Saturday, 06 October 2012 15:03

የልጆች ባለውለታው

Written by  ብርሃኑ ሰሙ
Rate this item
(6 votes)

በያዝነው ዓመት መስከረም ወር መጀመሪያ ላይ ለእህቶቿ ልጆች የመማሪያ ቁሳቁስ ለመግዛት ወደ ጽሕፈት መሣሪያዎች መሸጫ መደብር የሄደችው ወ/ት ከበቡሽ፤ መደብሩ ውስጥ ባያቸው በአሜሪካ ባንዲራ የደመቀ “Proud to be an American!” የሚል ጥቅስ የታተመበት እርሳስ ከመገረምም በላይ አስደንግጧታል፡፡
የመደንገጧ ምክንያት “እርሳሱ በእጁ የገባ ልጅ በየዕለቱ በእርሳሱ ላይ የተፃፈውን ጥቅስ አእምሮው ላይ እያተመ ሲያድግ፣ ለማንነት ቀውስ ሰለባ መዳረጉ አይቀርም” የሚል አርቆ አሳቢነት ነበር፡፡


የወ/ት ከበቡሽ ስጋት ልጆች ላይ ብቻ የተጋረጠ አደጋ ነው ማለት አይቻልም፡፡ የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ሰለባ እንድንሆን ተመቻችተው የቀረቡልን ነገሮች አንድ ሁለት ተብለው በቀላሉ የሚቆጠሩና የሚያልቁ አይደሉም፡፡ ዕድሜን፣ ፆታን፣ የትምህርት ደረጃን፣ የሙያ ዓይነትን፣ የከተማና የገጠር ነዋሪን ሳይቀር ሁሉንም አካቶ እያጠቃ ያለ ወረራ መሆኑ በስፋት የሚታይ ነው፡፡ ገጣሚ መቅደስ ጀምበሩ “ንባስል” በሚል ርዕስ በ1984 ዓ.ም ባሳተመችው የግጥም መጽሐፍ ውስጥ ማንነቴን የሚያስጥል አደጋ ከብቦኛል የሚል መልዕክት ያዘለ አንድ ግጥሟ እንዲህ ይላል:-
ይዣቸው ባልገኝ…
የእጆችሽን ሙያ… የእጆችሽን ጥበብ
አንቺ እንደተቀበልሽ….
አልቀበልም ብል ካንቺ ባልረከብ
ከቶ ሆኖ አይደለም…
ስራሽን በመጥላት…. ሙያሽን በመናቅ
ራሴን ለመቻል… ሰርቼ ለማደር፤
ዘርቼ ለመብላት ኑሮዬን ለማረቅ
ሞያዬ አደረግሁት… የራሴን አግልዬ….
የሌሎችን ማወቅ… የሌሎችን ማድነቅ
በእርግጥ በጉዳዩ እየተጠቀሙበት ያሉ ወገኖች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ደስታውም ሆነ ጥቅሙ ዘላቂነት የለውም በሚል አቋም የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት ወረራውን ለመመከት ያስችላል ያሉትን ሀሳብ፣ ዕውቀትና ተግባራዊ ሥራዎች ለማከናወን የሚታገሉ ወገኖች ደግሞ በሌላ ጎን ቆመዋል፡፡
ለኢትዮጵያዊያን ሕፃናት የተረት፣ የእንቆቅልሽና የጨዋታ መፃሕፍትን አዘጋጅተው የሚያሳትሙ ደራሲያን፤ ትውልዱን ለማዳን ትግል ከሚያደርጉት ወገኖች ተርታ ሊመደቡ ይችላሉ፡፡ በ45 ዓመት የሕይወት ዘመን ቆይታቸው ለአንደኛና ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ለመማሪያነትና ለንባብ የሚያገለግሉ ከ40 በላይ መፃሕፍትን ያሳተሙት ዶ/ር ማይክል ዳንኤል አምባቸው በዚህ ምድብ ውስጥ ይካተታሉ፡፡
የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ከሚያዝያ 24-26 ቀን 2003 ዓ.ም የአፍሪካ ደራሲያን ዓለም አቀፍ ጉባኤ በአዲስ አበባ ባዘጋጀበት ወቅት ባሰራጨው አነስተኛ መጽሔት ላይ የዶ/ር ማይክል ዳንኤል አምባቸውን የጥናት ጽሑፍ ቀንጭቦ ያተመ ሲሆን ጽሑፉም የአፍሪካ ወጣቶች ለተዘዋዋሪ ቅኝ ግዛት ሰለባነት ስለመዳረጋቸው ይጠቁማል፡፡ እንዲህ ዓይነት ግንዛቤ ያለው ደራሲ የአገሩን ልጆች ታሳቢ አድርጎ የሚያዘጋጃቸው መፃሕፍት ምን ዓይነት ይዘት ሊኖራቸው እንደሚችል መገመቱ አስቸጋሪ አይሆንም፡፡ ልጆችን ተደራሽ ያደረገ ከ40 በላይ መጻሕፍት ወይም መጣጥፍ ማቅረብ መቻል በራሱ ያስገርማል፡፡ በዶ/ሩ ሥራዎች ላይ ጥናት የሰሩ ወይም ሙሉ ሥራዎቻቸውን የሚያውቁ አካላት በሚያገኙት አጋጣሚና በሚችሉት አቅም ምስክርነታቸውን ቢሰጡ ብዙዎች ይማሩበታል የሚል ግምት አለኝ፡፡ ዶ/ር ማይክል ዳንኤል አምባቸው ማን ነበሩ? ለሚለው ጥያቄ ባለፈው ሳምንት የቀብር ሥነ ሥርዓታቸው በተፈፀመ ወቅት ከተነበበው የሕይወት ታሪካቸው በጥቂቱ ላቀርብላችሁ፡፡
ከአቶ ዳንኤል አምባቸውና ከሲስተር ባርብራ ዳንኤል፣ ሞስኮ /ሩስያ/ ውስጥ በ1960 ዓ.ም የተወለዱት ዶ/ር ማይክል፤ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ሳንፎርድ ትምህርት ቤት ተምረው ሲያጠናቅቁ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ገቡ፡፡ እንግሊዝኛ ቋንቋና ስነ ጽሑፍ አጥንተው በ1979 ዓ.ም በዲግሪ ሲመረቁ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ ነበሩ፡፡ ከዩኒቨርስቲ ትምህርታቸው ጎን ለጎን በአሊያንስ ፍራንሲስ ትምህርት ቤት የፈረንሳይኛ ትምህርት በመከታተል በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡
በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ተመድበው በመስራት ላይ እያሉ ስኮላርሺፕ አግኝተው ወደ እንግሊዝ በመሄድ በሥነ ትምህርት የማስትሬት ዲግሪያቸውን አገኙ፡፡ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ያገኙት በደቡብ አፍሪካ በሚገኘው የፕሪቶሪያ ዩኒቨርስቲ ሲሆን፤ በእንግሊዝኛ ቋንቋና በስነ ጽሁፍ ነበር ያጠናቀቁት፡፡
በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ በመምህርነት 9 ዓመት ባገለገሉበት ወቅት በፍሪላንስነት ትምህርት በቴሌቪዥን አቅራቢ ሆነው ሰርተዋል፡፡ ከኮተቤ መምህራን ኮሌጅ በተጨማሪ በብሪቲሽ ካውንስል፣ በእንግሊዝ ሕፃናት አድን ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን፣ በኢትዮጵያ የትብብርና ምርምር ኤጀንሲ፣ በኢትዮጵያ የሰላምና ልማት አለም አቀፍ ኢንስቲትዩት በተርጓሚነት፣ በኤክስፐርትነት፣ ኮርሶችን በመቅረጽና ማንዋሎችን በማዘጋጀት ሙያዊ አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡
ብዙ መስራት በሚችሉበት ዕድሜ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ዶ/ር ማይክል ዳንኤል አምባቸው፤ ለኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ፕሬስ፣ ለሊንክ ኮሚዩኒቲ ዴቨሎፕመንት፣ ለኖርዌይ ሕፃናት አድን ድርጅት፣ ለኦፍታልሚክ ሶሳይቲ ኦፍ ኢትዮጵያ ሙያቸውን፣ ልምዳቸውን ዕውቀታቸውን በተለያየ ደረጃ አካፍለዋል፡፡
ከተለያዩ አካላት በርካታ ሽልማቶችን ያገኙት ዶ/ር ማይክል ዳንኤል አምባቸው አዘጋጅተው ያሳተሟቸው መጻሕፍት፣ ተደራሽነቱን ለሕፃናት በማድረጉ ምክንያት ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ሕፃናት አድን ህብረት ልዩ ምስጋናና ሰርተፍኬት ተበርክቶላቸዋል፡፡
ከዚህ ዓለም በሞት እስከተለዩበት ጊዜ ድረስ በአፍሪካ ሕብረትና በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የቋንቋ መምህር በመሆን በማገልገል ላይ የነበሩት ዶ/ር ማይክል ዳንኤል አምባቸው ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነበሩ፡፡ ከአሁን በፊት የታተሙላቸውን ሳይጨምር ለልጆች ያዘጋጇቸውን 11 መፃሕፍት ለማሳተም ከ”ፊደል አሳታሚ” ጋር ተዋውለው ሕትመቱ ተጀምሮላቸው የነበሩት ዶ/ር ማይክል ዳንኤል አምባቸው፤ በእንግሊዝኛና በአማርኛ ቋንቋ ካሳተሟቸው መፃሕፍት መካከል የሚከተሉት ይገኙባቸዋል:-
Tales of Toteet
Butu Lord Of The Ants
A Cluster Of Rejections
Shadows
Alemayehu
Adey’s Pigeons
Cheray’s Great Run
Tales of Abuna Aregawi
Welcome To Addis
Animal Tales From Sidama
Blame Me Not
Traditional Sidama Tales
የሚጣ ሚስጥር
ካሣ
ኩኩሉ

Read 3858 times