Saturday, 02 July 2022 17:41

ይድረስ ለጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ፡-

Written by  አያሌው አስረስ
Rate this item
(0 votes)

  “ትሕነግ ሌላ ጥፋትና ውድመት እንዲፈጽም ሊፈቀድለት አይገባም!”
                    
            አሸባሪው የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ድርጅት (ትህነግ)፤ የትግራይ ክልልን ከኢትዮጵያ ገንጥሎ፣ ትግራይ የምትባል ነፃ አገር ለመመስረት ፍላጎትም ሆነ ዓላማ ያለው ድርጅት ነው ብሎ ለማመን ይከብዳል።
ዓላማው ትግራይን አገር አድርጎ ማቆም ቢሆን ኖሮ፣ ደርግ ትግራይን ለቆ እንደወጣ ነጻነቱን ማወጅና ከኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ከሌሎች መንግሥታት እውቅና መጠየቅ ይችል ነበር፤ ቡድኑ ግን ይህን አላደረገም።
የትሕነግን ፍላጎት ተከትሎ የተረቀቀውና  የፀደቀው የኢፌዲሪ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 39፣ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች የራሳቸውን እድል በራሳቸው የመወሰን መብት እስከ መገንጠል ድረስ የሚያጎናፅፍ መሆኑ የታወቀ ነው። በትግራይ ክልል ውስጥ ከትግሬ ብሔረሰብ ሌላ እንደ ኢሮብና ብሌን ያሉ ብሔረሰቦች ቢኖሩም፣ ሁሉንም ጠቅልሎ እንደ አንድ የትግራይ ብሔር አድርጎ የሚያስበው ትህነግ፤ ትግራይን ከኢትዮጵያ ገንጥሎ  ነፃ አገር መፍጠር ቢፈልግ ኖሮ፣ ሁሉ በእጁ ሁሉ በደጁ በነበረበትና የኢትዮጵያን መንግሥታዊ ሥልጣንን እንደ ፈለገ በሚዘወርበት ዘመኑ፣ የክልሉ ምክር ቤት የመገንጠሉን ጥያቄ እንዲደግፍ፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሳኔውን  እንዲያስፈጽምና ህዝቡ ደግሞ የትግራይን ነጻነት ደግፎ ድምጽ እንዲሰጥ  በማድረግ  ነፃ ትግራይን በመሰረተ ነበር።
መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም አድርጎ ሰኔ 22 ቀን 2013 ዓ.ም የመከላከያ ሰራዊቱን ከትግራይ  ክልል ባወጣ ጊዜ፣ “ከእንግዲህ በኢትዮጵያ መንግሥት ስር መተዳደርም ሆነ በኢትዮጵያዊነት መጠራት አልፈልግም” ብሎ “ ነጻ አገር” ማወጅ ይችልም  ነበር።
ቡድኑ ሁሉንም ያላደረገው ዋና ፍላጎቱና ዓላማው ኢትዮጵያን ማዳከም፣ በደካማዋ ኢትዮጵያና መንግሥት ጀርባ ታዝሎም፣ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ጥቅሙን ማስጠበቅ በመሆኑ ብቻ ነው።
ትህነግ ከሰሞኑ ደግሞ ዝግጅት ሲያደርግበት የቆየውን ዳግም ጦርነት በይፋ አውጇል። ሌተናል ጄነራል  ታደሰ ወረደም ጦርነቱ አይቀሩ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡ ለጦርነቱም ከመቼውም ጊዜ የላቀ ዝግጅት መደረጉን በይፋ ተናግረዋል፡፡
 ትሕነግ ዝም ከተባለ  ዳግም ጦርነቱን የሚከፍተው እንደለመደው በአማራና አፋር ክልልና ሕዝብ ላይ መሆኑ ግልጽ ነው። ሁለቱ ክልሎች ደግሞ ከዚህ ቀደም በነበረው የትህነግ ወረራ ከፍተኛ ውድመት ደርሶባቸዋል። በአፋር ክልል 75 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር የሚገመት ውድመት ደርሷል። 750  ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ፈርሰው የማስተማር ስራቸውን ለማቋረጥ ተገድደዋል። 150 ሺህ የሚደርሱ ተማሪዎችም ከትምህርት ገበታ መራቃቸው  ተነግሯል፡፡
ከስድስቱ  የአፋር ዞኖች አራቱ በትህነግ ወራሪ ሰራዊት ክፉኛ የወደሙ ሲሆን፤ ከ300 ሺ በላይ ሕዝብም ከመኖሪያው  ተፈናቅሏል።
የአማራ ክልላዊ መንግስት፣ ጦርነቱ ከመቆሙ ጥቂት ቀደም ብሎ ባወጣው መግለጫ፣ ጦርነቱ 280 ቢሊዮን ብር የሚገመት ውድመት ማድረሱን አስታውቋል። 1,217 ሴቶች መደፈራቸው፣ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአሸባሪው ትህነግ መገደላቸው እንዲሁም ከየአካባቢው አፍኖ የወሰዳቸው ሰዎች መጨረሻቸው አለመታወቁም መገለጹ አይዘነጋም።
በአማራ ክልል በአስር ዞኖች ውስጥ የሚገኙ 150 ወረዳዎችና 78 ከተሞች፣ በአፋር ክልል ደግሞ አራት ዞኖችና በርካታ ከተሞች በአሸባሪው ትህነግ ወረራ ክፉኛ ወድመዋል። ትህነግ  አሁንም የዛተውን ጦርነት  የሚከፍተው ያለጥርጥር በእነዚህ አካባቢዎች ላይ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡
ያለፈው ጦርነት፣ ዝርፊያና ውድመት ወትሮም ደካማ የነበረውን የአካባቢውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ጭራሽኑ አሽመድምዶት፣ አስርና አስራ አምስት ዓመታት ወደ ኋላ መልሶታል፡፡ ክልሎቹ ከጦርነቱ ውድመትና ጥፋት ገና በቅጡ ማገገም እንኳን አልጀመሩም፡፡
በዚህ ሁኔታ አሸባሪው ትህነግ የዳግም ወረራ እድል ካገኘ፣ በክልሎቹ ላይ ለመናገር የሚከብድ የከፋ ውድመት እንደሚደርስ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡
የተከበሩ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሆይ፤ይህ በእጅጉ ያስፈራኛል፤ ያሳስበኛልም። የምንገጥመው በዓለም አቀፍ የጦርነት ህግ ከማይመራ፣ እጅግ ጨካኝና አረመኔ ከሆነ  አማጺ ኃይል ጋር በመሆኑ መፍራት ተገቢ ነው፤መፍትሄ ግን አይደለም፡፡ በተለይ ወረራውን ከመፈጸሙ በፊት የማያዳግም እርምጃ ካልተወሰደበት ከበፊቱም የከፋ ጥፋት ከማድረስ ወደ ኋላ እንደማይል ይታወቃል፡፡  
አሸባሪው ትህነግ ወደ ጦርነቱ የገባው ከሁለት እስከ ሶስት ሚሊየን የሚደርሱ የትግራይ ወጣቶችን ህይወት ለመገበር ቆርጦ ወስኖ እንደሆነ በተግባር እያየን ነው፡፡ ለዚህም ነው 300 ሺህ  የትግራይ ወጣቶች በጦርነቱ ማለቃቸውን ለትግራይ ህዝብ ባረዳ ማግስት፣ ለአዲስ ጦርነት ዝግጁ መሆኑን ይፋ ያደረገው፡፡  
ቀደም ሲል እንደገለፅኩት፤ የትሕነግ  ዓላማ፣ ትግራይን መገንጠል ሳይሆን፣ እንዳሻው የሚዘውራትን ደካማ የፈራረሰች ኢትዮጵያን መፍጠር ነው። አሸባሪው ትህነግ የአማራና የአፋር አዋሳኝ አካባቢዎችን በድጋሚ የመውረር እድል ካገኘ አካባቢዎቹ ላይ የከፋ ውድመትና ዕልቂት ማድረሱ እርግጥ ነው። ለዚህ ደግሞ ዛቻውና ፉከራው ምስክር ናቸው፡፡ እናም አሸባሪው ሃይል እንደዛተውና እንዳቀደው በዜጎቻችን ላይ ጥቃት እንዲፈጽም  ጨርሶ መፈቀድ የለበትም፡፡
መንግስት “አሸባሪው ትህነግ ትንኮሳ እየፈጸመ ነው” የሚለውን መግለጫውን ትቶ፣ አሸባሪው ቡድን፣ በጫረው እሳት ራሱ እንዲለበለብ ማድረግ አለበት። ባለፈው ወረራ ትህነግ እስከ ደብረሲና ድረስ ያለከልካይ መዝለቅ በመቻሉ በአማራ ክልል ላይ ያደረሰውን ከፍተኛ ውድመት አይተናል፡፡
አሁን የሰላም ድርድር እያሉ አሸባሪውን ሃይል ለማባባል ወይም ለማስታመም መሞከር፣ ከዚህ ቀደም ከፈጸመው ጥፋት የከፋ ጥፋት እንዲፈጽም ጊዜና እድል መስጠት እንደሚሆን ክቡር የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ  ያጡታል ብዬ አልገምትም። ስጋቴንና ፍርሃቴን ለመግለፅ ያህል ነው፡፡  መከላከያው ከሕዝብ ጋር ሆኖ  አሸባሪውን ትሕነግ፣ ከራሱ ክልል እንዳይወጣ ሲያደርግ ብቻ ነው፣ የአማራና የአፋር ህዝቦች የሰላም እንቅልፍ መተኛት የሚችሉት፡፡ ያኔ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ህዝብም  በየእለቱ መርዶ ከመስማት ይገላገላል፡፡
ክቡር ጠ/ሚኒስትር፤ የአገሪቱ የጦር ሃይል አዛዥ እንደመሆንዎ፣ ባለዎት ሥልጣንና አቅም ሁሉ ተጠቅመው ህዝባችንን ከአሸባሪው ሃይል ዳግም ወረራና ስቃይ ይታደጉት ዘንድ እማጸንዎታለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ አሸባሪው ሃይል ወደ ሰላምና ድርድር ይመጣል ብሎ ማሰብ አንድም  የዋህነት፣ አሊያም ራስን ፈቅዶ ማሞኘት ነው የሚሆነው፡፡
የኤርትራ አንድነትና አንድ አገርነት በተነሳ ቁጥር፣ ኤርትራዊያን፤ “አፄ ምኒልክ ለጣሊያን አሳልፈው ሰጥተውናል” የሚል ክስ ደጋግመው ሲያነሱ ይደመጣል፡፡ በትህነግ በሃይል የተያዘው ትግራዋይም በእርስዎ ላይ ተመሳሳይ ክስ እንዳያቀርብ፣ ህዝቡንና ክልሉን ከአሸባሪው ሃይል ነጻ የማውጣት መንግስታዊ ሃላፊነትና ግዴታ አለብዎ ብዬ አምናለሁ፡፡ የሚቀድመው ግን ጥላቻና ጦር ወድሮ ወደ አማራና አፋር ክልሎች ለመገስገስ ያለመውንና ያቆበቆበውን አሸባሪ ሃይል በአጭር ማክሸፍ ነው፡፡ ጽሁፌን የምቋጨው በአደራ ነው!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!!


Read 2237 times