Saturday, 21 May 2022 11:21

ከአፈር ዘገና እስከ አስፋልት እንብርክ!

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(1 Vote)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
እኔ የምለው... የግንቦት ፀሀይ እንዲህ እሚያንቀለቅለን የተፈጥሮ ጉዳይ ነው ወይስ የሆነ ‘መልእክት’ ነገር አለው! (ብዙ ነገር ግራ ስለገባን በሁሉም ነገሮች ላይ ትርጉም መፈለግ ለመደብንና እኮ ነው፡፡ ልክ የቀድሞው ግንቦት ወር የዝናብና የበረዶ የነበረ ይመስል፣ “የግንቦት ፀሀይ ምን ቆርጦት ነው አንድ በአንድ ልብሳችንን የሚያስወልቀን ያሰኛል፡፡ እሺ አጅሬው ደግሞ ይሄን ውሰድና በአልጋ ልብስ አይነት... ‘ኮምፈርት’... ነው የሚሉት!)  ስፋውና “ይኸውላችሁ አጅሬው በአሽሙር ፖለቲካው ውስጥ ገባላችሁና አረፈው፡፡ እነኚህ ሰዎች በቃ ፖለቲካ ካላወሩ ወዮልን ለእናንተ የሚል ንግርት አለባቸው እንዴ!” በል አሉ፡፡
ስሙኝማ ይሄ ቦተሊካ የሚሉት ነገር አልፎ፣ አልፎ “ላቭ ኢዝ ብላይንድ” ምናምን ነገር ውስጥ ሁሉ እየገባ ይበጠብጣል፡፡ አንድ ረዘም ላለ ጊዜ ውጭ የኖረ ሰው፣ የትዳር አጋር ይዞ ለመሄድ እዚህ ይመጣል አሉ፡፡ ያው ሁሉም ነገር ቀደም ሲል በአብዛኛው በስልክ አልቆ ቤተሰቦቿ “እኛም ፈቅደናል ይሁን፣” ብለዋል፡፡ በአካል የተዋወቁት አሁን መጥቶ ቤታቸው ድረስ ሲሄድ ነው፣ ነገርም የተጀመረው እዚህ ላይ ነው፡፡ በወሬ መሀል፣ በዘንድሮው አነጋገር፣ የየት አካባቢ ሰው እንደሆነ ይጠይቁትና ይነገራቸዋል አሉ፡፡ ተሰናብቶ ከሄደ በኋላ ግን ቤቱ ቀውጢ ይሆናል፡፡ አንድ አጎት ነው፣ እንደዛ አይነት ነገር የሆነ ዘመድ ነው አሉ፣ እንዴት ተደርጎ በሚል “ያዙኝ ልቀቁኝ” ያመጣው፡፡
“ልጃችንን በምንም አይነት ለእነሱ አንሰጥም!” አለ አሉ፡፡ አያችሁልኝማ...እዛ ቤት ውስጥ ሌላ ሰው ሳያስከትል በእንግድነት የመጣው ሙሽራው ብቻ ነበር፡፡ ግን ዘመድ የተባለው ሰውዬ “ለእነሱማ አንሰጥም!” ያለው፣ ምናልባትም ሙሽራው የተገኘበትን ማህበረሰብ አባላት በሙሉ አንድ ሳጥን ውስጥ በመክተት ነው፡፡ የቦተሊካችንን አስቀያሚነት አያችሁልኝ! ሁለት ነገሮች አሉ...አሳዛኙ ወላጆቿን ጨምሮ ሌሎች ዘመድ አዝማድ የተባሉትም ደገፉትና “ልጃችንን አንሰጥም!” የሚል የጋራ አቋም አይነት ነገር ያዙ፡፡ ደስ የሚለው ነገር ደግሞ ልጅቱ የራሳችሁ ጉዳይ ብላ ማናቸውም ሳይጠረጥሩ እብስ ብላ ከሰውየዋ ጋር ውቅያኖስን ተሻገረችላችሁ! ልክ ነዋ...ታዲያ እጩው ሙሽራ ከስንት ዘመን በኋላ እንደገና “አባትሽን ባስጠይቅ ስለፍቅር አይገባኝም አሉ...” ምናምን ብሎ ይዝፈን እንዴ!
ስሙኝማ...ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...እንደው ከእለታት አንድ ቀን የአፈር መሸርሸር አጀንዳ ሆኖ እንነጋገር ቢባል ጉድ አይወጣም?!  እነእንትና ‘ግልጥና ግልጡን’ እንነጋገራ! “ከአብሮ አደግህ ጋር አትሰደድ” የሚባለው ነገር እኮ ዝም ብሎ የተወረወረ አባባል አይደለም!
እናማ...ወዳጆቼ ለአፈር መሸርሸር እኮ የእናንተም እጅ አለበት፡፡ (“የእኛም” ብሎ ማሟሟቅ ይቻላል፡፡ ያው የ‘አነካካው’ ዘመን አይደል!) አሀ... ልክ ነዋ “እንትን የተደረገበትን እርጥብ አፈር ዘገን አድርገህ ኪስህ ከትተህ መከተል ነው፣” እየተባልን የታየውን ስንት ‘አድቬንቸር’ መርሳት ልክ አይደለማ! “ሮጣ ወደ አንተ ትመጣለች” እየተባልን ጭራሽ ኪሳችንን የቆሸሸ መሬት የተወለወለበት አሮጌ ጨርቅ አስመስለን ‘ሮጠው ያመለጡንን’ ሊስት እኮ ማቅረብ ይቻላል፡፡
እኔ የምለው... በሪቨርስ ማርሽ እዛ ድረስ እየተንደረደራችሁ “የዋህ ዘመን!” የምትሉ ሰዎች ተረጋጉማ! ገና ለገና ‘ሞደርኑን’ ስላላወቃችሁት “የእኛ ብቻ አሪፍ!” ብሎ ነገር በራሱ አሪፍ አይደለማ! ኮሚክ እኮ ነው... አሁን በሀገር ሰላም በመከራ ታሽቶ ንጹህ የሆነ ጃኬት ኪስ ውስጥ ጭቃ ዘግኖ መክተት ምን የሚሉት ‘መስተፋቅር’ ነው! አሀ...“ልክ ይህንን ነው የምትመስይው ብለህ በአሽሙር መናገርህ ነው!” ብትል ምን ይባላል!
የምር ግን...እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ...አንዳንዴ እኮ የዋህነት በቃ አሪፍ ነው፡፡ ልክ ነዋ...እንቅልፍ ማጣት የለ፣ መበሳጨት የለ... “ቲማቲም አንዷ ራስ ሰባት ብር ከስሙኒ ልትሆን ነው; ብሎ ነገር የለ! በቃ ዘገን አድርጎ ኪስ ከከተቱ በኋላ ቀሪውን ሥራ ለእርሱ መልቀቅ! ‘ሲምፕል’ እንዲህም አይደል!                                                                                                                                                 እናላችሁ....ያኔ የ‘ሀቲ ሜር ሳቲ’ መመልከቻ ፍራንክ ያጣ ኋላ፣ ኋላዋ እየተከተለ “ምነው አፈር ያለበት ስፍራ ደርሳ ተፈጥሮ ባጣደፈልኝ!” ባይል ነው! ቂ...ቂ...ቂ...
ስሙኝማ...እንግዲህ ጨዋታም አይደል...
ታሜም አልተኛ ሞቼም አልቀበር
ጨርሼ ሳላየው የዛችን ልጅ ነገር
የምትል ስንኝ አለች አይደል! አሪፍ አይደለች! ግን ያለንበት ዘመን ማናቸውንም ነገር “ጠምዝዝ፣ አስጠምዝዝ” ነገር ስለሆነ በስንት በኩል ሊተረጎም እንደሚችል አስባችሁት ታውቃላችሁ! በመጀመሪያ ደረጃ ይዞ የማይለቅ ‘ላቭ’ ስለጨመደደው “አግኝቻት ቁርጡን ካልነገረችኝ ምንም አይነት እረፍት አይኖረኝም!” ምናምን ነገር ለማለት ሊሆን ይችላል፡፡ ይቅናውማ!
በሁለተኛ ደረጃ ግን ወይ ቢንጠራራ፣ ቢንጠራራ አልደርስባት ብሎ፣ ወይ ደግሞ ጥያቄ ሲያቀርብ “እኔ የአንተ ገርልፍሬንድ ልሆን! እንደው ዘመድ፣ ጎረቤት ቢሰማ ምን ይላል፤ ጭራሽ በተከበርኩበት ሀገር መሳቂያ ልሁንልህ!” የሚል ከ‘አቢዩዝ’ በምንም የማይተናነስ መልስ ሰጥታው “ምን አለ እንዲህ የኮራሽበትን የተወለወለ መልክሽን እግር የበዛበት ምንጣፍ አድርጎ ባሳየኝ!” ምናምን ማለት ሊሆን ይችላል፡፡ (ግጥሟ ለምን ወይ ደግሞ  በማን የተነሳ ትዝ ልትልኝ እንደቻለች ገና ራሴም ጠንቅቄ አላወቅሁም!) 
ስሙኝማ...
እስከመቼ ድረስ በብር አባብዬ
ገንዘቤን ላጣራ ወደሽኛል ብዬ፣
የምትል ነገር ነበረች አይደል! የምር ግን እኮ የሆነ አሪፍነት ነገር አለባት፡፡ ልክ ነዋ...እቅጩን “የፍራንክ እጥረት ገጥሞኛል፣” ከማለት ይልቅ ምክንያት መፍጠሩ እኮ መከራ ነው፡፡
“ስማ፣ ነገ ክትፎና ዋይን አትጋብዘኝም?”
“ምን መሰለሽ ከአሜሪካ ገንዘብ የሚልኩልኝ ዘመዶቼ ችግር ገጥሟቸው...”
“አንተ... ያ ያሳየሁህን ጫማ ግዛልኝ እንጂ! አንዴ ካለቀ እኮ ተመልሶ የዛ  አይነት ፋሽን ላይመጣ ይችላል!”
“ለካስ አልነግርኩሽም...”
“ምኑን ነው ያልነገርከኝ?”
“የጓደኛዬ መኪና ተበላሽታ አበደርኩትና አሁን ኪሴ ብትገቢ እጅሽ አቧራ በአቧራ ነው የሚሆነው!” ስሙኝማ... ዘንድሮ በየአስፋልቱ እየተንበረከኩ “አታገቢኝም?” ነገር ተስፋፍቷል ነው የሚባለው፡፡ ድሮ አፈር ዘገና፣ አሁን አስፋልት እንብርክ...ኸረ ይቺን ምድር ፋታ ስጧት! ቂ...ቂ...ቂ...
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 1518 times