በሌላ በኩል በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከተሾሙ ከ20 ቀናት በላይ ያስቆጠሩት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እስካሁን ቤተመንግስት አለመግባታቸው ተገቢ አይደለም ተባለ፡፡ የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር ባለቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን የጠ/ሚኒስትር መለስን የ80ኛ ቀን ተዝካር ሳያወጡ ቤተመንግስቱን ለመልቀቅ አለመፍቀዳቸውን የጠቀሱ ምንጮች ጉዳዩ ትክክል አይደለም ሲሉ ተችተዋል፡፡ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ብስራተ ገብርኤል አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው እየተመላለሱ አገሪቱን ማስተዳደራቸው ለአገሪቷም ክብር ጭምር ተገቢ እንዳልሆነ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡ ወ/ሮ አዜብ ቤተመንግሥቱን ማስረከባቸው ላይቀር ውዝግብ ማስነሳቱ ተገቢ አይደለም የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች፤ አገሪቱን የሚያስተዳድሩት አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር በውጭ ሆነው እሳቸው ከውስጥ መቀመጣቸው ሌላ ትርጉም ያሰጠዋል ብለዋል፡፡