Saturday, 18 June 2022 17:30

በ6.5 ቢሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመው አማራ ባንክ ዛሬ ይመረቃል

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(0 votes)

    70 ቅርንጫፎቹ ዛሬ ስራ ይጀምራሉ

               አማራ ባንክ አክስዮን ማህበር ዛሬ ሰኔ 11 ቀን በ70 ቅርንጫፎች  በይፋ ስራውን እንደሚጀምር አስታወቀ፡፡ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም የቅርንጫፎቹ ብዛት 100 እንደሚደርስም የባንኩ ሀላፊዎች አስታውቀዋል፡፡
አማራ ባንክ አክስዮን ማህበር በተፈረመ ካፒታል ብር 6 ቢሊዮን 516 ሚሊዮን 327 ሺህ 599፣ በተከፈለ ብር 4 ቢሊዮን 825 ሚሊዮን 763 ሺህ 703 አቅሙን ገንብቶ፤ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ በባለአክስዮኖች ብዛት ክብረ ወስን በመስበር ገበያውን  መቀላቀሉን ነው ሀላፊዎቹ  የተናገሩት፡፡
ባንኩ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአክስዮን ሽያጭ ወይም የባለ አክሲዮን ቁጥር ከማስመዝገብ ባሻገር ከመላ የሐገሪቱ ክፍሎችም ሆነ በውጭ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን መጠነ  ሰፊ ተሳትፎ የተመሰረተ  ሲሆን “ከባንክ ባሻገር” የሚለው መሪ ቃሉም ባንኩ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ላይ ከባንክ አገልግሎት ባሻገር የሚተገብረውን መጠነ  ሰፊ ስራዎች የሚያሳይ ነው ተብሏል፡፡
ባንኩ በበጎ ፈቃደኝነት፣በነፃና የተቋም ግንባታ ፋይዳ በገባቸው፣እንዲሁም የተናገሩትን በሚተገብሩ አደራጆች መመስረቱ አሁን ያለበት ስኬት ያሳያል ሲሉ ሀላፊዎቹ ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት እሴት ጨማሪ ባንክ ለመሆን የቅድመ  ዝግጅት ሥራውን አጠናቅቆና ህዝባዊ መሰረቱን ጠብቆ ለመጓዝ የያዘውን ቁርጠኝነት በፅናት መቀጠሉን በተለይ ባንኩ በፋይናንሱ ዘርፍ አስተውሎት ያላገኙ፣ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ አዳዲስ አሰራሮችን እየቀየሰ ዘመናዊ የባንክ አገልግሎት መስጠት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫው እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡
የባንኩን ጅማሬ በጉጉት ለሚጠብቀው ህብረተሰብ የተለያዩ የተግባቦት ሥርዓቶችን አንግቦ እየመጣ ነበር ያሉት ሃላፊዎቹ ከነዚህም መካከል “ከጎንዎ ማን አለ” የሚለው ጋባዥና ልብ አንጠልጣይ መሪ ቃል ይገኝበታል ብለዋል። በዚህም ብዙዎችን ማሳተፍና  ቀልብ መሳብ መቻሉን ሀላፊዎቹ ጠቁመው “አማራ ባንክ ከጎንዎ አለ”  በማለትም ባንኩ ራሱን መግለጹን ሀላፊዎቹ አብራርተዋል፡፡
በዛሬው የባንኩ ምረቃና ይፋዊ የስራ ጅማሮ ለገሀር በሚገኘው  የባንኩ ዋና መስሪያ ቤት እንደሚበሰርም  ታውቋል። ባንኩ ዛሬ በሚካሄደው የምረቃ በዓል በልዩ ሁኔታ ለአዲስ አበባና በዙሪያው ለሚገኙ አንበሳ  አውቶቡስ ተጠቃሚዎች የሙሉ ቀን (ከጠዋቱ 12፡00 እስከ ምሽት 3፡00) የጉዞ ክፍያን ባንኩ የሸፈነ ሲሆን የዕለቱ የአንበሳ አውቶቡስ ተጠቃሚዎች በነፃ ወደሚፈልጉበት ቦታ መጓጓዝ እንደሚችሉ አብስሯል፡፡
ዛሬ ረፋድ ከ3፡00 ጀምሮ በሚከናወነው የባንኩ ምረቃ  ስነ- ሥርዓት ላይ ትልልቅ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች የግልና የመንግስት ባንኮች ከፍተኛ አመራሮች፤ ባለ አክስዮኖች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚታደሙ ታውቋል፡፡

Read 11698 times Last modified on Saturday, 18 June 2022 17:48