Saturday, 25 June 2022 00:00

በወለጋ የተፈጸመውን የጅምላ ጭፍጨፋ መንግስት በአስቸኳይ እንዲያጣራ የተመድ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን አሳሰበ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

 በፓርላማ ጉዳዩን የሚያጣራ ቡድን ተደራጅቷል
                                      
             የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ በምዕራብ  ወለጋ ቶሌ መንደር የተፈጸመውን አሰቃቂ የጅምላ ግድያ፣ መንግስት በአፋጣኝ ጥልቅና ገለልተኛ ምርመራ እንዲያካሂድ ያሳሰበ ሲሆን የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በበኩሉ፤ ጉዳዮን የሚያጣራ ቡድን ማደራጀቱን አስታውቋል።
ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም ወለጋ ቶሌ በተባለች መንደር የተፈጸመው የጅምላ ግድያ በእጅጉ ረብብሾኛል ያሉት የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሼል ባችሌት፤ ድርጊቱ ተድበስብሶ ሊታለፍ የሚገባው አይደለም ብለዋል።
በእለቱ በመንደሩ የገቡ ታጣቂዎች ባገኙት ሰው ሁሉ ላይ እየተኮሱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ላይ የጅምላ ፍጅት መፈጸማቸውንና ከሟቾቹ አብዛኞቹ ሴቶችና ህጻናት መሆናቸውን ከአካቢው እማኞች መረጃ  ማግኘታቸውን ከፍተኛ ኮሚሽነርሯ ገልጸዋል።
በጥቃቱ ከሞት የተረፉ ከ2 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎችም ከአካባቢው መፈናቀላቸውንና ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን፤ አራት ሰአታትን በፈጀው ጥቃትም በሰዎች ላይ ከደረሰው የጅምላ ፍጅት ባሻገር መኖሪያ ቤቶችና የተለያዩ ንብረቶች በታጣቂዎቹ መቃጠላቸውንና መውደማቸውን ኮሚሽኑ ይጠቁማል።
ለሰአታት በተፈጸመው ጥቃት የተገደሉ ሰዎች አስክሬን በየቦታው ወድቆ ሊገኝ እንደሚችልም ሚሼል ባችሌት በመግለጫቸው አክለዋል።
መንግስት ጥቃቱን ያደረሰው “አሸባሪው ሸኔ” መሆኑን መግለጹን፤ በአንጻሩ ታጣቂ ቡድኑ ቃል  “እጃችን የለበትም፤ ጥቃቱ በመንግስት ሚሊሻዎች ነው የተፈጸመው” ማለቱን የጠቀሰው የተመድ የሠብአዊ መብት ኮሚሽን ቢሮው፤ ይህን ጉዳይ መንግስት በአፋጣኝ በገለልተኛ አካል በጥልቅ ምርመራ ሊያጣራ ይገባዋል ብሏል።
በሚካሄደው ምርመራ  ግኝት መሰረትም፤ አጥፊዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ፣ ተጎጂዎችም እንዲካሱ ኮሚሽኑ ጥሪውን አቅርቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ  የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በበኩሉ፤ በጋምቤላና በወለጋ በአሸባሪው ሸኔ በንጹሃን ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ የሰብአዊ መብት ጥሰትን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አጣርቶ እንዲያቀርብ አዟል።
በተጨማሪም መረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔና ምላሽ ለመስጠት ይቻል ዘንድም የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፈጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ ወቅታዊ ጉዳዮችን የሚያጣሩና ከምክር ቤት አባላት የተውጣጡ ሁለት ቡድኖችን በማቋቋም ስምሪት መስጠታቸው ታውቋል። ቡድኖቹ ተግባራቸውን አከናውነው የሚያመጡት ግኝ፤ት ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግና አስፈላጊው አቅጣጫ እንደሚሰጥ አፈጉባኤው አስረድተዋል።

Read 1142 times