Saturday, 04 June 2022 14:26

በመንግስትና በህወሓት መካከል ዘላቂ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥረት እያደረጉ መሆኑን ኦባሳንጆ ገለጹ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)


              በመንግስትና በህወሓት መካከል በቅድሚያ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ የማሸማገል ተግባር እያከናወኑ መሆኑን ሰሞኑን በመቀሌና አዲስ አበባ የሰነበቱት የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ኦሊሴንጎ ኦባሳንጆ አስታወቁ።
ኦባሳንጆ በመቀሌና በአዲስ አበባ የነበራቸውን ቆይታ አስመልክቶ ከቢቢሲ አፍሪካ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ፤ በፌደራል መንግስቱና በህውሓት መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
 አፍሪካ ህብረትን በመወከል የማሸማገል ጥረት እያደረጉ የሚገኙት ኦባሳንጆ በቅድሚያ ወደ መቀሌ ማምራታቸውንና ከህወሓቱ ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ጋር ተገናኝተው በቀጠናዊ ጉዳዮችና ሰላም በሚሰፍንበት ሁኔታ ላይ እንደተወያዩ ገልጸዋል።
ባለፉት 6 ወራት በፌደራል መንግስቱና በህወሓት መካከል የጎላ ግጭት አለመከሰቱን የጠቆሙት ኦባሳንጆ፤ ለሰብአዊ እርዳታ ሲባል ተኩስ አቁም መደረጉ በፊት ከነበረው የተሻለ የሰላም ተስፋ ያጫረ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በአፍካ ህብረት በኩል በፌደራል መንግስቱና በህወሓት መካከል ሰላም እንዲፈጠር በዝግታም ቢሆን ያልተቋረጠ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። ግጭቱ በዘላቂነት እንዲፈታ ለማስቻል በቅድሚያ በሁለቱ ወገኖች መካከል መተማመን መፍጠር እንደሚያስፈልግ የገለጹት ኦባሳንጆ፤ እስካሁን ሁለቱ ወገኖች ወደ መተማመን እንዲያመሩ የሚያስችሉ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውንም ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅት በእሳቸው በኩል እየተደረገ ያለው ጥረት ሁለቱ ወገኖች ወደ ተኩስ አቁም እንዲመጡ ማድረግ እንደሆነና የመጨረሻው ግብም መደበኛ የተኩስ አቁም ተደርጎ ሙሉ መግባባት እንዲፈጠር ማስቻል እንደሆነ ተናግረዋል።
መቼ የተኩስ አቁም ስምምነት እንደሚፈጸም እንዲሁም ሁለቱ አካላት መቼና በምን ሁኔታ እንደሚደራደሩ ቁርጥ ያለ መረጃ ለመንገር እንደሚቸገሩ ኦባሳንጆ በቃለ-ምልልሳቸው ላይ አመልክተዋል፡፡
በትግራይ እስካሁን ለሰብአዊ እርዳታ ሲባል ተኩስ መቆሙና የሰብአዊ እርዳታ እየገባ መሆኑ የሚደነቅ እንደሆነ ያወሱት መልዕክተኛው፤ በቀጣይ በክልሉ የተቋረጡ እንደ መብራት፣ የውሃና የባንክ አገልግሎት መስጠት በሚጀምሩበት ሁኔታ ላይ ንግግር መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡


Read 8338 times