Saturday, 18 June 2022 17:47

"ኢዜማ በግለሰቦች ፍላጎት እንዳይፈርስ ሆኖ የተሰራ ነው"

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(0 votes)

 አዲስ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች የአመራረጥ መንገድን ለኢትዮጵያ ፖለቲካ እያስተዋወቀ የሚገኘው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)፤ ለቀጣይ ሦስት ዓመታት ፓርቲውን የሚመሩ እጩዎችን እያወዳደረ ነው፡፡ በተመሳሳይ የፓርቲውን የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ለመምራትም አባላቱ ለሊቀመንበርነትና ለምክትልነት ሊቀመንበርነት  እየተወዳደሩ ይገኛሉ፡፡
ፓርቲውን ለቀጣይ ሶስት ዓመታት በሊቀመንበርነት ለመምራት እየተወዳደሩ ከሚገኙት እጩዎች መካከል ዶ/ር ባንትይገኝ ታምራት አንዱ ናቸው። ኢዜማን በሊቀመንበርነት ለመምራት የፈለጉበትን ምክንያትና አላማቸውን እንዲሁም ኢዜማ እስከዛሬ የተጓዘባቸውን መንገዶችና ወደፊት የሚጠብቁትን ተግዳሮቶችና መልካም እድሎች በተመለከተ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገዋል።

                    ኢዜማ  ከተመሰረተ በኋላ ባለፉት ሦስት ዓመታት የተጓዘባቸውን መንገዶች እንዴት ይገመግሙታል?
ባለፉት ሶስት ዓመታት ኢዜማ ይዞት የመጣው የራሱ የፖለቲካ ፍልስፍና አለ፤ የፖለቲካ ፕሮፖዛልም አለ። ይሄን ጉዟችንን በተለያዩ አጋጣሚዎች ተቀምጠን የገመገምንባቸው ጊዜያት አሉ። በአጠቃላይ የገዥውን ፓርቲ ጨምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እይታና ልማዳዊ አመራር መሰረት፤ አንዴ ሊቀመንበር ወይም መሪ የሆነ ሰው እስከ መጨረሻው ድረስ በዙፋኑ እንደጸና ይቆያል። ለ10 ዓመት  ወይም 15 ዓመት ሁሌ መሪ ሁሌም ሊቀመንበር ሆኖ የሚታየው አንድ ሰው ነው። እንደዚህ አይነት አሰራርን ወይም ባህልን ነው ኢዜማ የቀየረው። ኢዜማ ሲደራጅ የጀመረው ከወረዳ ነው። ከታች ወደ ላይ ነው ተዋረዱ የመጣው። ከ350 በላይ የምርጫ ወረዳዎች ላይ ጠንካራ መሰረት ያለው ፓርቲያችን፤ በአንድና ሁለት ሰው ላይ ብቻ ሊንጠለጠል አይችልም። አዳዲስ አቅም ያላቸው ሰዎችም እንዳሉ ማሳየት ተገቢ ነው የሚሆነው። አሁን ያሉት መሪዎችም ተተኪ መኖሩን ለማሳየትና ተተኪ ለማፍራት ችግር የለባቸውም። ኢዜማ ውስጥ የሰው ሃይል ችግር የለም። የሰው ሃይል ችግር ከሌለ ደግሞ ኢዜማን ወደፊት ሊያራምዱ የሚችሉ አዳዲስ ፊቶች መምጣት አለባቸው የሚል እምነት አለን። ኢዜማም ለዚህ ዝግጁ ነው።
እርስዎን ወደ ውድድሩ እንዲገቡ ያደረገዎት የተለየ ምክንያት አለዎት?
 ወደዚህ ውድድር እንድገባ ከጋበዙኝ ነገሮች አንዱ ባለፉት ሶስት አመታት እንግዲህ የተሰሩ ጠንካራ ስራዎች አሉ። ነገር ግን ክፍተት ያለባቸውና ሊሞሉ ይገባል የምንላቸው በኛ በኩል ነቅሰን ያወጣናቸው ጉድለቶችም አሉ። እነዚህን ጉድለቶች ደግሞ ለመሙላት እንችላለን ብለን እናስባለን። ከዚህ አንጻር አዳዲስ አሰራሮችን ቀይሰን የመጣን ስለሆነ እንድንወዳደር ያደረገን አንዱ ምክንያት ይህ ነው። ሌላኛው በተለይ እኛ የምርጫ ወረዳዎችን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ አሰላለፍ ነው ያለን። ከታች ወደ ላይ ነው የፖለቲካ አሰላለፋችን። ስለዚህ በእያንዳንዱ ወረዳ ውስጥ ያሉ መሰረታዊ ችግሮች ምን ይመስላሉ የሚለውን ነገር በደንብ ካየን በኋላ እነዛ ችግሮች በዘላቂነት ሊፈቱ የሚችሉበት አማራጭ መፈጠር አለበት ከሚል መነሻ ነው፣ ወደዚህ ውድድር የገባነው።
ኢዜማ ከተመሰረተ በኋላ ይዞ የተነሳውን አላማ ከማሳካት አንጻር የገጠሙት ተግዳሮቶችና መልካም አጋጣሚዎች በእርስዎ ግምገማ  ምን ይመስላሉ ?
ከኢዜማ ምስረታ ጀምሮ ያለው የ3 ዓመት እድሜ በጣም ብዙ ነው ብሎ መውሰድ  አይቻልም። በእነዚህ በቆየንባቸው ጊዜያት ግን ቢያንስ ከሌሎቹ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በተሻለ አቅም ወረዳን ማዕከል ያደረገ መዋቅር መዘርጋት የቻለ ትልቅ ፓርቲ ነው። ምክንያቱም በወረዳ ደረጃ መዋቅር ዘርግቶ እየሰራ የቆየ ፓርቲ የለም። ለ20 እና ለ30 ዓመታት ዝም ብለው እድሜ እየቆጠሩ የዘለቁ  ፓርቲዎች አሉ። እኛ በ3 ዓመት ውስጥ ይሄን ማሳካታችን በራሱ እንደ ትልቅ ድል አድርገን እንወስደዋለን። በሁለተኛ ደረጃ፣ በተለይም የ2013 አገራዊ ምርጫን ተከትሎ በተለይም እጩ ምልመላን በተመለከተ በብዙዎቹ ወረዳዎቻችን እጩዎች ማቅረባችንና በተለይ ከገዥው ፓርቲ ጋር ተወዳዳሪ ሆነን የቀረብንበት ሁኔታ አንዱ ትልቅ ስኬት ነው የሚል ግምገማ አለን። በሶስተኛ ደረጃ፣ የያዝነውን የማህበራዊ ፍትህ ፍልስፍና ለማስረጽ የበኩላችንን ከፍተኛ ጥረት አድርገናል። ከእነዚህ መመዘኛዎች አንጻር ውጤታማ ነበርን ብለን እናስባለን። ነገር ግን ከባለፈው ምርጫ ጋር ተያይዞ ወደ ምርጫ ከመግባታችን በፊት በስርአትና በወጉ የብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ በምርጫው የሚወዳደሩ ፓርቲዎችን አስተሳሰብና አሰላለፍ በደንብ በመፈተሽ በኩል ክፍተት ነበረብን ብለን እናስባለን።
እነዚህን ጉድለቶች ለማስተካከል በእናንተ በኩል የተነደፉ ሥልቶችና ዕቅዶች ምንድን ናቸው ?
ለእቅዳችን መነሻ የሚሆነን ባለፈው ሶስት ዓመት የነበረው ስራ አስፈጻሚ በእቅድ ደረጃ የያዛቸው የፓርቲው ስራዎች አሉ። እነዚህን አጠቃላይ እቅዶች በሰከነ መንገድ ቁጭ ብለን የመፈተሽ ስራ እንሰራለን። ሁላችንም የምንሰራው ለኢዜማ እስከሆነ ድረስ በተቻለ አቅም የተከናወኑት እንደተጠበቁ ሆኖ፣ እነሱን እያጠናከርን መቃናትና መተግበር ያለባቸው ጉዳዮችን ካየን በኋላ እነሱን ተግባራዊ ለማድረግ አበክረን እንሰራለን። ከዚህ በተጨማሪ አዲስ አመራር ሆነን ስንመረጥ፣ በየ3 ወሩ የሚገመገም የራሳችንን እቅድ ይዘን እንመጣለን። በሌላ በኩል፤ሁላችንም እንደምናውቀው በኢዜማ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች አንድ ባህል አለ። ሁሉም የስራ አስፈጻሚ አባል ብዙ ጊዜ የሚዋቀረው እዚሁ አዲስ አበባ ከሚኖሩ የፓርቲው አባላት ነው። ይሄ በኛ እምነት መስተካከል ያለበት ነው። እኛ ከተመረጥን በተቻለ መጠን በየክፍለሀገሩ የሚገኙ መዋቅሮቻችን በስራ አስፈጻሚም ሆነ በተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎች ውስጥ አብረው የሚካተቱበትን ሁኔታ እንፈጥራለን። ሌላው መሰረታዊ ነገር እንግዲህ ከዚህ በፊት በእኛና በተለያዩ ፓርቲዎች አባላት ላይ የሚደርሱ ግፎችና በደሎች አሉ። በዚህ ዙሪያ ጠንካራ ስራ እንሰራለን። በመንግስት ካድሬም ሆነ አመራር የሚዋከብና የሚታሰር የኢዜማ  አባል እንዳይኖር ጠንካራ ክትትል ማድረጊያ ሥርዓት እንዘረጋለን፡፡ ሌላው እያንዳንዱ የምርጫ ወረዳ የራሱን የበጀት ፍላጎት ማሟላት አለበት የሚል አሰራር አለን። አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታና ከህዝባችን አቅምና ንቃተ ህሊና አንጻር ይህን የሚፈቅድ ሁኔታ እምብዛም የለም። ተፎካካሪ ፓርቲዎችን በገንዘብ መደገፍ በኢትዮጵያ ውስጥ የተለመደ ነገር አይደለም። እዚያ ደረጃ ለመድረስ ገና ብዙ መሰራት ያለበት ስራ አለ። ስለዚህ የምርጫ ወረዳዎቹ በገንዘብ እጥረት ምክንያት ቢሮአቸውን እንዳይዘጉና አባላት እንዳይፈናቀሉብን፣ በማዕከል ደረጃ ከሃገር ውስጥም ከውጪም ፈንድ የማሰባሰብ ስራው በጠንካራ ሁኔታ እንዲሰራ ተደርጎ የሚደጎሙበትን ስርዓት መፍጠር አለብን የሚል እምነት አለን።
አሁን በመጀመሪያ ዙር ከታዩ የመወዳደሪያ ቅስቀሳ መልዕክቶችና ከቀረቡ ሃሳቦች በመነሳት ኢዜማ ውስጥ  የአቋምና የአላማ ልዩነቶች እንዳሉና ምናልባትም ከምርጫው በኋላ ፓርቲው ሊከፋፈል እንደሚችል ስጋቶች ተፈጥረዋል፡፡ እርስዎ ምን ይላሉ?
ይህ ጥሩ ጥያቄ ነው፤ በሚገባ መብራራትም አለበት። እውነት ለመናገር ከሆነ እኛ ኢዜማን ስንመሰርት ወደ ስምንት ፓርቲዎች ነበርን። እነዚያ ፓርቲዎች ፈርሰው እንደገና ሁላችንም እያንዳንዱን ወረዳ ማእከል አድርገን እንደ አዲስ የተደራጀንበት ሚስጥር እንዲህ አይነቱን ነገር ለማስቀረትና ለመከላከል ነው። ያ ማለት አንድ ሰው በሆነ ምክንያት ከኢዜማ ቢያፈነግጥ፣ ይሄ ሰው ራሱን ችሎ ወጥቶ ይቀራል እንጂ የፓርቲውን መዋቅር ሊያፈርስ የሚችልበት አቅም በምንም መልኩ የለውም። ምክንያቱም መሰረታችን ወረዳ ነው። በወረዳ ያለንን መዋቅር ደግሞ ማፍረስ የሚቻልበት እድል የለም። ለምሳሌ እኔና ሃሳቤ አልተመረጥንም የሚሉና በዚህም የሚያኮርፉና መውጣት የሚፈልጉ ካሉ ራሳቸውን ይዘው ይወጣሉ እንጂ የፓርቲውን መዋቅር አፍርሰው የሚወጡበት እድል የለም። በሌላ በኩል ጽንፍ ይዞ የመከራከር የመወዛገብ ነገር አለ የሚለው በአመዛኙ በውጭ የሚወራ ነው እንጂ በመካከላችን የሃሳብ ልዩነት ቢኖርም እንኳ ሌላ ችግር መፍጠር የሚችል አቅም የለውም። በጣም ጤናማ ነው። ከዚያኛው የተሻለ መሪ እሆናለሁ ወይም የተሻልኩ መሪ ነኝ ብሎ ሃሳቡንም በዝርዝር ይዞ መዋጋት በጣም ጤናማ አካሄድና የውስጠ ፓርቲ ዲሞክራሲያችን ማሳያ ነው እንጂ ችግር አይደለም።
እኔ እንደ ሊቀመንበር ከተመረጥኩ በመሪነት ደረጃ ካሸነፈው ጋር ተጣጥሞ ለመስራት ነው ዝግጁነቴ። የኢዜማ መርህና አሰራርም ይሄው ነው። እንደ መልዕክት ማስተላለፍ የምፈልገው በተለይ የኢዜማ ጉባኤ አባላት የመምረጫ መመዘኛችሁ በግለሰብ ማንነት ላይ ብቻ ሳይንጠለጠል፣ ኢዜማን የሚያስቀጥለው ሃሳብ የቱ ነው በሚለው ላይ እንዲሆን ነው፡፡ እንዲሁም ይሄን የኢዜማ ጉባኤን ሂደት የምትከታተሉ ውድ ኢትዮጵያውያን፤ የያዝነውን የማህበራዊ ፍትህ ፍልስፍናን ለማስረጽ በምናደርገው ትግል የበኩላችሁን ድጋፍ እንድታደርጉልን ከወዲሁ ጥሪ አቀርባለሁ። አመሰግናለሁ።

Read 2954 times