Monday, 23 May 2022 00:00

ዘጠኝ ሺህ የጎዳና ልጆችን ይታደጋል የተባለ ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ኤስኦኤስ የህጻናት መንደሮች በኢትዮጵያ በሦስት ከተሞች ለጎዳና ተዳዳሪነት የተዳረጉ ህፃናትና ታዳጊዎችን ይታደጋል የተባለለትን  የ5 ዓመት ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል፡፡ ፕሮጀክቱ ይፋ የሆነው ግንቦት 2 ቀን 2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል ሲሆን ፤ለፕሮጀክቱም 273 ሚ. ብር (4 ሚ 376 ሺህ 073 ዩሮ) መመደቡን የኤስኦኤስ ኢንተርናሽል ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰናይት ገብረእግዚአብሔር ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ በዚህ ፕሮጀክት ለአራት የአፍሪካ ሀገራት ማለትም-ለኢትዮጵያ፣ለኬኒያ ለሩዋንዳና ለኡጋንዳ 30 ሚ ዩሮ በጀት መለቀቁን የጠቆሙት ኢንተርናሽናል ዳይሬክተሯ በመጀመሪያ ለኢትዮጵያ ለኡጋንዳ 15 ሚ ዩሮ  መለቀቁን ተናግረዋል፡፡ድርጅቱ የዛሬ 48  ዓመት የሰሜኑን የሀገራችንን ድርቅ ተከትሎ፣ ለችግር ተጋላጭ ወገኖች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ በመስጠት ስራውን የጀመረውንና በኋላም ፊቱን ወደ ቤተሰብና ማህበረሰብ  ልማት ማዞሩን ያመለከቱት የኤስኦኤስ የህጻናት መንደሮች በኢትዮጵያ ናሽናል ዳይሬክተር አቶ ሳህለማሪያም አበበ፤ የገለፁ ሲሆን እስካሁንም ከ30 ሺህ በላይ ህጻናትና ወጣቶች በኤስ ኦኤስ ታቅፈው ሁለንተናዊ ድጋፍና እንክብካቤ እየተደረገላቸው ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ በርካታ የጎዳና ልጆች ለሚገኙባቸው ሁለት ሀገራት የሚውል በጀት እንደሚለቀቅና በኢትዮጵያም የ5 ዓመቱ ፕሮጀክቱ ስኬት ካስመዘገበ ተጨማሪ በጀት ሲለቀቅ እንደሚችል የተገለጸ ሲሆን በዚህ ፕሮጀክት በአዲስ አበባ፣ በድሬደዋና በአዳማ በጎዳና ላይ ህይወታቸውን  ያደረጉ ዘጠን ሺህ ህጻናትና ታዳጊዎች ከገቡበት ሱስ፣ ከደረሰባቸው የስነ- ልቦናም ሆነ የጤና ጉዳት ተላቅቀው ወደ ቤተሰቦቻቸው የሚላቀሉበት ሁኔታ የፕሮጀክቱ ዋናኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም የድርጅቱ ናሽናል ዳይሬክተር አቶ ሳህለማርያም አበበ ጨምረው ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ በሰባት ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች የሚንቀሳቀሰው ኤስኦኤስ የህጻናት መንደሮች በተጠቀሱት ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ያሉት ቢሮዎች ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ በርካታ የቤተሰብና የማህበረሰብ ጥበቃና እንክብካቤዎችን እንደሚሰራ  ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡
እንደ አቶ ሳህለ ማርያም ገለፃ፤ በዚህ ፕሮጀክት በጣም ትኩረትና ቅድሚያ የተሰጣቸው ህጻናትና ታዳጊዎች በጤና፣ በስነ- ልቦናና በአጠቃላይ ሁኔታቸው ከፍተኛ ጉዳትና ችግር ውስጥ የገቡት ናቸው፡፡በፕሮጀክቱ ተካተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሲደረግ ልጆቹ ወደ ጎዳና የወጡባቸው ምክንያቶች አብረው መጠናታቸውን የጠቆሙት አቶ ሳህለማርያም፤ አብዛኛዎቹ ልጆች ወደ ጎዳና ለመውጣት ምክንያት የሆናቸው በቤታቸው ውስጥ ምቹ ሁኔታ አለመኖር ነውም ብለዋል፡፡
በዚህ የፕሮጀክት ይፋ ማድረጊያ መርሃ  ግበር ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ኤስኦኤስ የህጻናት መንደር፣  በኢትዮጵያ በተለይ በህጻናት ጥበቃና እንክብካቤ ላይ የሚሰራውን ስራ አድንቀው፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸውም ቀደም ባለው ጊዜ በ11 ክልሎች 22 ሺህ የጎዳና ተዳደሪዎችን ማንሳት እንደተቻለ ገልጸው፤ በሌሎች ከተሞችም ቀጣይ ስራዎችን ለመስራት ዝግጅት መጠናቀቁን አብራርተዋል፡፡
የህጻናትና ታዳጊዎች ወደ ጎዳና መውጣት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የገለፁት ሚኒስትሯ ችግሩን ከምንጩ ለመቅረፍ በሚያስችል ሁኔታም ላይ እየተሰራ ስለመሆኑ ገልፀዋል፡፡
በዚህ ረገድ በዕለቱ በኤስ ኦኤስ የህጻናት መንደር ይፋ የሆነው የአምስት ዓመት ፕሮጀክት ትልቅ ሚና እንደሚጫወትና በትግበራውም ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ለግብረ ሰናይ ድርጅቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል። ኤስ ኦኤስ የህጻናት መንደር ከተመሰረተ በዓለም  አቀፍ ደረጃ 70 ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን በኢትዮጵያ 48 ዓመት እንደሞላውና በመላው ዓለም በ137 አገሮች እንደሚሰራም ታውቋል። የመንግስት ሪፖርት በአገር አቀፍ ደረጃ 150 ሺህ ህጻናት በጎዳና ላይ እንደሚኖሩ ከነዚህም ውስጥ 60 ሺህ ያህሉ አዲስ አበባ እንደሚገኙ ቢያመለክትም ዩኒሴፍ ግን በኢትዮጵያ ከ600 ሺህ በላይ ህጻናትና ታዳጊዎች በጎዳና ላይ ይኖራሉ ተብሎ እንደሚገመትና ከ100 ሺህ በላይ ያሉት በአዲስ አበባ እንደሚገኙ ይፋ ማድረጉም በእለቱ ተገልጿል፡፡

Read 1944 times