Saturday, 04 June 2022 14:23

የ2015 በጀት 786.61 ቢሊዮን ብር እንዲሆን የውሳኔ ሃሳብ ቀረበ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 የሚኒስትሮች ም/ቤት ትናንት ባካሄደው 9ኛ መደበኛ ስብሰባው፣  የ2015 በጀት 786.61 ቢሊዮን ብር እንዲሆን ለውሳኔ አቅርቧል፡፡
ከዚህ በጀት ውስጥ 347.12 ቢሊዮን ብር ለመደበኛ ወጪ፣ 218.11 ቢሊዮን ብር ለካፒታል ወጪ እንዲሁም ለክልል መንግስት ድጋፍ 209.38 ቢሊዮን ብር  ሆኖ ሲደለደል፤ 12 ቢሊዮን ብር ደግሞ ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈፀሚያ እንዲሆን ተመድቧል፡፡
የ2015 በጀት ካለፈው የ2014 በጀት ጋር ሲነፃፀር፣ በ111.94 ቢሊዮን ብር የሚበልጥ ሲሆን ይህም በመቶኛ ሲሠላ የ16.59 በመቶ እድገትን አመላክቷል፡፡
በጀቱ በተለይ የአስር ዓመት መሪ የልማት እቅድን ከማስፈፀም አንፃር፣ የሃገር ደህንነት ከማስጠበቅ፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን ከመርዳትና መልሶ ከማቋቋም እንዲሁም በጦርነትና በግጭት የወደሙ መሰረተ ልማቶችንና አገልግሎቶችን መልሶ ከማቋቋም አንጻር ታሳቢ ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑ ታውቋል፡፡
በጀቱ በቀጣይ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ቀርቦ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ያለፈው ዓመት (2014) አጠቃላይ በጀት 561.7 ቢሊዮን የነበረ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 162 ቢሊዮን ብር ለመደበኛ ወጪዎች፣ 183 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለካፒታል ወጪዎች፣ 203 ነጥብ 95 ቢሊዮን ብር ለክልሎች ድጋፍ የተሰጠ ሲሆን ይህም ለ2015 ከተያዘው ተመሳሳይ ባጀት ጋር ተቀራራቢ ሆኗል፡፡ ለዘላቂ የልማት ግቦች ተብሎ በ2014 ተመድቦ የነበረው ከ2015 ጋር በተመሳሳይ 12 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡
ለ2015 የመደበኛ ወጪዎች የተመደበው 347.12 ቢሊዮን ብር ለ2014 ከተመደበው 162 ቢሊዮን ብር ተመሳሳይ ባጀት ጋር ሲነፃፀር፣ የ185 ቢሊዮን ብር  ብልጫ እንዳለው ለመረዳት ይቻላል ፤ከፍተኛ ልዩነት የሚታየውም ለመደበኛ ወጪዎች በተመደበው በጀት ላይ ነው፡፡
ለ2015 የካፒታል ወጪዎች የተመደበው 218.11 ቢሊዮን ብር ሲሆን በ2014 የነበረው 183.5 ቢሊዮን ብር ነበር፡፡ ይህም በ2014 ዓ.ም ለካፒታል ወጪዎች የተመደበው በጀት ለመደበኛ ወጪዎች ከተመደበው በ21 ቢሊዮን ብር ገደማ ይበልጥ እንደነበር መረዳት የሚቻል ሲሆን ለ2015 ዓ.ም ደግሞ የመደበኛ ወጪ በጀት በ129 ቢሊዮን ብር ብልጫ አሳይቷል፡፡
በ2014 በአጠቃላይ ከተመደበው 561.7 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ  በጥር ወር 2014 ዓ.ም 122 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት ተመድቦ እንደነበርም ይታወቃል፡፡
መደበኛ በጀት  መንግስት ለሚያከናውናቸው አስተዳደራዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ለሚያስፈልጉ የደመወዝ ስራ ማስኬጃ ወጪ የሚመደብ በጀት ሲሆን፤ ካፒታል በጀት ደግሞ ለመንግስት የልማት ወጪዎች የሚውል ባጀት ነው፡፡

Read 8336 times