Saturday, 11 June 2022 19:44

ጨቅላ ሲወለድ የሚታይ የሰውነት መጉዋደል…

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

  በአለም አቀፍ ደረጃ ከ60.142 ውልደቶች ወደ 384 የሚሆኑት ጨቅላዎች Congenital malformation ተፈጥሮአዊ ችግር ያለባቸው መሆኑን እ.ኤ.አ ኖቨምበር 30/2020 የወጣ መረጃ ያስነብባል፡፡ ችግር ያለበት ተፈጥሮ በእዛኛውም የጡንቻና የጀርባ አጥንት ችግሮች መሆናቸውን መረጃው ይጠቁማል፡፡ ይህ ተፈጥሮአዊ ችግር በአብዛኛው ከልብ እና የነርቭ መስመሮች ጋር በተያያዘም እንደሚከሰት እ.ኤ.አ ፌብሩዋሪ/2022 የወጣ መረጃ ይጠቁማል፡፡
Congenital malformation ተፈጥሮአዊ ችግር ያላቸው ሕጻናት በታዳጊ አገሮች ምን ያህል ይወለ ዳሉ ተብሎ ለሚነሳው ጥያቄ መረጃው እንደሚጠቁመው በአለም ላይ ከሚወለዱት 85% ያህሉ ችግ ያለባቸው ህጻናት የሚወለዱት በታዳጊ ሀገራት ነው፡፡ ከእነዚህ ሀገራት አራት ያህሉ ብቻ ችግር ያለባቸውን እርግዝናዎች በሚመለከት የሚመለከቱባቸው አሰራሮች አሉዋቸው ያሉት በቻይና ብሔራዊ መረጃ ላቦራቶሪ የስነተዋልዶ ጤናና የህጻናት ጉዳይ ዳይሬክተር Li Zhu, ተናግረዋል፡፡
ጨቅላዎቹ ሲወለዱ የሚታዩት የሰውነት መጉዋደሎች የተለያዩ ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ከደረት በላይ ወይንም በታች ያለው አካል ሙሉ በሙሉ ላይፈጠር ይችላል፡፡ ጭንቅላት ላይ ምንም ሌላ ነገር ሳይጨምር ማለትም አይን አፍ ጆሮ ሳይኖረው ድቡልቡል ቅርጽ ይዞ ሊወለድ ይችላል፡፡ የጀርባ አጥንት አለመኖር፣ እጅ ወይንም እግር አለመኖር፣ አለዚያም እጅና እግር ተፈጥረው ነገር ግን አጥንት ሳይኖራቸው ወይንም ሰው መሆኑ እስኪያጠራጥር የተለያዩ ቅርጽ ይዞ የመወለድ አጋጣሚ ሊኖር ይችላል። የጣት ቁጥር መጉደል፣ የከንፈር መሰንጠቅ እና የውስጥ የአፍ አካላት መታየት፣ የብልት ሁኔታ በተሙዋላ መልክ አለመፈጠር የመሳሰሉት ሁሉ ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች ምክንያት ምንድናቸው የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የተለያዩ መረጃዎቸ ያስነበቡትንና ለዚህ እትም ማብራሪያቸውን እንዲሰጡን ከአሁን ቀደም የጋበዝናቸው እንግዳ ዶ/ር ብርሀኑ ከበደ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት ናቸው፡፡
በሳይንሳዊ ቃሉ (Congenital malformation) የሚባለው ጽንስ በማህጸን ውስጥ እንዳለ ተፈጥሮአዊውን ሂደት በትክክል ወይንም በተሙዋላ መልኩ ሳይጨርስ አካላቱ በተጉዋደለ መልኩ እንዳለ ሲወለድ ማለት ነው እንደመረጃዎች እማኝነት፡፡ ይህ የሰውነት መዛባት ልጆች ይዘውት የሚወለዱት ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ተፈጥሮአዊ ችግሩ የባሰ እና በተለያዩ የምርመራ ዘዴዎች ሲገኝ እና በተለይም ሕይወት የሌለው ከሆነ እስከ ዘጠኝ ወር ድረስ በማህጸን መቆየቱ ቀርቶ ጽንሱ እንዲቋረጥ በሕክምና ባለሙያዎች የሚመከርበት ጊዜም ያጋጥማል፡፡
ዶ/ር ብርሀኑ ከበደ ቀደም ሲል ለዚህ እትም እንደገለጹት የወንድና የሴት የዘር ፍሬ በዘር ማስተላለፊያ ውስጥ መገናኘታቸውን ተከትሎ ጽንሱ ይፈጠራል፡፡ ከዚያም የተፈጠረው ጽንስ በመጀመሪያ ወደአልዳበረ ሼል ከዚያም የዳበረ ሼል እየሆነ ደረጃ በደረጃ በአማካኝ በ7/ቀን ውስጥ ጉዞውን ወደ ማህጸን ግድግዳ በማድረግ ግድግዳው ላይ ይጣበቃል፡፡ ከዚያም ቀስ በቀስ በተለያዩ ጊዜያት የሰውነት ክፍሎች ይፈጠራሉ። በጠቃላይም በጣም ትንሽ ከሚባሉ የነርቭ ስርአት እና የመራቢያ አካላት ውጪ የሽሉ የአካል ክፍሎች ሽሉ በተፈጠረ በ8/ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ተፈጥረው ያልቃሉ፡፡ ከዚያ በሁዋላ  የተፈጠሩት አካላት አካላዊ እድገት ይቀጥላል፡፡
እንደ ዶ/ር ብርሀኑ ማብራሪያ የአፈጣጠር ችግር ሲባል የመጀመሪያውና አብዛኛውን ድርሻ የሚይዘው ጽንሱ ገና ከመጀመሪያው ማለትም ከመነሻው የሚገጥመው ውስጣዊ የአፈጣጠር ችግሮች ሲሆኑ ይህም ማለት…››
1/ ችግር ገጥሞታል የሚባለው አካል ላይፈጠር ይችላል፡፡
2/ ወይንም በከፊል ሊፈጠር ይችላል፡፡
3 /አለበለዚያም በተበላሸ ወይንም ትክክል ባልሆነ መንገድ ሊፈጠር ይችላል ማለት ነው፡፡
እነዚህ ችግሮች በአብዛኛው ሊፈጠሩ  የሚችሉት ጽንሱ በተፈጠረ ስምንት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ሲሆን ጽንሱ ተፈጥሮ ካለቀ በሁዋላም በጽንሱ ቅርጽና ይዘት ላይ የሚመጡ ችግሮች አሉ፡፡ይህም በማህጸን አካባቢ በሚከሰቱ አንዳንድ ችግሮች…ለምሳሌም
ጽንሱን አቅፎ የሚይዘው የሽርት ውሀ መጠን መቀነስ፣
የማህጸን እጢዎች፣ አልፎ አልፎም የእራሱ የማህጸን የተፈጥሮ ችግር በሚኖርበት ጊዜ፣
አልፎ አልፎም መንታ ሆነው በሚፈጠሩበት ጊዜ ሊያጋጥም በሚችል የቦታ መጣበብ ምክንያት በሽሉ ላይ የተለያዩ የቅርጽ ለውጦች ይታያሉ፡፡
ተፈጥሮ ባለቀው ጽንስ ላይ አልፎ አልፎም በደም ስሮች መዛባት፣ ከእናት ወደልጅ በሚሄዱ ኢንፌክሽኖች ምክንያት እንዲሁም በተለያዩ በሚያጋጥሙ ጉዳቶች ምክንያት የተፈጠረው ጽንስ መበላሸት ሊያጋጥመው ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜም የተፈጠሩ ሕዋስ ወይንም ሴሎች በተደራጀ መልኩ ወደተደራጀ ሕዋሳት ወይም (ቲሹ) በትክክል አለመቀየራቸውም ችግር ሊያስከትል ይችላል፡፡
ለመሆኑ የአፈጣጠር ችግር ሊያስከትሉ ይችላሉ የሚባሉት ነገሮች ምንድናቸው?
ለመርዛማ ቁሳቁስ ተጋላጭነት፡-
እርጉዝ እናቶች በመድሀኒት ምክንያት ፣በሚለበሱ ልብሶች፣ ወይንም በተለያዩ ሱስ አስያዥ እጾች ምክንያት ፣በስራ ወይንም በአኑዋኑዋር ምክንያት ለመርዛማ ቁሳቁሶች ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡ ለእነዚህና ለመሳሰሉት መርዛማ ነገሮች ተጋላጭ የሆኑ እናቶች የሚወልዱዋቸው ልጆች የሆርሞን መዛባት፣
የደም ህዋሳት መዛባት ፣
የኦክስጂን እጥረት እና የመሳሰሉት ችግሮች ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡
ሲጋራ የሚያጨሱ ወላጆችም በልጆቻቸው ላይ የካንሰር ተጋላጭ ነታቸውን እድል ይጨምረዋል፡፡
በአንድ ወቅት 200/ግለሰቦች ላይ በተደረገ ጥናት እንደታየው  2/በመቶ የሚሆኑት ከመርዛማ ቁሳቁሶች ግፋ ቢል ለአንደኛው ተጋላጭ እንደነበሩ መረጃው ይጠቁማል፡፡
መድሀኒቶች፡-
ጽንስን ለአካላዊ እክል ከሚዳርጉ ምክንያቶች መካከል መድሀኒቶችና አጋዥ የሆኑ እንክብሎች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ መድሀኒቶች ሲባል እጅግ ታዋቂ ከሆነው ቴላማይድ ከተባለው መድሀኒት ጋር የሚገናኘውን ይጨምራል ፡፡ ይህ መድሀኒት በ1950/ዎቹ የተገኘ መድሀኒት ሲሆን እርጉዝ ሴቶች በእንቅልፍ እጥረት ምክንያት የሚያጋጥማቸውን መረበሽ ለመቀነስ ይታዘዝ የነበረ መድሀኒት ነው፡፡ ለዚህ አገልግሎት በሚል ከ1956-1962/ዓ/ም በ50/አገራት ውስጥ በስፋት ሲታዘዝ ነበር፡፡ በተመሳሳይ ጊዜ በተወለዱ ከ8-10‚000/በሚደርሱ ልጆች ላይ የታየው የረጅሙ አጥንት መዛባት ከመድሀኒቱ ጋር በመያያዙ በ1961/ዓም ጥቅም ላይ እንዳይውል ቢደረግም አሁንም በተለያዩ ምክንያቶች ጥቅም ላይ መዋሉ አልቀረም፡፡ ይህን መድሀኒት የሚወስዱ ወላጆች የሚወልዱዋ ቸው ልጆች ላይ ከሚታዩ እክሎች መካከል የጆሮ፣ የልብ፣ የምግብ መፈጨት ስርአት መዛባት እና ሌሎች መዛባቶችን ያደርሳል፡፡
አልኮሆል፡-
ባገኘነው መረጃ እንደተጠቆመው በመጀመሪያ ደረጃ ወላጆች አልኮሆል ተጠቃሚ መሆናቸው ለጽንሱ ተፈጥሮአዊ ችግር ማስከተል አንዱ ምክንያት ነው፡፡ ጽንሱ ለአልኮሆል ይዘት ሲጋለጥ የፊት ገጽታ፣  የአእምሮ መበላሸት እና የንቃተ ሕሊና ዝቅተኛነትን ሊያስከትልበት ይችላል፡፡ በተጨማሪም የልጆች የመረ ዳት ክህሎት መቀነስ ፣የባህሪይ መዛባት ፣የማስታወስ ችሎታ መቀነስ፣ የጭንቀት ስሜ ትን መቋቋም አለመቻል ከወላጆች አልኮሆል ተጠቃሚነት ጋር እንደሚያያዝ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡


Read 21260 times