Sunday, 26 June 2022 10:02

“መሪ እና ንፉግ…”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 የኛ ሀገር መንገድ አይመች ለፈረስ
ደጋግ ሰዎች መጡ እኛ ስንመለስ።
(እንዲል ባለቅኔ)
“በስልክ አነጋግሪኝ በቀጭኑ ሽቦ፣
ትዝታ እንዲመጣ ደርቦ ደራርቦ”… አይነት ነገራችን በራሱ ትዝታ ሆኖ ቀረም አይደል?... እውነቴን እኮ ነው። ይኸውና አሁን ዕለት አንዷ ቆንጅዬ በሬዲዮ መስመር ላይ ገብታ ከወዳጇ ጋር መስማማት እንዳልቻለችና መለያየት ስለምትፈልግ ከእንግዲህ በኋላ እንዳይደውልልኝ ስትል በአደባባይ ተናግራ ስታበቃ፣ የነጻነት መለሰን ዘፈን ለቀቀችበት። የሚያስቀው ዘፈኑ ምንድነው መሰላችሁ? “አትደውልልኝ!” ወይ ጉድ ሲጀምር የሚደውለው እኮ ኔትዎርኩ ሲኖር ነው። ቂ ቂ ቂ! (ማነው እንኳን ወዳጃችን ገና ድሮ የኔትወርካችንን ነገር ታዝቦ ይህ ነገር “ኔትዎርክ” ነው ወይስ “ኖት ዎርክ” ነው? ብሎ የጠየቀው?)… አሁንማ አምስተኛው ትውልድ ላይ ደርሷል። ሳፋሪኮም ያሯሩጥልን እንጂ፤ አዝማሪው እንዳለው፤ ደጋግ ሰዎች መጡ እኛ ስንመለስ የሚያስብለን ብዙ ነገር አለ።
ሰሞኑን ፈገግ ያስባለችኝን ተረት ልንገራችሁማ፤ “መሪና ንፉግ እያደር ይቆጨዋል” ቂ-ቂ-ቂ!...ምነው ታዲያ እኛን የመሩንና እኛን የነፈጉን ሰዎች ሲቆጡ እንጂ ሲቆጩ አላየን? በነገራችን ላይ የአፍሪካ መሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ ሲካሄድ አቤት የመንገዱ ውጥረት፤ ያው እነሱ ሲሰበሰቡ እኛ መበተኑን ለምደነዋል። እኔ የምለው ቀኑን ሙሉ በተለይም የሜክሲኮና ብሄራዊን መንገድ እያሳጠሩ እንዲያ ሲመላለሱ በምን ሰዓት ተሰብስው ነው ውሳኔ የሚያስተላልፉት?... አንድ ወዳጄ ምን ብሎ ሲቦጭቃቸው ሰማሁ መሰላችሁ? “እነዚህ ሰዎች ለሻይም ለሽንትም ከግቢ ውጪ ናቸው እንዴ?” ብሎላችኋል። እኔ ግን የለሁበትም።… ወዳጄ እዚህ “መሪና ንፉግ እያደር ይቆጨዋል” ይሉት ተረት የሚሰራም አይመስለኝም።
የመሪዎቻችን መቆጨት እንጃ እንጂ የንፉጎቹስ ታሪክ ብዙ ተብሏል። እዚህች´ጋ አንዲት ታሪክ ቀመስ ተረት እንካችሁ። በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን የግምጃ ቤት ኃላፊ እንደሆኑ የሚነገርላቸው አባሃና፣ በጣም ስስታም እንደሆኑ ይወራባቸዋል። ታዲያ አንድ ቀን የአፄው ባለቤት እቴጌ መነን በገነት ውስጥ ሲኖሩ፣  (በሰማይ ቤት መሆኑ ነው) የግምጃ ቤት ሃላፊ የነበሩት አባ ሃና ደግሞ በሲኦል ውስጥ ወድቀው ነበር።
ይህን የሰሙት አባሃና እቴጌን ወደ ገነት ሄደው እጅ ለመንሳት ጥያቄ ያቀርቡና ይፈቅድላቸዋል።  ከገነት እንደደረሱ እቴጌይቱን ሲያዩዋቸው በደስታ ዘለው ይጠመጠሙባቸዋል። የሆድ-የሆዳቸውን ሲጨዋወቱ ቆይተው ወደመጡበት ሲኦል እንዲመለሱ ቢጠሩ “እምቢ አሻፈረኝ” ብለው ድርቅ ይላሉ። ድርጊታቸው በገነት ውስጥ ግርግር ፈጥሮ ቢለመኑ አሻፈረኝ ብለው፤ ለያዥ ለገራዥ በማስቸገራቸው ጉያቸው ወደ ገነት አስተዳዳሪው ዘንድ ደረሰ። ገነት አስተዳዳሪውም፤ “ችግር የለም ይህ ሰው ስስታም እንደሆነ አውቃሁና መላ አይጠፋለትም” ብሎ ጥቂት አሰብ አደረገ። ከዚያ ቅዱስ ጴጥሮስ ወደ ገነት መግቢያ በር ሄዶ ድምጹን ከፍ በማድረግ፣ “ይሄ ገንዘብ የማነው?” ብሎ ጮኸ። አባ ሃናም፣ “የኔ ነው!” ብለው ሮጠው ወጡ። በዚህም በጥቂት ሳንቲም ምክንያት ገነትን አጡ ተብሎ ይተረታል፡፡ “አሳ ጎርጓሪ ዘንዶ ያወጣል፣ የሰው ፈላጊ የራሱን ያጣል” ይህ ተረት ትዝ አላችሁ?...
ለሰው ሁሉ የሚወደው ነገር መጥፊያውም መልሚያውም ነው። አንዳንዶች ላባቸውን ጠብ አድርገው፤ ሀብት ንብረት አፍርተው፣ “ቋጥሬ” ያኖርኩት ቅርስ ነው ይላሉ። ሌሎች ደግሞ በንፍገት ባከማቹት ሀብት ምክንያት ጠላት አፍርተው ብቻቸውን በልተው፣ ወደማይቀርበት የሞት ድግስ በእራፊ ጨርቅ ተጠቅልለው ሲሸኙ ታዝበናል። አንድዬ ብቻ ሁሉ ነገር ካለፈና ከረፈደ በኋላ በአደባባይ ከሚጸጸት “መሪና ንፉግ” ይሰውረን አቦ።
“ጎበዝ ምንጊዜም “ሥልጣንና ሀብት ሲጨምር ደም ግፊትና ስኳርም  እንዲሁ ይጨምራል።” ያለውን የወዳጄን ምክር ማስታወሱ የሚናቅ አይደለም። እኛ አለን የምንለው ሀብትና ስልጣን ሁሉ ለሌለው ሊያስቀና ይችል ይሆናል እንጂ ጣዕሙስ ሬት እና ምሬት የበዛበት ሊሆን እንደሚችል መጠርጠር ደግ ነው። አራዶች “ጠርጥር ከገንፎም ውስጥ አይጠፋም ስንጥር” እንዲሉ። የአንዳንድ ሰው ቁጭትና ቅብጠት ደግሞ “የኔን ወጥ ብትቀምሺው ፣ ያንቺን በደፋሽው” አይነት ነገር ይስተዋልበታልና ልብ ይስጠን። በየመስኩ ከተደነቀሩብን ውሎ አድሮ ከሚቆጩብን “መሪዎችና ንፉጎች” ይጠብቀን። ይኸውና በኑሮ ይሁን በዕድሜ አይታወቅም በሽበት ብዛት ገብስማ ዶሮ መስለን ከአዝማሪ ቤት ቅኔ መዝረፍ ጀምረናል።
እስቲ ራሴን እዩት፣ ሸብቼ እንደሆን
እንዲህ አያድርግም ፍቅር ብቻውን።
(ከአሸናፊ ደምሴ “የራስ ብርሃን እና ሌሎች ወገኛ ታሪኮች” የተቀነበበ)

Read 1995 times