Saturday, 25 June 2022 18:09

ማማ በርዝ… የሰርቶ ማሳያ መሳሪያ

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

  ማንኛውም ባለሙያ ትምህርቱን ጨርሶ ወደስራ ከመሰማራቱ በፊት እንደየሙያው አይነት ትምህርታዊ ልምምድ ማድረግ የበለጠ በእውቀት እንደሚያንጸው የታወቀ ነው፡፡ የህክምና ባለሙያዎችም ከዚህ ጋር በተያያዘ መንገድ የተለያዩ ትምህርታዊ ልምምዶችን የሚያደርጉባቸው መሳሪያዎች ቢኖሩአቸው ትምህርቱን ከጨረሱ በሁዋላ በቀጥታ የሚሰማሩበትን ሰዎችን የማዳን ስራ በተገቢው ሁኔታ ይፈጽሙታል የሚል እምነት አለ፡፡
ወ/ሮ አለምነሽ ተክለ ብርሀን
ማማ በርዝ የምትባል ሰርቶ ማሳያ አዋላጅ ለሆኑ ሐኪሞች ስልጠና ተዘጋጅታ መመሪያዋም ተዘጋጅቶ ይፋ ሆኖአል፡፡ ወደዚያ ከማለፋችን በፊት ማማ በርዝን ከሰራው ድርጅት ላርደል ከኖር ዌይ የመጡትን ወ/ሮ አለምነሽ ተክለብርሀን እረታን ስለ ቀዶ ሕክምና ያነጋገርናቸውን እውነታ እናስቀድማለን፡፡ ወ/ሮ አለምነሽ የጤና ባለሙያ ሲሆኑ በሚድዋይፍ ከዚያም በህብረተሰብ ጤና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የሰሩ ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት በኖርዌይ በላርደን ውስጥ የሚሰሩ ናቸው፡፡
ማማ በርዝን ወደሀገር ከማስገባት እና ለጥቅም ከማዋል በፊት ሴቶችን በቀዶ ሕክምና ለማዋለድ ልምምድ የሚያደርጉ ሙያተኞች ልምምድ የሚያደርጉበትን መንገድ ስናጠና በተለይም በቅዱስ ፓውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ያገኘነው ምላሽ የከብት ወይንም የበሬ ልብና ምላስ መሆኑን ምላሽ አግኝተናል ያሉት ወ/ሮ አለምነሽ ተክለብርሀን እረታ ናቸው፡፡ ወ/ሮ አለምነሽ እንደሚሉት በአለም አቀፍ ደረጃ 35% የሚሆኑት ሴቶች ከወሊድ ጋር በተያያዘ ችግር ሊገጥማቸው ይችላል፡፡ ምናልባትም የቀዶ ሕክምና ድጋፍ ሊያስፈልጋቸው ይችላል ተብሎ ይገመታል፡፡ ያንን መነሻ በማድረግም የአለም የጤና ድርጅት የአንዲትን ሀገር የተሟላ እርግዝናና የወሊድ አገልግሎት አለ ለማለት ያስችላሉ ተብለው የተቀመጡ ደረጃዎች ወይንም መለኪያዎች አሉት፡፡ ከእነዚህም አንዱ የኦፕራሲዮን ወይንም የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ከ15-25 % በሚሆን ደረጃ ይሰጣል ከተባለ እንደ አንድ ጥሩ የአገል ግሎት ተደራሽነት ይቆጠራል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የሚታየው ሁለት የማይገናኙ ወይንም በተለያዩ ጠርዞች ያሉ ነገሮች ናቸው፡፡ እነርሱም …
Too early--------Too late እጅግ በጣም በፍጥነት ወይንም ደግሞ እያስፈለጋቸው በመዘግየት እና
Too much------- Too small ለማያስፈልጋቸውም ለብዙ ሰዎች ወይንም ደግሞ ለሚያስፈል ጋቸውም ሰዎች እንኩዋን ያለመዳረስ በሚል ይከፈላል፡፡
ከላይ የተጠቀሰው ችግር በመላው አለም በብዙ ሀገራት የሚታይ ችግር ሲሆን ምናልባትም በሀገር ደረጃ የሚታይበት ሁኔታም ይበልጥ ግልጽ ያደርገዋል፡፡ ወ/ሮ አለምነሽ ኢትዮጵያን እንደምሳሌ ሲጠቅሱ በገጠርና በከተማው ያለው ሁኔታ የተለያየ ነው፡፡ እንደሀገር ስሌቱ ሲሰራ ከ80% በላይ ነዋሪው በገጠር የሚገኝ ስለሆነ በዚያ መንገድ ሲታይ የኦፕራሲዮን አገልግሎት የሚ ያገኘው ሰው ብዛት ከ3-5% በላይ አይደለም፡፡ ይህ በጣም ዝቅተኛ ስለሆነ የሚያሳየው የአገልግሎቱን ተደራሽ አለመሆን ነው፡፡ በአንጻሩ በአዲስ አበባ እና ሌሎች ትላ ልቅ ከተሞች ያለውን አገልግሎት ስናይ ከ40-50% የቀዶ ህክምና አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ምናልባትም በቅርብ ጊዜ የተደረገ ጥናት በእጃችን ባይገኝም ቀደም ሲል የነበረ ጥናት እንደሚገልጸው ጥሩ ኑሮ የሚኖሩ ሰዎች የኑሮ ደረጃና የሀብት መገለጫ ወይንም ደግሞ የተማሩ ሴቶች አገልግሎቱን በስፋት ለመጠቀም ቅርብ ሆነው የሚታዩበት ነገር ስላለ በከተሞች አካባቢ ሰፋ ብሎ ይታያል ብለዋል ወ/ሮ አለምነሽ፡፡
የቀዶ ሕክምና አገልግሎትን ከጤና ድርጅቶች አኩዋያ ለሚመለከተውም በግል የጤና ድርጅቶች እና በመንግስት የጤና ተቋማት መካከል ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ አንድ መቶ እናቶች በመንግስት ሆስፒታል ለመውለድ ቢቀርቡ እና የቀዶ ሕክምና የሚደረግላቸው ቁጥር በግል ተቋማቱ ከሚቀርቡ አንድ መቶ እናቶች መካከል በቀዶ የህክምና አገልግሎት የሚወልዱት ይበልጣል፡፡ ወ/ሮ አለምነሽ እንደሚሉት ይህ የብዙ ነገሮች ነጸብራቅ ቢሆንም ነገር ግን አለም አቀፍ ችግር ነው፡፡ ይህ ችግር በጣም በአደጉት ሀገራትም እንደችግር የሚቆጠር ሲሆን በጥቅሉ ሲታይ አገልግሎቱ በሚፈለግበት ወቅት ማግኘት አለመቻልና አገልግሎቱ በህክምና ሳይንስ ሳይረጋገጥና ሳያስፈልግ እንደአስፈላጊ ነገር ቆጥሮ መተግበር በገሀድ የሚ ታይ ነው፡፡ ባላደጉት ሀገራት ደግሞ ቀዶ ሕክምናው እያስፈለጋቸው ባለማግኘት ምክንያት እናቶችም ልጆቻቸውም የሚሞቱበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ ባአለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ስሌት በመጠኑ ስምንመለከት አሉ ወ/ሮ ለምለም……በላቲን አሜሪካ በቀዶ ሕክምና የሚ ወልዱ እናቶች ብዛት ወደ 58% ሲሆን ባላደጉት በተለይም ከሰሀራ በታች ኢትዮጵያን ጨምሮ ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ግን ከ3-6% ብቻ ነው፡፡ ይህ የሰፋ ልዩነት ሲሆን በሁለቱም በኩል ያለው ልዩነት ጤናማ ልዩነት አይደለም ፡፡     
ማማ በርዝ …ከዚህ ጋር የተያያዘች በትምህርት ላይ ላሉ የህክምና ባለሙያዎች ማዋለድን በተመለከተ ሰርቶ ማሳያ መሳሪያ ነች፡፡ ከአሁን ቀደም በዚህ እትም ያነጋገርናቸው እንግዳችን ዶ/ር ራሔል ደምሰው የጽንስና ማህጸን ሕክምና ስፔሻሊስት እና የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐከሞች ማህበር ቦርድ አባል ያነሱትን ሀሳብ በድጋሚ ልናስታውሳችሁ ወደድን፡፡
ማማበርዝ የምትባለው ሰርቶ ማሳያ የተሰራችው ላርደል በሚባል መቀመጫውን በኖርዌይ ያደረገ ድርጅት ነው፡፡ ነሐሴ 24/2013 ዓም በአዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒ ታል ተካሂዶ በነበረ አውደ ጥናት መነሻነት ዶ/ር ራሔል እንደገለጹት እስከአሁን ድረስ ብዙ የቀዶ ሕክ ምና አገልግሎት ስልጠና በኢትዮጵያ ወይንም በአፍሪካ በመሰልጠኛ መሳሪያዎች የታገዘ አይደለም፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ የልምምድ መሳሪያዎቹ ለአቅ ምም ፈታኝ ስለሆኑ ነው፡፡ አንድ ሰው አውሮፕላን ላይ ለመስራት ከመውጣቱ በፊት በልምምድ መሳሪያ ተለማምዶ ጨርሶ መሆን እንዳለበት ሁሉ በሕክምናም ወደ ታካሚዎ ቻችን ከመሄዳችን በፊት መጀመሪያ ስልጠናዎች ይደረጋሉ፡፡ ሰልጣኙ በስልጠና መሳሪያው ላይ እጁን ፈትቶ በደንብ ተለማምዶና በከፍተኛ ሐኪም እየተረዳ አተገባበሩን በደንብ ሲያ ውቅ ከዚያ በሁዋላ እራሱን ችሎ ቀዶ ሕክምና እንዲያደርግ ይፈቀዳል። ስለዚህ ማንኛው ንም የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ለመስጠት ልምምድ የሚያደርግ ሐኪም በመሳሪያዎች ታግዞ ይህንን ቅድመ ዝግጅት ማሟላት ይጠበቅበታል፡፡
በአለማችን ላይ እያንዳንዱን የቀዶ ሕክምና አተገባበሮችን የሚያስተምሩ በጣም የሚገርሙ ዘመናዊ እና ኮምፒተራይዝድ የሆኑ ብዙ መሳሪያዎች አሉ፡፡ እነዚህ መሳሪያዎች በዋጋ አንጻ ርም ውድ ስለ ሆኑ፤ በአገልግሎት ዘመናቸውም ብልሽት ሊገጥማቸው የሚችል በመሆኑ እና በቀላሉ የመለዋወጫ እቃዎችን ማግኘት አስቸ ጋሪ ስለሚሆን በተለይም በአፍሪካ ውስጥ እን ዲኖሩ ለማድ ረግ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ከምንም በላይ የአገልግሎት ዘመናቸውም የሚያልፍ ሊሆኑ ስለሚችሉ በቀላሉ እየለዋወጡ አዲስ በተሰሩ መሳሪያዎች እየተኩ መጠቀም አስቸ ጋሪ ስለሚሆን እነርሱን ወደሀገር ለማስገባት እስከአሁን ሙከራ አልተደረገም ፡፡  ከዚህ አንጻር ብዙ ጊዜ የሚመከረው በአካባቢ በሚገኙ ወይንም በቀላሉ መተካት በሚችሉ፤በቀላል ዘዴ በሚሰሩ እቃዎች መለማመድ ነው፡፡
ማማ በርዝን በልምምድ ለማዋል የሚያስችል መመሪያ Guide ማዘጋጀት ግድ ስለነበር ይህ መመሪያ ላርደል የተሰኘው አምራች ድርጅት ከኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞ ማህበር ጋር እንዲሁም ከኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ተሰርቶ በማለቁ እ.ኤ.አ May 6/2014 ከተለያዩ አካባቢዎች ለተውጣጡ የህክምና ባለሙያዎች ቀርቦአል፡፡
ማማ በርዝ ወደሀገር ትግባ እንጂ ለስልጠና እንድትበቃ መመሪያው የወጣው ገና በቅርቡ ነው፡፡ ነገር ግን እናቶች ለዚህ ሁሉ ማለትም አሁን እስከደረስንባቸው አመታት በተቻለ መጠን የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ሲያስፈልግ እርዳታው ሲሰጥ ቆይቶአል፡፡ እናም በመሰልጠን ሂደት ሁኔታው ምን ይመስል ነበር ስንል ዶ/ር ብሩክ ጋሻው በዛ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትን ጠይቀናቸዋል፡፡
በቀዶ ሕክምና አገልግሎት ልጅን ማዋለድ ትንሽ ከበድ ያለ አካሄድ አለው፡፡ ከውጫዊ የሰ ውነት አካል በቀጥታ ተቀዶ ልጅን ማግኘት አይቻልም፡፡ በደረጃ ከላይኛው ወደታችኛው… አሁንም ወደታችኛው…..አሁንም ወደታችኛው አካል እየሰነጠቁ በጥበብ በመጉዋዝ ልጁ ካለበት ማህጸን ይደረሳል፡፡ ምንጊዜም ወደውስጥ በተመጣ ቁጥር አደጋው ከፍ ያለ ስለ ሚሆን ልምድ ይፈልጋል፡፡ በከፍተኛ ሐኪሞች ቁጥጥርና ክትትል እንጂ ተለማማጁ በቀጥታ የሚሰራው አይደለም። ስለዚህም አንድ የህክምና ተማሪ በቀጥታ ወደ ሰው ሰውነት ሄዶ የቀዶ ሕክምናውን ልምምድ ማድረግ ስለማይችል አስቀድሞ የተለያዩ ሞዴሎችን መለማ መድ ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ማማ በርዝ የተሰኘው ሰርቶ ማሳያ ለአዋላጅ ሐኪሞች ጥሩ ሰርቶ ማሳያ ነው የሚል እምነት አለኝ ብለዋል ዶ/ር ብሩክ ጋሻው በዛ፡፡

Read 10932 times