Print this page
Wednesday, 25 May 2022 00:00

ብክለት በየአመቱ 9 ሚሊዮን ሰዎችን ለሞት ይዳርጋል ተባለ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 • በአለማችን ከሚከሰተው ሞት 16 በመቶው ከብክለት ጋር የተያያዘ ነው
• በአለማችን 1 ቢሊዮን አካል ጉዳተኞች ድጋፍ ሰጪ መሳሪያዎችን አላገኙም
            በመላው አለም በየአመቱ 9 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በተለያዩ አይነት ብክለቶች ለህልፈተ ህይወት እንደሚዳረጉና  በየአመቱ በመላው አለም ከሚከሰተው አጠቃላይ ሞት 16 በመቶ ያህሉ ከብክለት ጋር የተያያዘ መሆኑን ከሰሞኑ የወጣ አንድ አለማቀፍ ጥናት አመልክቷል፡፡
ላሰንት የተባለው የሳይንስ መጽሄት ከሰሞኑ ያወጣውን የጥናት ውጤት ጠቅሶ አሶሼትድ ፕሬስ እንደዘገበው፣ ከአለማችን አገራት መካከል በርካታ ሰዎች በብክለት ሳቢያ የሚሞቱባት ቀዳሚዋ አገር ህንድ ስትሆን በአገሪቱ በአመት 2.4 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በብክለት ለሞት ይዳረጋሉ፡፡ በአመት 2.2 ሚሊዮን ያህል ሰዎች ከብክለት ጋር በተያያዘ ለሞት የሚዳረጉባት ቻይና ሁለተኛ ደረጃን መያዟንም ጥናቱ ያመለክታል፡፡
በአለማችን ከመኪኖችና ከኢንዱስትሪዎች በሚወጣ በካይ ጋዝ ሳቢያ በሚከሰት ብክለት ለሞት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር  ባለፉት 20 አመታት በ55 በመቶ ያህል ጭማሪ ማሳየቱንና በየአመቱ ከሚከሰተው አጠቃላይ የብክለት ሞት ሁለት ሶስተኛ ያህሉን የሚያስከትለው የአየር ብክለት መሆኑን የሚጠቁመው ጥናቱ፤ ብክለት በሚል ካካተታቸው መካከል የመኪኖችና ኢንዱስትሪ በካይ ጋዞች፣ የውሃ ብክለትና ከሲጋራ አጫሾች የሚወጣ በካይ ጭስ እንደሚገኙበትም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ በመላው አለም የሚገኙ 1 ቢሊዮን ያህል ህጻናትና አዋቂ አካል ጉዳተኞች ድጋፍ ሰጪ መሳሪያዎችንና ቴክኖሎጂዎችን ማግኘት ቢኖርባቸውም ተጠቃሚ እንዳልሆኑ በ70 የአለማችን አገራት ላይ የተሰራና ሰሞኑን የወጣ አንድ አለማቀፍ ሪፖርት ገልጧል፡፡
የአለም የጤና ድርጅትና የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት በጋራ ይፋ ያደረጉት ጥናት እንደሚለው፣ በመላው አለም ከ2.5 ቢሊዮን በላይ አካል ጉዳተኞች ተሸከርካሪ ወንበርና ማዳመጫን የመሳሰሉ አንድ ወይም ከዚያ በላይ ድጋፍ ሰጪ መሳሪያዎችን ማግኘት ቢኖርባቸውም 1 ቢሊዮን ያህሉ ተጠቃሚ መሆን አልቻሉም፡፡
በተለይም አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት የሚኖሩ አካል ጉዳተኞች መሰል ድጋፍ ሰጪ መሳሪያዎችን የሚያገኙት 3 በመቶ ያህሉ ብቻ እንደሆኑ የጠቆመው ጥናቱ፤ በመላው አለም 240 ሚሊዮን ያህል ህጻናት አካል ጉዳተኞች እንደሚኖሩና መሰል ድጋፍ የማግኘት መብታቸውን ለማስጠበቅ መንግስታትና አለማቀፉ ማህበረሰብ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባው ያመለክታል፡፡


Read 6242 times
Administrator

Latest from Administrator