Saturday, 11 June 2022 18:16

መንግስት የሸኔንና የአልሸባብን ትስስሮሽ የመፍጠር እንቅስቃሴ ማምከኑን ገለጸ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

በሶማሌ ብሄራዊ ክልልና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች አልሸባብ ሲያደርጋቸው የነበሩ እንቅስቃሴዎችን እንዲሁም ከሸኔ ጋር የሞከራቸውን ትስስሮሽ የመፍጠር እንቅስቃሴ የጸጥታ አካላት በተጠና መልኩ ማክሸፋቸውን መንግስት አስታውቋል።
በወቅታዊ ሃገራዊ የደህንነትና ፀጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ሰሞኑን መግለጫ ያወጣው ብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤት፤ ባለፈው አንድ ወር በሁሉም ክልሎች የተከናወኑ የጸጥታ ማስከበር ተግባራት ውጤት እያመጡ መሆኑን አመልክቷል።
በተለይም በሃገሪቱ ደህንነት  ላይ አደጋ ደቅነው የነበሩ ሸኔ፣ ጁንታው እና አልሸባብን ከድርጊታቸው የሚገታ መጠነ ሰፊ እርምጃ መውሰዱን መግለጫው ጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም ብሄራዊ ም/ቤቱ ባለፈው ሚያዚያ ወር ባካሄደው ስብሰባው፤ ከኮንትሮባንድ፣ ከህገ-ወጥ ታጣቂዎች፣ ከፅንፈኛ የሚዲያና የፖለቲካ ቡድኖች፣ ከአክራሪ ሃይማኖተኞችና ከሙሰኞች የሚመጡ ፈተናዎች በሀገሪቱ ላይ ያስከተሉትን ስጋት መመልከቱን እንዲሁም የመንግስት መዋቅር የጥራትና ቁርጠኝነት ጉድለት እንደታየበት፣ የውጭ ሃይሎች ሴራና የውክልና ጦርነትን በተመለከተ ጥልቅ ማድረጉን አስታውሷል።
በዚህ ችግሮችን የለየ ግምገማ መነሻም ለእያንዳንዱ ችግር ምላሽና የማስተካከያ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ነው መግለጫው ያወሳው።
በወቅቱ ም/ቤቱ በተደራጁና ያለ ፍቃድ በታጠቁ ቡድኖች ላይ ህግን የማስከበር ስራ መሥራት እንዳለበት፣ በሁሉም አካባቢዎች የሚታዩ ህገ-ወጥ ተግባራት በፍጥነት መስተካከል እንዳለበት፤ በየአካባቢው የህዝብ ቅሬታ ምንጭ የሆኑ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ማስተካከል፤ ግጭት ቀስቃሽና ጽንፈኛ የሚዲያ አካላት፣ የፖለቲካ ቡድኖችና አክቲቪስቶች ህጋዊውን ስርዓት ብቻ እንዲከተሉ የሚያደርግ ስራ መስራት እንደሚገባና የመንግስትን መዋቅር ማጥራት እንደሚያስፈልግ አቅጣጫ አስቀምጦ እንደነበር አስታውሷል፡፡
በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የመንግስትን ሃይል በብቸኝነት የመጠቀም ህጋዊ ስልጣን የሚገዳደሩ ሃይሎችንና የህገ-ወጥነት ተግባራትን ወደተገቢው ስርዓት የማስገባቱ ስራ በታቀደለት መንገድና በተሻለ ጥራት እየተከናወነ መሆኑን ያመለከተው ም/ቤቱ፤ ሥራውም የታለመለትን ግብ እያሳካ እንደሆነ ማረጋገጡን አስታውቋል።
በኦሮሚያ ክልል በተከናወነ የህግ ማስከበር እርምጃ የሸኔን ልዩ ልዩ ቡድኖች መደምሰስ መቻሉን፣ በርካታ መሳሪያ መማረኩን፣ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን ማምከን መቻሉን፣ የቡድኑ አባላት ተቆጣጥረዋቸው የነበሩ አካባቢዎችን ማስለቀቅ መቻሉን አመልክቷል። በዚህም የሸኔን ሃይል ማዳከም መቻሉን እንዲሁም በሶማሌና በኦሮሚያ ክልል አዋሳኞች አልሸባብ አቅዶት የነበረውን እንቅስቃሴ መግታቱንና የሸኔና የአልሸባብን የጥምረት እንቅስቃሴ ማክሸፍ መቻሉን በመግለጫው አስታውቋል፡፡
በአማራ ክልል በተወሰዱ ተመሳሳይ የህግ ማስከበር እርምጃዎች፣ ከጸጥታ ተቋማት የከዱ አባላት መያዛቸውን፣ በተለያዩ ወንጀሎች የተሳተፉ መታሰራቸውን፣ ለጸጥታ ስጋት የሆኑ የጦር መሳሪያዎች መሰብሰባቸውን፣ በህገ-ወጥ ተግባር የተሰማሩ አክቲቪስቶችን ስርአት በማስያዝ የተሻለ የጸጥታ ስራ መሰራቱን ም/ቤቱ ባወጣው መግለጫው አመልክቷል።
በተመሳሳይ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ አዲስ አበባ በተወሰዱ ሰላምና ጸጥታን የማረጋገጥ እርምጃዎች፣ ውጤት መገኘቱን የብሄራዊ ምክር ቤቱ መግለጫ አመልክቷል። የተጀመረው ሰላምና ጸጥታን የማስፈን፣ ህግና ስርዓትን የማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተገልጧል፡፡




Read 11344 times