Saturday, 11 June 2022 18:14

ኤስኦ ኤስ በጦርነቱ የተጎዱትን ለመደገፍ የ145 ሚ.ብር ፕሮጀክት ይፋ አደረገ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

  ኤስኦ ኤስ የህፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ፣ አሸባሪው የህወሃት ታጣቂ ሃይል በቀሰቀሰው ጦርነት ከፍተኛ ጉዳት ለደረሰባቸው የአማራ አካባቢ ዜጎች፣ የ145 ሚ. ብር አዲስ ፕሮጀክት ይፋ አደረገ። ግብረሰናይ ድርጅቱ ይህን ይፋ ያደረገው ባለፈው ረቡዕ ረፋድ ላይ በኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ህወሃት በቀሰቀሰው ግጭትና በፈጸመው ወረራ በርካታ ዜጎች ለርዳታ  ጠባቂነት መዳረጋቸውን የጠቆመው ድርጅቱ “ጦርነቱ በተለይም ወደ አማራና አፋር ከተስፋፋ በኋላ ቢያንስ ለ6 ወራት ጦርነቱ ሳይበርድ መቀጠሉ እንዲሁም ከነዚህ ክልሎች የተወሰኑት በህወሃት ቁጥጥር ስር ሆነው በመቆየታቸው ንፁሃን ህይወታቸውን አጥተዋል፣ በርካቶች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል፣ የመንግስትና የግል ተቋማትና ሀብቶች ወድመዋል ብሏል-ግብረሰናይ ድርጅቱ። በዚህ ምክንያት 9.4 ሚሊዮን ዜጎች የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ የሚሹ ሲሆኑ ቀሪዎቹ 2.4 ዜጎች ደግሞ መፈናቀላቸውን የኤስ ኦ ኤስ ህፃናት መንደሮች በኢትዮጵያ የሀገር ውስጥ ተጠሪ አቶ ሳህለ ማሪያም አበበ በመግለጫው አብራርተዋል።
እንደ 2022 የኢትዮጵያ የሰብአዊ ድጋፍ እቅድ ከሆነ፤ የሰብአዊ ድጋፍ የሚሹት ዜጎች ቁጥር በተያዘው የፈረንጆቹ ዓመት 25.9 ሚሊዮን መሆናቸው ሪፖርት መደረጉንና ይህም ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ 20 በመቶው እንደሆነም በመግለጫው ተብራርቷል።
በጦርነቱ የተጎዱትን  ለመደገፍም የጀርመኑ  የኤስ ኦ ኤስ ድርጅት፤ ለጦርነቱ በጣም ተጋላጭ ለሆኑ የአማራ፣ አፋርና ትግራይ ክልል ዜጎች 4 ሚ ዩሮ አስተዋፅኦ አድርጎ የነበረ ሲሆን በወቅቱ የነበረው የፀጥታና የደህንነት ስጋት ትግራይንና አብዛኛውን የአፋር ክልል ለችግር ተጋላጮች ለማገዝ አስቸጋሪ እንዳደረገው አቶ ሳህለ ማሪያም ተናግረዋል።
ኤስ ኦ ኤስ በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል በጦርነቱ  ምክንያት ከፍተኛ የስነ-ልቦና  ጉዳት፣ የአዕምሮ ችግርና አካላዊ ጉዳት ላጋጠማቸው እንዲሁም ሀብት ንብረታቸውን ላጡ ዜጎች ድጋፍ ለማድረግ የ145 ሚሊዮን ብር ፕሮጀክት ይፋ ያደረገ ሲሆን በቀጣይም በአፋርና በትግራይ የተጎዱትን ለማገዝ ሌላ ፕሮጀክት ይፋ እንደሚደረግም አቶ ሳህለማሪያም አበበ ጨምረው ገልጸዋል።
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተገኙት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ፣ ፕሮጀክቱ ስኬታማ እንዲሆን ከመንግስት ተቋማት ከሲቪል ማህበረሰብና ከሌሎች ባድርሻ አካላት ድጋፍ ሊደረግ እንደሚገባ ገልጸዋል። ከጀርመኑ ኤስ ኦ ኤስ የህጻናት መንደር በተገኘው በዚህ 4 ሚሊዮን ዩሮ፣ በሁለት አመት ውስጥ 200 ሺህ ተጎጂ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ ተገልጿል።

Read 11098 times