Saturday, 02 July 2022 17:37

የስነ ተዋልዶ ጤና በግጭት አካባቢ

Written by  ሀይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

  “ጀርባዬን መቶኝ መሬት ላይ ከጣለኝ በኋላ ነው ጥቃቱን የፈጸመብኝ’’
በጦርነቱ ሳቢያ ጾታዊ ጥቃት ከደረሰባት አንዲት እናት ንግግር ላይ የተወሰደ
የሰው ልጅ በዚህ ምድር ላይ ሲኖር ከውልደት ጀምሮ አስከ ሞት ደስታ እና ሃዘን፤ ረሀብ እና ጥጋብ፤ መውደቅ አና መነሳት፤ መውጣት እና መውረድ እየተፈራረቀ እለት ከእለት የሚያሳልፈው እውነታ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። ታዲያ በዚህ ውጣ ውረድ ውስጥ “አንኳን ሰው እግር እና እግር ይጋጫል” አንደሚባለው ሀሳብን መነሻ ባደረጉ ልዩነቶች አለመግባባቶች ይፈጠራሉ። ብሎም ወደ አካላዊ የሀይል ሚዛን ማሳያ ገዝፈው አውዳሚ ወደ ሆነ ግጭቶች ሲያመሩ ይስተዋላል።
በዚህም ግጭት ክቡር አና ከማይተካው የሰው ልጅን ህይወት ከማጥፋት ጀምሮ የሰው ልጅ መጠቀሚያ የሆኑ ቁሳቁሶችን ማውደም እና በሰዎች ላይ ከባድ ጠባሳ አሳርፎ ማለፍ የግጭቶች መገለጫ ውስጥ የሚመደብ ነው። እንደዚህ አይነት ክስተቶች በሚፈጠሩበት ቦታ ሴቶችና ህጻ ናት ይበልጡኑ ተጎጂ እንደሚሆኑ እሙን ነው፡፡ የስነ ተዋልዶ ጤናን በሚመለከትም በግጭት አካባቢዎች አገልግሎቱን መስጠትም ሆነ አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ማቅረብ እንደማይቻል በአለም አቀፍ ደረጃ የተረጋገጠ ነው፡፡  
በአማራ ክልል፤ በአፋር፤ በትግራይ ባጠቃይም በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭትን ተከትሎ በተፈጠረ የስነተዋልዶ ጤና ችግር ላይ ትኩረት በማድረግ የሚሰራው የኢትዮጵያ የጽንስ እና የማ ህጸን ሀኪሞች ማህበር ከዚህ ቀደም በአማራ እና በአፋር ክልል በጦርነቱ ምክንያት ለተ ጎዱ አከባቢዎች ጾታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ሰዎች እና ለህክምና ተቋማት የሚሆን ወደ 3.5 ሚሊዮን ብር የፈጀ የቁሳቁስ ድጋፍ አበርክቷል።
እንዲሁም ከቁሳቁስ ድጋፍ ባለፈ በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ ጾታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው አካላት የህክምና አገልግሎት ለሚሰጡ ባለሙያዎች ሙያዊ ስልጠና የሰጠ ሲሆን በተመሳሳይ ከአማራ እና አፋር ክልል ለተውጣጡ ባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት ድጋፉን አጠናክሮ ቀጥሏል።
ከግንቦት 29 እስከ ሰኔ 3 ለ5 ቀናት በደሴ ከተማ በቆየው በዚህ ስልጠና ላይ ከአማራ እና አፋር ክልል ተውጣተው ለተሳተፉት ባለሙያዎች ጥያቄ አቀረብንላቸው። ጥያቄውም “ግጭቱ በነበረበት ወቅት የነበረው ጾታዊ ጥቃት እና የስነተዋልዶ ጤና ምን ይመስል ነበር” የሚል ነው።
በአፋር ክልል ዱብቲ ሆስፒታል የቀዶጥገና ባለሙያ አቶ ኑሩ ሰኢድ በሆስፒታሉ አቅራቢያ ግጭት ከነበረባቸው ስፍራዎች ይህን ቃለመጠይቅ እስከሰጡን ጊዜ ድረስ ተጠቂዎች ወደ ሆስፒታሉ እየሄዱ አንደሚገኙ ነው የተናገሩት።
ባለሙያው አክለውም እነዚህ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ወደ ህክምና ተቋም ለመሄድ የመንገድ መዘጋት ስላጋጠማቸው ተገቢውን ህክምና ሳያገኙ ላልተፈለገ እርግዝና ተጋልጠዋል ብለዋል። ስለሆነም ተቋሙ አስከ 6ወር የደረሱ ነፍሰጡችን ጽንስ የመቋረጥ ችግር ገጥሞአ ቸዋል፡፡
በወልዲያ ሆስፒታል ጠቅላላ ሀኪም የሆኑት ዶክተር ተስፋዬ አለሙ አንደሚናገሩት በአከባቢው ጦርነት በሰፈነበት ወቅት እሳቸውን ጨምሮ አብዛኛው የህክምና ባለሙያ ለህይወቱ በመስጋት ከአከባቢው ሸሽቶ ነበር። በሆስፒታሉም በ2 ዶክተሮች እና ቁጥራቸው አነስተኛ በሆነ ሌሎች የህክምና ባለሙያዎች ብቻ ነበር የተወሰኑ አገልግሎቶች ሲሰጥ የቆየው።
ዶክተር ተስፋዬ ጦርነቱ ከተገባደደ እና መረጋጋት ከሰፈነ በኋላ ወደ ስራ ገበታቸው ሲመለሱ በጦርነቱ መሀል የቀዶ ጥገና ህክምና የሚያስፈልጋቸው ነፍሰጡሮች አንዲሁም በቋሚነት መድሃኒት የሚወስዱ ሰዎች በህክምና ቁሳቁስ እና የመድሃኒት አጥረት ሳቢያ ህይወታቸው ማለፉን ገልጸዋል፡፡   
በተመሳሳይ በጦርነቱ ወቅት ከስራ ገበታቸው ርቀው አንደነበር የነገሩን ወደ ደሴ ኮምፕሪሄን ሲቭ ሆስፒታል ጎራ ስንል በስራ ላይ ያገኘናቸው የሆስፒታሉ የጋራ ምላሽ መስጫ (One stop center) ሀላፊ ሲስተር መዲና ወርቅነህ ናቸው። ሲስተር መዲና እንደገለጹት ሆስፒታሉ ወደ አገል ግሎት ከተመለሰበት ጊዜ አንስቶ አስከያዝነው ሰኔ ወር በግጭቱ ወቅት ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ተጠቂዎች ለህክምና በመቅረብ ላይ ይገኛሉ።
ሲስተር መዲና የሆስፒታሉ ዋን ስቶፕ ሴንተር የምስራቅ አማራ ክልል አጠቃላይ ህክምና የሚሰጥበት መሆኑን ገልጸው 5መቶ ሴቶች እና 12 ወንዶች ጾታዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል ብለዋል። እነዚህ ተጠቂዎች ከባሎቻቸው ጋር ፍቺ መፈጸምን ጨምሮ በህብረተሰቡ ዘንድ መገለል እና ስነልቦናን የሚነካ ንግግር ይሰነዘርባቸዋል። በተለይ ወንዶቹ ተጠቂዎች ከችግሩ ለማገገም አስቸጋሪ እንደሆነባቸው ነው የሚናገሩት።
ስለሆነም የሚደርስባቸውን የስነልቡና ቀውስ ለመቋቋም በመቸገራቸው የተነሳ ቁጥራቸው ያልታወቀ ተጠቂዎች ወደ ህክምና ተቋማት ሳይሄዱ ተሸሽገው የተቀመጡ መኖራቸውን ሲስትር መዲና ጠቁመዋል። ለዚህም ማሳያ ያደረጉት ከወራት በኋላ ወደ ሆስፒታሉ እየመጡ የሚገኙትን ተጠቂዎች ነው።      
በደሴ ኮምፕሪሄንሲቭ ሆስፒታል ስሟ አንዲጠቀስ ያልፈለገች እድሜዋ ወደ 40ዎቹ መጀመሪያ የምትገመት እናት በህክምና ላይ ትገኛለች። ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ ዘግይተው ከመጡ ታካሚ ዎች ውስጥ የምትመደብ ሲሆን ቃለመጠይቁን ስታደርግ ሁለተኛ የህክምና ቀኗ ላይ ነበረች።። በላሊበላ አከባቢ በሚገኝ ገጠራማ ስፍራ አንደምትኖር የተናገርችው ይቺ እናት ባለትዳር እና የልጆች እናት ናት።
ከ7 ወራት በፊት የሰሜኑ ግጭት ወደዚች ሴት መኖሪያ አከባቢ ሲቃረብ የመንደሩ ሰው በሙሉ ጦርነቱን ፍራቻ ለቆ መሄድ ይጀመራል። አሷም አንደመንደሯ ሰው ከቤተሰቧ ጋር ደህንነት እናገኛለን ካሉበት ስፍራ ይደበቃሉ።ለ5 ቀናት ህይወትን ለማትረፍ ከጦርነት ሽሽት በሚደረግ ድብብቆሽ አለፈ። በዚህ የድብብቆሽ ሂደት ውስጥ ቦታ ያልተሰጣቸው ነገር ግን የሚርባቸው እና የሚጠማቸው ከብቶች በበረት ውስጥ መታጎራቸውን አስታወሰች። ባለቤቷ በሽታ ስላለበት እና ልጆቿም ስላልጠነከሩ የችግሩ መፍትሄ በእርሷ ላይ እንደወደቀ ተሰማት። ስለሆነም ለማንም ሳትናገር በረሀብ እና ጥም ለተኮማተሩት የቤት አንስሳት ለመድረስ ወሰነች።
ታዲያ ይቺ ሴት ለቀናት ፈርታ የተደበቀችበት ጉዳይ ከሀሳብነት አልፎ ነፍስ ዘርቶ መጣ። በረቱ ደጃፍ ላይ እንደቆመች አንዳች ነገር ጀርባዋ ላይ በሀይል ሲያርፍ ተሰማት። መሬት ላይ በጀርባዋ ወደቀች። በዚህ ቅጽበት ነው ከባሏ እና ከልጆቿ ብሎም ከእንስሳቶቿ መጎዳት እኔ ልቅደም ያለችው ሴት አስገድዶ መደፈር የተፈጸመባት።  
“ጀርባዬን መቶኝ መሬት ላይ ከጣለኝ በኋላ ነው ጥቃቱን የፈጸመብኝ” በማለት የምትናገረው ይቺ እናት ከ7 ወራት በኋላ ወደ ህክምና ተቋም የሄደችው ከማህጸኗ በሚፈሰው ፈሳሽ ምክንያትነት ነው። ይህም ወደ ካንሰር እንዳይለወጥ የሚል ስጋት ስላሳደረባት ለህምናው ቀርባለች።
ይሁን አንጂ ህክምና ለማግኘት ወደ ሆስፒታል አንድትሄድ የገፋፋቻት ጓደኛዋ ነበረች። እሷም የጓደኛዋን ምክር በመውሰድ ለሌሎች በቤታቸው ተቀምጠው ህክምና ላላገኙ ተጠቂዎች በወቅቱ ህክምና አንዲያገኙ በማለት ምክር እና መልእክት አስተላልፋለች።
ወሲባዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሰዎች አካላዊ እና ስነልቦናዊ ህክምና ይደረግላቸዋል። ይችም ሴት ይህ ህክምና እየተሰጣት ሲሆን ጤንነቷም ተረጋግጦላታል።
በዚህ ጽሑፍ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ጾታዊ ጥቃት የድረሰባቸው ሰዎች ያሉበትን ሁኔታ እና በህክምና ባለሙያዎች እየተሰጣቸው ያለውን ሙያዊ ድጋፍ ቃኝተናል። ጥቃቱ በስነልቦና ላይ የሚያሳድረው ጥቃት ረዘም ላለ ጊዜ በተጠቂው እና አለፍ ሲልም በማህበረሰብ ላይ ሊቆይ የሚችል ነው። ስለሆነም በስነልቦና ላይ ስለሚያሳድረው ተጽእኖ እና እንደ እያንዳንዱ ሰው ሊወሰድ ስለሚገባው የመፍትሄ ሀሳብ እንዲሁም ተግባር በቀጣይ ሳምንት እንድታነቡ ለህት መት እንለዋለን፡፡


Read 12454 times