Sunday, 26 June 2022 10:16

የአዲስ አበባ ከተማ ቦታ ግብር፤ “በዝክረ ነገር” እይታ

Written by  ነቢይ መኮንን
Rate this item
(0 votes)

  አምስቱ አድራጊ ፈጣሪ የከተማችን ሴቶች
                           
            ዛሬም “ዝክረ ነገር” ስለተባለውና  በብላቴን ጌታ ማኃተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል ስለተጻፈው መፅሀፍ ጥቂት ብንናገርና  ወደ ሌላ ጉዳያችን ብናመራ አይከፋም፡፡ በተለይ  ስለ አዲስ አበባ ከተማ ቦታ ግብር የተጻፈው ክፍል፣ ትልቅ ፋይዳ ያለው ይመስለኛል፡፡ ምነው ቢሉ፡-
አንድም “አፄ ምኒልክ፤ በእቴጌ ጣይቱ ብጡል አዲስ አበባ ተብሎ ተሰይሞ የተቆረቆረው ከተማቸው አቅድና መልክ እያገኘ፣ ነዋሪውን ህዝብ ለሚመራው ወይም ለሚገዛው ርስቱ የታመነ የምስክር ወረቀት አግኝቶ፣ ይህንኑ ቦታውን ያለስጋት በዋስትና ለማስያዝ ወይም ለመሸጥና ለመለወጥ እንዲችል፣ የከተማው ቦታ ሁሉ ስፋቱ በመሀንዲስ እየተለካ፣ በሜትር ካሬ ታውቆ፣ ከቦታው ስዕል አንድ ግልባጭ ለባለቤቱ እንዲሰጥ አንድ ግልባጭ ደግሞ በምስክርነት በማዘጋጃ ቤቱ የርስት ክፍል  ፅፈት ቤት እንዲቀመጥ” የአሰራሩን አይነት ዘርዝሮ በ፴፸ ቁጥር የተጻፈ ሙሉ ደንብ በጥቅምት ፳ ቀን ፲፱፻ ዓ.ም ለማዘጋጃ ቤቱ ስጡ” ይላል፡፡
ሁለትም ደግሞ፤ “ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ፡፡ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ፡፡ ስዩመ እግዚአብሔር ንጉስ ነገስት ዘኢትዮጵያ። ከዚህ በታች የተጻፈው አዋጅ “በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆነው ህዝብ መንግስት በማዘጋጃ ቤቱ አማካይነት በየጊዜው በሚሰጠው ልዩ ልዩ ህግና አገልግሎት ተጠቃሚ ሆኖ ሳለ፣ ካርታ ያለው  ባለቦታ ብቻ ሲገብር፣ የቀረው ህዝብ እንዲያው በመቀመጡ ቤት ያለው ሁሉ ግብር እንዲከፍል የሚያዝ ነው፡፡" በሚል ስለ አዲስ አበባ ከተማ  ቦታ ግብር  የሚያትት ነው፡፡  
ያዘለው አንኳር ሀሳብም፡-
1ኛ. ማዘጋጃ ቤት  ለከተማውና ለህዝቡ ጥቅም ሲል ባሰራው መንገድና  ባቆመው ዘበኛ ስለሚጠቀም፣ ግብር መክፈል አለበት። ካርታ ማስነሳትም ግዴታ ነው!
2ኛ. ስለቦታው የምስክር ወረቀት ሳያቀርብና ካርታውን ሳያስነሳ እስከ 5 ዓመት ቢዘገይ፣ በማዘጋጃ ቤት በዓመት ተወስኖለት ሲከፍል የቆየውን ግብር ስለመቀጫ በእጥፍ ያስከፍለዋል፡፡
የምስክር ወረቀቱን አቅርቦ ማዘጋጃ ቤት ካርታ ሳያስነሳለት ቢቀር ግን፣ ኃላፊ ማዘጋጃ ቤት ይሆናል እንጂ ባለቦታው አጠፌታ መክፈል የለበትም። ካሁን  በፊት ካርታ ተነስቶ እስካሁን በካርታው ስለሚገብረው፤ እስካሁን የሚገበረው ቦታ ርካሽ በነበረበት ጊዜ የነበረውን ግብር ነበር፤ አሁን ግን ቦታ እየተወደደና ባለቦታውም ጥቅም እያገኘ በመሄዱ ግብሩ እንዲቀጥል ፈቅደዋል።
በቦታው ላይ በሽያጭ ሳይሆን ሌላውን ሰው ቤት አሰርቶ የሚኖር፣ ባቅራቢያው የሚመስለው ቤት በኪራይ የሚሰጠው ጥቅም ታስቦ፣ ባመት ከመቶ ሶስት ብር ከሶስት ሩብ ሂሳብ ባለቦታው በየዓመቱ ይክፈል፤ ባለቦታ ይክፈል ስላልን የቦታው ጌታ በፈቃዱ የቤቱን ጌታ ስለ ቤቱ ግብር ለማዘጋጃ ቤቱ ካገጣጠመ ባለቦታው መያዝ የለበትም።
ባለቦታው በቦታው ላይ ቤት ሰርቶ ለመኖሪያና ወይ ለንግድ ለሚያደርገው ሰው ያከራየ እንደሆነ፣ በኪራይ ከሚያገኘው ጥቅም ባለርስቱ ከመቶ ሶስት ብር ከሶስት ሩብ ሂሳብ ይከፍላል።
ያከራየው ቤት ለፋብሪካ/ የመስሪያ የሆነ እንደሆነ ግን ከመቶ ሶስት ብር ብቻ በአመት ይከፍላል።
በቦታው ላይ በሰራው ቤት ራሱ ባለቤቱ የሚኖርበት የሆነ እንደሆነ ግን ለጊዜው እንደ ደንቡ ይገብራል፤ ይህ ደብዳቤ ከ1926 ዓ.ም ከመስከረም ወር ጀምሮ ወደፊት እንዲጸና ሥራው ይጀመራል። ነሐሴ 1 ቀን 1925 ዓ.ም”
“የአዲስ አበባ ከተማ ቦታ ግብር” እስከዛሬ ድረስ ሲያጨቃጭቅ፣ ሲያፋጭና ሲያጋጭ ይኸው ከ25 ዓመታት በላይ የፈጀ ጉዳይ ሆኗል። ሁኔታውን ለማሻሻል ብዙ ተደክሞበታል።
የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት አዋጅ ወጥቶበትና የሚኒስቴር መ/ቤት ተቋቁሞበትም ማነጋገሩና ማከራከሩ አልቀረም።
ነገሩ በየዓመቱ ልጃገረዶች፤
“… አበባየሁሽ ለምለም
ባልንጀሮቼ ግቡ በተራ
እንጨት ሰብሬ ቤት  እስክሰራ
እንኳን ቤትና የለኝም አጥር
እደጅ አድራለሁ ኮከብ ስቆጥር…”
እያሉ መዝፈናቸው መሰረታዊውን የቦታና ቤት ችግር አመላካች ነው፣ ብንል ማጋነን አይሆንም።
እንደ አፈ ታሪክና አፈ-ተረት የሚነገር ይህንኑ ጉዳይ ጠቋሚ ወግ አለ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በጣም ዕውቅ ዕውቅ የተባሉ በ1970ዎቹ የነበሩ እና አሁንም ያሉ አምስት ሴቶች አሉ፡፡ የደርግ አባላት ሚስት-አከል ቅምጦች ወይም ውሽሞች ናቸው ይባላል፡፡ በዚህም መንግስት ላይ ጫና እስከማድረግ ተፅዕኖ ፈጣሪ ናቸው ይባላሉ። አንዱ የደርግ አባል ሌላኛውን ለመጉዳት እንዲነሳሳ፣ እንዲጋጭና እስከመጠፋፋትም እንዲደርስ፤ እኒሁ እንስቶች አድራጊ-ፈጣሪ እንደሆኑ ይነገራል። ይኼ እንግዲህ አንድም፤
“ሴት የላከው ሞት አይፈራም” የሚለውን ተረት፣ አንድም ደግሞ “Behind every successful man there is a strong woman; የሚለውን ብሂል አሊያም ፍልስፍና የሚያጸኸይልን ነው፡፡ ከእያንዳንዱ ስኬታማ ወንድ ጀርባ አንዲት ጠንካራ ሴት ትኖራለች እንደማለት ነው!
በዚያን ዘመን አንዷ እጅግ የበለፀገች ሴት ላይ የምትቀና የደርግ አባል  ቅምጥ፣ ውሽማዋ ላይ ተፅዕኖ በማድረግ የቦታና ትርፍ ቤቶችን አዋጅ እስከ ማሳወጅ ደርሳለች ይላሉ፡፡ ይህቺ ታሪከኛ አገር ታሪካዊ አገር ናት የምንለው ያለ ነገር አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ ቤት ለባለቤቱ ይመለስ የሚለው የመንግስት ፖሊሲ ማሻሻያ አዋጅ ትግራይ ክልል ላይ ብቻ እንዲሰራ ተደርጎና ቤት ለባለቤቱ ተመልሶ ሲያበቃ፣ በዚያው ክልል ተገድቦ መቅረቱ ሁሌም እንደገረመኝ አለ፡፡ በወቅቱ የተሰጠን ምክንያት ብዙ ትርምስና ንትርክ ይፈጥራል የሚል ነበር፡፡ “ቢከፋ ቢከፋ ከኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት ይከፋልን?” ብለን ነበር ያኔ!  በፊውዶ ቡርዥዋ ሥርዓትና በቢሮክራሲያዊ ካፒታሊዝም ሙስና ለተተበተበች አገር አንድ ሁሉን-አቀፍ መፍትሄ፣ በአንድ ጀምበር መስጠት ባይቻልም፣ ቢያንስ ለውጥ ማምጣት መጀመራችንን አይተን እፎይ ማለት ነበረብን- A change is as good as rest ይሏልና፤ ለውጥ የእፎይታ ያህል መልካም ነገር ነው፤ እንደማለት መሆኑ ነው፡፡

Read 2447 times