Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 06 October 2012 15:17

ገብረክርስቶስ ደስታ በሚካኤል ሙዚቃ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

በሀገራችን የስነ - ፅሁፍ ታሪክ ከበቀሉት ገጣሚያን ገ/ክርስቶስ ደስታ ተጠቃሹና የራሱ የሆነ ልዩ ማንነት ያለው ነው፡፡ ሰዓሊና ገጣሚ ገ/ክርስቶስ ከነበረው ጥልቅ የስነ - ጥበብ ፍቅርና የምዕራባዊው ስነ - ጥበባዊ መረዳትና ተሞክሮ፣ የስነ - ግጥም ስራዎቹ ከተለመደው የአማርኛ ስነ - ግጥም ዘይቤ በቴክኒክም ሆነ በይዘት ፍፁም የተለየ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ከሁሉም በላይ የገብሬ ግጥሞች አይነተኛ መለያቸው የሚያቀነቅኑት በተፈጥሮ፣ በሰው ልጅ፣ እና በኑሮ ረቂቅ እንቆቅልሽ ላይ የተመሰረተው ጭብጣቸውና በነፀሩ ስሜቶች የበለፀጉ መሆናቸው ነው፡፡


ይህን የገብሬን ታላቅ ስነ - ጥበባዊ ልቀት እንዳለ ሆኖ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ ባለፈው ሳምንት በተለቀቀው የሚካኤል በላይነህ “ፍቅርና ናፍቆት” በተሰኘው አልበም ውስጥ በዜማ የተቀነቀነው “ውድ እወድሻለሁ” የሚለው የገብረክርስቶስ ደስታ ታዋቂ የፍቅር ግጥም ነው፡፡
በአንድ በኩል ሚካኤል በላይነህ የገብሬን ግጥም በዜማ ሰርቶ ለህዝብ በማቅረብ ይህን ታላቅ ሰዓሊና ገጣሚ ለጊዜው ሰው ማስተዋወቁና ማስታወሱ፣ በሌላ መልኩ አርቲ - ቡርቲ በሆኑ የፍቅር ዜማዎች በምንደነቁርበት በዚህ ጊዜ ፍቅርን የመሰለ ታላቅ ስሜት እንዴት በቃላትና በአገላለጽ በልጽጐ ህይወት ማግኘት እንደሚችል ማሳያ መሆን እንደሚችል ማሰቤ አስደስቶኛል፡፡
ከገብረክርስቶስ ግጥሞች ለመጀመያ ጊዜ በዜማ የተሰራው በተስፋዬ ገብሬ የተቀነቀነው “የፍቅር ሰላምታ” የሚለው ግጥም ነበር፡፡ በዚህ ዘፈን ደግሞ ሚካኤል “ውድ እወድሻለሁ”ን በዜማ ለመስራት ተነሳሽነቱን በመውሰዱ ምስጋናዬና አክብሮቴ ይድረሰው፡፡
ወደ ግጥሟና ዜማዋ ስንመጣ፣ የፍቅር ስሜት ከፍታና ጥልቀት ሌላ ልዩ ፍልስፍናና የከበደ ቋንቋ ሳያስፈልግ በምናውቀው የቀን ተቀን የአድናቆት መሰረትና ቋንቋ እጅግ በልጽጐ የተገለፀበት ነው፡፡ ይህች ግጥም ገ/ክርስቶስ በድምፁ እያነበበ ከተቀረፁት ጥቂት ግጥሞቹ አንዷ ናት፡፡
ከግጥሟ የመጀመሪያ ማሟሻ መስመሮች ስንነሳ
ፍቅሬ አንቺን ስወድሽ
ቀኑ ረዘመብኝ
ሚሊዮን መሰለኝ
እኔ እወድሻለሁ
የሰማይ መሬቱን፣ የባህር ስፋቱን
የርቀቱን ያህል፤
በማለት ውስጡ ያለው ፍቅር ምን ያህል ግዙፍ፣ ከውድድር፣ ከንፅፅርና ከአገላለጽ በላይና ባሻገር እንደሆነ ያሳየናል፡፡ ፍቅሬ አንቺን ስወድሽ/ ቀኑ ረዘመብኝ/ ሚሊዮን መሰለኝ በማለት በዚያ በለመደው የቀን ርዝመት ውስጥ ፍቅሯን ማሰላሰል ሲጀምር ከስሜቱ ግዝፈት የተነሳ ምን ያህል ያ ቀን እንደሚረዝም የሚሊዮን ያህል እንደሚበዛ፣ በመቀጠል ደግሞ ምን ያህል ከንፅፅር ባሻገር እንደሆነ የሰማይን፣ የመሬትና የባህርን ስፋትና ርቀት ያመጣል፡፡
በመቀጠል ገብሬ ወደ ንፅፅሩ ይገባል፡፡ ንፅፅሩ በተለመደው ስነ - ግጥም ውስጥ እንደምናየው የተፈቃሪዋን እንስታዊ ውብ አካላት ከንፈርሽ፣ ወገብሽ፣ አይኖችሽ፣ ፀጉርሽ…እያለ የፍቅርን መሰረት አካላዊ የውበት ማራኪነት ላይ መሰረት በማድረግ አይደለም የሚልፀው፡፡
ፍቅር ከአካላዊ የውበት መስህብ የላቀ እንደመሆኑም ፍቅሩን ፍፁማዊ ውበት ካለው የተፈጥሮ መስህቦች ጋር በማነፃፀር የፍቅሩን ረቂነት ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮንም ምሉዕ ውበት ያስታውሰናል፡፡
እኔ እወድሻለሁ…እንደ ማታ ጀምበር፣ እንደ ጨረቃ ጌጥ፣ እንደ ከርቤ ብርጉድ፣ እንደ እጣን ጢስ እንጨት፣ እንደ ሎሚ ሽታ፣ እንደ አደይ አበባ…እያለ በማነፃፀር፣ ልክ በአድናቆት ማሰላሰሉ መካከል ድንገት እንደሚገረም ሰው ማሰላሰሉን በመደነቅ ገታ ያደርገዋል:-
...አበባ እንዳየ ንብ ጫካ እንደሚያስሰው
ፍቅርሽን በፍቅሬ፣ በፍቅርሽ ልቅመሰው
ማር ወለላዬ ነሽ ከረሜላ ስኳር
አማርኛ አይበቃ
(ወይ ጉድ!)
ባለም ቋንቋ ሁሉ ቢወራ ቢነገር
ይህ የፍቅር መገረሙና መደነቁ ምኞቶቹም ሁላ ጊዜያዊና የወረት እንዳልሆኑ፣ ከዚህም በላይ እንደሚቀጥሉና እንደሚጠነክሩ እየነገረን :-
…እንደ ማታ ጀንበር፣ እንደ ጨረቃ ጌጥ
እንደ ተወርዋሪ ኮከብ የማልጠግብሽ
ስወድሽ …ስወድሽ…ስወድሽ
ስወድሽ…ስወድሽ
የመውደዱ መጨረሻም በሚወዳት ፍቅር ውስጥ ሰጥሞ መቅረት፣ ልክ ወደ አፈር እንደመመለስ እንደሆነ ነግሮ ሃሳቡን ያጠቃልልናል፡፡
…ጣይ ላይ ያለ ቅቤ
ገላዬ ገላሽን ሲነካ የሚያልቀው
አፈር መሬት ትቢያ ውሃ እንደሚበላው
ዓይኖችሽን በዓይኔ ተዳክሜ እያየሁ
ብዙ ሺ ዘመናት
እልፍ አዕላፍ ሌሊት
ስወድሽ …ስወድሽ
ወድ እወድሻለሁ፡፡
ገ/ክርስቶስ ተመሳሳይ በስሜት የተሞሉና ፍንትው ያለ ህይወት ያላቸው የፍቅር ግጥሞችም አሉት፡፡ ከነዚህም “የፍቅር ሰላምታ”፣ “ፍቅር ጥላ ሲጥል”፣ “ያገረሸ ፍቅር” ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በነዚህ ግጥሞቹም በምናውቀው ቋንቋ፣ ሃሳብና ስሜት የፍቅርን ኃያልና ክቡር ማንነት ያመላክተናል፡፡ “ፍቅር ጥላ ሲጥል” የሚለው ግጥሙ በአንድ መስመር ላይ አንድ ቃል ብቻ በመጠቀም ወደ ታች እየወረደ የሚሄድ ግጥም ሲሆን፣ ለሚወዱት የቱንም ያህል ቢደረግ ምን አለበት የሚል መንፈስ አለው፡፡
በገና
ቢቃኙ
ሸክላ
ቢያዘፍኑ
ክራር
ቢጫወቱ
ለሚወዱት
ምነው?
(…)
አበባ
ቢልኩ
ደብዳቤ
ቢልኩ
ምነው
ቢናፍቁ…ይቀጥላል፡፡
ስለ ገብረክርስቶስ ሊቀ ጠበብትነት ለመናገር ይህ ኢምንት ቢሆንም አንባቢያን ይህ ዜማ የተካተተበትን የሚካኤልን ተወዳጅ አልበም ገዝተው እንዲያዳምጡት በመጋበዝ እንዲሁም ሚካኤልን ስለዚህ የሚደነቅ ጥረቱ እያመሰገንኩ ልጨርስ፡፡

Read 9167 times Last modified on Saturday, 06 October 2012 15:33