Print this page
Saturday, 21 May 2022 11:07

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ
                                   (ጌታሁን ሔራሞ)                   አዲስ አበባ “ግራጫ ትሁን” ተብሏል። ግራጫ፣ ነጭና ብርማ “ቀለሞች” ከኪነ ሕንፃ ታሪክ አኳያ ሞደርኒዝም ከናኘበት ከዛሬ 60 ዓመታት በፊት በብዙ ሀገራት ተሞክረው ቀለሞቹ በሰው ልጆች ሥነ ልቦናና አካል ላይ ከሚያስከትሉት ተፅዕኖ አንፃር በብቸኝነት ጥቅም ላይ እንዳይውሉ የተደረጉ ናቸው። ሲጀመር እነዚህ በዘልማድ በቀለምነት ይፈረጁ እንጂ ቀለም-አልባ ዝሪያዎች(Achromatic) ናቸው።
   ከሥነ ልቦናዊ ተፅዕኖ አንፃር በተለይም ግራጫ ቀለም ሰፊ ቦታ ከተሰጠው ራስን የማጥፋት (Suicide commitment) ውሳኔን የሚያበረታታ “ቀለም” መሆኑ በብዙ ጥናቶች የተረጋገጠ ነው። ለዚህም ምክንያቱ ግራጫ “ቀለም” ሲያይል ድባቴን (Depression) ፈጥሮ ሰዎች ከራሳቸው ወጣ ብለው እንዳይንሸራሸሩ የሚያደርገውን “Introvert” ሰብዕናን ማበረታቱ ነው። በተለይም በሌሎች የግልና ማህበረሰባዊ ችግሮች ለተወጠሩ ሰዎች(ለምሣሌ ኑሮ ውድነት፣ጦርነት) “Extrovert” እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው አካባቢ ነው መፈጠር ያለበት። ይህም መሠረታዊ የሁባሬን መርሆችን (Harmony principles) የተከተለ የቀለማት አጠቃቃም(Chromatic environment) ይተገበር ዘንድ ግድ ይላል። በተለያዩ ቀውሶች ለተከበበ ማህበረሰብ ድባቴን የሚፈጥሩ “ቀለሞችን” እንካችሁ ማለት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍን እንደመጥራት ይቆጠራል።    በነገራችን ላይ የአንድ ከተማ ቀለም ከመወሰኑ በፊት በከተማው ማስተር ፕላን ውስጥ ዕቅዱ መካተት አለበት። የአዲስ አበባ ከተማ ማስተር ፕላን ደግሞ ቀለምን በተመለከተ የሚለው አንዳች የለውም። በማስተር ፕላኑ የሌለውን መርህ ለመተግበር መሞከር በራሱ አጠያያቂ ነው። አንዳንድ የአሜሪካ፣ የካናዳ፣የአውሮፓና የእስያ ከተሞች በማስተር ፕላናቸው ውስጥ “City Color Planning” ዲፓርትመንት አላቸው። በዲፓርትመንቱ ውስጥ የከለር አማካሪዎችና ኢንቫይሮመንታል ሳይኮሎጂስቶች፣ የከተማ ፕላነርስና አርክቴክቶች፣ ሠዓሊዎች፣ ግራፊክ ዲዛይነሮችና የታሪክ ባለሙያዎች ተካትተው በይነዲስፒሊናዊ በሆነ መልኩ የቀለም ፕላኒንግ ንድፍ ያወጣሉ። አንድ ሕንፃ ከመገንባቱ በፊት ልክ እንደ ግንባታ ፈቃዱ የቀለሙም ፈቃድ በቅድሚያ ዲዛይን ውስጥ ተካትቶ ይጠናና ውሳኔው ይሰጣል። ስለዚህም የትኛውም የከተማ ቀለም ከመወሰኑ በፊት ፕላኒንጉ በማስተር ፕላኑ መታቀፍ አለበት። ይህ ባልሆነበት የከተማን ቀለም መወሰን  እንደ ሕገወጥ ግንባታ መቆጠር አለበት። አቅሙ ካለ ከሁሉም አስቀድሞ ማስተር ፕላኑ ውስጥ የከለር ፕላኒንግ መካተት አለበት። ይህ በኮሚቴ የሚወሰን ርዕሰ ጉዳይ አይደለም።  አንዳንዶቻችሁ በዚህ ሥራ ተሳታፊ ሆኜ የበኩሌን እንዳበረክት ስትጠይቁኝ ነበር። እስከ አሁን ባለው መረጃ በግልፅ ከሚመለከታቸው የከተማ ኃላፊዎች በሥራው እንድሳተፍ የተደረገ ጥሪ የለም፣ በእርግጥ አንድ ወጣት አርክቴክት (በኮሚቴው ሳይኖር አይቀርም) በግል ጠይቆኛል። በእኔ አረዳድ ጥያቄው መቅረብ ያለበት  በግለሰቦች ሳይሆን ከሚመለከታቸው ኃላፊዎች መሆን አለበት ባይ ነኝ። ብዙውን ጊዜ ደግሞ ውሳኔዎች በችኮላ ስለሚሰጡ፣ እንደ እኛ ዓይነት ባለሙያዎች ውሳኔ አሰጣጡን ልናዘገይ ስለምንችል እንደ እንቅፋት ሳንቆጠር አንቀርም። መኪና ማርሽ፣ ነዳጅ መስጫና ፍሪሲዮን ብቻ አይደለም ያለው። ፍሬን የሚባል መቆጣጠሪያም አለው። በአብዛኛው በፖለቲከኞች ዘንድ ፕሮፌሽናልስ እንደ “ፍሬን” ብቻ ነው የሚታዩት! ፍሬኑ ተገፍቶ በማርሽና በነዳጅ መስጫ ብቻ ምን እንደሚደርስና የት እንምንደርስ አብረን የምናያው ይሆናል።


_______________________________________


                            ጌታሁን ሔራሞ ከቴዎድሮስ ተ/አረጋይ ጋር

             ስለ ቀለም ሥነ ልቦናዊና አካላዊ ተፅዕኖ  በተመለከተ ከዓመታት በፊት ከወዳጄ ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ ጋር በ#ፍልስምና ቁ 3; መፅሐፉ ላይ መልካም ቆይታ ነበረን። ዛሬ ቴዲ ከመፅሐፉ ቀንጭቦ በመውሰድ ገፁ ላይ ያጋራውን እኔም ላካፍላችሁ ወደድኩ። ምናልባት ዘርዘር ባለ መልኩ ለመረዳት ለምትፈልጉ ምላሽ ሊሆን ይችላል ብዬ አስባለሁ።
ቴዎድሮስ:- ቀለማት በሥነ ልቡናዊና አካላዊ ማንነታችን ላይ የሚያሳድሩት የተለያዩ ተፅእኖዎች አሉ ብለናል፡፡ ባህሪያችንን እንዲለውጡ ያደረጋቸው እኛ ከቀለማቱ ጋር ያለን መለማመድ ነው ወይስ ተፈጥሯዊ ጠባይ ኖሯቸው?
ጌታሁን:- ይህ ጥያቄህ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ከአንድ ሰው ጋር የነበረውን ቆይታ ሲያጠናቅቅ “አንተ ከእግዚአብሔር መንግሥት የራቅህ አይደለህም” በማለት የተናገረውን እንዳስታውስ አደረገኝ፡፡ እኔም ከምታቀርብልኝ ጥያቄዎችህ ተነሥቼ እልሃለሁ፦አንተ ከቀለም ፍልስፍናና ሳይንስ የራቅህ ሰው አይደለህም፡፡ ለምሳሌ ከላይ ባነሳኻው ጥያቄህ ውስጥ የቀለማት አካላዊና ሥነልቡናዊ ተፅዕኖዎች ( psychophysiological impacts) መንስኤን በተመለከተ እንደ ፍራንክ ማሂንኬ ያሉ የዘርፉ ጠበብት ከሚያስቀምጡት ስድስት ምክንያቶች ውስጥ ሁለቱንና ዋናዎቹን አንስተሃል፡፡ ከተፈጥሯዊው መንስኤ እንጀምር፡፡ ተፈጥሯዊ ስንል ግን የቀለሙንም የተመልካቹንም ማካተት አለብን፡፡ የቀለማት ሥርወ ምንጭ የብርሃን ሞገድ እንደሆነ ቀደም ሲል አንስተናል፡፡ ታዲያ የዕይታ ታሪክ በዓይናችን ተጀምሮ እዚያው በዓይናችን የሚጠናቀቅ አይደለም፡፡ ቀለም ተሸካሚው የብርሃን ሞገድ በዓይናችን መስኮት ገብቶ ውስብስብ በሆነው የነርቭ መዋቅራችን ጎዳና እስከ አንጎላችን ድረስ ይዘልቃል፡፡ ታዲያ ጉዞው የሽርሽር እንዳይመስልህ! ማዕከላዊውን የአንጎል ክፍላችንና (hypothalamic midbrain region) አንጋፋ ዕጢዎቻችንን (Pineal and pituitary glands) ቀስቅሶ ልዩ ልዩ ስሜቶችን ለመፍጠር ነው፡፡ ለምሳሌ አረንጓዴና ሰማያዊ ቀለም በብርሃን መልክ ወደ አይጥ አንጎል በሚላኩበት ጊዜ በአይጡ መላ አካሉ ላይ የድብርት ሆርሞኖች ተለቀው እንቅስቃሴው ሁሉ ይገታል፡፡ እንዲሁም ዶሮ ቀይ ቀለምን በብርሃን መልክ በምታይበት ጊዜ እንቁላል የመጣል አቅሟ ይጎለብታል፡፡
ቴዎድሮስ፦ ጥናቶቹ ከአይጦችና ዶሮዎች ባለፈ በሰዎች ላይስ ምን ውጤት አምጥተው ታዩ?
ጌታሁን፦ በሰዎች ላይም አያሌ ጥናቶች ተደርገዋል፡፡ ለምሳሌ ራይካርድ ኩለር የተባለ ሳይንቲስት በ1976 (እ.ኤ.አ.)በስድስት ወንዶችና ስድስት ሴቶች ላይ ያደረገው ጥናት፤ ቀለማት በአንጎል ሞገድ ምትና በነርቭ መዋቅሮቻችን ላይ የሚያሳድሩትን አካላዊም ሆነ ሥነ ልቡናዊ ተፅዕኖ ሳይንሳዊ በሆነ መልኩ ያመላከተ ሆኗል፡፡ በጥናቱም መሠረት ግራጫ ቀለም ውስጥ ለሦስት ሰዓታት ያህል የቆዩ ሰዎች የ“አልፋ” የአንጎል ሞገድ እንቅስቃሴ (alpha brain-wave activity) በመሳሪያ በሚለካበት ወቅት በጣም ከፍተኛ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ እንደ ግራጫ ያሉ ደብዛዛ ቀለማት ትኩረትን የመሳብ አቅማቸው በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ሰዎቹ አካባቢውን በመርሳት ለራሳቸው ጉዳይ ንቁ (concisous) ለመሆን በመገደዳቸው ነው፡፡ ስለዚህም ግራጫ ቀለም በተቀባበት ክፍል የተቀመጠ ሰው ሁሌም ስለ ራሱ ሁኔታ በማጠንጠን ስለሚጠመድ ውጥረቱ ሊጨምርና ራሱን ለማጥፋት ሊነሳሳ ይችላል፡፡ በተቃራኒው ሞቃት የሆኑ ቀለማት (ቀይ ፣ ቢጫ ፣ ብርቱካናማ) በተቀባበት ክፍል ለተወሰኑ ሰዓታት በምንቀመጥበት ወቅት የሚጨምረው የ“ቤታ” የአንጎል ሞገድ ምት(beta brainwave activity) ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ምት በሚያይልበት ወቅት አንጎላችን ለራስ እንቅስቃሴ ዕውቅናን ይነፍግና (Unconcious state) በአካባቢያችን ሁኔታ መመሰጥ ይጀምራል፡፡ ተመስጦው እየጨመረ በሄደ ቁጥር ብዙ ደም ወደ አንጎላችን ስለሚላክና ልባችንም በዚሁ ሥራ ስለሚጠመድ በቆይታ የልብ ምታችን እየቀነሰ ሊሄድ ይችላል፡፡ ስለዚህም አካባቢያችንን ዲዛይን በምናደርገበት ወቅት እነዚህን ሁለቱንም ጫፎች (understimulation and Overstimulation) ማስወገድ አለብን ማለት ነው፡፡ እንግዲህ እስከ አሁን ያነሳሁልህ ከስድስቱ የቀለማት ተፅዕኖ መንስኤዎች ውስጥ አንዱና ተፈጥሯዊ ስለ ሆነው ስለ ሥነ ሕይወታዊው (biological reactions) ሥርዓት ነው፡፡    (አሁን #ፍልስምና ፫;  መፅሐፍ ገበያ ላይ የለም። ሆኖም ሙሉ ቃለ መጠይቁን ጃፋር መጻሕፍት ጎራ ብሎ ከ “ ፍልስምና ፩ +፪ + ፫ “ መጽሐፍ ማግኘት ይቻላል።)

_________________________________________________

                         አቦሌ
                        ( በእውቀቱ ስዩም)


        ከማውቃቸው ሰዎች መሀል በነውጠኝነቱ ወደር የሌለው አቦሌ ነው፤ ከብዙ ጊዜ በሁዋላ አንድ የጫማ መሸጫ ቤት ውስጥ ሳገኘው ገረመኝ፤ በፊቱ ያለው ውስብስብ ሰንበር የቀለበት መንገድ ይመስላል፤ ግንባሩ ላይ የብረት ቦክስ ጠባሳ አለ፤ ግራ ጉንጩ ላይ የሰንጢ ጭረት ይታያል፤ ማላመጫው ግድም የኮብልስቶን ምልክት ታትሟል፡፡
የባጥ የኮርኒሱን ስናወጋ ከቆየን በሁዋላ።
“ስማ ፤ ያለፉትን አራት አመታት ብዙ መንፈሳዊ መጻህፍት በማንበብ አሳልፍያለሁ፤ ከራሴ ጋራ ተመካክርያለሁ፤ ሁሉንም አውጥቼ አውርጄ ጌታ ቡድሀን ተቀብያለሁ፤ የድሮው አቦሌ እንደሞተ ቁጠረው” አለና ትካዜ የተቀላቀለበት ፈገግታ አሳየኝ፡፡
ወዲያው አንድ ሰውዬ ገብቶ ንግግሩን አናጠበው፤
“ካልሲ አለ?” አለ ሰውየው፡፡
“ይሄ የጫማ መሸጫ ቤት ነው፤ ካልሲ እንዴት ትጠይቃለህ?; አለ አቦሌ፡፡
“ጫማ ቤት ውስጥ ካልሲ መጠየቅ ምን ነውር አለው? ኬክ ቤት ገብቼ ካልሲ የጠየቅሁ አስመሰልኸውኮ”
አቦሌ ሰውየውን ትክ ብሎ አየው፥ አስተያየቱ የዘጠኝ ቡዳ አስተያየት ድምር ነው፤ ከዚያ ቡጢውን ጨበጠ፤ ከንፈሩን ነከሰ፥ ከገዛ ሀይሉ ጋር ታገለ፤ በመጨረሻ በረጅሙ ተነፈሰና፤ “እባክህ ለግልና ላካባቢ ሰላም ሲባል ተፋታኝ” አለው፡፡
ሰውየው መሰስ ብሎ ወጣ፡፡
“እውነትም ተለውጠኻል; አልኩት፡፡
“ቀላል ተለውጫለሁ፤ ከሁለት አመት በፊት ቢሆን ይሄን ሰውዬ ጎድኑን እንደ አሮጌ ሳጠራ ጠርምሼለት ወህኒ ወርጄ ነበር፤ ወህኒ ወርጄ ሁለት እስረኛና አንድ ዘበኛ መግደሌ አይቀርም ነበር፤ “እባክህ; ከሚል ቃል ጋራ የተዋወቅሁት በቅርብ ነው! ጌታ ኢየሱስ እንደ ርግብ የዋህ እንደ እባብ ብልህ ሁኑ ይላል፤ ይቅርታ አድርግልኝና እኔ በዚህ ህዝብ ላይ ብልህ ልሆንበት ምኞት የለኝም፤ እኔ እንደ ርግብ የዋህ እንደ ሰርከስ እባብ ገራም ነኝ”
“እንዲህ ተለውጠህ ማየት ደስ ይላል; አልኩኝ ልቤ ተነክቶ፡፡
“ክንዴ ላይ የነበረው ንቅሳት ትዝ ይልሀል?” አለኝ፡፡
“ደቁሰው” የሚለውን” አልኩ እየሳቅሁ፡፡
“አዎ ! ባለፈው ታቱ የሚሰራው ልጅ በጠባዬ አዲስነት ተገርሞ #ቁ” ን ወደ “ጉ” ቀይሮልኛል”
“ጌታ ቡድሀ የተመሰገነ ይሁን; አልኩት፡፡
“አሜን!”
አቦሌ ጫማ ቤቱን በጊዜ ዘግቶ ወደ አንድ ግሮሰሪ ሄደን ትንሽ ቀማመስን፤
“ስራ ፈልግልኝ፤ ይሄ ስራ አይመጥነኝም” አለ አቦሌ፤
ካገባደደ በሁዋላ ሁለተኛውን ቡትሌ፤
“ምንድነው ችግሩ?” ስል ጠየኩት፤
#ጫማ ሊለኩ ጫማቸውን ሲያወልቁ ከካልሲያቸው የሚያፈልቁት ጨረር አስመረረኝ፤ ሳስበው ያፍንጫ ካንሰር ሳይዘኝ አልቀረም፤ ያፍንጫ ካንሰር የሚባል ነገር ከሌለ በኔ ጀምሯል”
“ይሄን ያህል?”
“ተወኝ ባክህ! አንዳንዴ ሳስበው ፤ ላለፈው ሀጢያቴ ቅጣት ይሆን እላለሁ?; አለና ተከዘ፡፡
ትንሽ አሰብኩና ፤
“በሰኔ ስድስት ብሄራዊ ትያትር የማቀርበው ሾው አለኝ ፤ ደና ዝግ ከዘጋሁ ቦዲጋርድ አድርጌ እቀጥርሀለሁ” አልኩት፡፡
“ቦዲጋርድነት አልፈልግም፤ አንተም የኢትዮጵያ ህዝብ ስለሚወደህ ቅጥረኛ ጠባቂ አያስፈልግህም፤ ከፊትህ ያለው ስጋት ርጅና እና በሽታ ነው፤ ደምብዛት እና ጉብጠትን ደሞ በቦዲጋርድ አትመክታቸውም” አለና ተፈላሰፈ፡፡
“ሌላ ምን ስራ ልሰጥህ እችላለሁ?”
“ለምን መኪና ገዝተህ ሾፌር አታረገኝም፤ ቀለል ያለ ቴስላ ግዛ ! እኔ እሱን እሾፍርልለሀለሁ’፤;
“መንጃ ፍቃድ አለህ?”
“መንጃ ፈቃድ ባይኖረኝም ማሽከርከር እችላለሁ”
“እንደሱማ አይሆንም፤; ገገምሁ፡፡
አቦሌ ዘጠነኛውን ቢራ ጨለጠና እንዲህ አለ፤
“የመንጃ ፍቃድ ትምህርት ቤት ያለው ጎረቤት አለኝ፤ መንጃ ፈቃዱን ዱቅ እንዲያረገው እለማመጠዋለሁ፤ እምቢ ካለ ሰላሳ አምስት ጥርሱን አራግፍለታለሁ”
_______________________________________________

                             ኑር ባታምንም!!
                                    (ዮሐንስ ሞላ)

           “በአንድ ሳምንት ውስጥ ሦስት ሴቶች አዲስ አበባ ውስጥ ራሳቸውን ከፎቅ ወርውረው ገድለዋል።”  
ራስን መግደል ያስደነግጣል። ከፎቅ መውደቅ ያስደነግጣል። በአንድ ሳምንት ውስጥ ሶስት (ያልተቆጠረና ለዜና ያልበቃ አይጠፋም) ሰው አንድ አይነት አሟሟት መሞቱን መስማት ያስደነግጣል።  የአሟሟትም ወረት አለው? ፋሽን አለው? በተለያዩ ጊዜያት የሰማናቸው አይነት አሟሟቶች አሉ። ፎቅ ስለበዛ የሚል ነሆለልም አይጠፋም።
ያም ሆነ ይህ የአእምሮ ጤንነት በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ያመላክታል። ወጉን፣ ባህሉን፣ ማንነቱን፣ ቀስ እያልን እየናድነው መተከዣ ጎረቤት ለማጣት እንለፋለን። ልባዊ ጓደኝነት ጥንታዊ ሆኗል። ለአስር ብር የሚሸጠን ብዙ ነው። ከቁስ ውጭ ሌላ ምንም እንዳናስብ ወላጆች (የጠቀሙን መስሏቸው ሁሉን በማሟላት) እና ባለስልጣናት እየታገሉ ነው። እምነታችንን እንድንተው፣ በመንፈስ እንዳንጽናና በስልጣኔ ስም ሊያስጥለን ደጅ የሚጠናው ብዙ ነው።
ድራግ እንደ ማስቲካ ነው አሉ። ማኅበራዊ ሚዲያም አለ። መለስ ቀለስ ብሎ ለማሰብ በምን ፋታ?
ወድቆ ለመሞት ሲታሰብ፣ ድንገት ብተርፍስ? ብሎ ማሰብ ቢቻል ጥሩ ነበር። ነበር። ነበር።
ራስ ወዳድ ሆነን ራሳችንን ለማጥፋት ስንቆርጥ፣ ለመሞት ወድቀን እምቢ ቢለን፣ ከነስብርብራችን ተቀብለው የሚያስታምሙን ቤተሰቦች አሉን እና አንጨክን። እንጠቅማለን። ጨክነን የምንተዋቸው የሚወዱን ብዙ አሉ።
ኑር ባታምንም!!

__________________________________________


                             የአእምሮ ጂምናስቲክ የሚያሰራ የዘመኔ ድንቅ ደራሲ


             ሌሊሳ ግርማ እስካሁን ወጥ፟ ልቦለድ አልፃፈም። ስራዎቹ አጫጭር ታሪኮች፣ ወጎችና ሃሳብ ላይ ያተኮሩ ማሰላሰሎች ናቸው። የሌሊሳን መፅሐፎች አንስቼ ጭልጥ አድርጌ አልጨርስም። በጭራሽ ያን አላደርግም። የሚፅፋቸው አጫጭር ታሪኮችና ወጎች ከሚፈጥሩብኝ መደነቅና መብሰልሰል ጋር አብሬ መቆየትን እመርጣለሁ። አንዱን አጭር ታሪክ ሳላጣጥም ወደ ሌላ አልሄድም። አንዱን ወግ በደንብ ሳልጫወትበት ወደ ሌላ ፅሁፍ አልሻገርም። ታዲያ ስጫወት የምጫወተው ከሌሊሳ ጋር አይደለም። ከራሴ ጋር ነው። እርሱማ አንዴ ኳሱን ሜዳው ላይ ጥሎልኝ ሄዷል። ሌሊሳ የአእምሮ ጂምናስቲክ የሚያሰራ የዘመኔ ድንቅ ደራሲ ነው።
ብዙ ጊዜ የምናነባቸው መፅሐፎች እራሳቸው ጀምረው የሚጨርሱ ናቸው። ለአንባቢ የተተወ ክፍት ቦታ (Space) የላቸውም። ያ ከሰለቸህ ሌሊሳ አጭር ታሪክ ጀምሮ እንድትጨርሰው መንገድ ሊያመቻችልህ ይችላል፤ ያኔ በራስህ መንገድ ትጨርሰዋለህ። #የንፋስ ህልም; ላይ ያለች አንድ አጭር ታሪክን ልብ ብትል እንደዚያ ነው...
- አጫዋች ፍልስፍናዊ ወጎችን ከፈለግህ ሌሊሳን አንብብ !!
- ሌላ አይን የሚፈጥርልህ ደራሲ ከፈለግህ ሌሊሳን አንብብ !!
- ከተራ ነገሮች ሃሳብ ማስገር ከፈለግህ ሌሊሳን አንብብ !!
ሌሊሳ በአንክሮ መነበብ ያለበት ደራሲ ነው !!
ሌሊሳን በላቀ መረዳት ውስጥ ሆነን ልናነበው የሚገባ ደራሲ ነው !!...
የፃፋቸው ስድስት መፅሐፍቶች እኒሁና፡-
1- የንፋስ ህልም አና ሌሎች የምናብ ታሪኮች
2- አፍሮጋዳ
3- መሬት አየር ሰማይ
4- የሰከረ እውነታ
5- እስቲ ሙዚቃ እና ሌሎችም አጫጭር ታሪኮች
6- ነፀብራቅ
(Book for ALL)

Read 576 times
Administrator

Latest from Administrator