Saturday, 28 May 2022 13:33

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

    የሎከርቢው ፍንዳታ…
                              አሌክስ አብርሃም


               በፈረንጆቹ 1988 …ንብረትነቱ የፓን አሜሪካ አየር መንገድ የሆነ ግዙፍ የመንገደኞች አውሮፕላን የሎከርቢ ሰማይ ላይ ፈነዳ! ሎከርቢ የስኮቲሾች ከተማ ናት፡፡ በፍንዳታው 243 መንገደኞችና 16 የበረራ ሰራተኞች እንዲሁም ፍንዳታው በተከሰተባት ከተማ አገር ሰላም ብለው ቤታቸው የተቀመጡ 11 ነዋሪዎች ድንገት በዘነበባቸው እሳት ህይወታቸውን አጡ፡፡ በኋላ ሲጣራ ለካስ የሽብር ጥቃት ነው፡፡ እንደ ሻንጣ ቦምብ ጭነውለት ነበር የተነሳው፡፡ እዛ ሲደርስ ቡምም!! በዩናይትድ ኪንግደም ትልቁ የሽብር ጥቃት ነው፤ እስከዛሬ ይባላል!
ባጭሩ ይህን የቦንብ ጥቃት እንዲፈፀም ያዘዙት የሊቢያው መሪ ሙዓመር ጋዳፊ መሆናቸው ተደረሰበት ተባለ፡፡ ጋዳፊ ታዲያ ሽምጥጥ አድርገው ካዱ፡፡ እንደውም ያቀናበሩት ሰዎች ሊቢያ መሽገው መልካም ስማችንን ሊያጠፉ እንደሆነ ደርሰንበታል፤ እናደባያቸዋለን ምናምን ብለው ሐዘናቸውን ሁሉ ገለፁ፡፡ በእርግጥ ከ15 ዓመታት በኋላ ሐላፊነቱን ወስደው ግን በቀጥታ አላዘዝኩም ካሉ በኋላ ለእያንዳንዱ የአደጋው ተጎጂ ቤተሰብ ጠቀም ያለ ካሳ ለመክፈል ተስማምተው ነበር፡፡
ዋናው ወጋችን እሱ አይደለም …ጋዳፊ "እኛ አላዘዝንም ከደሙ ንፁህ ነን፤ የዚህ ሽብር አቀናባሪዎች ሊቢያ መመሸጋቸውን አውቀን እርምጃ እንዲወሰድ ትዛዝ ሰጥተናል…" እያሉ በሚከራከሩበት ወቅት አንዲት ቀልቃላ ጋዜጠኛ ወደ አንድ ዝቅተኛ የሊቢያ አየር ሃይል አዛዥ ጋ ሄደች አሉ! ሄደችና ...
"ሽብሩን ያቀነባበሩት ሰዎች በሊቢያ እንደሚገኙ ታውቋል?" ስትል ጠየቀች፡፡
"አዎ ታውቀዋል፤ ያሉበትም ተለይቷል"
"እርምጃ እንድትወስዱም ታዛችኋል?"
"አዎ አየር ሃይሉ እርምጃ እንዲወስድ ታዞ ተዘጋጅቶ ነበር"
"እና ለምን አልወሰዳችሁም?"
"የሽብርተኞቹን ስልክ ጠልፈን ያሉበትን ቦታ ለየን"
"እና ምን ትጠብቃላችሁ፤ መሳሪያ የላችሁም?"
"ሞልቶ!"
"እና?" አለች በስሜት፡፡
"ችግሩ ምን መሰለሽ" አሉ ሰውየው ፀጉራቸውን እያከኩ … "የጠለፍነው ስልክ ሲግናል የሚያሳየው ሰዎቹ መሪያችን ጋዳፊ ያረፉበት ቤተመንግስት ውስጥ ማረፋቸውን ነው!"
እንዲህ ያለ ትግል ነው የገጠመን! (ሳይሉ አልቀሩም በአረብኛ)

___________________________________________

                          ሽልማቱ
                            በእውቀቱ ስዩም

            “በምርጥ ነጠላ ዜማ ዘርፍ ያመቱ ኮከብ ተሸላሚ ማሞ መንገሻ; ብሎ ለፈፈ፥ የመድረክ መሪው፡፡
አዳራሹ በጭብጨባ ተርገበገበ፡፡
የማሞ ልብ በሀይል መምታት ጀመረ፥ ተሸላሚነቱን ከሰማ ጊዜ ጀምሮ መኪና እሸለማለሁ የሚል ሰመመን ጭንቅላቱን ተቆጣጥሮት ቆይቷል፤ ምን አይነት መኪና ይሆን እሚሸልሙኝ የሚል ሀሳብ ጠመደው፤
ወደ ሽልማቱ አዳራሽ የመጣው የሰፈሩን ላዳ ሹፌር አስቸግሮ ነው፤ በሰፈሩ የታወቀውን የላዳ ሹፌር ከዚህ በሁዋላ ማሞን በዱቤ ላለማጓጓዝ ምሎ ነበር፤ ይሁን እንጂ ማሞ ለሽልማት የታጨበትን መጥርያ ሲያሳየው ተረታ፡፡ ደንበኛው፤  #ገንዘብ ከሸለሙኝ እስከዛሬ ያለብኝን እዳ እጥፍ አድርጌ እከፍልሀለሁ፤ መኪና ከሸለሙኝ ላንድ ወር ራይድ ትሰራባታለህ” የሚል ተስፋ ሰጥቶታል፡፡
ማሞ ከወንበሩ ተነስቶ ወደ መድረኩ አቅጣጫ ለመራመድ ሲቃጣ የፕሮግራሙ መሪ፤ “ማሞን ወደ መድረኩ ከመጥራታችን በፊት ለዚህ ሽልማት እውን መሆን ከፍተኛ ደጋፍ ያደረጉ ስፖንሰሮቻችንን እናስተዋውቃለን፤; ብሎ ጀመረ #ጌድዮን ሪል ስቴት ለድርጅታችን ቢሮ እንደሚሰጠን ቃል ስለገባ እናመሰግናለን! ጠንበለል ቢራ አንድ ሚሊዮን ብር ስላበረከልን ደስታችን ወደር የለውም፤ እባካችሁ ጭብጨባ ያንሳል”
ጭብጨባው አዳራሹን ነቀነቀው፡፡
የፕሮግራሙ መሪው ዝርዝር ውስጥ ያልተጠቀሰ የንግድ ድርጅት የለም፤ ማሞ በቆመበት እግሮቹ ሊክዱት ሲያንገራግሩ ተሰማው፤ "ከዚህ በሁዋላ ሁለት ደቂቃ ከቆምኩ ዊልቸር እንጂ መኪና አያስፈልገኝም" ብሎ አሰበ፡፡
ሁለት ቆነጃጅት ሴቶች አጅበው ወደ መድረክ ወሰዱት፤ ከመድረኩ ጫፍ እስከ ሸላሚው ድረስ ያለው ርቀት አገር አቁዋራጭ ሆነበት፤ መሸለሚያው ላይ ሲደርስ ሁለት ግላድያተር እሚያካክሉ ወጠምሾች የብረት ሙቀጫ እሚያክል ዋንጫ መዳፉ ላይ አስቀመጡለት፡፡
ወደ ወንበሩ ሲመለስ ጋዜጠኞች አንገቱን በየማእዘኑ እየጠመዘዙ የካሜራ ብርሀን ነሰነሱበት፥
የፕሮግራም መሪው ሌሎችን ተሸላሚዎች አንድ ባንድ መጥራት ቀጠለ፤ ባዳራሹ ውስጥ ካሉት ታዳማዊዎች መካከል ዘጠና በመቶው ተሸላሚዎች ሳይሆኑ አልቀሩም፤ ማሞ የመዳፉ መስመሮች እስኪደበዝዙ ሲያጨበጭብ ቆየ፡፡
የመድረኩ ወከባ በረድ ሲል አንድ ዘፋኝ መድረክ ላይ ወጦ እንደ ድንገተኛ ዝናብ ታዳሚውን መበትን በሚችል ድምጽ መዝፈን ጀመረ፤ ማሞ ቀስ ብሎ ዋንጫውን እንደ ግንድ ጉማጅ ትከሻው ላይ አድርጎ ካዳራሹ መሰስ ብሎ ወጣ፤ ትንሽ እንደተራመደ፤ የቤትና የጉዋዳ እቃዎችን የሚሸጥ ሱቅ ተመለከተ፥
“ይሄንን ስንት ትገዛኛለህ?” አለው ባለሱቁን፡፡
“ምንድነው?” አለ ባለሱቁ ሽልማቱ ላይ አፍጥጦ፡፡
“ዋንጫ;
“ይሄማ ዋንጫ ሊሆን አይችልም”
“ታድያ ምንድነው?" አለ ማሞ፤የተሸከመውን ሽልማት እንደገና እየቃኘ፡፡
“ባለ እጄታ ዳምቤል ነው የሸለሙህ” ባለሱቁ ዘለግ ያለ ሳቅ ሳቀ፡፡
“እሺ ስንት ትገዛኛለህ?” ማሞ በቅጡ በማይሰማ ድምጽ ቀጠለ፡፡
“በነጻ ብትሰጠኝ ንክች አላደርገውም፤ ያንድ ደርዘን ስኒ ቦታ ይይዝብኛል፥ ለምን ጂም ቤት አትሞክርም?;
ከጥቂት ደቂቃ በሁዋላ ማሞ ራሱን የሞላ ሚኒባስ ውስጥ አገኘው፡፡
ወያላው ትከሻውን ሲነካው ቀና አለ፤
“ጀለስ!" አለው ወያላው፤ ማሞን ቁልቁል እያየው፡፡
“አቤት”
“ለእቃው ትከፍላለህ”

________________________________________________________

                              እርግጠኛነት - እግር ኳስ -
                             Spatiotemporal Continuity
                                    ገመቹ መረራ ፋና

              አንድ የፍልሥፍና ዕንቆቅልሽ (Philosophical conundrum) አለች፣ ቲዎሪው “ስፓሺዎቴምፖራል ኮንቲኒውቲ” ሲባል በቅንፍ የOxford Dictionary of Philosophyን ትርጉም አስቀምጬልሃለሁ። ከረዘመብህ ወይም ከደበረህ እለፈው፣ ከርሱ በታች በምሳሌ ተብራርቷል።
([It is] the property of well-behaved objects in space and time, that they do not ‘jump’, or in other words if a body exists at one time and a later time, then it exists throughout the interval, and if it is in one place at a time and a different place at a later time, then it traced a path through space from the one place to another.)
«የቲሲየስ መርከብ»
ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት የነበረው ግሪካዊ የታሪክ ሰው እና ጸሐፊ ፕሉታርክ አንድ ተረክ ፅፏል፣ የቲሲየስ መርከብ የሚል። ቲሲየስ ምናልባት አቴንስን እንደመሰረተ የሚነገርለት የግሪክ ንጉስ ነበር። በርካታ ጦርነቶችን ገጥሞ ድል ያደረገው ጀግናው ቲሲየስ ሲሞት አቴናውያን ለመታሰቢያው ብለው ቲሲየስ ለዘመቻ ይጠቀምባት የነበረችውን መርከቡን ወደብ ላይ ለመታሰቢያነት አቆሟት። በጊዜ ሂደት መርከቧ አረጀች። ነዋሪዎቹም የመርከቧን አካል በአዲስ ጥርብ እንጨት እየተኩና እያደሱ የቲሲየስ መታሰቢያ የሆነቸውን መርከብ አቆይዋት። በጊዜ ሂደት ሁሉም የመርከቧ አካል በእርጅና ወላልቆ በአዲስ ተተክቷል። ይሄኔ ነው ጥያቄው የሚነሳው። ይቺ አሁን ያለችው መርከብ እውን የቀደመችው ያቺ የቲሲየስ መርከብ ነች? ወይስ ሙሉ ለሙሉ ሌላ መርከብ ነች? ሌላ ሆናለች ካልን እንዴት ነው የሰውዬው መታሰቢያ ልትሆን የምትችለው?
የክለብ ድጋፍ
የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ማየት የጀመርኩት ሀይስኩል ተማሪ እያለሁ ነበር። ጓደኛዬ አሹ እና የዲኤስቲቪ እየከፈለልን ያሳየን የነበረው ፍሬአለም የተባለው ጓደኛችን የቼልሲ ደጋፊዎች ነበሩ። አጋጣሚው የቼልሲ ደጋፊ አድርጎኝ አረፈ። በዚያው የጆሴ ሞሪንሆ ወደ ቼልሲ መምጣት የበለጠ ደጋፊነቴን አጠነከረው። ማሸነፍ ደስ ይላል። እነ አስቶን ቪላን የመሳሰሉ ክለቦች 7 እና 8 ለ 0 እያሸነፈ «ተከላካይ ቡድን» ቢሉትም ግድ አልሰጠኝም። ሰማያዊዎቹን ወጥሬ ደገፍኩ። ከዚያ ዩኒቨርሲቲ ገባሁ። ቼልሲም ለ4 ዓመታት አብሮኝ ገባ። በኳስ ተሸንፎ በቃላት ጦርነት የሚያሸንፈው The Special One ለሚያበሽቁን ጓደኞቻችን መድሃኒት ሆነልን። አሸንፈው እንኳን ደስታቸውን እንዳያጣጥሙ ማድረግ ይችላል። እኛን ከጓደኞቻችን ምላስ ካሳረፈ ተጫዋቾቹን ደግሞ እንዴት እንደሚከላከላቸው ማሰቡ ያስደስታል።
ከተመረቅኩና ሥራ ከጀመርኩ በኋላ ባሉት ዓመታት ግን ቀስ በቀስ ኳስ ማየት ቀነስኩ። ከዚያም አቆምኩ። እግር ጥሎኝ ትልልቅ ጨዋታዎች ካልሆኑ አሊያም የአህጉራት ዋንጫ ካላየሁ በስተቀር ከእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ቋሚ ተመልካችነት ተፋታሁ። ሳቆም ለራሴ የሰጠሁት ምክንያት ሞሪንሆ ከቼልሲ ከወጣ በኋላ ስለፍራንክ ላምፓርድ ያደረጋት ያቺን ንግግር ነበር። «ቼልሲ ያለ ላምፓርድ ቲማቲም የሌለው ሰላጣ ማለት ነው» . . .
እውነትም . . . እነዚያ የምወዳቸው ተጫዋቾች በጊዜ ሂደት የሉም። አርሰናልን ሁሌ የሚያስለቅሰው ድሮግባ፣ ከዳሚየን ደፍ ጋር በክንፍ እየበረሩ የቼልሲን የማይረታ ቡድን የፈጠረው አሪየን ሮበን፣ የፕሪምየር ሊጉን «ክሊን ሺት» ሪከርድ ሰብሮ «ሚስተር ዜሮ» የሚል ቅፅል የተሰጠው ፔትር ቼክ፣ መሀል ሜዳውን እንደጉድ የሚፈነጭበት አጭሩ ማኬሌሌ፣ በጆን ቴሪ የእንግሊዛዊነት ፕሪቪሌጅ አስደናቂ አቋሙ የተሸፈነው የሊጉ ምርጥ ተከላካይ ሪካርዶ ካርቫልሆ፣ ለኔ የዓለማችን ቦክስ ቱ ቦክስ ምርጡ ሆልዲንግ ሚድፊልደር የሆነው ማይክል ኢሲየን፣ ወዘተ የሉም። በሌሎች ተተክተዋል። አሰልጣኞች ሄደው ይመጣሉ። ኳስ የማይወዱት አቭራም ግራንት እንኳን አሰልጥነዋል። ከአሰልጣኞቻቸው ጋር የኳስ ፍልስፍናው ተቀይሯል። እና የቱን ቼልሲ ነው የምደግፈው? ውስጡ ያሉትና ክለቡን እንድወደው ያደረጉኝ ተጫዋቾች እንዲሁም አጨዋወት ከሌለ ክለቡ ባዶ ካርቶን ነው። ካርቶኑ ቲማቲምም፣ ድንችም፣ አፈርም ሲይዝ አብሬ መደገፍ አለብኝ?
በጭራሽ።
እናም ከቼልሲ ተፋታሁ . . .
እንግዲህ ይሄ የኔ ሎጂክ በሀገር በቀል ቡድኖች ላይ አይሰራም። ምክንያቱን በምሳሌ ላስረዳ። የአምቦ ልጆች የሙገር ደጋፊዎች ናቸው/ነበሩ። እኔም የሙገር ደጋፊ የነበርኩት ሙገር ፕሪምየር ሊጉን ከተማችን ድረስ ያመጣ የከተማችን ክለብ ስለነበረ ነው።
እንዲያ ባይሆን ኖሮ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ለኛ የቲቪና የሬዲዮ ዜና ላይ የሚቀርብ ተራ ነገር ነበር የሚሆነው። የጎንደር ልጆች ፋሲል ከነማን፣ የአዳማ ልጆች አዳማ ከነማን፣ የሶዶ ልጆች ወላይታ ዲቻን፣ የሀዋሳ ልጆች ሀዋሳ ከነማን ወዘተ ይደግፋሉ። የክለቡ ውጤት ወይም ጨዋታ አማረም አላማረም ይደግፉታል፤ ክለባቸው እንዲያሸንፍላቸው ይፈልጋሉ። ይሄ የከተማህ ክለብ የሚያመጣልህ የባለቤትነት ስሜት፣ የታማኝ ደጋፊነት ስሜት ነው።
አንዳንዴ በአንድ ከተማ ውስጥ ሁለት ክለቦች ይኖራሉ። እንደ ቡናና ጊዮርጊስ። ከሁለቱም እኩል ርቀት ላይ ትገኛለህ - የምታውቀው ተጫዋች የለም፣ የተለየ ቁርኝት የለህም፣ ጓደኞችህ እኩል እኩል ደጋፊዎች ናቸው ምናምን። ይሄኔ የተሻለ የሚጫወተውን ልምረጥ በቃ ልትል ትችላለህ። ቡናን ወይም ጊዮርጊስን ልደግፍ ትላለህ። ይሄኔ በአጨዋወታቸው መዝናናትና በውጤታቸው መደሰት ስለምትፈልግ የአሁን ብቃታቸውን፣ ውጤታማነታቸውን ምናምን ታይና ትወስናለህ።
አንድ ኢትዮጵያዊ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ክለቦችን ሲደግፍ ግን እነዚህ ኤለመንቶች በሙሉ የሉም። ልክ እንደኔ ጓደኛህ፣ ቤተሰብህ ወይም ወላጆችህ ያወረሱህ የክለብ ድጋፍ ታሪክ ነው የሚኖርህ። ለዚያ ነው የእንግሊዝ ክለቦች ድጋፍ እንደሀይማኖት ከወላጆች ወይም ከጓደኞች የሚወረስ ነው ያልኩት። ለዚያም ነው ዛሬም የአርሰናል እና የዩናይትድ ደጋፊዎች የሚበዙት።
እንደዚያ ባይሆን ኖሮ (የሚወረስ ባይሆን ኖሮ)፣ ወቅታዊ አቋም እናይና እንደግፍ ነበር። ወቅታዊ አቋም ስናይ ደግሞ ባለፉት አንድ ደርዘን ሲዝኖች ማንችስተር ሲቲ ምርጥ የሚባል አጨዋወት፣ አቋምና ውጤት ነበረው። አንድ ወጣት በደንብ አጣጥሞ ኳስ ማየት በ13 ዓመቱ ጀመረ ብንል፣ በዚህ ሰዓት ጥሩ ጨዋታ፣ ጥሩ ውጤትና የክለብ አቋም ላይ የተመሰረተ ድጋፍ የሚሰጡ፣ ዕድሜያቸው ከ13 እስከ 25 የሆነ፣ ከአርሰናል፣ ቼልሲና ዩናይትድ ደጋፊዎች እኩል ቁጥር ያላቸው ሲቲን የሚደግፉ ወጣቶች መኖር ነበረባቸው።
(ከቅድሙ ፖስት በኋላ እኔን ፌስቡክ ላይም ሆነ መሬት ላይ አጋጥመውኝ ባያውቁም በርካታ የሲቲ ደጋፊዎች እንዳሉ ሰምቻለሁ። ይሄ አሪፍ ነገር ነው።)

______________________________________________

                               የአለማችን ታዋቂ ሰዎች ስለ ንባብ


 1. “ማንበብ ትልቅ ሀብትን ያጎናፅፋል። እስከዛሬ በአለማችን ላይ ስለተከሠቱ እና በሌሎች ሰዎች ስለተሰሩ ነገሮች በሙሉ ማወቅ የምንችለው ማንበብ ስንጀምር ነው።” (አብርሃም ሊንከን)
2. “በህይወቴ ማወቅ የምፈልጋቸው ነገሮች በሙሉ መጽሐፍቶች ውስጥ አሉ። የኔ ምርጥ ጓደኛ ብዬ የምቀርበው ሰው ያላነበብኩትን መጽሐፍ “እንካ አንብብ” ብሎ የሚሰጠኝ ነው።” (አብርሃም ሊንከን)
3. “እዚህ ምድር ላይ ግዜ የማይሽረው ደስታን የሚሰጠን ብቸኛው ነገር መጽሐፍ የማንበብ ልምድ ነው። ሁሉም ደስታዎቻችን በወረት ከእኛ ሲለዩን መጽሐፍ የማንበብ ልምዳችን ግን ዘወትር ደስተኞች ያደርገናል።” (አንቶኒ ትሮሎፔ)
4. “ዘወትር ባነበብኩኝ ቁጥር ውስጤ የነበረውና ያለው ትልቁ የመቻል አቅም ይቀሰቀሳል።” (ማልኮምኤክስ)
5. “የኔን የግል ህይወት ብቻ ሳይሆን በዙሪያዬ ያሉ ሰዎችን ህይወት መለወጥ የቻሉ ሀሳቦችን መተግበር የቻልኩት መጽሐፍ በማንበቤ ነው።” (ቤል ሑክሥ)
6. “መጽሐፍን የሚያነብ ሰው በህይወት ውጣ ውረዱ አያማርርም። ሠዎች ለምን ጎዱኝ፣ ለምንስ አያስቡልኝም ብሎም ሌሎችን አይወቅስም። ከሌሎች ጋርም አይቀያየምም፤ ምክንያቱም መጽሐፍ የሚያነብ ሰው ለራሱ ስኬትና ደስተኛነት ራሱ ብቁ ነውና ከሌሎች ምንም ስለማይጠብቅ።”(ባሮው)
7. “ዛሬ ላይ ያለህ ማንነት የዛሬ አምስት አመት ከሚኖርህ ማንነት ጋር ፍፁም ለውጥ ሳይኖረው ተመሳሳይ ነው። ግን በነዚህ አመታቶች ውስጥ መጽሐፎችን ካነበብክ አዎ! ከአሁኑ ይልቅ የዛሬ አምስት አመት የተሻለ ማንነት ይኖርሃል።” (ቻርሊጃንሥ)
8. “ለአንድ ሠው መጽሐፍ ስትሸጥ የሸጥከው ብዙ ወረቀቶችን፣ የተፃፈበትን ቀለምና ጥራዙን አይደለም። ለርሱ የሸጥክለት ዋናው ነገር ሙሉ የሆነ አዲስ ህይወትን ነው።”(ክርስቶፈር ሞርሌይ)
9. “በዚህ ዘመን በየትኛውም ሁኔታ በጣም ግዜ የለኝም፣ እረፍት የለኝም ብለህ የምታስብ ቢሆን እንኳን ለማንበብ የግድ ግዜ መስጠት አለብህ። ይህን አላደረክም ማለት ግን በገዛ ፍላጎትህ ራስህን አላዋቂ እያደረከው ነው ማለት ነው።”(ኮንፊሽየሥ)
10.“ድሮ ልጅ ሣለሁ ወደ ትምህርት ቤት ስሔድ ዘወትር አፍንጫዬን በመጽሐፍ ደብቄ ነበር። ይኸው ዛሬ ላይ ታዲያ እዚህ ለመድረሴ ዋና ምክንያት ሆኖኛል።”(የሙዚቃ አቀንቃኙ ሱሊዮ)
መልካም ጊዜ  with Mekibebe Ayalew.

Read 599 times