Print this page
Saturday, 06 October 2012 13:34

የፍቅር ቀን ሽርሽር፣ የአመት በዓል ድግስ፣ የኦሎምፒክ ውድድርና ልብወለድ መፅሐፍ... ዘመዳሞች ናቸው

Written by  መልካሙ ተክሌ melkamutekle@gmail.com
Rate this item
(3 votes)

ላይ ላዩን ስናስብባቸው፣ “ጥቅም” የሌላቸው ይመስላሉ - (“Art for Art’s Sake” እንደሚባለው)

በተግባር ሲታዩ፤ የሚያጓጉና የሚያስደስቱ ይሆኑብናል - (በፕሪሜር ሊግ ወይም በሆሊውድ ፊልም እንረካለን)

“ጥቅም” የማያስገኙ፤ “እርካታ”ን ግን የሚሰጡ - (ይህን እንቆቅልሽ ስንፈታ ነው ምንነታቸውን የምናውቀው)

ግን፤ ትልቅ ጥቅም አላቸው፤ ጥቅማቸው “መንፈሳዊ” ስለሆነ በግልፅ ባይታየንም።

ልብወለድ ለማንበብና ፊልም ለማየት ብለን እንቅልፍ የምናጣው ለምንድነው? ምንስ ይጠቅመናል? እንዲሁ ስታስቡት፣ ለልብወለድና ለፊልም እንዲያ መንገብገባችን አይገርምም? “እውነትም...” ብለን ማሰብ ስንጀምር ግን፣ አልዋጥ ይለናል። እንደ አዲስ “ኪነጥበብ ምን ይጠቅመናል?” ብሎ ጥያቄ ማንሳት፤ አጉል “መፈላሰፍ” ይሆንብናል።

የኦሎምፒክ ውድድርና የፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎችን ለምን ትከታተላለህ? ልብወለድ መፅሃፍ ለማንበብና ፊልም ለማየት... ገንዘብሽን፣ ጊዜሽንና ጉልበትሽን ለምን ታጠፊያለሽ? ...ጥያቄዎቹን ለመመለስ ይቅርና፤ ለመስማትም ትዕግስት እናጣለን። ጥያቄዎቹን ስለምንንቃቸው አይደለም። ግን በደፈናው፣ “እንዴት እንዲህ እጠየቃለሁ?” የሚል እልህ ይተናነቀናል። የንዴትና የንጭንጭን ስሜት በተቀላቀለበት እልህ እንንጨረጨራለን። የልደት ቀንና የፍቅር ቀን ለምን ታከብራለህ? ለሰርግና ለዓመት በዓል ድግስ ገንዘብ ማፍሰስሽ ምን ይጠቅምሻል?... ተብለን ስንጠየቅም እንበሳጫለን። የሚያጠግብ የሚያረካ መልስ ስለምናጣ ሊሆን ይችላል።

በጣም የምታደንቁትን አትሌት ወይም የእግር ኳስ ተጫዋች ሲያናንቁባችሁ ምን እንደሚሰማችሁ ታውቁታላችሁ። የምትወዱትን ዘፈንና አርቲስት ሲያጣጥሉባችሁም እንደዚያው። ልባችሁን የነካ ልብወለድ መፅሃፍ ላይ፣ ወይም ልክ እንደራሳችሁ ጉዳይ የምትጨነቁለት ገፀባሕሪ ላይ፤ የሚያሾፍ ሰው ቢገጥማችሁ ምን ያህል እንደምትበግኑ ይታያችሁ። የልደት ቀን ማክበራችንም ሆነ ለዓመት በዓል ድግስ ማሰናዳታችን፣ የኦሎምፒክ ውድድር መከታተላችንም ሆነ ልብወለድ ማንበባችን፤ ከነጭራሹ ጥያቄ ውስጥ መግባታቸው ያንገበግበናል። በቃ፤ ህልውናችን፣ ሰብዕናችን፣ ማንነታችን የተደፈረ ሆኖ ይሰማናል። ከህይወታችን ጋር እጅጉን የተሳሰሩ ከመሆናቸው የተነሳ፤ ፈፅሞ ለ”ድርድር” ልናቀርባቸው አንፈልግም።

እሺ ይሁን...፤ ለድርድር አናቅርባቸው። ግን፤ ረጋ ብለን ስናስበው ደግሞ፤ እንዲያ የምንወደው የልደት ቀንም ሆነ የአዲስ አመት በዓል፤ እንዲያ የምንጓጓለት ልብወለድ ድርሰትም ሆነ የስፖርት ውድድር፤ ለምን እንደምንወደውና እንደምንጓጓለት፣ ለምን እንደምናከብረውና እንደምንሳሳለት ማወቅ የለብንም? ምንነቱንና ጥቅሙን (አገልግሎቱን) አብጠርጥረን ማወቅ አይኖርብንም? እንዴትስ አስችሎን ለማወቅ ሳንጥር እንቀመጣለን? ምናልባት፤ የኪነጥበብን ምንነት አልያም የዓመት በዓልን ጥቅም ለማወቅ፣ በማስረጃና በሎጂክ ትንታኔ ስንጀምር፣ ክብራቸው የሚኮስስብን እየመሰለን እንሰጋ ይሆናል። ግን ከንቱ ስጋት ነው።

ስለ ሳይንስና ስለ ቴክኖሎጂ ምንነትና ጥቅም ይበልጥ ባወቅን መጠንኮ፤ ለሳይንስ ግኝትና ለቴክኖሎጂ ፈጠራ የሚኖረን ክብርና ፍቅር ይበልጥ ይጨምራል። የረሃብ ወይም የጥም ስሜት ሲፈጠርብን፤ ለውኃ ወይም ለምግብ የሚኖረን ክብር የተራራ ያህል ገዝፎ ይታየን የለ! የምግብና የውሃ ጥቅም በተጨባጭ ስለሚታየን፤ ለንፁሕ ውኃና ለተስማሚ ምግብ የሚኖረን ክብር ጎልቶ ይወጣል። ቢሮ የሚሰራ ሰው፣ ለምቹ ወንበር ትልቅ ክብር የሚኖረው አለምክንያት አይደለም። ጥቅሙን (አገልግሎቱን) ስለሚያውቅ ነው። በቀሽም ወንበሮች ምክንያት፣ የአንገትና የጀርባ ህመም ተሰቃይቷላ።

የኪነጥበብም ሆነ የዓመት በዓል ክብር ገዝፎና ደምቆ በግልፅ ሊታየን የሚችለውም፣ ምንነቱን አብጠርጥረን ስናውቀውና ጥቅሙን ስንገነዘብ ነው። የኔ ሙከራም፤ የኪነጥበብ ምንነትና ጥቅም ላይ በማተኮር የማምንባቸውን ሀሳቦች በጥንቃቄ ማቅረብና ውይይትን መጋበዝ ነው።

ለትምህርትና ለስራ፣ ለቢዝነስና ለኑሮ በቀጥታ የሚጠቅሙ የሙያ መጻሕፍትን ማንበብ ከባድ ሸክም የሚሆንባቸው ሰዎች፤ የልብወለድ መጽሐፍ ለማንበብ ይጓጓሉ፤ ማንበብ ከጀመሩ በኋላም ማቋረጥ ያስጠላቸዋል። በጉጉት ቶሎ አንብበው ለመጨረስ እየፈለጉ፤ ቶሎ እንዳያልቅባቸው ደግሞ በስስት ይጨነቃሉ። ተከታታይ የቴሌቪዥን ፊልሞችን ተከራይተው፤ አይናቸው እስኪቀላ ድረስ ሲያዩ ያመሻሉ። “ይህቺን ልጨርስና እተኛለሁ” ይላሉ፤ ግን እንደገና በታሪኩ የተመሰጠ ልባቸው ተንጠልጥሎ ተከታዩን ክፍል ማየት ይቀጥላሉ። ሌሊቱን ያለእንቅልፍ ያሳልፋሉ። የፊልሙ 20ኛ ክፍል ገና ካልመጣና ሳምንት ሙሉ መጠበቅ ካለባቸው፤ ሳምንቱ ይረዝምባቸዋል።

ለልብወለድና ለፊልም እንዲህ የምንሆንበት ሚስጥሩ ምንድነው? (ኪነ ጥበብ ምንድነው)?

ምን አይነት ጥቅም ብናገኝበት ይሆን? (የኪነ ጥበብ አገልግሎት ምንድነው)?

ሁለቱ ጥያቄዎች (የምንነት እና የአገልግሎት ጥያቄዎች)፣ እርስ በርስ የተሳሰሩ ናቸው። ምንነቱን ካወቅን፣ አገልግሎቱን ለማወቅ አይከብደንም። አገልግሎቱን ከተገነዘብን፣ ምንነቱን ለመገንዘብ አይሳነንም። ለአንደኛው ጥያቄ ምላሽ ካገኘንለት፤ ሁለተኛውን ጥያቄ መመለስ አያቅተንም። ለዚህም ነው፤ አንዳንድ ሰዎች የኪነጥበብ ምንነት ላይ በማተኮር፤ ሌሎች ሰዎች ደግሞ የኪነጥበብ አገልግሎት ላይ በማተኮር ምላሽ ለመስጠት የሚሞክሩት። እኔም፤ የኪነ ጥበብ አገልግሎት (ወይም ጥቅም) ምንድነው የሚለው ጥያቄ ላይ በማተኮር ነው የምጀምረው። ለጥያቄው ምላሽ ይሆናሉ ተብለው የሚቀረቡ ሃሳቦች አሉ። ደግሞም ብዙ አይደሉም። በስፋት የሚታወቁት የምላሽ ሃሳቦች ሁለት ብቻ ናቸው። ለብዙዎቻችንም አዲስ አይደሉም። ሃሳቦቹን፣ በሙያ ቋንቋ ባይሆን እንኳ፤ በተለምዶ ቋንቋ እናውቃቸዋለን። “እያዝናኑ ማስተማር” ሲባል አልሰማችሁም? ይሄ የተለምዶ አባባል፤ አንድ ምላሽ ነው።

“የኪነጥበብ አገልግሎት፣ እያዝናኑ ማስተማር ነው” በሚለው ምላሽ በተደጋጋሚ ከሚጠቀሱት የአገራችን ሰዎች መካከል አንዱ፤ ዮሐንስ አድማሱ ነው። የኪነ ጥበብ አገልግሎት፤ ማህበረሰብን በማንቃት ማነፅና ለስራ ማነሳሳት፣ የአገርን ገፅታ መገንባትና አገርን ማልማት ነው ይላሉ - እነዚህኞቹ ወገኖች። የኪነ ጥበብ ጥቅም፤ በዚህም ሆነ በዚያ ለማህበረሰብ የሚጨበጥ የሚዳሰስ ለውጥ ማምጣት ነው፤ አልያም መሆን ይገባዋል በማለት ይከራከራሉ። ይህን ስትሰሙ፤ የሶሻሊዝም ወይም የፋሺዝም ጠረን ቢያፍናችሁ አፍንጫችሁ አልተሳሳተም። ለነገሩ ሶሻሊስቶቹና ፋሺስቶቹ ብዙ ልዩነት የላቸውም። በጣም ተቀራራቢ ናቸው። ህዝብንና አገርን፣ ቡድንና ማህበርን እንጂ፣ ግለሰብን የማየት ፍላጎት የላቸውም።

ከሶሻሊዝም ሰባኪያንና ምዕመናን አፍ የማይጠፉ ቃላት፤ “ማህበረሰብ” እና “ህዝብ”፤ “አብዮት” እና “ትግል” የሚሉ ናቸው። ኪነ ጥበብ የማህበረሰብና ህዝብ አገልጋይ መሆን አለባት ከማለትም አልፈው፤ “ለጭቁኖችና ለድሆች ትግል፣ ለወዛደርና ለአርሶአደሮች አብዮት... ማገልገል አለባት” ይላሉ። የፋሺዝም ሰባኪያንና ምዕመናን ደግሞ፤ “አገር” እና “ታሪክ”፤ “ባሕል” እና “ቋንቋ” የሚሉ ቃላትን ያዘወትራሉ። የአገር ታሪክን በማሳወቅ የአገር ፍቅርን ማጋጋል፣ የአገር ባህልንና ቋንቋን በመጠበቅ የአገር ገፅታን መገንባት፤ ዜጎች ለግል ጥቅማቸው እንዳያስቡ ማስተማርና ለመስዋእትነት ዝግጁ እንዲሆኑ ማነሳሳት... የኪነ ጥበብ ድርሻ ነው በማለት ምላሽ ይሰጣሉ። ከመጠነኛ የዜማ ልዩነት በስተቀር፤ የሶሻሊስቶቹም ሆነ የፋሺስቶቹ ምላሽ ተመሳሳይ ነው - የኪነ ጥበብ አገልግሎት፣ እያዝናኑ ማስተማር፣ መስበክ፣ ፕሮፓጋንዳ መንዛት ወዘተ...

ሁለተኛው ምላሽ፤ “ኪነ ጥበብ፣ ሌላ አገልግሎት የላትም” የሚል ነው። “ለኢንፎርሜሽን፣ ለእውቀት፣ ለስነምግባር ግንባታ፣ ለማህበረሰብ እድገት፣ ለአገር ልማት...” የሚሉ አገልግሎቶች የኪነጥበብ ድርሻ አይደሉም በማለት ሲሟገቱም፤ “ለኪነ ጥበብ የሚፈጠረው ለኪነ ጥበብነቱ ነው” ይላሉ። ከእነዚህ የአገራችን ሰዎች መካከል በተደጋጋሚ የሚጠቀሰው ሰለሞን ደሬሳ፤ ይህንን ሀሳብ ለማስረዳት የብስክሌት ምሳሌ ያነሳል። ልጆች ብስክሌት የሚያሽከረክሩት የትራንስፖርት አገልግሎት ፈልገው አይደለም፤ የሆነ ቦታ ለመጓዝና በፍጥነት ለመድረስ ቸኩለው አይደለም። በቃ ብስክሌት ለማሽከርከር ነው ብስክሌት የሚያሽከረክሩት። ኪነጥበብም እንደዚያው ለኪነጥበብነቱ ነው ይላል ሰለሞን ደሬሳ።

የዮሐንስ አድማሱና የሰለሞን ደሬሳ ምላሾችን፤ ባፈሩት ፍሬ እንመዝናቸው ካልን፤ የሚያስደስት ነገር አናገኝም።  “ኪነጥበብ ለኪነጥበብነቷ” ከሚለው አባባል ያተረፍነው ነገር የለም። በተቃራኒው፤ ኪነጥበብ በቆሻሻ እየተደፈቀች ነው። የፌስታል አይነት ከየሱቁ ገዝቶ የኤግዚቢሽን አዳራሽ ውስጥ ደርድሮ ስላሳየ አርቲስት የሚባልበት ዘመን ላይ ደርሰናል። አሁን ይሄ እንዴት ኪነ ጥበብ ይባላል? ብለን ብንጠይቅ ብዙም አያስኬደንም። “ኪነ ጥበብ አይደለም ለማለትስ ምን ምክንያት አለህ?” ብሎ ያፋጥጠናል። በእርግጥም፣ ኪነ ጥበብ አንዳችም ልዩ አገልግሎት ከሌላት፤ ኪነ ጥበብ የሆነውንና ያልሆነውን ለመለየት አይቻልም። ሌላው አርቲስት ደግሞ ገንዘብ ማውጣም አይፈልግም። የወዳደቁ ፌስቶሎችን ለቃቅሞ ያመጣና፤ ከአዳራሹ ጥግ ከምሮ ያሳየናል - ኪነ ጥበብ መሆኑ ነው። በአራት ማዕዘን፣ በክብ፣ በሦስት ማዕዘን ቅርፅ የተቆራረጡ ባለቀለም ወረቀቶችን ፍሬም ውስጥ ለጣጥፎ የሚመጣም አለ - ከስር የኪነጥበብ ስራው በስንት ሺህ ብሮች እንደሚሸጥ በመጥቀስ። ቀለሞቹን በዘፈቀደ ሸራው ላይ ደፋፍቶ፣ በብሩሽ ሞነጫጭሮ “ድንቅ” የሥዕል ጥበቡን የሚቀርብልንም ሞልቷል። ይህ ነው የሚባል ታሪክ የሌለው አጭር ልብወለድ፣ ጭራና ቀንዱ የማይታወቅ ቅዠት የሚመስል ረዥም ልብወለድ፤ የሚጨበጥ መልዕክት የሌለው ግጥም፤ ከዚህም አልፎ... ቃላት የሌሉት የፊደላት ስብስብም ግጥም ነው ተብሎ ይቀርባል ... ቧ፣ ሏ፣ ሟ፣ ጓ... እንዲህ ፊደላትን አጓርቶ፣ ገጠምኩ የሚል ሰውም በመድረክ ይቀርባል። ... በእርግጥም፤ “ኪነጥበብ ለኪነጥበብነቷ” የሚለው መፈክር... ኪነጥበብ ጥቅም የለሽና አገልግሎት አልባ ከሆነች፤ ፍሬውን ከገለባው፣ አሪፉን ከቀሽሙ፣ ድንቅና ውብ ፈጠራውን ከውዳቂ የቡቱቶ ክምር ለይተን የምናውቅበት ሚዛን አይኖረንም። ማንኛውንም የሥራ ውጤት የምንመዝነው፤ ለሰው በሚሰጠው ግልጋሎትና ጥቅም ነው። ለጌጥ (ለዲኮሬሽን) እንዲሁም እንደ ሃብት ማከማቻነት ከሚያገለግሉት ወርቅና አልማዝ ጀምሮ፤ ምግብና ልብስ፣ ሞባይልና ላፕቶፕ፣ መኪናና አውሮፕላን፣ የሂሳብና የታሪክ ትምህርት፣ የሸክላ ሥራና እና የህክምና ሙያ፣ መዋቢያዎቹ ሊፕስቲክና ማበጠሪያ፣ መረማመጃዎቹ ደረጃዎችና መሰላል፣ አልያም ውሃ እና ቢራ... ማንኛውም አይነት የሥራ ውጤት ለሠው ከሚሰጠው ግልጋሎት ውጭ ልንመዝነው አንችልም። ውሃ በጥቅሉ እልፍ አይነት አገልግሎት እንደሚሰጥ እናውቃለን።

በዝርዝር ደግሞ፤ አንዱን ወይም ሁለቱን አገልግሎት ብቻ ነጥለን ልንመዝነው እንችላለን። እየተመገብን የሚጠጣ ውሃ ያስፈልገን የለ? የደፈረሰ ውሃ ቢያመጡልን እንቆጣለን፣ እናዝናለን ወይም እናኮርፋለን... በምንፈልገው አገልግሎት ነው የመዘንነው። የደፈረሰ ውሃ ለመጠጥ አገልግሎት ቀሽም ነው። ለመስኖ አገልግሎት ግን ጥሩ ሊሆን ይችላል። ይሄ ጥሩ ቤት ነው ያኛው ዝቅ ያለ ነው ብለን የምንፈርደው፤ ሊሰጥ የሚችለውን አገልግሎት በመመዘን ነው። አገልግሎቱ ምን እንደሆነ ያላወቅነውን ነገር፤ መመዘን አንችልም። ኪነጥበብ ምንም አገልግሎት የላትም የሚባል ከሆነም፤ መመዘን አንችልም።

ሸራ ላይ የተለያዩ ፊደላትን እያንጋደደና እያጣመመ ፅፎ ሲያመጣ፤ “ይሄ የኪነጥበብ ስራ አይደለም። ነው ከተባለም፣ መናኛ ሥራ ነው” ብለን መናገር ያቅተናል። የሚጠበቅበትን አገልግሎት የማያሟላ ከሆነ ነው፤ መናኛ ልንለው የምንችለው። አገልግሎት የተለውም ከተባለ ግን... በቃ... ዝም ነው። በዚህ ጎዳና፤ ቀስ በቀስ የት እንደደረስን ተመልከቱ። ቧ፣ሏ፣ሟ የሚል ግጥም።

እውነት ከምር፤ ለኪነጥበብ እጅጉን የምንንገበገብ ከሆነ፤ የምንጓጓና የምንሳሳ ከሆነ፤ በቆሻሻና በቡቱቶ ተሸፍና እንዳትቀበር፤ ፍሬውን ከገለባ የምንለይበት ሚዛን ለማግኘት እንሞክር። የኪነጥበብ አገልግሎት ምን እንደሆነ በግልፅ ለማወቅ እንጣር። በእርግጥም፤ “የኪነጥበብ አገልግሎት እንዲህ እንዲህ ነው” ብለን ክብሯን እናስጠብቅ።

ኪነጥበብ አገልግሎት አላት ሲባል ግን፣ እነ ዮሐንስ አድማሱ እንደሚሉት አይደለም። የማስተማሪያ ወይም የማደንቆሪያ ወይም የስነምግባር መገንቢያ ወይም የፕሮፖጋንዳ ማሰራጫ መሳሪያ አይደለችም። የኪነጥበብ አገልግሎት፤ “ለአገር ልማት፤ ለህዝብ ጥቅም፤ ለጭቁኖች ትግል...” ምናምን የሚለው ሃተታ ምንም እንዳላተረፈልን፤ ካስገኘልን ፍሬ እና ውጤት ማየት ይቻላል።

ጣዕም የለሽ አገራዊና ልማታዊ ዘፈኖች፤ የኮብል ስቶን ታላቅነትን የሚሰብኩ አሰልቺ ድራማዎች፣ እንጨት መስለው የቆሙ የአርበኞች ሥዕል፤ ለራሥህ አታስብ ብሎ እየዘፈነ፣ ዘፈኑ በሚዲያ እንዲተላለፍለት ጉቦና ጉርሻ የሚሰጥ... በእርግጥ፤ ኪነጥበብ፤ የማስተማሪያ ወይም የማደንቆሪያ መሳሪያ አይደለችም ሲባል፤ ማስተማርና ማደንቆር አጠገቧ አይደርሱም ማለት አይደለም። ኪነጥበብ፣ እግረመንገድ በመረጃ የምታበለፅግ ትምህርታዊ ልትሆን ትችላለች፤ በተቃራኒውም ዘላባጅ አደንቋሪ ልትሆን ትችላለች። በሥነምግባር የምታንፅና ለሥራ የምታነሳሳ መካሪ ኮርኳሪ አልያም፤ አደንዝዛ ቅስም የምትሰብር ሰባኪ ደስኳሪ የምትሆንበት ጊዜም ያጋጥማል። የኪነጥበብ ዋና አገልግሎት ግን፤ ከዚህ ሁሉ የተለየ ነው። መኪና፤ ከዋና አገልግሎቷ ውጭ መጠለያ መሆን ትችል የለ? ህይወትና ንብረት ለማጥፋት የሚገለገሉባትም ይኖራሉ። አንዳንዶች ደግሞ እንደ ንግድ መደብር ሲጠቀሙባት ይታያል። የመኪና ዋነኛ አገልግሎት ግን፤ ትራንስፖርት ነው። ልክ እንደዚያው፤ ኪነጥበብም፤ አስተማሪ ወይም አደንቋሪ፣ መካሪ ወይም ደስኳሪ አድርገው የሚጠቀሙባት ይኖራሉ። ትልቁ አገልግሎቷ ግን ከዚህ የተለየና የላቀ ነው። እኮ ምን?

የሁለቱንም ስህተት የሚያስተካክል፤ የኪነጥበብን ምንነትና አገልግሎት የሚገልጽ ትክክለኛ ሃሳብ ማቅረብ እንደሚቻል አምናለሁ።

 

 

 

 

Read 5323 times Last modified on Saturday, 06 October 2012 14:08