Tuesday, 24 May 2022 07:47

የልጆችን አለአግባብ መወፈር መቆጣጠር …፡፡

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

 UCSF የተባለ የህጻናት ሆስፒታል በድረገጹ የህጸናት መወፈር ምን ችግር እንደሚያስከትል በዝርዝር ያስነበበ ሲሆን the Medindia Medical Review Team የተባለው ደግሞ እ.ኤ.አ Aug 24, 2018 ባወጣው ጽሁፍ ልጅዎ ክብደቱ ዝቅተኛ ከሆነ ምን መመገብ አለበት የሚል ቁምነገር አስነብቦአል፡፡ በዚህ እትም ከልክ በላይ የወፈሩ ልጆች ምን ሕመም ይገጥ ማቸዋል የሚለውን በቅድሚያ ታነቡ ዘንድ እነሆ ስንል ከክብደት በታች ስለሆኑት ልጆች ደግሞ በሌላ ጊዜ እናስነብባችሁዋለን፡፡  
ክብደታቸው ከፍ ያሉ ልጆች የተለያዩ ህመሞች ይገጥሙአቸዋል፡፡
አስም ፤
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ከልክ በላይ ወፍራም የሆኑ ልጆች የአስም ሕመም ይገጥማቸዋል፡
የስኩዋር ሕመም፤    
በተለይም ቁጥር 2 የተባለው የስኩዋር ሕመም ከልክ በላይ ወፍራም በሆኑ ህጻናት እና ታዳጊ ልጆች ላይም በስፋት ይታያል፡፡ በጣም ወፍራም በሆኑ ልጆች ላይ በ2000 CDC ባደረገው ጥናት ከሶስቱ ልጆች በአንዱ ላይ በህይወት ዘመናቸው ሁለተኛው አይነት የስኩዋር ሕመም እንደሚከሰት ይገልጻል፡፡
የሀሞት ጠጠር፤
ውፍረት ከልክ በላይ የሆነባቸው ልጆች የሐሞት ጠጠር ችግርም ሊከሰትባቸው ይችላል፡፡
የልብ ህመም፤ በተለይም Atherosclerosis የተባለው የልብ ህመም ብዙዎች ትልቅ ሰው ከሆኑ በሁዋላ የሚከሰት ቢመስላቸውም ነገር ግን ልጆች ሆነው የጀመረ ሊሆን እንደሚችል ባለሙያዎች ይገልጹታል፡፡ ይህ ሕመም የሚጀምረው በህጻንነት እና በታዳጊነት ዘመን በመሆኑ እጅግ አደገኛ በሽታ ነው፡፡ ይህ Atherosclerosis የተባለው የልብ ሕመም ከፍተኛ ከሆነ የደም ኮለስትሮል ጋር የሚያያዝና ደካማ ከሆነ አመጋገብ እንዲሁም ከልክ በላይ ከመወፈር ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ብዙ መረጃዎች ይመሰክራሉ፡፡
ከፍተኛ የደም ግፊት፤
ክብደታቸው ከፍተኛ የሆነ ህጻናት ከፍተኛ ለሆነ የደም ግፊት ሕመም እና  በዚያም ሳቢያ ለልብ ሕመም ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡
የጉበት ሕመም፤
ክብደታቸው ከፍ ያለ ህጻናት ወይንም ታዳጊዎች እንዲሁም ሌሎች ሰዎችም ጭምር አስከፊ ለሆነ የጉበት ሕመም ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡
የወር አበባ፤
ውፍረታቸው ከፍ ያሉ ልጆች ከወር አበባ ጋር በተያያዘ ችግር ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ ውፍረት ካለእድሜአቸው የወር አበባ እንዲያዩ ሊያደርጋቸውም ይችላል፡፡ በህይወት ዘመናቸውም የወር አበባ ኡደት መዛባት ሊገጥማቸውም ይችላል፡
እንቅልፍ፤
ውፍረታቸው ከልክ በላይ የሆኑ ህጻናት በሰላማዊ መንገድ እንቅልፋቸውን መተኛት አይች ሉም፡፡ ህጻናቱ እንቅልፍ በሚወስዳቸው ጊዜ የአተነፋፈስ ችግር፤ማንኮራ ፋት፤የመሳሰሉት ነገሮች ሊስተዋሉባቸው ይችላል፡፡ ይህ ሁኔታ በጊዜ ሂደት በህይወት ዘመናቸው የልብ ድካም ለተባለ ህመም ሊያጋልጣቸው ይችላል፡፡  
በአጠቃላይም ህጻናት ከልክ በላይ ውፍረት ያላቸው ከሆነ በታዳጊነት ዘመናቸውም ይሁን ትልቅ ሰው ሲሆኑ ጭምር ውፍረቱን ለመላቀቅ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ በዚህ ሁኔታ መኖር ደግሞ በገዳይነታቸው ተጠቃሽ ለሆኑ ሶስት ህመሞች ማጋለጡ የተረጋገጠ ነው፡፡ ህመሞ ቹም ካንሰር፤ስትሮክ እና የልብ ሕመሞች ናቸው፡፡ ምንም እንኩዋን የተከሰቱትን ሕመ ሞች በህክምና መርዳት የሚቻል ቢሆንም አስቀድሞ ውኑ ውፍረቱ እንዳይከሰት መከላከል ግን የሁሉም ድርሻ ይሆናል፡፡ ውፍረት ከተከሰተ በሁዋላ ግን ወላጆች ማተኮር የሚገ ባቸው ውፍረትን በመቀነስ ሂደት ላይ ሳይሆን ህጻናቱ ጤናማ ሊሆኑ በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ምናልባትም ተያይዞ ክብደትን ማስተካከል ሊከሰት ይችላል፡፡ ዋና ዋና ነጥቦች እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል፡፡
ጤናማ የሆነ አኑዋኑዋርን መፍጠር፤
መኖሪያ ቤት የተመቻቸ እንዲሆን ማስቻል ቀዳሚው ነው፡፡ ይም ሲባል አንዱ ትኩረት ጤናማ የሆነ ምግብ የሚዘጋጅበት እንዲሆን ማድረግ ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት አላስፈላጊ ምግቦችን ለምሳሌ ለስላሳ መጠጦች፤ጁውስ የመሳሰሉትን ለህጻናት ምቹ ናቸው ተብለው የሚታሰቡ አላስፈላጊ መጠጦችን ማስወገድ ነው፡፡ ህጻናት ከስኩዋር ነጻ የሆነ ወተት እና ውሀ እንዲጠጡ ማስለመድ ጠቃሚ ነው፡፡ ፍራፍሬዎችና አትክልቶችን መመገብ እንዲቻል መኖሪያ ቤቱን በእንደዚህ ያሉ ምግቦች ማሟላት ይገባል፡፡ ይህንን አመጋገብ ለህጻናቱ ብቻም ሳይሆን ለሁሉም የቤተሰብ አባላት ማስለመድ ይገባል፡፡ ምክንያቱም መላውን ቤተሰብ ጤናማ ከማድረግ ባሻገርም ህጻናቱ እንደተገለሉና ለእነሱ ብቻ እንደተዘጋጀ ወይንም ችግር እንዳለባቸው እንዲያስቡ ማድረግ አያስፈልግም፡፡ ወላጆች በዚህ መልክ ኑሮአቸውን ካስተካከሉ ቤተሰቡን በተለያየ መንገድ ይህንን መመገብ አለብህ፤ ይህንን መመገብ የለብም የለብህም ወደሚለው ድርድር ሳይገቡ ከወተት ተዋጽኦውም፤ ከስጋና አሳ፤ ዶሮም ጭምር በጣም ጤነኛ በሆነ መንገድ ግዢያቸውን እንያከናውኑ ቤታቸውን ቢመሩ ውፍረታቸው ከባድ የሆኑ ልጆች በዚህ ተጠቃሚ ይሆናሉ፡፡ በሂደት ክብደታቸውም ሊስተካከል ይችላል፡፡
ወላጆች ለልጆቻቸው ጥሩ ምሳሌ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡
ህጻናት ወላጆቻቸው የሚመገቡትን ነገር መመገብ ስለሚፈልጉ ወላጆች ጥሩ ምሳሌ ለመሆን ለልጆቻቸዎ ጠቃሚ የሚሆነውን ምግብ አብረው መመገብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ወላጆች በምግብ ዙሪያ ያላቸውን አስተሳሰብ፤ፍላጎት እና ባህርይ ወደ ልጆቻቸው ዝቅ አድርገው ለራሳቸው ግልጽና ያመኑበት ሆነው ምንም ንግግር በማያስፈልገው መንገድ መፈጸም አለባቸው፡፡ ይህም ማለት እኔ እኮ ይህንን የምመገበው ለአንተ ወይንም ለአንቺ ብዬ ነው ሳይሉ መደበኛው ምግባቸው አድርገው ከህጻናቱ ጋር መመገብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በምግብ ጠረጴዛው አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ጥራጥሬን ማቅረብና በተቃራናዊውም ጣፋጭ እና ጨው እንዲሁም ስብ የበዛባቸውን ምግቦችን ማስወገድ እንዳለባቸው በመናገር ሳይሆን ባለማቅረብ የመመገብ ልምዱ እንዳይኖር ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ መንገድ ለልጆቻቸው ምሳሌ የሆኑ ወላጆች በዘዴ የልጆቻቸውን ከልክ በላይ ውፍረትና ጤንነት መቆጣጠር ይችላሉ፡፡
መጠንን መወሰን፤
ወላጀች ለልጆቻቸው ማድረግ ከሚገባቸው ጥሩ ነገር አንዱ ህጻኑ ምን ያህል መመገብ እንዳለበት መመጠን ነው፡፡ ወላጆች ይህንን በጥንቃቄ ሊቆጣጠሩ ይገባል፡፡ በዚህ መልክ ልጆችን መምራት ለብዙ አደገኛ ለሆኑ ባህርይዎችና ከልክ በላይ የመመገብ ፍላጎታቸውን ለማስቆም ያስችላል፡፡ ህጻናት በራሳቸው ከዚህ በላይ ወይንም በየሰአቱ መመገብ አይገባኝም ብለው ለራሳቸው መወሰን አይችሉም፡፡ በዚህ ረገድ የወላጆቻቸውን እርዳታ ይፈልጋሉ፡፡
ጣፋጭ መጠጦችን ማስወገድ፤ ህጻናት እንደለስላሳ ወይንም ጣፋጭነት ያላቸውን መጠ ጦች፤ በኢንዱስትሪ የሚዘጋጁ ጭማ ቂዎች የመሳሰሉትን እንዳይጠጡ መወሰን ይገባል፡፡ ስኩዋር እና ጣፋጭ ምግቦች ወይንም መጠጦች አላስፈላጊ የሆነ ጠቀሜታው ሳይሆን ጉዳቱ የበዛ አመጋገብ ነው፡፡   
ቴሌቪዥን መመልከትን አለመጋበዝ፤
እድሜአቸው ከ2 አመት በታች የሆኑ ልጆች በምንም ምክንያት ቴሌቪዥን መመልከት የለባ ቸውም፡፡ ከ2 አመት በላይ እድሜ ያላቸው ልጆች ከአንድ ወይንም ከሁለት ሰአት በላይ ቴሌ ቪዥን መመልከት የለባቸውም፡፡ ጥናቶች እንደሚያስረዱት ህጻናት ቴሌቪዥን የሚመለከቱበትን እድሜና የሚመለከቱበትን ሰአት ልክ መወሰን ህጻናቱ ከልክ በላይ እንዳ ይወፍሩ እና ንቁና ፈጣን እንዲሆኑ ይረዳቸዋል፡፡
ሽልማት፤
ህጻናት በጎ የሆነ ምስጋናና ሽልማትን ይወዳሉ፡፡ በእድሜአቸው መጠን ብዙም ገንዘብ ሳያወጡ ምግብን ያላካተተ ስጦታ ወይንም ሽልማት ቢያገኙ ወደፊት መቀጠል ስላለባቸው ነገር በውል እንዲያስቡ ውጤታማ እንዲሆኑም ያደርጋቸዋል፡፡ ምርጥ የሆነው ሽልማት ደግሞ ወላጅ ለልጁ በቂ ጊዜ መስጠቱ ነው፡፡ ታዳጊ ለሆኑት በተለይም ምስጋና ፤ሽርሽር መውሰድ፤ ሲኒማ መጋበዝ፤ ከጉዋደኞቻቸው ጋር እንዲዝናኑ ጊዜ መስጠት…ወዘተ የመ ሳሰሉት አስፈላጊ ናቸው፡፡  

Read 6920 times