Saturday, 25 June 2022 18:05

የጎንደር ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የወለጋውን የንፁሃን ጭፍጨፋ በሰላማዊ ሰልፍ አወገዙ

Written by  ናፍቆት ዮሴፍ
Rate this item
(1 Vote)

 “እኛም ያልሞትነው ወለጋ ስላልተገኘን ነው” - ተማሪዎች
                             
        ሰሞኑን በምዕራብ ወለጋ የተለያዩ ቀበሌዎች በአሸባሪው የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች የተፈጸመውን የጅምላ ጭፍጨፋ በማውገዝ ትላንት ረፋድ ላይ የጎንደር ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ፡፡  በሰላማዊ ሰልፉ ላይ የአፄ ቴዎድሮስ፣ የፋሲልና የማራኪ ካምፖሶች ተማሪዎች መሳተፋቸውን የገለጹት የጎንደር ዩኒቨርስቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ወ/ሮ ይዳኙ ማንደፍሮ፤ ሰላማዊ ሰልፉ እጅግ በተረጋጋና ያለችግር የተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
ሃላፊዋ አክለውም “ሰው አይገደል፣ መንግስት ህግ ያስከብርና፣ በዜጎች ላይ የተፈጸመውን ግድያ እናወግዛለን የሚሉ መፈክሮችን በሰላማዊ ሰልፉ አሰምተው ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመልሰዋል ብለዋል።
በሰላማዊ ሰልፉ ከተሳተፉት የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች እንደሰማነው፤ ተማሪዎቹ በሰልፉ ላይ “ሰላም ከሌለ ትምህርት ምን ይሰራል”፣ “እኛ ያልሞትነው ወለጋ ስላልተገኘን ነው”  የሚሉ መፈክሮችን ማሰማታቸውን ገልፀው፣ አሁንም ቢሆን መንግስት ህግ እንዲያስከብር፣ ወለጋ ያሉና በጭንቅ ውስጥ ሆነው የድረሱልን ጥሪ የሚያሰሙትን ዜጎች እንዲታደግ፣ ለተፈናቀሉት አስቸኳይ ድጋፍ እንዲደረግና ከዚህ በኋላ የንፁሃን ግድያ እንዲቆም በሰላማዊ ሰልፉ መጠየቁን ተማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
ሰላማዊ ሰልፉ በሶስቱ ካምፓሶች ተማሪዎች ለአጭር ጊዜ በሰላማዊ ሁኔታ የተካሄደ ሲሆን፣ ተማሪዎቹ ከሰልፉ በኋላ ያለምንም ችግር ወደ መደበኛ ትምህርታቸው መመለሳቸውንም ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል።



Read 11590 times