ቡድን ማረጋገጫ ማግኘቱንም ጠቁሟል።
አንድ ስሙን መግለጽ ያልፈለገ ወጣት እንደሚያስረዳው፣ ከዚህ መልዕክት በኋላ ወደ ማስገደድ እርምጃ የተገባ ሲሆን በዚህም የቅርብ ጎረቤታሞች በጥርነፋ ስልት አውጫጭኝ ስብሰባ እንዲቀመጡና ወደ ጦርነት መላክ ያለበትን እንዲልኩ መገደዳቸውን ይናገራል፡፡
በወቅቱም እርሱ በስራ ገበታው ላይ በነበረበት ሰዓት “ባለቤትሽን አምጪ” በሚል ነፍሰጡር ባለቤቱ ታስራ እንደነበር፤ ወደታሰረችበት ፖሊስ ጣቢያም በማምራት “እባካችሁ ሚስቴን ልቀቋት፤ እኔ ወታደር ሆኜ በጦርነት እንድሳተፍ ሙያዬ አይፈቅድልኝም። የዕርዳታ ሰጪ ድርጅት ውስጥ የምሰራ የእርዳታ ባለሙያ ነኝ; ብላቸውም አልተቀበሉኝም ይላል። ባለቤቱም በእስር ቤት ካደረች በኋላ ከእርሷ ጋር በእስር ላይ የነበሩ ሴት ታሳሪዎች “እንዴት ነፍሰ ጡር ሴት አስራችሁ ታንገላታላችሁ” የሚል አመጽ በመፍጠራቸው ከእስር ልትፈታ እንደቻለች አስረድቷል፡፡
ሌላኛው ስሙን መግልጽ ያልፈለገ ግለሰብ በበኩሉ፤ የሕውሓት ሃይል በፌደራል መንግስት ተመትቶ ከአማራና ከአፋር ክልል ከተባረረ በኋላ በትግራይ በጦርነቱ ለመሳተፍ የነበረው ፍላጎትና ተነሳሽነት መክሰሙን፣ በአሁኑ ወቅት ህዝቡም ወጣቱም በጦርነቱ ለሕውሓት ተሰልፎ ለመዋጋት ሞራል ማጣቱንና ጦርነቱ የማይጠቅምና ጉዳቱ የከፋ መሆኑን መረዳቱን ይናገራል፡፡
ህብረተሰቡ በጦርነቱ ለመሰላቸቱና ሞራል ለማጣቱ ሌላኛው ምክንያት በታጠቁ የህውሓት ሃይሎች ከእለት ወደ እለት የሚደርስበት እንግልትና ጥቃት እያየለ መምጣቱ እንደሆነ ይነገራል።
ልጆቻቸውን ወደ ግዳጅ አንልክም በሚሉ ቤተሰቦች ላይ የሚደርሰውን ስቃይና እንግልት በተመለከተ ለሮይተርስ ያስረዱት አንድ የመቀሌ ከተማ ነዋሪ፤ አንድ የ70 ዓመት አዛውንት “ሴት ልጅህን ለጦርነቱ ካልሰጠኸን; በሚል ለሳምንታት በእስር ቤት መሰቃየታቸውን ይገልጻሉ።
ይህ መሰሉ እስርና እንግልት ከመቀሌ በተጨማሪ በሽሬ፣ ውቅሮ፣ አዲግራትና አድዋ አካባቢዎች በሰፊው ተጠናክሮ መቀጠሉን፣አብዛኞቹም በፖሊስ ጣቢያዎች ምቹ ባልሆነ ሁኔታ ታስረው እንደሚገኙ  የምርመራ ሪፖርቱ  ያመለክታል።
“በአሁኑ ወቅት በትግራይ ወጣት ሴቶችና ወንዶች በተገኙበት ይታደኑ የተባለ ነው የሚመስለው፤ ወጣት ሆኖ ከቤተሰብ ጋር መኖር ወንጀል የሆነ ይመስላል። እኛም ይህን እንደ ባህል ተለማምደነዋል; ያለው የ17 ዓመቱ ተገዶ ዘማች ታዳጊ ነው።
ትግራይ ለወጣቶችዋ ሲኦል ሆናለች የሚለው ይኸው ታዳጊ፤ አብዛኛው ሰው በጦርነቱ መሰላቸቱንና ሞራሉ መላሸቁን ለሮይተርስ ተናግሯል፡፡


Read 11352 times