Monday, 27 June 2022 00:00

እዚህም እሳት መለኮስ፣ እዚያም ደም ማፍሰስ!

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

  ሁሉም ሰው፣ “ፖለቲከኛ” መሆን አማረውኮ። ይሄ የምኞትና የሕልም እጦት ነው።  የበሽታ ምልክትም ጭምር እንጂ።
“ፓይለት”፣ “ሐኪም፣ ዶክተር”፣ “የአውሮፕላን ኢንጂነር”፣ “ሳይንቲስት”፣ “የሂሳብ ሊቅ”፣… ወይም “ጋዜጠኛ”፣ “ደራሲ”፣ “ዘፋኝ”፣ “የእግር ኳስ ኮከብ”፣… ለመሆን ይመኛል - ሰው። ማቴ፣…የሚመኝ ይመስለኛል - ሕልም ያልጠፋበት ሰው።
ሙያ ባይመርጥ እንኳ፣… በደፈናው፣ “ታዋቂ ሰው” ለመሆን፣ በውርስም ይሁን በሎተሪ ሚልዮነር፣ ቢልዮነር ለመሆን መመኘትም አለ። “የዓመቱ ተወዳጅ ሰው” ተብሎ ለመመረጥ፣ “ወይዘሪት ኢትዮጵያ” የሚል ዘውድ ለማግኘትና ለማጌጥ የሚመኙ ወጣቶችም ቢኖሩ፣… ይቅናቸው።
ተወዳጅነትና የቁንጅና ዘውድ፣ ራሳቸውን የቻሉ የሙያ ዓይነቶች አይደሉም ብንል እንኳ፣ መጥፎ ምኞቶች አይደሉም። ሁሉም ሰው ፖለቲከኛ ለመሆን ከመሞክር ይልቅ፣ የቁንጅናም ሆነ የተወዳጅነት ዘውድ ለመጫን መመኘት፣… በጣም ይበልጣል። የትና የት! ሙያ ባይሆኑም፤ ጥሩ ናቸው። ደግም በከንቱ አይገኙም።
መልካም ምኞትና ሕልም፣ ትንሽም ይሁን ትልቅ፣ ለኑሮ በረከትን የሚያመጣ፣ ሕይወትን የሚጣፍጥ መሆን ነበረበት። እውነት ነው። ቁምነገር ባይኖረውም ግን፣ እንዲሁ ለአይን የሚያምር፣ ለጆሮ የሚጥም ነገር ለማግኘት መመኘትም በጎ ነው።
ደግነቱ፣ ፓይለትና የአውሮፕላን ኢንጂነር፣ ሳይንቲስትና አርቲስት፣ ሐኪም ወይም ገጣሚ ለመሆን ከመመኘት ጋር፣ ገና በልጅታቸው የሚሞክሩ አሉ። ግጥምን አንብበው በፍቅር በቃላቸው የሚይዙ፣ የጥበበኛ ሰዎችን ታሪክ የሚከታተሉ፣… በተግባር የቴክኒክ ስራዎችን የሚሞክሩ ልጆች፣ ጥቂት አይደሉም። እንዲያውም፣ አንዳንዴ፣ በሬዲዮ እንሰማቸው፣ በቴሌቪዥን እናያቸው ነበር።
በእርግጥ፣ ጋዜጠኞች፣ የልጆችን የቴክኒክ ሙከራና ውጤት ላይ ከማተኮር ይልቅ፣ “ከወዳደቁ እቃዎች…” የሚል አገላለጽን እንደ ዋና ቁምነገር እየደጋገሙ ያወራሉ። ከጣሳ፣ ከቁራጭ ብረት፣ ካገለገለ ብርጭቆ የተሰራ ፈጠራ ብለው መናገር እየቻሉ፣ “ ከወዳደቁ እቃዎች…” ብሎ መናገር አላስፈላጊ ነው።
ቢሆንም ግን፣ ከምንም ይሻላል። ልጆች ስለፖለቲካ እንዲያወሩ ከማድረግ ይልቅ፣ ስለቴክኖሎጂ መናገር  ደግሞ በጣም ይሻላል።
ዛሬ ዛሬ´ኮ፣ ሐኪም ወይም የአውሮፕላን ኢንጅነር ለመሆን መመኘት፣ አዲስ ፈጠራዎችን የመስራት የቴክኖሎጂ ሙከራዎች ከቁም ነገር አይቆጠሩም።
አሁን፣ የፖለቲካ ወሬ ነው የነገሰው። ሕፃን አዋቂው ሁሉ፣ ፖለቲከኛ ካልሆንኩ ባይ ሆኗል።
ለዚያውስ ደህና ፖለቲካ ቢሆን። ግን፣ ከየት መጥቶ! ማን አሳይቶ፣ ከማን አይቶ ደህና ፖለቲካ ያመጣል? እንዲሁ መደናቆር፣ ከዚያም መናቆር ነው-ፖለቲካው!
ምን ይሄ ብቻ!
“የወዳደቁ የጥላቻ ስሜቶችን እየለቃቀሙ”፣… ሰዎችን የማናቆር ፉክክር ነው… የዘመናችን ፖለቲካ።
በጥላቻ የሰከሩ ሰዎች፣ ቢደናቆሩና ቢናቆሩ፣… ለጥቃት ቢዘምቱ፣… ክፋት ቢፈጽሙ፣ ሕይወት ቢያጠፉ፣ ያሳዝናል፤ ያናድዳል።
የአገራችን አሳዛኝና አስፈሪ ችግር ግን፣ ከዚህ ይብሳል። በጥላቻ የሰከሩ ክፉ ሰዎች፣ አገር ምድሩን አስክረው ናላውን እስከ ማዞር መድረሳቸው ነው - ትልቁ ችግር። መደናቆር ብቻ ሳይሆን አብዛኛውን ሰው ማደናቆር መቻላቸው፣ መናቆር ብቻ ሳይሆን፣ የማናቆር  እድል ማግኘታቸው ነው - ትልቁ አደጋ።
በጥላቻ የሰከሩ ሰዎች፣ ለጥቃት ከመዝመት አልፈው፣ ጥላቻን በሰፊው ማዛመት መቻላቸው፤ ብዙ ሰዎችን የጥቃት ዘመቻ ተሳታፊና አጃቢ፣ አጨብጫቢና ተሟጋች እንዲሆኑላቸው የማነሳሳት አቅም ማግኘታቸው ነው- አስፈሪው አደጋ።
የቱንም ያህል ዘግናኝ ጥፋት ቢፈጽሙ፣ አጃቢና ተሟጋች እንደማያጡ ያውቁታል። በጎራ የመቧደን በሽታ የነገሰበት ፖለቲካ ውስጥ፣  ለወንጀለኞች ፊት የሚሰጡ ቡድኖችና ጎራዎች ይበራከታሉ። አንዱ ጎራ ቢያወግዛቸው፣ ሌላ የድጋፍ ጎራ እንደሚያገኙ እርግጠኛ ናቸው- ክፉ የጥላቻ ሰዎች።
በበሽታ ላይ በሽታ እንደማለት ነው። በጥላቻ የሰከሩ ሰዎች፣ ሁሌም ነበሩ፣ ይኖራሉ። በየትኛው አገር አሉ። በየቦታው በጅምላና በእሩምታ ንፁሃን ሰዎችን የሚገድሉ ጨካኝ ወንጀለኞች በየአህጉሩ በየአገሩ እናያለን። ትልቁ ልዩነት ምንድን ነው? ክፉ ነፍሰ ገዳዮች፣ በአውሮፓ ወይም በአሜሪካ ብዙ አጨብጫቢ አያገኙም። “የኛ ወገን” ብሎ የሚከራከርላቸውና አቅፎ የሚቀበላቸው ጎራ  የለም። የክፋትና የጭካኔ ወንጀላቸውን፣ በሰበብና በማመካኛ ሊሸፋፍንላቸው የሚሞክር ተሟጋች እንደማያገኙ ካወቁ፣  ብዙዎቹ ወንጀለኞች ንፁሃን ሰዎችን በጥላቻ ከጨፈጨፉ በኋላ፣ ራሳቸውን በጥላቻ ያጠፋሉ። በአሜሪካና በአውሮፓ የምናየው እንዲህ አይነቶቹን ነው።
እንደ ኢትዮያ በመሳሰሉ አገራት ግን፣ በጭፍን እየተቧደኑና ጎራ እየፈጠሩ፣ …የጥላቻ፣ የክፋት፣ የጭካኔ ጥቃቶችን ለመሸፋፈን ብቻ ሳይሆን፣ ለማቆንጀት ጭምር መሞከር ተለምዷል።
የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ፣ ለዚህ ያመቻል። እያንዳንዱን ሰው በግል ድርጊቱ ከመዳኘትና ከመመዘን ይልቅ፣ በብሔረሰብ የምንቧደን፣ በጎራ የምንበሻሸቅ ሆነናል። አንዱ ጎራ፣ ክፉ የጥላቻ ጥቃትን ካወገዘ፣ ሌላኛው ጎራ በእልህ ስሜት የወንጀለኛ ተቆርቋሪና ተሟጋች ይሆናል።
 ማንም ክፉ ሰው፣ የጥላቻ ጥቃት ሲፈጽም፣ ጭካኔው በብሔር ብሔረሰብ የፖለቲካ መነጽር እንዲታይለት ማድረግ ከቻለ፤ የሚያጨበጭብለት የሚሟገትለት ጎራ አያጣም።
የሃይማኖት ፖለቲካም፣ ከዚህ አይነት ስካር  አያመልጥም። አሳዛኝና አስፈሪ አደጋ ነው፤ የሃይማኖትና የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካ መጨረው።
በጥላቻ የሰከሩ ክፉ ሰዎች፣ ጥላና ከለላ የሚያገኙት በዚህ በዚህ ሰበብ ነው። አገር ምድሩ፣ በዘረኝነት ወይም በጭፍን እምነት ከተቧደነ፣… ክፉ ሰዎች፣ ከአንድ ጎራ በኩል ቢወገዙ፣ ከሌላ ጎራ በኩል ተቆርቋሪ እንደሚያገኙ፣ ወይም ከውግዘት እንደሚያመልጡ ያውቃሉ።
ይሄ ነው አስፈሪው የአገራችን ችግር።
በየጊዜው የሚፈፀሙ አሳዛኝና አሰቃቂ የጥፋት ድርጊቶች፣… ሌላ ነገር ሳይጨመርባቸው፣ እጅግ የሚያስቆጡ  ክፉ ድርጊቶች ናቸው። በጣም የሚያሳስቡ ፈተናዎችም ናቸው።
የክፋት ጥፋቶችን የሚቀሰቅሱ፣ ሽፋን የሚሰጡ፣ በማመካኛና በሰበብ ለማቆንጀት የሚያገለግሉ ስሁት አስተሳሰቦች መኖራቸው ደግሞ፣ አደጋውን ክፉኛ ያባብሰዋል።  ምን ለማለት ፈልጌ ነው?
የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካን ሳይመክቱ፣ የሃይማኖት ፖለቲካን በእንጭጩ ሳይገቱ፣ “ሃብታ እና ድሃ” እያለ የሚያቧድን የምቀኝነት ፖለቲካንም ሳያስወግዱ፣… “የክፋት ጥቃቶችን ለመከላከል የሚችል አስተማማኝ አቅም” ማግኘት አይቻልም። እና፣ የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካን መመከትና ማሸነፍ ይቻላል ትላላችሁ? የዚህን ያህል ነው አደጋው።
 ከዘረኝት ጋር የተዛመደና ለጥላቻ ዘመቻ የሚያመች የፖለቲካ ቅኝትን እያንጎራጎርን፣ የጥላቻ ጥቃቶችን የመግታት አቅም ሊኖረን አይችልም።
ግን ይህ ብቻ አይደለም። “የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካን የሚተካ፣ ትክክለኛ የፖለቲካ ሃሳብ መያዝ አለብን” የሚል ተስፋ ጨርሶ በአጠገባችን አይታይም። በውናችን ቀርቶ፣ በሕልማችንም የሚመጣልን አይመስልም እንጂ።
በሌላ አነጋገር፣ “የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካን ትተን፣ በዚያ ምትክ ትክክለኛ ሃሳብ በሰፊው ቢታወቅ፣ በብዙ ሰው ዘንድም ተቀባይነት ቢያገኝ፣ መልካም ለውጥ ያመጣ ነበር” የሚል የተስፋ ችቦ አልያዝንም። ጭላንጭሉም የለም። ተስፋ ልንይዝ ቀርቶ፣ እንደ ምኞት፣ እንደ ሩቅ ሕልም፣ ውል አላለልንም።
ብዙ የተሳሳቱ ሃሳቦች በጊዜ ብዛት ተሰፋፍተው ስር መስደዳቸው፣ አደገኛ ጥፋቶችም መበራከታቸው ብቻ አይደለም - የአገራችን ችግር። የተስፋ ብርሃን ተጋርዶብናል። ብሩህ ህልም አጥተናል።
ይብዛም ይነስ፣ የአስተሳሰብ ስህተቶች፣ መጥፎ ልማዶች፣ እና አጥፊ ተግባሮች፣ በየአገሩ በየዘመኑ ያጋጥማሉ። የዘረኝነት ፖለቲካ፣ የሃይማኖት ፖለቲካ፣ ሰዎችን እንደማገዶ የሚቆጥር የሶሻሊዝም ፖለቲካ፣… በየጊዜው እየተፈራረቁና እየተደራረቡ የሚነግሱ የአስተሳሰብ ስህተቶች ሞልተዋል። በቀላሉ የማይስተካከሉ መጥፎ ልማዶችና በአጭር ጊዜ የማይቃኑ ጠማማ ባሕሎችም፣ በየአገሩ በብዛት አሉ፤ ነበሩ።
በዘርና በጎሳ አቧድኖ የማባላት ሱስን ጨምሮ፣ ባርነትን እንደ መደበኛ ልማድ የሚቆጥር ጠማማ ባሕል ያልነበረበት አገር የለም። በሃይማኖት ፖለቲካ ምክንያት ያልተንገጫገጨ አገር የለም። አብዛኞቹማ፣ በሃይማኖት ፖለቲካ ሰበብ፣ ለይቶላቸው፣ ከአንድም ሁለት ሶስቴ በጦርነት ወድመዋል - ኢትዮጵያም ጨምር። በሶሻሊዝም ወይም በሕዝባዊነት ፖለቲካ ሳቢያ፣ አልያም፣ “ድሃ እና ሃብታም” በሚል ልማዳዊ  ቅስቀሳ አማካኝነት፣ ብዙ አገራት በአመፅ ተቃውሰዋል። ተሰቃይተዋል።
ከተሳሳቱ አስተሳሰቦችና ከመጥፎ ልማዶች ጎን ለጎን፣ ንፁሃን ሰዎችን ለእልቂትና ለስቃይ የሚዳርጉ የጭካኔ ጥቃቶች፣ አገርን የሚበጠብጡና የሚያመሳቅሉ የጥላቻ ትርምሶች፣ ይበራከታሉ። በየአገሩ በየዘመኑ ታይተዋል፤ ተፈጥረዋል።
የጭካኔ ጥቃቶችና የጥላቻ ትርምሶችም፣ በተራቸው፣ ነባሮቹን የአስተሳሰብ ስህተቶች ያዛምታሉ። መጥፎ ልማዶችን ያባብሳሉ። አዙሪት ነው። የዘረኝነት ጥቃት፣ የዘረኝነት ስሜትን ያባብስ የለ?
መከራው ድርብርብ ነው። መፍትሔውም እንደዚያው ድርብርብ መሆን አለበት።
 ለጊዜው፣ በተገኘው አቅም ሁሉ፣ የተሳሳቱ ሃሳቦችን ለመመከት፣ መጥፎና ጠማማ ልማዶችን ለመቋቋም በብርቱ መጣር ተገቢ ነው። ቢሆንም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ ትልቅ ለውጥ አያመጣም።  ለዚያውም፣ የተሳሳቱ ሃሳቦችን ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል። ስህተቶችን የሚተኩ ትክክለኛ ሃሳቦችን መያዝ ይኖርብናል። አለበለዚያ የተሳሳቱ ሃሳቦችንና መጥፎ ልማዶችን የመከላከል  አቅም ከየት  እናገኛለን? ቢሆንም ግን፣ ቸል መባል የለበትም።
የጭካኔ ጥቃቶችን፣ የጥላቻ ዘመቻዎችን እለት በእለት ለመከላከል፣ ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር መትጋት ደግሞ፣ የግድ አስፈላጊ ነው። ውጤትም አለው። ሙሉ ለሙሉ መከላከል ባይቻልም፣ ጥፋቶችን ለመቀነስ ያስችላል።
የጥላቻ ወንጀለኞችን ከመግታት ጎን ለጎን፣ ሕግና ሥርዓት ለማስከበር የሚደረግ ጥረት፣ ትክክለኛ አስተሳሰብ ለመያዝ ይረዳል። ሕግና ሥርዓት፣ በተፈጥሮው፣ ይብዛም ይነስ፣ “እያንዳንዱ ሰው፣ እንደየ ግል ተግባሩ፣ እንደየ ግል ተሳትፎውና ድርሻው ዳኝነት ያገኛል” የሚል መልዕክት ያዘለ ነው።
“ሕግና ሥርዓት”፣… በጭፍን የመቧደን፣ በጅምላ የመፍረድ፣ በመንጋ የመንጋጋት አስተሳሰብን ለመመከት ያግዛል።
አዎ፣ በበርካታ ሕጎች ውስጥ የተሳሳቱ ሃሳቦች ሊኖሩ ይችላሉ። በርካታ የአሰራርና የአወቃቀር ሥርዓቶች ውስጥም፣ ጠማማና ገዳዳ ነገር አይጠፋም።
ለዚህም ነው፤ አንዳንዴ ወደ አምባገነንነት የመሸጋገሪያ መሳሪያ ሊያደርጉት- “ሕግና ሥርዓትን” ሌላ ጊዜም፣ ፍ/ቤትን የአመጽ መቀስቀሻ መድረክ ሊያደርጉት ይሞክራሉ።
ቢሆንም ግን፣ “ሕግና ሥርዓት” ከተባለ፣… በአመዛኙ አዎንታዊ ገፅታዎቹ ይበልጣሉ።
ሰዎችን፣ በዘርና በሃይማኖት፣ በሃብትና በድህነት፣  በጎራ የሚያቧድን፣ በጅምላ የሚዳኝ ሊሆን አይችልም - “ሕግና ሥርዓት” ከተባለ። በጭፍን ስሜት የመንጋጋት ዝንባሌን ለመግታትና፣ በማስረጃ ላይ የመተማመን መንፈስ ጨርሶ እንዳይጠፋ ለማዳን ሊጠቅም ይችላል - “ሕግና ሥርዓትን” በቅንነትና በፅናት የማስከበት ጥረት።
ይህም ብቻ አይደለም። ሕግና ሥርዓት፣ መሰረታዊ የህልውና ጉዳይ ነው። የተሳሳቱ አጥፊ አስተሳሰቦችን፣ መጥፎ ልማዶችንና ክፉ የጥላቻ ጥቃቶችን ተቋቁሞ፣ ለከርሞና ለመጪው ዓመት፣… አገር በሕልውና መቆየት የሚችለው፣ “ሕግና ሥርዓት” እስካልፈራረሰ ድረስ ነው።
“አገር” ማለት፣ “ሕግና ሥርዓት” ማለት ነውና።
በሕልውና ለመቆየት፣ ክፉ ጥቃቶችን ለመከላከል፣ ለመመከትና ለመቀነስ፣… ሕግና ሥርዓትን ማክበር የራሱን ድርሻ ማበርከት ይችላል። ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር በብርቱ መጣር ደግሞ፣ የመንግስት ዋና ስራ፣ ዋና ሃላፊነትና ግዴታ ነው።
ሕግና ስርዓትን የማስከበር ጥረት፣ የተሟላ ውጤት ባያስገኝም፣ ሥር የሰደዱ የአስተሳሰብ ስህተቶችንና መጥፎ ልማዶችን ለማሸነፍ ባያስችልም፣… የጥፋት ድርጊቶችና ወንጀሎች ላይ ግን፣ ለጊዜው በተጨባጭ ሊታይ የሚችል ለውጥ ያስገኛል።
ከዚህም ጎን ለጎን፣ ሕግና ሥርዓት የማከበር ጥረት፣… “ለአገር ጊዜ ይሰጣል”። መሰረታዊዎቹን ችግሮች የመግታትና የማስወገድ እድል ወደፊት ይገኝ እንደሆነ ለማየት፣… አገር ሳይተራመስ፣ ሕልውናው ሳይፍረከረክ ማቆየት የሚቻለው፣ ሕግና ሥርዓትን በማስከበር ነውና።
በእርግጥ፣ “ጊዜ”፣ ችግሮችን በራሱ ጊዜ አይፈታልንም።
“የዘረኝነት፣ የጭፍንነትና የምቀኝነት መጥፎ ዝንባሌዎች”፣ በዓመት በሁለት ዓመት አይስተካከሉም። የብሔር ብሔረሰብ ፖለቲካን፣ የሃይማኖት ፖለቲካን፣ ዜጎችን እንደ ጭሰኛ የሚቆጥር የሶሻሊዝም ፖለቲካን፣… እነዚህ የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን መመከት፣ በሌላ ትክክለኛ የፖለቲካ አስተሳሰብ መተካት፣… የአንድ የሁለት ዓመት ስራ አይደለም።
የእገሌ ብሔር፣ የእገሊት ብሔረሰብ እያሉ በፓርቲ መደራጀት፣… የእንቶኔ ሃይማኖት፣ የእንቶኒት ሃይማኖት እያሉ ለፖለቲካ መቧደን፣ ድሃና ሃብታም፣ ወይም ገጠሬና ከተሜ እያሉ ተቀናቃኝ ጎራዎችን የመፍጠር ልማድ፣… በቀላሉ የሚሽር በሽታ፣ በአንድ ውሳኔ የሚቃና ጥመት አይደሉም። በጠማማነት የደነደኑ ፅኑ በሽታዎች ናቸው። በትክክለኛ ሃሳብና በተቃና መንገድ፣ ለረዥም ጊዜ በፅናት መትጋትን የሚጠይቁ አደጋዎች ናቸው።
በሌላ አነጋገር፣ ትክክለኛ ሃሳብና የተቃና መንገድ ብቻ ሳይሆን፤ የሩቅ ሕልም ሊኖረን ይገባል።Read 9847 times