Saturday, 02 July 2022 17:24

የኑሮ ውድነት ስጋት ያጠለባት የነዳጅ ዋጋ ጭማሪበህትመት

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(3 votes)

          • ለነዳጅ ድጎማ በየወሩ 12 ቢሊዮን ብር ወጪ ይደረጋል
           • የነዳጅ ድጎማው አገሪቱን ለ132 ቢ. ብር የዕዳ ክምችት ዳርጓታል
           • ለ2015 በጀት ዓመት ለነዳጅ መግዣ 5.6 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋል ተብሏል
           • የአገሪቱ አጠቃላይ ዓመታዊ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ከ4 ቢሊዮን ዶላር አይበልጥም
           • መንግስት ለነዳጅ ድጎማው የሚያወጣውን ወጪ ለኑሮ ውድነቱ ማሻሻያ ሊያውለው ይገባል
             
                በመጪው አርብ ሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም ተግባራዊ መደረግ የሚጀምረው የነዳጅ  ድጎማ ማንሳት ተግባር ለኑሮ  ውድነቱ መባባስ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል። እርምጃው ወቅቱን ያላገናዘበ፣ በጥናት ያልተደገፈና ግብአታዊ እርምጃ ነው ሲሉ በተቃራኒው ደግሞ እርምጃው በአግባቡና በስርዓቱ እንዲመራ ከተደረገ ዘላቂ የኑሮ መሻሻልና ለውጥን ሊያመጣ ይችላል የሚሉ ወገኖችም አሉ፡፡ በቀጣዩ አርብ ተግባራዊ መደረግ  በሚጀምረው የድጎማ ማንሳት እርምጃ የሚታቀፉት የቤት መኪናዎችና አገር አቋራጭ ተሽከርካሪዎች እንደሆኑም ታውቋል፡፡
የነዳጅ ድጎማው ለሚመለከታቸው እንደ ባጃጅ ታክሲ፣ የህዝብ ትራንስፖርቶች፣ የከተማ አውቶቡሶችና መሳል ተሸከርካሪዎች በአዲሱ የመንግስት የድጎማ ስርዓት የሚታቀፉ ሲሆን ድጎማ ለማይመለከታቸው ተሽከርካሪዎች ግን መንግስት የድጎማውን 25 በመቶ የሚያነሳ መሆኑ ታውቋል፡፡
በመጪው መስከረም ወር 2015 ደግሞ የድጎማው 50 በመቶ  የሚያነሳ ሲሆን በታህሳስ ወር 2015 የድጎማው 75 በመቶ እንዲነሳ ተደርጎ በሚያዚያ ወር 2015 ዓ.ም ድጎማው ሙሉ በሙሉ እንዲነሳ ይደረጋል ተብሏል፡፡
ይህ አዲሱ የነዳጅ ድጎማ ስርዓት ተግባራዊ መደረግ ሲጀምር፣ በቋፍ ባለው የኑሮ ውድነት ላይ ተጨማሪ ጫና በመፍጠር ከፍተኛ ማህራዊ ቀውስ ያስከትላል የሚል ስጋት ያላቸው የምጣኔ ሃብት ምሁራን፤ ውሳኔው ጊዜውን ያላገናዘበ፣ ወቅቱን ያልጠበቀና ጥናት ያልተደረገበት ነው ሲሉ ይኮንኑታል፡፡
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶ/ር ይታገስ ሙሉቀን እንደሚናገሩት፤ መንግስት በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ከፍተኛ ድጎማ እያደረገ ወደ አገር ውስጥ የሚያስገባው ነዳጅ፣ ማደያ ሳይደርስ ጎረቤት አገር ሲቸበቸብ ማየቱ የተለመደ ጉዳይ ሆናል ከዚህ በተጨማም ለህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሠጡ ታክሲዎች የነዳጅ ፍጆታቸው እጅግ ከፍተኛ የሆነና የቅንጦት መኪኖች በድጎማ የመጣውን ነዳጅ እኩል ተሰልፈው የሚቀዱበት አሠራር መኖሩ እየታወቀ ምንም አይነት የማሻሻያ እርምጃ ሳይወሰድ መቆየቱ አስገራሚ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ድጎማው በባህርይው ለተወሰነ ጊዜ የሚደረግና  ለአጭር ጊዜ መፍትሔ የሚሰጥ ሆኖ ማሳካት የፈለገው ግብ በውል መለየት ያለበትና በየጊዜው መመርመርና መፈተሽ ያለበት ጉዳይ ነው እንዲህ ለረዥም ጊዜና ወጥ በሆነ መልኩ የሚያደረጉት ድጎማ ውሉን ያስታል። ድጎማው የሚደረግለትን ወገንም በአግባቡ መለየት ያስፈልገዋል። ታክሲና ሊሞዜን በእኩል የሚቀዱት ነዳጅ ሊኖር አይገባም-ብለዋል
ለነዳጅ ድጎማው ከፍተኛ ወጪ እንደሚወጣ የሚገልጹት ባለሙያው በቅርቡ በነዳጅና ኢነርጂ ባስልጣን የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ መንግስት ለነዳጅ ድጎማው በየወሩ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ያደርጋል፡፡ ድጎማው መንግስትን ባጠቃላይ ከ132 ቢሊዮን ብር ለሚበልጥ የዕዳ ክምችት ዳርጎታል ብለዋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ለ2015 ዓ.ም ለነዳጅ መግዣ 5.6 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው ሰሞኑን ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡
በአገሪቱ ለነዳጅ ግዥ ይህን ያህል መጠን ያለው ገንዘብ ወጪ ሲያስፈልግ  የመጀመሪያው ሲሆን ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ የነዳጅ ዋጋ መናርና የመርከብ ማጓጓዣ ዋጋ ንረት ያስከተለው ጭማሪ ነው ተብሏል፡፡ በኪቪድ 19 ወረርሽ ወቅት በከፍተኛ መጠን ቅናሽ አሳይቶ የነበረው ዓለማቀፍ የነዳጅ ዋጋ የወረርሺኙን መቀነስ ተከትሎ አየጨመረ የሄደ ሲሆን በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ማግስት በበርሜል በ140 ዶላር  በላይ እየሆነ መጥቷል፡፡   ዓለም አቀፉ የነዳጅ ዋጋ ንረት ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መሄዱና አገሪቱ ያጋጠማት የውጭ ምንዛሬ እጥረት ችግሩን እያባባሰው እንደመጣ የሚገልጹት የምጣኔ ሃብት ከማንሳቱ በፊት ሊያከናውናቸው የሚገቡ ተግባራትን ሳያከናውን ወደ ድጎማ ማንሰቃት መሄዱ የኑሮ ውድነቱ በማናር ከባድ ማህበራዊ ቀውስ እንደሚስከትል ይገልጻሉ፡፡
ያልተሰሩ የመንግስት የቤት ስራዎች በሚል የምጣኔ ሃብት ባለሙያው የሚያስቀምጧቸው ተግባራት ምስቅልቅሉ የወጣውን ኢኮኖሚ ማስተካል የአገር ውሰጥ ምርቶችን ማሳደግና የህዝብን የመግዛት አቅም መጨመርን መሆኑን ይጠቅሳሉ። አሁን አገሪቱ የምትገኝበት  ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና፣ ፖለቲካዊ ምስቅልቅሎሽ ባልተስተካከለበት ሁኔታ የነዳጅ ድጎማውን ማንሳት ሃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው ሲሉም ይገልጻሉ፡፡
በጦርነት፣ በግጭትና በኮቪድ ወረርሽኝ የቆሰለ ኢኮኖሚ፣ የሸማቹን የመግዛት አቅም አድቅቆታል፡፡ የሰው ገቢ ሳንቲም ባልጨመረበትና ጭራሽ እንደቀነሰ በሄደበት ሁኔታ ወጪውን ማናሩ፣ የወጪኛ ገቢ ልዩነቱን በማስፋት የከፋ ችግር ማስከተሉን አይቀሬ ነው ይላሉ- ባለሙያዎቹ፡፡
በውድ የውጭ ምንዛሬ የሚደጎመው ነደዳጅ እያከበረ ያለው ህገ-ወጥ ነጋዴዎችን ነው የሚሉት ሌላው የምጣኔ ሃብት ባለሙያ አቶ መስፍን በቀለ የድጎማ ስርዓቱን 70 በመቶ የሚሆነውን ድሃና 30 በመቶ የሚደርሰውን ሃብታም ነው ሲደጉም የኖረው፤ ይህ ደግሞ ከድጎማ ፅንሰ ሃሳብ ጋር የሚጣረስና ትክክለኛ ግቡን የሳተ ጉዳይ ነው ሲሉ ይተቻሉ፡፡
የነዳጅ ዋጋ በአለም አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መሆኑን የሚገልጹት አቶ መስፍን በዚህ ሁኔታ እየደጎሙ መቀጠሉን የማይቻል በመሆኑ የዓለም ዋጋን ያንጸባረቀ ዋጋን ከህዝብ ጋር ለመጋራት መታሰቡ ተገቢ ነው፤የሚል እምነት አለኝ ብለዋል፡፡
ነዳጅ ኢትየጵያ ውስጥ የሚሸጥበት ዋጋ አገሪቱን ነዳጅ አምራች አስመስሏል ያሉት ባለሙያው፤ ይህም መንግስት ለነዳጅ ድጎማው በሚያወጣው ከፍተኛ ወጪ እየተሸፈነ መሆኑንና አሁን ባለው ኢኮኖሚ ዳግም በዛ መንገድ መቀጠሉ የማይቻል መሆኑን ይገልፃል፡፡ ስለዚህም የነዳጅ ድጎማ የማንሳቱ ውሳኔ ተገቢ ነው ይላሉ፡፡ የኑሮ ውድነቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበትና የህዝቡ የመግዛት አቅም ፈተና ላይ በወደቀቤት በዚህ ጊዜ የነዳጅ ድጎማውን የማንሳቱ እርምጃ ችግሩን አያባብሰውም ወይ? ለሚለው ጥያቄያችን ሲመልሱ፤ እኔ ከድጎማው መነሳት ይልቅ የተነሳው ገንዘብ የሚውልበት ቦታ ያሳስበኛል፡፡ ከድጎማው የሚነሳው እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ ነው፡፡ ይህ ገንዘብ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የህዝቡን ገቢ ማሻሻል፤ ህዝቡ መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያገኝባቸውን ሁኔታዎች ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ ይህንን በአግባቡና በስርዓት ለመምራት የሚያስችል አሠራር መዘርጋት አለበት፡፡
ይህ በአግባቡ ተግባራዊ ከተደረገ ጭማሪው ለኑሮ ውድነቱ መባባስ የሚኖረው አስተዋጽኦ እምብዛም የጎላ አይሆንም ብለዋል፡፡

Read 13515 times