Sunday, 26 June 2022 10:06

"ሐሰተኛው"ንና "የተጠላው እንዳልተጠላ"ን እንደ አንድ መጽሐፍ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 ("…አንተ የተወለድከው ለእኔ፣ እኔ የመጣሁት ለአንተ ነው" ኖላዊ)

                ደራሲውና ድርሰቱ
በቅድሚያ፤ ልብወለዱ ከምናብ ዓለም ቅምምስ በላቀ፣ ደራሲው ለባዘነባቸው ቀናት ያደሉ የትረካ ቤቶች እንዳሉት ሊሰማኝ የቻለባቸውን ምክንያቶች ላስቀምጥ፡፡ ምክንያቱም ይህን ተከትለው የሚመጡ ደራሲውን ከድርሰት ሥራው ለይቶ ማየት የሚገባባቸውን አግባቦች [Relevance] ችላ በማለት አለመሆኑን ማስረገጥ ስለሚያስፈልግ ነው፡፡
አንደኛው በመውቀሻና በመጥቀሻ እቃው ነው፡፡ ይሄ ትልቁና ዋነኛው መግፍኤ ነው፡፡ በመውቀሻ፡- ገፀ ባሕርያቱ የሚቆጩባቸውና የሚሰነዝሯቸው የተግሳፅ ጦሮች መጥተው የሚያርፉበት ክልልና ልብ ላይ የሚፈጥሩት እውከት፣ ከባሕርያቱ በላቀ በቁመተ ሥጋ ወዳለው ፊት የሚያስመልሱ መሆናቸው ነው፡፡ ከታች በዝርዝር የምናያቸው በድርሰቱ ውስጥ የተነሱ እረፍት የማይሰጡ ሀሳቦችና ክሶች እኛን (ሥጋ ድንበር የሆነንን) የሚበረብሩበት ቅርበታቸው ማሳያ ነው፡፡ ሌላው ልብወለዱ Euphemistical መቅለስለስ የማይታይባቸው ቆንጣጭ ቃላትን መያዙና፣ በዚህም የመጣ ለመጀመሪያ ንባብ የሚሰጠው ምላሽ ዘራፍ! ን ማስቀደሙ ነው፡፡ ይህ የሆነበት ምክንያት፣ ድርሰቶቹን ያኮሳተረ ተናቻፊ የጽርፈት [Blasphemy] ቃላት መያዙ ሊሆን ይችላል። በዚህም የተነሳ አንባቢን ከድርሰቱ በተሻገረ፣ ለደራሲው ሀሳቦች ፊቱን ያስመልሰዋል፡፡
በመጥቀሻ፡- ልብወለዱን በበጎ ጎን (የድርሰቱ ጠባይ አድርጌ ስለምቀበለው) የምቀበላቸው የተለያዩ መፅሐፍትና ፈላስፎችን ሥራና ሕይወት ማጣቀሱ ላይ ነው፡፡ የገፀ ባሕርያቱ የዕጣ ፍኖት የተዘረጋበት ዠላጣ የጠቢባንን ሕይወትና ሥራ ለምስክርና ለንፅፅር ለሚጠራበት የተመቸ በመሆኑ፡፡ ይህም የቆሙለትንና የቆሙበትን የሕይወት ሰገነት በማየት ይመለሳል፡፡ ይህ የማመሳከርና የማነፃፀር መንገድ የደራሲውን የንባብ ክህሎት ከነግርማው ይዞት ይመጣል፡፡ የተጠቀሱ፣ የተጠየቁና የተፍታቱ የሌሎች ሰዎች ሀሳቦችንና ደራሲው በሚኖርበት ዘመን ላይ ሊነሱ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ ጉዳዮችን በማዛመድ የባሕርያትን ጉዞ በወዳጅነት ለማገዝ የተገባበት መሆኑን መጠርጠር ያስችላል፡፡ አንዳንዴም በደራሲው የሕይወት አቅድ ባህሪው እንዲገባ እስከመገደድ፣ የሚያደርስ ጣልቃ ገብነት ሊፈጠር ይችላል፡፡
ሁለተኛው- የገፀ ባሕርያቱ የኑሮ፣ የፍልስፍናና የሕይወት መሽከርከሪያ ኦርቢት የደራሲውን አፀድ የሚታከክ መምሰሉ ነው። ይህም ደራሲው በመጻሕፍቱና በሌሎች ጉዳዮች ላይ የሰጠውን ቃለ መጠይቅ በማድመጥ ይደረስበታል፡፡
ሦስተኛው፤-  Meta-fictional Approach -  ይሄ በሌሎች ድርሰቶችም ላይ የሚዘወተር ብሒል ነው፡፡ ደራሲው ራሱን ከገፀ ባሕሪያቱ ተርታ በማቆም የኃልዮ ልዩነት ለማጥበብ የሚጥርበት ቅጥ ነው፡፡ ይህንንም በልብወለዱ ውስጥ ‹‹ደራሲ አለማየሁ ሞተ›› በሚል አዋጅ ሲያቀራርብ እናያለን፡፡
በእኚህ ሁለት ስራዎቹ ውስጥ ደራሲው እንደ ግሪኩ ባለቅኔ ፒንድራ Creature for a day! What is man; what is he not; እኛ የአርብ ፍጡራን፣ ማን ነን፣ ምንድን ነን፣ ማን ነኝ፣ የት ነኝ፣ እንዴት ነኝ፣ እንዴት ነን፣ ለምን እንዲህ ሆንን፣ ማንስ እንዲህ አደረገን፣ ማን ይከሰሳል በዚህ፣ ሊልባቸው ጣልቃ መግባቱን ከላይ በጠቀስኳቸው ምስክሮቼ ስም እጠረጥራለሁ፡፡
ጠንካራ ትንቢት ያመጣው መሲህ…
ሐሰተኛው ለየተጠላው… መንገድ ጠራጊ ሆኖ የመጣ ነው፡፡ ትንቢት እንዲፈፀምባቸው ሲባል ተወልደው ፍዝ ንቅናቄ ሰብቀው እንደሚያልፉ የመፅሐፍ ሰዎች ሳይሆን፤ ከሕልማቸው ለእውናውያኑ መመሪያ በሚቀረፅላቸው ትንቢቶች ሞገስ እንጂ። በዚህም የመጣ የተጠላውን… በርብሮ እውስጡ ያለን ሀቅ ለማወቅ ሲታሰብ፣ በቅድሚያ ሐሰተኛውን ማንበብ ግድ እንዲል ሆነው የተጣመሩ ናቸው፡፡ ‹‹ሐሰተኛው ተነጠፈ፤ የተጠላው… ሄደበት›› ብል ያብራራኛል፡፡ ሐሰተኛው ባይመጣ የተጠላው… ላይመጣ ሳይሆን፣ የተጠላው እንዲመጣ ሐሰተኛው መምጣቱ ላይ በማተኮር ጭምር፡፡ ልክ፣ ኢሳይያስ፣ ዳዊት… ባይተነብዩለት፣ ዮሐንስ ሀሩር ለሀሩር ባይሰብክለት ክርስቶስ መምጣቱ ላይቀር፤ ተሰብኮና ተተንብዮ ሲመጣ ስለሚገኘው ጥቅማ ጥቅም ሲባል አካሄዱ ላይ ብቻ ማተኮር ቢቻል እንደማለት፡፡
… ሕዝቡ ስለ መንፈሳዊ እግረ ሙቅ መበጠስ በየቤቱ አለቀሰ፡፡ (ገፅ 78፣ የተጠላው…)
እኚህን ሁለት መጻሕፍት ሳነብ እንደ አረንገማ ልቤን ይዞ አላራምድ ያለኝን ሀሳብ የማሾልክበት ቀዳዳ  ሰሎሞን እንዲህ ይምሳል፣ … ጨክነው እውነቱን ለነገሩኝ… ይቅርታ! (ልጅነት፣ ሰሎሞን ዴሬሳ)
እርግጥ እውነቱ የሚነገረን ነው? ከሆንነውና ካደረግነው የተሰወረ አለ? እውነቱን ለመገንዘብ የሚሰንፍ ንቁነት ይጎድለናል? ማንስ ነው እውነቱን ሊነግረን የተገባው? በቅድሚያ እነኚህን ጥያቄዎች መመለሱ ተገቢ ይመስለኛል። በመፅሐፍ ቅዱስም ሆነ በሌሎች ሰው ራሱን ሊያስተዳድርባቸው በተሰጡትና በመረጣቸው ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ መልዕክተኞች ሲላኩ ማየት የተለመደ ነው። ዮናስ ሕዝቡ ከሀጢያት እንዲመለስ ወደ ተርሴስ መላኩ፣ ሌሎችም፣ እንደ እንባቆም፣ ኤርሚያስ፣ ኢሳዪያስ ያሉ ወደተለያዩ ሕዝቦች መልዕክት ይዘው እንደሄዱ እናያለን። ይህም የሚያሳየው፣ አንድም፣ ሰው አነባብሮት የተቀመጠው እግሩን መደንዘዝ፣ ቆሞ እስኪያፍታታ አይለየውምና ነው። ሌላው፣ ራስን ከመገንዘብ አልፈው የማህበረሰብን ልብ የሚበረብሩበት ጥበብ በተሰጣቸው ጥቂቶች በመመራት። ይሄኛው ብዙውን ጊዜ በግለሰቦች እንጂ እንደ ማህበረሰብ ሲከወን አይታይም፡፡ እንደ ማህበረሰብ ያለበትን የሞራልና የመንፈስ መላሸቅ ችግር ቢረዳ እንኳ፣ መተግበሪያው ላይ እክል የሚያመጣበት አንድነት ማጣት ይጠልፈዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የነቁት በሚያሳድሩበት እምነት እየተመራ ራሱን ያድሳል፡፡ አንድም፣ የግለሰብ ተጠያቂነቱን የሚከሉለት ማህበራዊ አመክንዮዎች ይዞ የተሻገራቸው መሪርና ፀያፍ ምዕታትን ሊደግም እጅ ለእጅ በተያያዘበት፣ ከጌታው መልዕክት ይመጣለታል፡፡ የመልዕክተኛውን የማንቂያ ደወል ተከትሎ የሚመጣ በትር አለ፡፡ ሰሚ ሲድን፣ ቸልተኛ የሚረግፍበት። ‹‹የአምናው ሞኝ፣ ዘንድሮም ደገመኝ›› ተረት ተረት ሆኖ እንዳይቀር ይሆናል፡፡ በዚህ ስርዓት ውስጥ ያለፉ ሰዎች ስለመኖራቸው ታሪክም ቅዱስ መፅሐፍም ምስክር አለው። እንዲህ ባለ፣ የንቅናቄ ግጥምና ዜማ በሚወርድበት ልብወለድ ውስጥ ስናልፍ ይህ የመጀመሪያችን ይመስለኛል፡፡ ይህም የሰላም ቅጥራችንን የሚረብሽ ጩኸት እንጂ፣ ለአመክንዮ ቀጠሮ የሚያሽቀረቅር ጥንቁቅነት አያሲዘንም፡፡ ጥያቄው የመልሶቻችንን ጉባዔ ለጥርጣሬ ስለሚያጋልጥ ያስቆጣናል፡፡ ይህን መሰል ባሕሪያችንን ተከታትሎ የመዘገበ፣ ጉስታቭ ለ ቦ የተባለ የማህበራዊ ስነልቦና ባለሙያ እንዲህ ብሎናል፡-
... The masses have never thirsted after the truth. Whoever can supply them with illusions  is easily their master, Whoever attempts to destroy their illusions is always their victim.
በዚህ አካሄድ፣ እኚህን ሁለት መጻሕፍት በአጥቂ ዐይኖች እስካላየንና ለቁጣችን መውጫ እስካልሰጠነው ድረስ፣ የእውር ዳንስ በሚቋቋምበት ጥበብ፣ የተሰነዘሩ መቃኛዎች አናጣበትም ባይ ነኝ፡፡ ደራሲው ወንበር ዘርግቶ የክህደትን ወንጌል የሚሰብክ ከሚያስመስለው ቀኖና ባሻገር፣ በለሆሳስ የምትፈስ የፍቅሩ እንባ ታተኩሳለችና፣ አብረን ባናለቅስ የሚያረጥበን አናጣምና፣ ልብ ብንል…፡፡ ይህ ሳይሆንልን ቢቀር፣ በካሊጉላ ምክር ብንሆን፣ … all that’s needed is to be logical right through, at all costs.
ታለ (አልአዛር)
በቅድሚያ፣ እዚህ የማመጣው ታለ፣ በቀደሙት ሁለት መጻሕፍት ላይ የምናውቀውን ታለ አለመሆኑን ልብ ላስብል እወዳለሁ፡፡ ስንት ታለ አለ? የበፍቅር ሥሙ ታለ ከሐሰተኛው ታለ ምን ለየው?
ታለ በተገኘበት (በዋለበት)፣ በደረሰበት የእድሜና የእውቀት ደረጃ፣ ፅዋ በተጣጣቸው ማህበራቱ ተጽዕኖ (ጓደኞቹ) ራሱን የሚፈለቅጥበትና የሚክብበትን ክፍተት ሕይወት እንደምትተውለት ምስክሩ ሰው ነው። ሰው ሥጋዊ፣ ሰው መንፈሳዊ፡፡ ይሄን፤ ሰው በጊዜና በቦታ ራሱን የሚያሳልፍበትን ለዋጭ እጣ፣ ታለ እንዲቋደስ መፍቀድ፣ የደራሲው መብት ቢሆንም፡፡ ይሄን የመስጠትና የመንሳት ፈቃዱን ተጠቅሞ፣ በሦስት ራሳቸውን ችለው መቆም በሚችሉ የሕይወት ምዕራፋት ውስጥ፣ ደራሲው ታለን ያደረገውን ማየት በቂ ነው። ደራሲው በእኚህ ሦስት ድርሰቶች ውስጥ፣ ታለንና ትናንሽ የሕይወት ማለፊያ በሮቹን የለወጠበትን አቅም፣ ማንነት የመለወጥ አቅም መያዝ መቻላቸውን በምሳሌ ላሳይ፣
ስለ ትናንሽ ለውጦች ጉልበት በምሳሌ፡- እግዚአብሄር አዳምን ሊፈጥርበት የመረጠው ቦታ ላይ ትንሽ ማሻሻያ ቢያደርግ ብለን እናስብ … በኤደን ፈንታ ጭው ያለ በረሀ መሀል ቶርኒ ዴቭል፣ ጊንጥ፣ አንበጣና ምናምኑን እያስተዳደረ (ቀስ እያለ ወደ ጫካው እንዲመጣ) ቢያስቀምጠው … ምናልባት መፈተኛውም ከአፕል ወደ ቴምርና በድንጋይ ወደተከበበች የምንጭ ውኃ ሊቀየር ይችል አልነበር? … በመፈተኛው የሚደርስበት ቅጣት ባይቀየር፣ ቅጣቱን ተከትሎ ለዘሩ የሚቀረው ትርክት መልኩን አይለውጥም? … አይደል ፈተናውና ቅጣቱ፣ አሳቹ በጠላትነት ዛሬ ድረስ አልመጣም፤ … ሰው በትርክቶቹ የሚይዘው ቁመና አለው። … ባሕሉ፣ ስርዓቱና ልማዱ ትርክቱን አልተከተለም? … ባሕሉስ ሰውን ያስከተለ (ያስቀደመ) አይደለም? … ሰውስ የሚከተለውን አልመሰለም? … እና መፈተኛውን መለወጥ ሰውን አይለውጠውም? …
ስለዚህ እኔ ላወራበት የመረጥኩት እንዲህ ባሉና ትናንሽ በሚመስሉ መፈተኛዎች የተለወጠውን ታለ ነው፡፡ አይደለምና፣ ሕይወት በሰዶ ማሳደድ የሸለመችው፣ በሥጋውና በነፍሱ እርምጃ ልክ ለውጥ የሚከተለው የታለ ዓይነት ባሕሪ ይቅርና፣ በልጅነት ፊቱ ለእርቅ የሚላክ ለውጥ የዘነጋችው ሥግው ሳይቀር በትናንሽ ለውጦች ባሕሪውንና ማንነቱን ይቀይራል። ብዙም ባይሆን ለዚህ የቀረበ ጨዋታ ሰሎሞንም ብሏል፤ እሱን ሰምተን እንምጣ፣
… ሰው እንደአጋጣሚ ጠበቃ፣ ጋዜጠኛ… እንደሚሆን፡፡ ግን ጠበቃም መደቡ ላይ ሲጋደም ጥብቅናውን ረስቶ በቅድሚያ ወንድም፣ አባት፣ ባል እንደሚሆን… (ልጅነት፣ ሰሎሞን ዴሬሳ)
ታለ ዘብሔረ ቅንብቢት፣ ወዐይነምሣ፣ ወዐይንአንባ፣ ወ፣…

አዕማዳት
ረድ ሠርዌ               ታለ             ኖላዊ
(የፍፁም እውነት መምህር) (ሀሳዊ መሲህ)
እኚህ ሁለት ምሰሶዎች ታለ ግራና ቀኝ ጠብቆ የታሰረባቸው የመንፈስ ወኪሎች ናቸው። የሚያቀዣብር ተምኔት በተሞሉ፣ የሲዖል ደጅ ትንታግና በኢየሩሳሌም አኮቴት መካከል ልቡን ልብ የተነሳ ሳምሶን። ሕይወት በግዞት የገባባት ወህኒ ያህል ጥብ ሆናው፣ የሚጨብጥና የሚንደውን ምሰሶ አስያዥ አጥቶ ይሰቃል፡፡
… ኑሮዬ በእርኩሳንና ቅዱሳን መዘላበድ ከተጨባጭነት አልወጣም
(ታለ፣ ሐሰተኛው ገፅ 158)
… ስለምን የእኔ ሕይወት ካለፈ ዘመንና ታሪካቸው ከተጠናቀቀ ሰዎች ጋር ተገናኘ (ታለ፣ ሐሰተኛው)
ታለ በቅዱሳትና እርኩሳት መናፍስት መሀል በተደረገ ውጊያ የጦር ሰፈር ሆኖ የዋለ፤ ያደረ። ንቃቱና (ስለ መመረጡ) እጣው ተቧድነው በሁለት ወገን የሚያስደቀድቁት ደረቅ ሳር። ታለ፣ እጣው ያመጣበትን የመተምተምና ወዲህ ወዲ የመበተን ታሪኩን በሽሽትና በመነጠል (Alienation) ሲያባብል ይኖራል፡፡ … ፈጣሪ አሮን ያሉ መጥፎ ፍቃዱን ይክዳሉ። ክሱትነታቸውን ተቀበሉ ምንምነት ላይ ይወድቃሉ፡፡ አማካኝ ላይ መገኘት ከንቱነት ለሚያምን የመወላወል እረፍት ማጣትን ያስከትላል፡፡ … (ገጽ 9፣ ሐሰተኛው)  እንዲህ እንደ ታለ ባለ ነገር ግን መልኩን በለወጠ መለኮታዊና ሥጋዊ ጦርነት መሀል ሕይወቱ የተጎተተች እንዲህ ሲል ለታለ ይመጣል፤
… The dual substance of Christ- the yearning so human, so superhuman, of man to attain God… Has always been a deep inscrutable mystery to me. My principle anguish and source of all my joys and sorrow from my youth onward has been the incessant, merciless battle between the spirit and the flash… and my soul is the Arena where these two Armies have clashed and met.
[The last temptation of Christ, Nikos Kazantazkis]
መፅሐፉ፣ ይህን በልዕለ ኃያላን የክብርና የወሰን ማካለል ግጭት መካከል ያነቃችው፣ በችግር ያሸበረቀች ሕይወቱን ሊያስታምም በዐቱን መሽጎ ከሚኖርበት ይጀምራል፡፡ ይህ በሐሰተኛው ውስጥ የምናገኘው ታለ፣ የሕይወትን ፋይዳ በትርጉም ለመድረስ ሲባክን ራሱን የጣለበት ባዶና፣ ከመከራ ጋር መርዝ የሚጠጣበት ሰቆቃ፣ በExistential vaccum እልፍኝ ያሳድረዋል። ታለ ከዓለም የድርሻውን ወስዶ አፈግፍጓል። በአቱን። ታለ፣ በዚህ አይለኬና አይሰፈሬ በሆነ በፈጣሪው ችላ የተባለ ዝርክርክ መሃል  ይባክናል፡፡ ሄዶ በማይጨርሰው፣ መርምሮ በማይዘልቀው፣ አባርሮ በማይይዘው፣ ቀቢፀ ተስፋ የሚመላለስበትን ሀዲድ የሚነቀንቅበት ጥግ፣ በአቱን አድርጎ ሹሞ አድፍጧል፡፡ በአቱ፣ ሽሽቱንና ደፈጣውን የሚይዝባት ኮሮጆው ናት። ለታለ ሕይወት በቀረበ መልኩ ቲም ሮት The legend of 1900 በሚለው ፊልም ላይ የሕይወትን ትርጉም በፒያኖው ያሰሰበትንና፣ አራት አስርታት መርከብ የመሸገበትን ምክንያት እንዲህ ይለዋል፡- Novecento:- Take piano, key begins key end. You know there are 88 of them and no one can tell you differently. They are not infinite, you are infinite. And on those 88 keys the music that you can make is infinite. That I can live by, that keyboard is infinite [the world] but, if that keyboard is infinite there is no music you can play. That’s God’s piano. Could you show me where it ends; the world; did you see the streets; there were thousands of them. How do you choose just one; one women, one house, one piece of land to call your own, one landscape to look at, and one way to die?
ታለ ከንፈር በሚመጠጥለት የሕይወት ጥግ፣ እየታከከ የሚመላለስበትን መስመር ማየት የርስቱን ጥበት ያስይዛል፡፡ ታለ ሂያጅ ውኃን የተጎራበተ የረጋ ኩሬ ነው፡፡ ቀበናን ዋስ ይዞ፣ ለተማጽኖ የሚቆምባቸው መመላለሻዎቹ ጊዜን ብቻ ሳይሆን ቦታን ያጠባሉ፡፡ ቀበናን እየተሻሸ ሲዞር ጉልበቱ መሄጂያ በማጣት የሚዝልበትን ብርክ ይያዛል፡፡ ቅንብቢትን ቢርቃት በጠንቋይ ማረፊያና በብቅ እንቅ ለመያዝ ነው፡፡ ኋላ ግን፣ የተተበተበበትን ክር ፈታትቶ የሽሽት አድማሱን ሲያሰፋ፣ የምትቀበለው ዐይነምሣ ትመጣለች፡፡ ዐይነምሣ በአብርሃም ልብ ተቀብላ ካስተናገደችው ብዙም ሳይርቅ፣ the last temptation of Christ ላይ እንዳለው ኢየሱስ፣ ሕይወቱን እግር በእግር በሚከተለው ፈተና ይያዛል፡፡   
The last temptation of Talle.
ታለ ለምስክር የቀረበባቸው (የሌሎቹን ባሕርያት ሰቆቃ ለመታዘብ ጭምር የገባበት) እና የእርሱን እገዛ የሚፈልጉ የተቀባባቸው የመከራ አዝማናት መሀል፣ በቦታና ስፍር በሌለው [Infinitesimal] የእምነት ሽግግር ተፈትኗል፡፡ ዐይነምሣ ላይ ያረጋት ነፍሱን የምታደፈርስ ፈተናው፣ በር አንኳኩታ ትገባለች። በስተመጨረሻም ታለ ሲቅበዘበዝበት ለኖረው ሕይወቱ ማረፊያ የሚሆን ፈተና ፊት ቆመ፡፡ በሽሽት ያዛለው ጉልበቱ ወስዶ Old airport ጣለው፡፡
… በቃኝ የኑሮ አጉራህ ጠራኝ
   እፎይ የዕድሜ አዚም ጠራኝ
   አስለመለመ መብራቱ
   በሕይወት የመዋተቱ
   የነግ-ነግ መንከራተቱ
   መንከላወሱ ልፋቱ…
   መከሬ ሻማዋ ጠፋ
   መሸ ቀኔ ላንቀላፋ…
በረድ ሠርዌ ሲኮተኮትና ሲታረም የባጀው ተክል፣ ሐሰተኛው ሊጠለልበት ተጎነበሰ፡፡ ታለ በሕይወት የሚዋትትበት ምዕራፍ በሚዘጋበት ቦታ፣ አርባ ቀንና ሌሊት ፀለየ (ዝኒ ከማሁ)። እዚህ ጋር አብሬ ላነሳው የምፈልገው ነጥብ ይመጣል፡፡ The last temptation of Christ ላይ፣ ኢየሱስ ለፀሎት በመረጠው ጭው ያለ በረሃ፣ በብዙ አሳች ፈተናዎች ሲበዘበዝ ፍንክች አለማለቱን ያስነብበናል፡፡ ይህ የኢየሱስ ፅናት ግን በመስቀል ላይ በሚገጥመው የመጨረሻ ፈተና ይመታል፡፡ በመልዐክ ተመስሎ በቀረበለት ፈተና ምክንያትም ባልተገባው ሕይወት እንዲመላለስ ይሆናል። ታለንም የገጠመው ይህን ዓይነት ፈተና ነው፡፡ ከቅንብቢት የጀመረውን ፈተና በፅናት አልፎ፣ እስከፅሞናው ጊዜ በትዕግስት ይመጣል፡፡ በመጨረሻ ግን እንደ The last temptation of Christ ‘ቱ ኢየሱስ በሐሰተኛው እጅ ሊወድቅ ይሆናል፡፡
የሐሰት አላባውያን
ይህ ንዑስ ምዕራፍ የሐሰተኛውን ማብቂያና የተጠላው እንዳልተጠላን አመጣጥ በመላምት የምደግፍባቸውን ሀሳቦች የያዘ ነው፡፡ በቅድሚያ ሁለቱ መጻሕፍት የተያያዙበትን ክር ልሳብ፤ ትንቢት፡፡ በትንቢት የተመራ ድርጊት፣ የሚፈፀምበት ቦታ ነው፣ የተጠላው እንዳልተጠላ፡፡ ይህንንም ለመጠርጠር፣ ድርጊታቸው ማንነታቸውን የሚገልፁበት እቃ ሆኖ የሚገለገልበት የገፀ ባሕርያት አሰላለፍን ማየት ይበቃል፡፡
ደራሲው በእሳት እየፈተነ ያቆያቸውን፣ ሦስቱን ባለ መንታ ባሕርያት፣ እንደ ሐሰት መስሪያ አላባ ይጠቀማቸዋል፡፡  
ታለ (አልአዛር)፣ ኖላዊ (ሃሳዊ መሲህ)፣ ረድ ሠርዌ፡፡ እኚህን ሦስት አላባዎች በመጠቀም በአንዱ ሞት የአንዱ ትንሳዔ እንዲመዘገብ፣ ዐይኑ በጠፋው ፋንታ ዐይኑ የበራውን፣ በተሰቃዩ ምትክ በሌላኛው ትንሳኤ እንዲገኝ አድርጎ ያቀርባል፡፡ ይህ የትንቢት አመጣጥ ረድፉንና የድርጊት አፈፃፀም ላይ ያለውን ሀቀኝነትና ታማኝነት ደራሲውን ምስጉን ያደርገዋል፡፡
…እኔ በመስቀል ላይ ስሞት እርሱ፣ መንትያዬ በሦስተኛው ቀን ትንሳኤዬን ይፈፅማል፡፡ ረድ ሠርዌን ያሳወሩት ዓይንአምባዎች በአምሳያ ወንድሙ ዓይኑ በርቶ እንዲያዩት ይደረጋል። የአንተ ንትያ አልአዛርን ሆኖ ይሞታል፣ በአንተ ከሙታን ሲነሳ የገነዙት ሁሉ ተአምረ ትንሳኤውን ለአለም ሁሉ ይመሰክራሉ፡፡… ብዙሃኑ ሳያውቁት ቀደም እንዲህ ሆኗል፣ አሁንም እንዲሁ ይሆናል።… (ገፅ 301፣ ሐሰተኛው)
ከእናቱ ከትርጉመ ቢስ እና ከአባቱ ከተስፋ ቢስ የተወለደው ‘ለውጥ’ የተባለው ሕፃን [Active Nihilism]
በዚህ ርዕስ ስር የምናያቸው ነጥቦች የመጻሕፍቱን ተዋረድ (በድርጊት ሂደት ትንቢት መሲህን መቅደሙን ልብ ይሏል) በተከተለ ይሆናል፡፡ ገፀ ባሕርያቱ መሽቶ መንጋት በሚያመጣው በረከትና መርገም፣ ከሚያመጣው ውዳሴና እርግማን በራቀ፣ ለኅልውናዊነት መብሰልሰል ፊታቸውን የመለሱ ናቸው፡፡
… Active nihilists are individual who actively destroy our old, fake false values and begin constructing our own subjective beliefs and interpretation of meaning. ሐሰተኛው ላይ የምናየው ሕይወት፣ ስልት በሌለውና እንደ ሲሲፈስ ሄዶ ባለማለቅ ምልልስ፣ ያዛለቻቸውን ባሕርያት ምሬት ነው፡፡ ይህን የምሬት ፅዋ ባለሳምንቱ ታለ ደጅ ስትደርስ ያለውን ላስታውስ፤
… ሕይወት ከከንቱ ውልደት ወደ ከንቱ ሞት የመጓዝ ከንቱ መናወዝ አይደለምን? … (ገፅ 14፣ ሐሰተኛው)
… የሰው ልጅ በከንቱ ተፈጥሯልና፣ ከተፈጠረም በኋላ እንዳልተፈጠረ ሆኗልና… የተፈጠርነው በግድ የለሽነት፣ በእንዝህላልነት እና በማን አለብኝነት ተራድኦ እንደሆነ መቀበል ነፍሴን እንደሻህላ የሚበላ እውነት ነው፡፡ (ገጽ 9፣ ሐሰተኛው)
ይህ ንግግር የሚወስደን ጨርቁን ወደ ጣለ ኒሂሊስታዊነት ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ኒሂሊስታዊ ገሸሽታ ራሱን ገፍቶ፣ ተስፋ ቢስነት ወደሚያስተዳድረው [Passive nihilism] ናዲር አልጣለውም፡፡ በአንፃሩ፣ ከመሰልቸቱና ትርጉም ከማጣቱ የምትወለድ ለዋጭ ወንጌሉን አትሮንሱ ላይ ይዘረጋል። በዚህ የመፃሕፍቱ ባሕሪ ምክንያት፣ የትንቢትና የድርጊት ተዋረድ የሚያሳልጥ ፅኑ ነቢይ ሆኖ አክቲቭ ኒሂሊዝም እንዲቀባ መንገድ ይሆናል፡፡
ያልጠጡትን እንዲከፍሉ፣ ያልበደሉትን እንዲክሱ የሕይወት ህቡዕ ችሎት ፊት የቀረቡ፣ እንደታለ ያሉ ሌሎች ገፀ ባሕርያትን ፈተናም ቆጥረን እናገኛለን፤ ሐሰተኛው ውስ። ኒሂሊስቶች የሕይወትን ትርጉመ ቢስነት በጉልህ የሚያስተምሩ ናቸው። እኔ፣ በእኚህ ሁለት መጻሕፍት ውስጥ ያሉትን ባሕርያት፣ እገሌ ኒሂሊስት ነው እገሊት ፔስሚስት ናት እያልኩ ለመፈረጅ በጊዜና በቦታ የሚለዋወጥ የባሕርያት ቁመና ያግደኛል፡፡ ስለዚህ፣ የገፀ ባሕርያቱን ዳና እየተከተልኩ ከማዛምዳቸው ‹‹ምናዊነት›› በተሻለ የመጻሕፍቱ ዝንባሌ ላይ ማተኮርን መርጫለሁ፡፡ ከሐሰተኛው የተነሳው ኒሂሊስታዊ ዝንባሌ በየተጠላው ላይ ወደ አክቲቭ ኒሂሊስታዊነት ማደጉን መዳሰስን እንደ አማራጭ ለማየት ሞክሬያለሁ። በቅድሚያ የአክቲቭ ኒሂሊስት መገለጫ የሆነውን በመጥቀስ በዝርዝር ወደሚቀርብበት እወስዳችኋለሁ። አንደኛውና ዋነኛው፣ የሕይወትን ትርጉመ ቢስነትና አይጨበጤ የመከራ ጉዞ ካወቅን በኋላ የምንወስደው እርምጃ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ይህም ለራስ ሕይወት ራስን አላፊ በማድረግ፣ አልያም፣ ራስን በራስ ላይ በመሾም [self-appointed] ትርጉሙን በራስ መፈለግን ይመለከታል፡፡ ይህን ተከትሎ የሚመጣው፣ ትርጉም የምንሰራበት እርምጃ ነው፡፡ ይህ የሚያካትታቸው ነጥቦች አሉት፡፡ ዋንኛዎቹ፣ ቀድሞ በነበሩን ባልጠራ እውነት ላይ የተመረኮዙ እምነቶቻችንን ማፍረስና፣ በምትኩ የኛን ተጨባጭ እውነት መቅረፅ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በዚህ መሀል ልብ እንድንለው የምፈልገው ነገር፣ በመጽሐፍቱ ውስጥ የምናየው የአክቲቭ ኒሂሊስም ቅምምስ [Experience] በራሱ ውስጥ የሚያሳየው እድገት መኖሩን ነው፡፡ ይህም Optimistic nihilism እድገቱን ሊቀበለው የሚችልበት አግባብ መተው መቻሉን ይመለከታል፡፡ ከዚህ ቀጥዬ ከስር በሚነሱ ርዕሰ ጉዳዮች፣ የአክቲቭ ኒሂሊስምን ጠባይ በሁለቱ መጻሕፍት እንዴት እንደተገለጠ ለማሳየት እሞክራለሁ፡፡ ከዚህ በፊት ግን ኒቼ ከኒሂሊዝም ጋር ስለሚኖረን መጻዒ እጣ ያለውን ላስታውስ፡-
… I praise, I do not reproach, [Nihilism] arrival. I believe It is one of the greatest crises, a moment of the deepest self-reflection of humanity. Whether man recovers from it, whether he becomes master of this crisis, is a question of his strength. It is possible. … [Complete works of Friedrich Nietzsche, Existential Nihilism. Vol, 13]  (ይቀጥላል)


Read 1473 times