Saturday, 18 June 2022 20:40

ሰዓሊ ፍሬው ከበደ፤ ስለ ኢትዮጵያ ሥነፈለክና ከምን አንፃር አውደርዕዮቹ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

  "--ብዙ ሰው ወደ ኤግዚብሽኑ የመጣው ሥነ ሥዕል ሊያይ ነው፡፡ እኔ ግን እንደ ሥነልቦና ባለሙያ የተመልካቹን ሁኔታ በሥእሎቼ ውስጥ ለመታዘብ ነው የተገኘሁት፡፡
በሰቀልኳቸው ሥዕሎች የተመልካቹን የአስተሳሰብ ደረጃ ለመመዘን ነበር  የፈለግሁት፡፡
ወደ ኤግዚብሽኑ ለሚመጡ ተመልካቾች እንደተለመደው ስለ ሥዕሎቹ ምንም መግለጫ አልተሰጣቸውም፤ ለማንም ሰው ስለ ሥዕሌ ለማውራት አልሞከርኩም፡፡--"
ሰዓሊ፤ ተመራማሪና የሥነጥበብ አስተማሪው ፍሬው ከበደ፤ ባለፈው ሳምንት በሥነ ጥበብ ፍልስፍና፣ በአዲስ አበባ ሥነ-ሕንፃና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዙሪያ ሃሳቡን አንጸባርቋል፡፡ ዛሬ ደግሞ በኢትዮጵያ ሥነፈለክ እና "ከምን አንጻር" በተሰኙት አውደርዕዮቹ ዙሪያ ሃሳቡንና ተሞክሮውን እንዲህ ያጋራናል፡፡
                 ግሩም ሠይፉ

             ስለ ኢትዮጵያ ሥነፈለክ  አውደርዕይ
ከ3 ወራት በፊት በአሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴስ ያቀረብኩት ኤግዚብሽን "የኢትዮጵያ ሥነፈለክ ወይም አስትሮኖሚ (Astronomy)" በሚል ርእስ የተዘጋጀ ነበር፡፡ በዚህ አውደርዕይ  1.85 ሜትር በ1.50 ሜትር መጠን ያላቸው 21 የሸራ ስራዎች ለእይታ በቅተዋል፡፡ ለአውደርእዩ መነሻ  የሆነኝ ጓደኛዬ ሰዓሊ ሳምሶን ከበደ ነው፡፡ እሱ በሰጠኝ ጥቆማ መሰረት የመሪ ራስ አማን በላይ መፅሐፍ የሆነውን "መጽሐፈ ብሩክ ዣንሸዋ ቀዳማዊ" አነበብኩ፡፡ ከዚያ መፅሐፍ በፊት በኢትዮጵያ ሥነፈለክ ላይ የነበረኝ እውቀት የጠለቀ አልነበረም፡፡ ስለ ሥነፈለክ በቂ እውቀት ያስጨበጠኝን መፅሐፍ ካነበብኩ በኋላ ብዙ ሥዕሎች የምሰራባቸውን ጭብጦች አገኘሁ፡፡ የመሪ ራስ አማን በላይ መፅሐፍ የአውደርእዩን ሥዕሎች ከግሌ ምልከታ አውጥቼ እውቀት ተኮር በሆነ መንገድ እንድሰራ አስችሎኛል፡፡ በሥነፈለኩ ምርምር ላይ በተለምዶ ሰባት ሰማይ ሲባል ምን ያካትታል? ዓለማት ምንድናቸው? ስንት ናቸው? የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ብዙ ለማወቅ ሞክሬአለሁ፡፡
ምዕራባውያን በቀረፁት ቁስ-ተኮር ትምህርት የተወሰኑ ፕላኔቶችና ጋላክሲዎች መኖራቸው ነው የሚወሳው፡፡ በዣን ሸዋ መፅሃፍ ላይ ያነበብኩት ግን 100 ዓለማት መኖራቸውን፤ በሰባቱ ሰማይ ስር ክፍለዓለማት እንዳሉ፣ ለምሳሌ በአንዱ ሰማይ ላይ 21 ዓለማት እንዳሉ....ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሥነፈለክ በሚል  በአሊያንስ ያዘጋጀሁት አውደርዕይ ወደ ማንነቴ የቀረብኩበትና ወደ ራሴ የተመለከትኩበት ነው። በአጠቃላይ እንደ ሥነፈለኩ የኤግዚብሽኑን ስዕሎች ሃሳቦች በዝርዝር ለመግለፅ ፈታኝ ነው። ወደ ማንነታችን ለመመለስ እኛ ማን ነበርን የሚለውን ማወቅ አስፈላጊ ነው፡፡ የነበረንበትን ከየትኛው ማዕዘን፣ ከምን አንጻር እንመልከተው የሚልም መሰረታዊ ጥያቄ ነው፡፡ የሥነፈለክ ባለሙያ ባልሆንም ዓለም በዚህ እውቀት የደረሰበትን ደረጃ ስገመግመው፣ አብዛኛው ቁስ ተኮር ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ የምዕራባውያኑ እውቀት በአብዛኛው በተደጋጋሚ ሙከራ - መሳሳት እና መሳካት (Trial and error) ላይ የተንተራሰ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ሥነፈለክ የሚገርመው የተሟላ ጥንቅቅ ያለ እውቀት በዝርዝር የሰፈረበት ነው፡፡ በሳይንሱ እንወዳደር ባንል እንኳን ለሲኒማ የሚመች የቢሊዮን ብር ሃብትና እውቀት የሚገኝበት ነው፡፡ ፈታኙ ነገር ይሄ አለም ይህን ይመስላል ሲባል በማታውቀው የተመሰለ ከሆነ ለመረዳት ይከብዳል፡፡ ስለዚህ ግብርና ባህርያቸው የተገለጸ ቢሆንም፣ ምስላቸውን ቅርፃቸውን በሥነሥዕል ለማምጣት አልሞከርኩም፡፡ ምክንያቱም እኔ በምከተለው የጥበብ እይታ ብቻ ተመርኩዤ፣ ይህን በመዳፈር ገንዘብ ለመስራት አልፈልግም፡፡ እውነትን ፍለጋ ነው የሰራሁት፡፡
በሥነፈለክ ከቆሎ ተማሪ እንስቶ እስከ ከፍተኛው ተቋም ድረስ አለመስራታችን በጣም ነው ያስገረመኝ፡፡ በመላው ኢትዮጵያ ብዙ ምእራባዊያን ተኮር ዩኒቨርስቲዎችን ብንገነባም፣ ሥነፈለክን የምናጠናበት የምንመረምርበት አንድ አይነት እኛን የሚመስል የትምህርት ስርዓት አለመዘርጋታችን የሚያስቆጭ ነው፡፡ ይህ በሁሉ የእውቀት ደረጃ እያለን እንዴት አልሰራንም የሚለውን ነው አውደርዕዩ እንዲያሳይ ያደረግሁት፡፡ እውቀት ያለው ምን ያህል አርቅቆ እንደሚያስብ ነው መታዘብ የቻልኩት፡፡
"ከምን አንፃር" አውደርዕይ  
በቅርቡ ማለትም ከ15 ቀናት በፊት በፈንዲቃ የባህል ማዕከል ያቀረብኩት አውደርዕይ  በአይነቱ ከ2 ወራት በፊት በአሊያንስ ኢትዮ-ፍራንሴስ ካቀረብኩት  በእጅጉ የተለየ ነው፡፡ "According to what" - "ከምን አንፃር; በሚል ርእስ በተዘጋጀው አውደርዕይ ላይ ያቀረብኳቸው ሥዕሎች የተለያዩ ዘውጎችን የአሳሳል ዘይቤዎች በመከተል የተሰሩ  ናቸው፡፡ አንድ ሠዓሊ በግሉ በሚያቀርበው አውደርዕይ  ላይ  ይህ ዓይነቱ አሰራር የተለመደ አይደለም፡፡ የተለያዩ የስዕል ዘውጎች በቡድን በሚቀርቡ አውደርእዮች  ላይ ነው የተለመደው። በግል (Solo) የሚካሄድ አወደርዕይ ላይ ሦስትና አራት አይነት የአሳሳል ቴክኒክና የመሳያ ሚዲያ  የሚጠቀም አይገኝም፡፡ "ከምን አንፃር" በሚለው አውደርዕይ ላይ ባቀረብኳቸው ስራዎች  ሪያሊስቲክ፤ ሰሚ ፊገራቲቭ፤ የኦሞ ቫሊ ፖርትሬት፤ በሌላም የአሳሳል ዘይቤ በተለያዩ የሸራ መጠኖች እንዲሁም  ጠንካራ ወረቀቶች - ሃርድ ቦርዶች የተሰሩ ለእይታ ቀርበዋል፡፡
በቅርፅ ዙርያ በዚህ አውደርዕይ ያቀረብኳቸው ስራዎች በተለመደው አሰራር አሰቃቀላቸው ተለክቶና ተመጥኖ  የተሰቀሉ አልነበሩም፡፡ በስእል አሰቃቀል ማመጣጠን የሚባለውን ነገር ሆን ብዬ በመተው ነው ስዕሎቹን ከታዳሚው ጋር ያገናኘኋቸው። ከዚህ በፊት በሚቀርብ አውደርእይ አንድ ሥዕል በተሰቀለበትና ሌላው በተሰቀለበት መካከል ያለው ልኬትን በተመለከተ ያልተፃፈ ግን የተለመደ የሚተገበር ህግ ቢኖርም፣ እኔ ግን ይህን አልተከተልኩም፡፡ የተለመደውን የሥዕል አሰቃቀልና አቀማመጥ ሆን ብዬ ትቼዋለሁ። የመሬትና የኮርኒስ ውሃ ልክ አላይመንት ተብሎ የሚሰራውን ሆን ብዬ በማንጋደድ አዘበራርቄዋለሁ፡፡ በአግድምም በቁመትም ሳይሆን በዲያጎናል አሰቃቀል ቀየርኩት፡፡ ከዚህ በፊት ንፁህ ሥነጥበብ ተብሎ የሚታሰበውንና ለሽያጭ ወይም ቱሪስት ተኮር የሚባለውን ስራንም አቀላቅየዋለሁ፡፡ የሌላውን ምስል ቀድቶ በመስራት የተሰቀለ ስእልም አለ፡፡ በቅርጽም በግብርም ይለያያሉ፡፡
በኢሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴስ #የኢትዮጵያ ሥነፈለክ; አውደርዕዬን የተመለከቱ የስዕል ታዳሚዎች፣ በፈንዲቃ የቀረበውን "ከምን አንፃር" ሲመለከቱ ተደናግጠዋል፣ ግራም ተጋብተዋል፡፡ እንደዚህ አልጠበቅንህም ብለው በብስጭት አስተያየት የሰጡኝም አጋጥመውኛል፡፡ ሠዓሊዎች ሂስ አቅራቢዎችና የሥነጥበብ አጋፋሪዎች ሁሉ "ከምን አንፃር" አውደርእይን ከተመለከቱ በኋላ ባቀረብኳቸው ስራዎችና በሁኔታው አለመደሰታቸውን በተለያየ መንገድ ገልፀዋል፡፡ ይህ ሁሉ አስተያየት ግን ለእኔ ትልቅ ደስታ ነው የፈጠረልኝ፡፡ በፈንዲቃ የባህል ማዕከል በሚገኘው የሥዕል ጋለሪ ከተለያየ ክፍለዓለማት የሚመጡ የሙዚቃም ሆነ የሥእል ታዳሚዎች እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ በዚህ አውደርዕይ ላይ ካቀረብኳቸው የሥዕል ስራዎች አንደኛው ሆን ተብሎ ተንጋድዶ እንዲሰቀል ነበር ያደረግኩት፡፡ ከየትኛውም ክፍለዓለም የመጣ  ታዳሚ፤ ይህን ሥእል በተመለከተ ከተዛነፈበት ሊያስተካክል ሲሞክር ነው የታዘብኩት፡፡ ይህን ያደረግኩት ሰው ሥነጥበብን እንዴት ነው የሚያየው? የሥነ ጥበብ ልኬታው ወይም ምዘናው መስፈርት ከምን አንፃር ነው? ለሚለው ጥያቄዬ ምላሽ ለማግኘት ነው፡፡ የተፃፈ ህግ አለ፡፡ ያልተፃፈ ህግ ኖሮስ እንዴት ነው ሰው ሁሉ በአንድ ነገር ሊስማማ የቻለው ወይም ያልቻለው? የሚለውን ሃሳብ ነው በአውደርዕዩ ላይ ሙከራ  ያደረግሁት፡፡
ብዙ ሰው ወደ አውደርዕዩ የመጣው ሥነ ሥዕል ሊያይ ነው፡፡ እኔ ግን እንደ ሥነልቦና ባለሙያ የተመልካቹን ሁኔታ በሥእሎቼ ውስጥ ለመታዘብ ነው የተገኘሁት፡፡ በሰቀልኳቸው ሥዕሎች የተመልካቹን የአስተሳሰብ ደረጃ ነበር ለመመዘን የፈለግሁት፡፡ ወደ ኤግዚብሽኑ ለሚመጡ ተመልካቾች እንደተለመደው ስለ ሥዕሎቹ ምንም መግለጫ አልተሰጣቸውም፤ ለማንም ሰው ስለ ሥዕሌ ለማውራት አልሞከርኩም፡፡ እናንተ ሥዕሎቹን አይታችሁ የተሰማችሁን የምታስቡትን ንገሩኝ ነበር ያልኳቸው፡፡ በተለይ ተንጋድዳ የተሰቀለችው ሥዕልን ከየትኛውም አገር የመጣ ተመልካች ማለት በሚቻል መልኩ ሁሉም ከተዛነፈችበት አሰቃቀል ሊያስተካክል ሲሞክር ነው የታዘብኩት፡፡ በእኔ አመለካከት ያ ተዛንፎ የተሰቀለው ሥዕል ልክ ነው አቀማመጡ። የሥዕሉን ማንነት በራሱ እንዲቆም ለምን አላከበሩትም፡፡ እንዲህ ተስተካክሎ ካልተሰቀለ ልክ አይደለም የሚለውን ድምዳሜ ለሁሉም ማነው የሰጣቸው፡፡ ባልሳሳት ይህን የፈጠረው ሰው ሰራሽ አመለካከት ነው፡፡ ወደ ጫካው ብንሄድ መልክዓ-ምድሩን ብንመለከት፣ ትክክለኛ አቀማመጥ የሚለው ነገር በራሱ በተፈጥሮ የተሰራ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ግን ተንጋዳ የተቀመጠችው ሥዕል ሆን ተብላ ነው ብሎ አንድም ሰው ሊያስብ አልቻለም። በሌላ በኩል ኪች አርት በሚለው ዘውግ የኦሞ ሸለቆ ማህበረሰቦችን ስዬ ያቀረብኩትና ከተመልካቹ የተገኘው ሁኔታ ነው፡፡ ስእሎቹን የሰራሁት ከሶሻል አንትሮፖሎጂ ጋር አያይዤ እንጅ ለመሸጥ አልነበረም፡፡ ዋናው ነጥቡ ማነው ይህን ሥዕል ለአንድ ጋለሪ (category) አድርጎ ሰጥቶ ያስተዋወቀው? እስከ አሁን የአሳሳል ዘይቤ ሆኖ ሊቀር የበቃው ከየት ተነስቶ ነው የሚል ነው፡፡ ሥዕሉ የተሰራበትን እይታ ስዘረዝር በዓለማችን ላይ ከሚገኙ ፍጡራን ራሱን የሚያስውብና የሚያስጌጥ ከሰው በቀር ማንም የለም፣ የሚለውን ፅንሰ ሃሳብ በመያዝ ነው፡፡ በሌሎች ፍጡራን ሥነ ውበት ቢኖራቸው እንኳን ራሳቸውን ለማስዋብ ሳይሆን ለማደን፣ ከአካባቢ ጋር ለመመሳሰል አሊያም ከአደን ለመትረፍ፣ ተቃራኒ ጾታን ለመማረክ፤ አካባቢያቸውን ያስጌጣሉ እንጅ በራስ መዋብ ብሎ ነገር የለባቸውም፡፡ ከሰው ደግሞ የራስን ተፈጥሮ ማስዋብን ከሌላ ባሕል ተምጣ የበረዛቸው ነገር ሳይኖር ቀድሞ የነበራቸውን እንደነበራቸው ይዘው በመቆየት የሚያደርጉት በኦሞ ሸለቆ ያሉ የኢትዮጵያ ህዝቦች ናቸው፡፡ የነሱ መመዘኛ የራሳቸው የሥነ ውበት ዋጋ ብቻ ነው፡፡ ዘመናዊ ነን ብለን ራሳችንን የምንቆጥር ሰዎች በምንለብሰው በምንበላው፣ በአብዛኛው ነገራችን የራሳችን ምርጫ ይመስለናል፤ ግን አይደለም። ፈረንሳይ፣ አሜሪካ፣ ለንደን ወይም  ጃፓን ውስጥ የተቀመጡ ኢንዱስትሪያል ወይም ፋሽን ዲዛይነሮች፤ የፋሽን ኩባንያዎች፤ በሙዚቃው በሲኒማው በሥነጥበቡ ታግዘው በዓለም ህዝብ ደመነፍስ ውስጥ የሰገሰጉት ነው። ተፈጥሯዊውን የሥነጥበብ ዋጋ አሳስተው በሰው ሰራሽ ምዘና የቀየሩበት ነው። በአለባበስ በአኗኗር ዘይቤ በተለያዩ ሁኔታዎች ራሳችንን ብናይ ለሥነ-ውበት የምንሰጠው ዋጋ ምርጫችን የሚሆነው በሌላው ዲዛይን ተጽእኖ ውስጥ ገብተን ነው፡፡ ወደ ኦሞ ሸለቆ ሄደን በዚያ ያሉ ህዝቦች በተፈጥሮ እና በመኖር ያገኙትን ራስን የማስዋብ ባህል በዚህ ቀይሩት ብንል ግን አይሰሙንም፡፡
በአጠቃላይ ከምን አንፃር አውደርዕይ ላይ ከተዛነፈ የሥዕል አሰቃቀል እና ከሥነውበት አንፃር ያራምድኳቸው ጭብጦች፤ ወደ አንዳች መደምደሚያ አድርሰውኛል፡፡ ከፖለቲካው ዓለም እንደሚመጣ የምናስበው የዓለማችን አዲስ የአገዛዝ መዋቅር፣ በሥነጥበብም ስር መስደዱን መገንዘብ ይቻላል፡፡ በሁሉም መስክ በሰው ሰራሽ መንገድ ተቀርፀን ተቀምጠናል ብዬ ነው የማስበው፡፡ አብዛኞቻችን የትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የምርት ውጤት ሆነናል። አብዛኞቻችን የኩባንያዎችን ማስታወቂያ ነው የምንኖረው፡፡ ሥነጥበባዊ ዋጋን ማንም በሌላው ላይ የሚጭነው እውቀት አይደለም። በተመሳሳይም ማህበረሰቡን የሚያሳቅቅ አይደለም፡፡ ማህበረሰቡ ተቀብሎታል በሚል ሙሉ ለሙሉ መዋጥ የለብንም ነው የእኔ አመለካከት፡፡ በደመነፍስ ከእነሱ የሰረፀብንን እውቀት ነው ገንዘብ ከፍለንበት እየኖርን ያለነው። በፈንዲቃ ባህል ማዕከል ከምን አንፃር በሚል ርእስ የቀረበው አውደርዕዬ  ሊያሳይ የሞከረው ነጥብ፤ ሊፈርስ የማይችልን ነገር እንዴት ነው ሊፈርስ ይችላል በሚል እሳቤ ተወጥረን፣ በዚህ በኩል ካልታየ ብለን የምንደመድመው? ወይም ራሳችንን አጥረን የምንቀመጠው የሚል ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ2018 ዓ.ም የዓለም የሥነጥበብ ኢንዱስትሪ ከ61 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ አስገኝቷል፡፡ አብዛኛውን የገበያ ድርሻ የሚወስዱት አሜሪካና አውሮፓ ናቸው፡፡ ኤሽያ 14 በመቶ ድርሻ ቢኖራት ነው፡፡
በተለያዩ የዓለም ኢንዱስትሪዎች የሥነውበት ልኬት፣ ኤስቴቲካል ቫሊው (Aesthetical value) መንጋደድ ወይም ዲስቶርሽን ምክንያት ፖሊሲዎቻችን ተንሻፍፈዋል፣ ማግኘት የሚገባንንም ገቢ እያጣን ነው፡፡ ከሥነጥበብ ጋር በተያያዘ እዚህ አገራችን ላይ የሚሰሩ ጋለሪዎች በግሎባላይዜሽን ግዴታ ውስጥ የገቡ መኖራቸውን አስተውላለሁ፡፡ አንዳንዶቹ ጋለሪዎች #ከምን አንፃር; በሚለው ጭብጥ የሰራኋቸውን አሳይቻቸው፣ በግልጽ ከአንተ ጋር መስራት አንፈልግም ነው ያሉት፡፡ የአሳሳል ዘይቤህን አንፈልገውም ብለው መልሰውልኛል። በአሁኑ ሰአት በዓለም የሥነጥበብ ገበያ፣ የአፍሪካ ሥነ-ስእል በጣም እየተፈለገ ነው ሲባል ይሰማል፡፡ ለአፍሪካ ሥዕል ያለው የአሳሳል ዘውግ ግን ይሄ ብቻ ነው ይባላል። የሁሉም ዲስኩር ይህን ስራ ነው - ነጥቡ፡፡ ማነው ያለው ሲባል የኛን ግምግማ የሚሰራው ቡድን ለንደን ወይም  ፈረንሳይ ነው ያለው ወዘተ ይባላል፡፡ ስለዚህም ለንደን ወይም ፈረንሳይ ያለ ኮሚቴ፣ በአፍሪካ ውስጥ የሚሳለውን ሥነ ሥዕል ከገበያ አንጻር ወይም ከራሱ መስፈርት ብቻ ተንተርሶ እየወሰነ ነው ማለት ነው፡፡ እኔ ለምሰራው ሥነጥበብ ወሳኙ የገዢው ሁኔታ አሊያም  ብሩ የሚመጣበት ቦታ ነው፡፡ ብሩን ለማግኘት ደግሞ የምሰራውን ሥዕል የሽያጭ ኮሚቴ ይወስነዋል፡፡ ኮሚቴው ከወሰነ ደግሞ ኮሚቴው የሚለውን ለመስራት ያስገድዳል፡፡ ባጠቃላይ ለብር ተብሎ ማንነትን ማጣት ነው። ከራስ ምልከታና እይታ ውጭ መሆን ነው። የእኔ ብቻ ሳይሆን የአብዛኛው ሠዓሊ የኑሮ ሂደትና እጣ ፈንታ ነው፡፡ የዓለም ሥነጥበብ በአውሮፓና አሜሪካ ወሳኝነት ተለውጧል። ጋለሪ የሚታየው ይሄ ነው ካሉ ወይም የሚሸጠውን ሥነ ሥእል ሲወስኑ፣ በሌላ ቋንቋ የምትሰራው ይሄ ነው ብሎ መወሰን ነው፡፡ ይህ ማለት ሠዓሊው  ተቀጣሪ (Comissioned)  ባለሙያ፣ ኩባንያዎቹ ደግሞ ሰዓሊ፡፡



Read 1390 times