Saturday, 04 June 2022 18:43

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

  የፍቅር የመውደድና የመስዋእትነት ጥግ!!

             ትላንት መፅሔት ሳገላብጥ ይሄን ልብ ሰባሪ አሳዛኝ ታሪክ አነበብኩ ...
አንዲት እናት በትዳር አለም ውስጥ የወለደችው አንድ ወንድ ልጅ ብቻ ነበር፡፡
ታዲያ ይሄ ልጅ ተወልዶ 1 ዓመት እንደሞላው አባት በድንገተኛ የመኪና አደጋ ህይወቱ አለፈ፡፡ በዚህም እናት ልጇን ያለአባት በስስት እየተንከባከበች የማሳደጉ ሙሉ ሃላፊነት በሷ ጫንቃ ላይ አረፈ፡፡ እናት የዘወትር ህልሟ ልጇን እያስደሰተች መኖር እንጂ ሌላ ባል አግብታ ልጇ በእንጀራ አባት እንዲያድግ አትፈልግም፡፡ ልጁ ወጣትነት እድሜ (የ16 አመት) ላይ ደርሶ ነበርና አንድ ቀን ‹‹እማ፤ 18ኛ አመት ልደቴን ሳከብር ምን ትሰጭኛለሽ?›› ሲል እናቱን ይጠይቃል፡፡
እናትም ‹‹ልጄ፤ ለ18 አመት እኮ ገና ብዙ ይቀርሃል›› ስትል ትመልሳለች፡፡
ልጁ አስራ ሰባት አመት ከሞላዉ በኋላ አንድ ቀን ራሱን ስቶ ይወድቅና እናቱ ወደ ሆስፒታል ትወስደዋለች፡፡
ያዩት ዶክተሮችም፤ ‹‹ልጅሽ ልቡ ጥሩ አይደለም›› ሲሉ ያረዷታል፡፡
ስትሬቸር ላይ የተቀመጠው ልጇ… ‹‹እማ፤ ዶክተሩ እንደምሞት ነገረሽ ወይ?›› ብሎ እናቱን ጠየቃት!
ይሄኔ እናት ስሜቷን መቆጣጠር ተስኗት ማልቀስ ትጀምራለች፡፡
በመጨረሻም ልጁ በ18ኛ አመት የልደት ቀኑ ላይ ወደ መልካም ጤንነቱ ተመልሶ፤ ወደ ቤቱ ሲመጣ፤ አልጋዉ ላይ እናቱ የተወችለትን ደብዳቤ ያገኛል፡፡ ደብዳቤዉም እንዲህ የሚል ነበር፡-
‹‹ልጄ፤ ይሄን ደብዳቤ እያነበብክ ከሆን፤ ይህ የሆነዉ ሁሉም ነገር በመልካም ሁኔታ በመሄዱ ነዉ፡፡ ለ18ኛ ዓመት ልደትህ ምን እንደምሰጥህ የጠየከኝንና የምመልሰው (መልስ) ያጣሁበትን ያን ቀን አስታውስ። የምወድህ ልጄ፤ ልቤን ሰጥቼሃለሁ። በጥንቃቄ ያዘው፡፡ መልካም ልደትም ይሁንልህ፡፡››
እናት ልቧን ለልጇ መስጠት ስለነበረባት (እናትነት አስገድዷት) ህይወቷ አልፏል፤ ምክንያቱም ከእናት ልብና ፍቅር በላይ የሆነ ምንም ነገር የለምና፡፡
እናቶቻችንን ፈጣሪ ከክፉ ነገር ሁሉ ይጠብቃቸው!
(የኔ አበሻ ግጥምና ሌሎች )

_______________________________________

                                   ከመጋቤ ሀዲስ እሸቱ አለማየሁ አንደበት
Eshetu Alemayehu Quotes - የመጋቤ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ ገራሚ እና አስተማሪ አባባሎች - Posts |  Facebook

               “በታክሲ ስትሄድ አንድ ጋጠወጥ ሰው ቢገጥምህና የማይሆን ቃል ቢናገርህ ለርሱ ቦታ አትስጠው፤ አንዱ ፌርማታ ላይ ይወርዳል፤ ከዚያ በኋላ አታገኘውም። አንተን ግን ቀኑን ሙሉ ሲበጠብጥህ ይውላል።”
 “ቁንጫ የጠረጉት ዕለት ባለጌም የመከሩት ዕለት ይብሰዋል” እንዲሉ  ምክር ለሁሉ አይሰጥም፤ መልስ ለሁሉም አይመለስም፤ ክርክር ከሁሉም ጋር አይደረግም ። “
***
“...16 ዓመት ሙሉ ትምህርት ላይ ቆይቶ ጭንቅላቱ ምንም ያልተዘራበት ሆኖ ይገኛል። ምሁራን ገለልተኛ መሆን የለባቸውም፤ ማንም ከአገር ጉዳይ ገለልተኛ ሊሆን አይችልም። አገር ሲኖር ነው ሁሉም ነገር የሚሆነው። አገር ከሌለ ማንም ሊኖር አይችልም። ለማበድ እንኳን አገር ያስፈልጋል፤ በአገር ጉዳይ ምሁራንም ሆኑ የሃይማኖት አባቶች ገለልተኛ መሆን አይችሉም። በአገር ጉዳይ ላይ ማንም ነው መሥራት ያለበት፤ የአስተሳሰብ ቀረጻ ላይ መሰራት አለበት። አንድ ኢትዮጵያዊ አሜሪካ ውስጥ ቢያብድ ማደንዘዣ ተወግቶ ቦሌ ይጣላል። አንድ ሰው ‹‹እግዚአብሔር የለም›› ማለት ይችላል፤ ‹‹ኢትዮጵያ የለችም›› ማለት ግን አይችልም። እግዚአብሔር የለም ቢል የሚመጣውን ራሱ ይቀበላል፤ ኢትዮጵያ የለችም ካለ ግን ሀገሩን ለቆ ኬንያ መግባት አለበት።”

_________________________________________

                        
                             ኑሮ
                               በእውቀቱ ስዩም

            ባለፈው ‘ ሰኔ ስድስት ብሄራዊ ትያትር ዝግጅት አለኝ ፤ ምርታችሁን ለማስተዋወቅ የምትፈልጉ በውስጥ መስመር አናግሩኝ ብዬ ለጠፍሁ፤ ሼክ መሀመድ አላሙዲን እና አቶ አብነት  ይፎካከሩብኛል ብዬ ጠብቄ ነበር፤ ባስር ደቂቃ ውስጥ አስር መልዕክት ተሰደደልኝ ፤ የሁሉም መልዕክት ሲጨመቅ #በውቄ free ትኬት የት ማግኘት ይቻላል?;  የሚል ነው ፤ ወገን ተው አንጨካከን፤ ብትችሉ አግዙኝ፤ ባትችሉ አትገዝግዙኝ!
ከአሜሪካ የመጣሁ ሰሞን እዚህ ቀበና አካባቢ “ ኮባ” እሚባለው በከተማው አንደኛ ውድ ሬስቶራንት ውስጥ  ቀብረር ብዬ እበላ ነበር፤ ይህን የታዘበ ባለንጀራዬ፤ “ጎሽ! ኮባ ለመግባት በቃህ? ከወር በሁዋላ ኮባ ለብሰህ አይሀለሁ” ብሎ አሟረተብኝ ፤አሁን የኑሮዬ ቃና እንደ ፍቅር እስከ መቃብር ማጀቢያ ዋሽንት ነው፤ እንደ ብዙ አገር-በቀል ላጤዎች ማብሰል የተሳነኝ ነኝ፥ እንደ ሼፍ ዮሀንስ ከምወጠውጥ እንደ መጥምቁ ዮሀንስ የበረሀ አምበጣ በማር አጣቅሸ ብበላ እመርጣለሁ፤ ላበስል ስሞክርም አይሳካልኝም፤ እድሌ ሆኖ ዳቦ እሚገነፍልብኝ ሰው ነኝ፤
 ወገን ! እየታዘባችሁ ነው? ኑሮው የሸቀጥ ብቻ ሳይሆን የስነምግባር እጥረት ፈጥሯል ፤ ባለፈው የሆነች ደከም ያለች ካፌ ገብቼ፣ አስተናጋጁን ጠርቼ፥
“እንቁላል ፍርፍር አለ?”
“አለ”
“እንቁላሉ ያበሻ ነው?”
“አይደለም የዶሮ ነው”
የሆነ ጊዜ ላይ ደግሞ ካፌ ገባሁ፤ ካፌው ውስጥ አንድ ታታሪ ተጨቃጫቂ ሴትዮ አትጠፋም፤
 በቀደም አስተናጋጁን ጠርታ “ አረፋ ያለው ሻይ አምጣልኝ “ ብላ አዘዘችው ::
አስተናጋጁ ሊሄድ ሲል ክንዱን ስንግ አድርጋ ይዛ፥
“ሻዩና አረፋው ለየብቻ ይምጣ” ብላ ደረቀች፥
 ትዝ ይላችሁ እንደሆነ ድሮ የድህነት ማምለጫ እንቅልፍ ነበር:: አሁን መኝታውም ተወደደ! ባለፈው “ አዳዲስና ያገለገሉ እቃዎች መሸጫ ሱቅ “ ገባሁና አዲስ አልጋ ገዛሁ፤ ስተኛበት የድምጻዊነት አገልግሎት እየሰጠ ምቾት ነሳኝ ፤
ከዚያ ወደ መሸጫው ሱቅ ሄድኩና” #ማኔጀሩን ማናገር እፈልጋለሁ; ብየ ቀወጥኩት፤
ማኔጀሩ ተጠርቶ ሲመጣ ፥
“ዠለስ! አልጋውን ከወዳደቀ ፒያኖ ነው እንዴ የሰራችሁት? ድምጹ አላስተኛ አለኝ “ ብዬ አጉረመረምሁ፤
“ምንድነው ችግሩ?” አለኝ ማኔጀሩ ፥
“በተገላበጥሁ ቁጥር ይንቋቋል ! “
ማኔጀሩ ትንሽ ሲያስብ ከቆየ በሁዋላ ፤
“አይዞህ! ከአርባ አመት በሁዋላ የሚጠበቅ ነው “ ብሎ በረጅሙ ተነፈሰ፤
“አርባ አመት ያገለገለ አልጋ ነው እንዴ የሸጣችሁልኝ ?”
“እያወራሁ ያለሁት ስላንተ ነው! አጥንት ህክምና ጎራ ብለህ መገጣጠሚያህን ቼክ ብታስደርግ ይሻላል“
_________________________________________

                        ከአዳም ረታ ብዕር
Adam Reta - የአዳም ዘመንና ራዕይ አለማየሁ ገላጋይ ደራሲ አዳም ረታ ከሎሬት ፀጋዬ ገብረመድኅን የተለየ  ስነ-ስጽሑፋዊ ብሒል አለው፡፡ ፀጋዬ "የሕዝቡ ሙቀት ካልሞቀህ፤ በሕዝቡ ሕዝባዊነት ውስጥ ካልታቀፍክ የእሱን ሕይወት ...

                1962 ዓ.ም፡፡ እኔ ያኔ እድሜዬ አስራአራት አመት ነበር። ማርታ ትዳር ከመያዟ ሁለት አመት ቀደም ብሎ ማለት ነው። አንድ ቀን አባቴ አዲስ ኳስ ገዝቶልኝ እንድንሞክረው ፈልጌ ቤቷ ሄድኩ። የቤታቸው የፊትለፊት በር ስለተዘጋ እናቷ እንዳይሰሙኝ በቀስታ በጀርባ ያለውን የመኝታ ቤቷን በር ሳላንኳኳ በርግጄ ገባሁ። እንደገባሁ ግን ያጋጠመኝ የለመድኩት ነገር አልነበረም። ፈዝዤ ቀረሁ። አፏን በእጇ እየተመተመች ሮጣ አልጋ ላይ ቁጭ አለችና ራቁት ገላዋን ቶሎ ብላ በጋቢ ሸፈነች። ምን ያክል ደቂቃ ፈዝዤ እንደቆምኩ ዛሬ ላይ ትዝ አይለኝም።
“ደብሽ ና እዚህ ጋር ቁጭ በል፤ አስመሮም የገዛው ካሴት አለ እንስማው።” አለችኝ።
(አስመሮም በቤተሰብ የመጣላት እጮኛዋ ነው።)
ኳሴን እንዳቀፍኩ ብዙም ሳልቀርባት አልጋዋ ግርጌ ተቀመጥኩ። ትልቅ ልጅ መሆኗን ለመጀመሪያ ጊዜ አየሁ። ጥቂት ብትበልጠኝም ግን ልጅ ነበረች።
“ሠውነቴን በመጥፎ ሳሙና ታጥቤ አሳከከኝ።” አለችኝ።
መልስ አልሰጠኋትም።ጋቢውን ከትከሻዋ ወረድ አደረገችና ሳቅ ብላ አየችኝ። ምንም አልመለስኩም።
#ኳስህን አስቀምጥና እከክልኝ።;
ኳሷን እያስቀመጥኩ ሳለ ‘ከእከክልኙ’ ጎላ ባለ በሚያስጠነቅቅ ድምፅ በሩን እንድቀረቅረው አዘዘችኝ። በዝምታ ትእዛዟን ፈፀምኩ። የማከኩን ነገር ፈርቼ ዝም ብዬ በሩ ስር ቆምኩ።
ዛሬ ሁሉ ነገሯ ተለውጦብኛል። ፈገግ ብላ እያየችኝ ራሷን በመነቅነቅ እንድጠጋት ጠራችኝ። በቀስታ እየተራመድኩ ሄጄ አልጋው ጠርዝ ላይ አጠገቧ ተቀመጥኩ።....በደረቷ ተገልብጣ ግንባሯን ትራሱ ላይ አስደገፈችና ጀርባዋን ሰጠችኝ። በመንታ ከተጎነጎነው ፀጉሯ ላይ የግማሽ ጣት ርዝመት ያላት ጭድ አየሁ። ለምን እንደሆነ እንጃ ለአፍታ ትኩረቴን ሰረቀው።
ትእግስቷ አልቆ ኖሯል ዞር ብላ እጄን ወደ ትከሻዋ ሳበች። አይኖቼ ከጭዱ አልተነሱም። ስለ ሳሩ ልነግራት ፈልጌ ዞር ስል እጄ ግራ ጡቷ ላይ ነው። ዝም ብዬ አስቀመጥኩት። ምን ላድርገው!? አንገቴን ሰብሬ ወለሉን ማየት ጀመርኩ። ጡቷ ከእጄ ስር ያረገርጋል፤ ዞሬ ላያት አልደፈርኩም፤ አፍታ አለፈ፤ እጄን አፈፍ አድርጋ ያዘችኝ፤ እንደፈለገችው እንዲሆን ለቀኩላት።
ትንሽ እጇ እጄ መሀል እንደ ዳረጎት የምትሳም ነበረች። እጮኛዋ አስመሮም ከሚያስተምራት ሴትነቷ ደረት ላይ መንፈላሰስን አስተማረችኝ። በትንሽ ቀዳዳዋ አለም የሚፈጠርበትን ህዋ አየሁ። ትዳር የሚሉት ነገር ይዟት እስኪሄድ ድረስ ቤተሰቦቿ ሳይኖሩ፣ ትምህርት ሽፍት ሲገጥም በተመቸ ጊዜ ሁሉ የምላፋት አድባሬ ሆነች።
ከልጅነት አረንጓዴ መስክ ላይ ነቅላ፣ አባብላ ወደ አዋቂነት ካመጣቺኝ እለት ጀምሮ እስከዛሬ ከአይኔ የማትጠፋው በአፍረት ስሽኮረመምና ከአንገቷ ስር ተጠግቼ ስጋደም ፀጉሯ ላይ ያየኋት ጭድ ብቻ ናት። ሰርግ ሲሰረግና ስትዳር እዛው ጎረቤቷ ነኝና አልጋዬ ውስጥ ገብቼ ወፋፍራም እንባ አነባሁ። የአስመሮም ሚስት ሆና እየተጨፈረ ስትሸኝ፣ እንዴት እንዳማረባት ላያት በሰዎች መሀል ስቃኝ በአይኖቿ አይታኝ አንገቷን ሰብራ ፊቷን በእጇ ቀብራ አለቀች።፨
***
ከዓመታት በኋላ የቤቴ በር ተንኳኳ፤ በእንቅልፍ የወዛ ፊቴን እያሸሁ ወደበሩ አመራሁና ከፈትኩ። ማርታን ሳያት ደነገጥኩ።
“ቶሎ አትከፍትም እንዴ?
ከፍቼ ካስገባኋት በኋላ በሩን ዘግቼ እዛው ቆምኩ። “እንግዳ እንዲመጣብህ አትፈልግም መሠለኝ።” አለችኝ። ልቤን እንደማታውቅ።
“አሁን የምትመጪ አልመሠለኝማ!”
በዚያች እለት ብዙ ነገር ተጨዋወትን። ትዳር እንደደበራት አስመሮም ለስራ ተቀይሮ ክፍለ-አገር እንደሄደ ወዘተ.... ከጥቂት ጊዜ በኋላ ተያይዘን አልጋ ውስጥ ገባን።
የውስጥ ሱሪዋ ነጭና እጅግ ንፁህ ናት። ይሄ ለእኔ ትንሽነቴን የሚነግር ደውል መሠለኝ። ወደ አልጋው ጥግ ወረወረቻት። ገላዋ ከፊቴ ውሀ እንደተሞላ ፊኛ ያረገርጋል። ፊቴን አንገቷ ስር ቀበርኩ። ሸሚዟ ወደ ላይ ተገልባ ጡቶቿ አይኖቼ ስር ተከፈቱ።
.....የጡቶቿን ጫፎች ሜሮን እንደፈሰሰበት ጥቁር አካል ሆኖ አየሁት። ሁለታችንም ፍጥነት ውስጥ ነን።....እሷ በደፈረ እኔ በፈራ።
እግሮቿ እንደ ክንፍ ግራና ቀኝ ሲዘረጉ ልጅነቷን ሟጣ እንደገደለች ገባኝ።.
....አንገቷን እንደነከስኩ ፍስሀ አጥለቅልቆኝ ከአይኔ ውስጥ እምባዬ ፈነዳ።
ግራ እግሬን ጭኖቿ መሀል አድርጌ እርሷም ፊቷን ደረቴ ላይ አድርጋ... “እማዬ ብቻ ሳትሆን ብዙ ሰዎች በልጅነታችን እኔና አንተ የምንባልግ ይመስላቸው ነበር።
ከተጋባን ከአመታት በኋላ እንኳን ለአስመሮም እኔና አንተ የነበረንን ግንኙነት ነግረውታል። ወንድ የማላውቅ ልጃገረድ ሆኜ ቢያገኘኝም አመናቸው። የአስመራ ሰዎች፣ የአገሩ ሰዎች ስለሆኑ ብቻ ያምናቸዋል።”
 (አዳም_ረታ፦ “ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ”)

______________________________________

                            "መመልከትም ጥበብ ነው!"
                                  ጌታሁን ሄራሞ

               በአጋር ፍለጋ ዘመንህ የቀጠርካት ልጅ ፀጉሯን አንጨባርራ እና አለባበሷን እንደነገሩ አድርጋ ካገኘችህ የሆነ መልዕክት እያስተላለፈች እንደሆነ ሳትነግርህ መረዳት አለብህ። የዕይታ ባህላችን ኋላ ቀር በመሆኑ ካልተነገረን ካልተወራ በቀር ድባቦችን በማየት ብቻ የማጣጣም ልምዳችን አነስተኛ ነው።
በፊልሙ ዓለም የዲያሎግ ድምፅ በግብዓትነት የገባው ዘግይቶ ነው...እ. ኤ. አ በ1920ዎቹ። ፊልሞች ጅምር ላይ በዕይታዊ ተግባቦት ላይ ብቻ የተመሠረቱ ነበሩ፤ ከነዚህም ውስጥ “The Great Train Robbery, Metropolis, and The Battleship Potemkin” በምሣሌነት ይጠቀሳሉ።
These films were based on non-dialog techniques. Hence Communication was effected visually. የድምፅ ግብዓት ወደ ፊልሙ ዓለም በገባ ጊዜ በተለይም እንግሊዞቹ ተቃውመው ነበር፤ ምክንያታቸው የተመልካቾች ዕይታዊ ክህሎት በዲያሎግ ይሸራሸራል የሚል ነበር። የፊልም ጥበብ ከዕይታ ይልቅ ወደ ዲያሎግ ካመዘነ ዘርፉ ልብ ወለድን ከማንበብ እምብዛም የሚለይ አይሆንም ማለታቸው ነበር።
በፊልም እንዱስትሪ ዕይታዊ ተግባቦት ዕውን የሚሆንባቸው አምስት ያህል መንገዶች በዋናነት ይጠቀሳሉ። ከነዚህም ውስጥ እንቅስቃሴና ቀለም በግንባር ቀደምትነት ይቀመጣሉ። በድምፅ አልባ እንቅስቃሴ ብዙ መልዕክት ማስተላለፍ ይቻላል፣ ቀለምም በዝምታ መልዕክትን የማስተላለፍ አቅም አለው።
በተለይም በዘርፉ ልምድና ዕውቀት ያካበቱ የፊልም ዳይሬክተሮች፣ ሲኒማቶግራፈርስና ከለርስቶች “Non -Verbal” በሆነ ስልት የታዳሚን ስሜት ለመንካት የሚያደርጉትን ጥረት ያስተዋለ ተመልካች ፊልም መስራት ብቻ ሳይሆን መመልከትም ጥበብ እንደሆነ ለመረዳት አያቅተውም።
ትናንት ከላይ በዘረዘርኳቸው በተለይም በቀለም ዕይታዊ ተግባቦት ዙሪያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አለ የሥነ ጥበብ ት/ቤት እንደ መንደርደሪያ ጥሩ የውይይት ጊዜ ነበረን። በፕሮግራሙ ላይ ልምዴንና ዕውቀቴን እንዳካፍል የጋበዘኝ በአዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ የትያትር ጥበባት ረዳት ፕሮፌሰሩ ተስፋዬ እሸቱ ነው። አመሠግናለሁ።


Read 1537 times