Saturday, 04 June 2022 15:23

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወደ ጦርነት የገቡ ወገኖችን ለማስታረቅ እንደምትፈልግ አስታወቀች

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  ቤተ ክርስቲያኒቷ በትግራይ ክልል ለሚገኙ ጳጳሳትም ጥሪ አቅርባለችየተባባሰው
                
                የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ወደ ጦርነት የገቡ ወገኖችን ለማስታረቅና ወደ ሠላም እንዲመለሱ ለማድረግ እንደምትፈልግ አስታወቀች።
ላለፉት 15 ቀናት በአዲስ አበባ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ሲጠናቀቅ ቤተ ክርስቲያኒቱ ባወጣችው መግለጫ እንዳስታወቀችው፤ በአገሪቱ በተቀሰቀሰው ጦርነት ሳቢያ በርካታ ወገኖች ለሞት ለአካል ጉዳትና ለንብረት ውድመት ተዳርገዋል። ይህ ጥፋት በዚህ መንገድ ሊቀጥል ስለማይገባ በጦርነቱ ተሣታፊ የሆኑ ወገኖችን ወደ ሠላምና እርቅ እንዲመጡ ለማድረግና ለማስታረቅ እፈልጋለሁ ብላለች።
ምልዓተ ጉባኤው በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ባለው የሰላም እጦት ላይ በሰፊው መወያየቱን የጠቆመው የቤተ ክርስቲያኒቱ መግለጫ፤ በቀጣይ ጦርነትና የእርስ በርስ ግጭት ተወግዶ አጠቃላይ ሰላም በሚሰፍንበት መልኩ ተነጋግሮ ችግሩን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍታት እንዲቻል፣ የአስታራቂነት ሚናዋን መጫወት እንድትችል ለማድረግ ለፌደራል መንግሥት ጥያቄ አቅርባለች።
 በትግራይ ክልል ለሚገኙ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትም ጥሪ ማቅረቧን የገለጸችው ቤተ ክርስቲያኗ፤ ሁላችንም ለሠላምና እርቅ ተባብረን ልንሠራ ይገባናል ብላለች።
በተጨማሪም፣ በቤተ ክርስቲያንና በኢትዮጵያ እንደ ሀገር የተከሰተውን የሰላም እጦት ተከትሎ የደረሰው ሕልፈተ ሕይወት፣ የካህናትና የምእመናን ሞት እንዲሁም የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠል ላይ ጉባኤው መክሮ ችግሩ መፍትሔ እንዲያገኝ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት እንዲቀርብ ተደርጓልም ተብሏል፤ በመግለጫው፡፡
በበዓል ማክበሪያ ቦታዎች መነጠቅ ዙሪያ አጥፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ፣ በቀጣይም በመንግሥት በኩል አስፈላጊው ጥበቃ እንዲደረግላት ቤተ ክርስቲያኒቱ ለመንግሥት ጥያቄ ማቅረቧን ገልጻለች። እስካሁን በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ደረሰ የተባለው ችግር በአይነትና በቁጥር ተለይቶ ለሚመለከታቸው የፌዴራልና የክልል መንግሥት አካላት ቀርቧልም ተብሏል፡፡
ቤተ ክርስቲያኒቷ አክላም በወቅታዊ ችግር ምክንያት ለተፈናቀሉና ለተሰደዱ ወገኖች፣ ለፈረሱና ለተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናት ማቋቋሚያ፣ ለተዳከሙ የአብነት ትምህርት ቤቶች መደጎሚያ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ መወሰኗንም ገልጻለች፡፡
 የትግራይ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ቤተ ክርስቲያኒቱን አስመልክተው ታህሳስ 30 ቀን 2014 ዓ.ም እና የካቲት 3 ቀን 2014 ዓ.ም ያወጡትን መግለጫ ምልዓተ ጉባዔው መገምገሙ የተገለጸ ሲሆን፤ በቀጣይ የክልሉ አባቶች በማዕከል እንደ ቅዱስ ሲኖዶስ አባልነታቸው ለአገር አንድነትና ሰላም በጋራ እንዲሠሩ ጥሪ ቀርቧል፡፡
በሌላ በኩል፤ ቤተ ክርስቲያኗ በምልዓተ ጉባኤው ላይ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት የሚሰጥ የሕክምና ማዕከል እንዲቋቋም ስለመወሰኗ በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡
የባሕርዳርና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑትን ብፁዕ አቡነ አብርሃም፣ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም የኒውዮርክና አካባቢው ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ (ዶ/ር) የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ በመሆን በጉባዔው ተመርጠዋል።


Read 11363 times