Saturday, 02 July 2022 16:59

በሰላም ድርድሩ ዋዜማ ህውሐት ዳግም ጦርነት አወጀ

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(4 votes)

 - በም/ጠ ሚኒስትሩ የሚመራው ተደራዳሪ ቡድን ሥራውን ጀምሯል
    - ህውሃት ካለው ድብቅ የሰላም አማራጭን ይቀበላል ተብሎ አይታመንም - የቀድሞ የፊንላንድ ዲፕሎማት
                
              ከቀናት በፊት ለሰላማዊ ድርድር ዝግጁ መሆኑን ያስታወቀው የህውሃት ታጣቂ ቡድን ከሰሞኑ ለዳግም ጦርነት ዝግጁ መሆኑንና ያወጀ ሲሆን ለዚህም በዘመናዊ መሳሪያ የተደራጀ ሃይል ዝግጁ መሆኑን አስታወቀ። ቡድኑ ለጦርነቱ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የገለጸው በሰላማዊ ድርድሩ የሚሳተፍ ከፍተኛ የልዑካን ቡድን ለመላክ መዘጋጀቱን ባሳወቀ ማግስት ነው።
የታጣቂ ቡድኑ አዛዥ ሌተናል  ጀነራል ታደሰ ወረደ፣ በትግራይ ክልል ለሚገኙ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች  ከትናንት በስቲያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ታጣቂ ሃይሉ ለጦርነቱ ሁሉንም ዝግጅቶቹን ማጠናቀቁን አመልክተው። አሁን የሚቀረን ጦርነቱን መቼና እንዴት እንጀምረው የሚለው ጉዳይ ነው ብለዋል።
“በቀጣይ የምናደርጋቸው ጦርነቶች ከዚህ በፊት ከነበሩት የገዘፉ ናቸው ያሉት ሌ/ጀነራል ታደሰ፤ “ጉሬሮ በሚባልና የኢትዮጵያ ጦር በማሚያውቀው  ስፍራ ተተኳሽ መሳሪያ ቀብረን ነበር” ብለዋል። ከኤርትራ ጋርም ቀጣይ የማይቀሩ ጦርነቶች እንደሚኖሩ ነው የጠቆሙት ሌለ/ጀነራሉ።
ይህንኑ  በሕወኃት ኃይል የታወጀውን ጦርነት ተከትሎ የአማራ ክልል አስተዳደር ባወጣው መግለጫ ጠላት አርፎ የማይቀመጥ ከሆነ ለሚመጣው ትንኮሳ ምላሽ ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን አመልክቷል፡፡ የክልሉ የፀጥታ ምክር ቤት አሁናዊ የጠላቶች እንቅስቃሴ በመገምገም አቅጣጫ ማስቀመጡንና ክረምቱን መነሻ በማድረግ የጠላት እንቅስቃሴ  እንደሚኖር እና ይህንን ጥቃት ለመመከት በሁሉም ዘርፍ መዘጋጀት እንደሚገበ አቅጣጫ መቀመጡን የክልሉ መንግስት ኮሚኒኬሽን መግለጫ ያመለክታል፡፡
አሸባሪውና ወራሪው የህወሀት ሀይል ለጦርነት ሲዝትና ሲዘጋጅ  እንደኖረ በመግለጫቸው ያወሱት የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሀላፊ  አቶ ግዛቸው ሙሉነህ #የአማራ ህዝብ የሰው አይሻም የራሱንም አሳልፎ አይሰጥም; ብለዋል። አክለውም ለሰላም ቅድሚያ እንሰጣለን ከዚያ በላይ ለሚመጣ ጉዳይ ግን ክል ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ህውሃትን ጨምሮ ከየትኛውም ሰላም ፈላጊ አካል ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆናቸውን የገለጹ ሲሆን ከህውሃት ታጣቂ ሃይል ጋር ለመደራደር የሚያስችል  ኮሚቴ መቋቋሙን ገልጸው ነበር።
በዚህም መሰረት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን የሚመራና የፍትህና የደህንነት ሃላፊዎች የተካተቱበት ከህውሃት ጋር ለመደራደር የሚችል ኮሚቴ ተቋቁሟል።
ይህንኑ ተከትሎም የህውሃቱ ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ድርድሩን አስመልክቶ የህውሃት አቋምን ለማሳወቅ ለአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀ መንበርና የሴኔጋሉ ፕሬዚዳንት ማኪ ሳል፣ ለኬኒያው ፕሬዚዳንት እሁሩ ኬኒያታ፣ ለተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ፕሬዚዳንትና ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ደብዳቤ መጻፋቸው ይታወሳል። ሊቀመንበሩ ቡድኑ ሚስጢራዊ ድርድሮችን ለማድረግ ዝግጁ አለመሆኑንና በኬኒያ ፕሬዚዳንት አደራዳሪነት በናይሮቢ ሊደረግ ለታሰበው ድርድር ተደራዳሪዎች ወደ ስፍራው እንደሚልክ አስታውቀው ነበር።
በመንግስት በኩል ለተደራዳሪነት የተመረጠው ኮሚቴ በስፋት ስራውን በጀመረ ማግስት ህውሃት ለዳግም  ለጦርነት ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ይፋ በማድረግ፣ ቀጣዩ ጦርነት ከዚህ ቀደሙ በእጅጉ የተለየና የተጠናከረ እንደሚሆን አሳውቋል።
የሰሞኑን የታጣቂ ቡድኑን የጦርነት አዋጅ የሚያወግዙ የፖለቲካ ምሁራን፤ መግለጫው በተጀመረው የሰላም ድርድር ላይ ውሃ የሚቸልና ለሰላምና እርቅ ያለውን ተስፋ የሚያጨልም ነው ብለውታል።
የፖለቲካ ምሁሩ ዶ/ር ሰለሞን ተስፋዬ በሰጡት አስተያየት መንግስት ከህዝቡና ከተለያዩ ወገኖች የሚደርስበትን ከፍተኛ ጫና ተቋቁሞ ለሰላምና ለእርቅ የዘረጋውን እጅ በከፋ መከራና ጭንቅ ውስጥ ያለው የትግራይ ህዝብ ህይወት ያላሳሰበውና ሃላፊነት የማይሰማው የሽፍቶች ቡድን ረግጦት ለመሄድ እየሞከረ መሆኑ አሳሳቢ ነው” ብለዋል።
የትግራይ ክልል ህዝብ  መከራና ስቃይ መቋጨት የሚችልበት ዕድል ሲያገኝ ሊጠቀምበት ይገባል ያሉት ዶ/ር ሰለሞን፤ የክልሉ ህዝብ በታጣቂ ቡድኑ ሃሰተኛ ፕሮፓጋንዳ ሳይታለል ራሱን ከቀጣይ መከራና ችግር ማዳን የሚችልበትን መንገድ መታደግ አለበት ሲሉ መክረዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በሰላም ድርድሩ የሚሳተፈው በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት የሚከናወን ከሆነ ብቻ መሆኑን  ሲሆን ህውሃት በበኩሉ፤ በአፍሪካ ህብረት በኩል የሚደረገውን የሰላም ጥረት እንደማያምንበት በመጠቆም ድርድሩ የኬኒያው ፕሬዚዳንት እሁሩ ኬኒያታ እንዲመሩ እንደሚሻ አስታውቋል። ይህ ሁኔታም ቡድኑ ለሰላምና ለድርድር ፍላጎት የሌለው መሆኑን የሚያመለክት እንደሆነ ዶ/ር ሰለሞን ይገልጻሉ።
የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ከትናንት በስቲያ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ላይ  በትግራይ ክልል በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ህዝቦችን ለመታደግ መንግስት መጠነ ሰፊ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑንና የህውሃት ታጣቂ ቡድን ግን ለቀጣይ ጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል።
የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትሩ ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በመግለጫው ላይ እንደተናገሩት፤ መንግስት የክልሉ ህዝብ ለከፋ ረሃብና ችግር እንይዳጋለጥ፤ በተለያዩ መንገዶች ሰብአዊ እርዳታዎችን ለማድረስ ሙከራ ቢያደርግም፣ ታጣቂ ቡድኑ የተለያዩ እንቅፋቶችን እየፈጠረ ነው ሲሉ ወንጅለዋል። በብዙ ችግር የሚቀርበውን ሰብአዊ እርዳታም ታጣቂ ቡድኑ ልጆቻቸውን በግዳጅ ለጦርነቱ ለሚሰጡ ቤተሰቦች እርዳታ እየሰጠ ነው ሲሉ ወንጅለዋል። ከፌደራል መንግስቱ ወደ ክልሉ የሚገባው ነዳጅም ለታለመለት አላማ እየዋለ አይደለም ሲሉም ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
ህውሃት እኩይ አላማዋን ለማሳካት እርዳታ የጫኑ አውሮፕላኖች በትግራይ ክልል እንዳያርፉ መከልከሉንም ያወሱት ዶ/ር ለገሰ በቅርቡ። ከዚህ ቀደም ሲልም ሰብአዊ እርዳታዎችን ጭነው ወደ ክልሉ የገቡ ተሸከርካሪዎችም ተመልሰው አለመምጣታቸው መገለጹ ይታወሳል። ይህንኑ የህውሃት ታጣቂ ቡድን የዳግም ጦርነት ፍላጎት ቡድኑ ለሰላማዊ አማራጭ ፍላጎት እንደሌለው የሚያመለክት መሆኔን የቀድሞ የፊንላንድ ዲፕሎማት ለኢዜአ ገልጸዋል። ዲፕሎማቱ እንደተናገሩት የህውሃት ታጣቂ ቡድን ለሰላማዊ ውይይቱ እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚያነሳቸው ጉዳዮች ቡድኑ ቀድሞውንም ሰላማዊ መፍትሄ ፍላጎት እንደሌለው አመላካች መሆኑን ዲፕሎማቱ ሲሞ ፓርቪኒያኒ ተናግረዋል።

Read 13909 times