Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Print this page
Saturday, 13 October 2012 10:54

ኢህአዴግ ምን ይላል?

Written by 
Rate this item
(6 votes)
ኢህአዴግ ተስፋ ከሚያስቆርጥ ንግግሩ በስተቀር ልማቱን ያለማቋረጡ ደስ ብሎኛል፡፡ አንዳንዱ ተቃዋሚ ለራሱ ከርስ የሚታገል ስለሆነ እርሱ ፎቅ ካልሰራ፣ ዙፋን ላይ ካልተፈናጠጠ፣ ልማት የለም ብሎ ያማርራል፡፡ መንገድ ይሰራ ጥሩ ነው፤ የሃገር መልክ ነው፡፡ ለኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ነው፡፡ መብራት ሃይል ይጨምር፤ ሃብት ነው፡፡

ክዋክብት በነጠፉበት ሰማይ እንኳ የንጋት ተስፋ ሊፈነጥቅ ይችላል ይላል ማርቲን ሉተር ኪንግ በአንድ መጽሃፉ ከብሩህ ሰማይ ብቻ አይደለም ወጋገን የሚታየው ይህንን ሃሳብ እንዳነሳ ያደረገኝ የሃገራችን መሪዎች ሁኔታ ነው፡፡ በተለይ ኢህአዴግ ምን እንደነካው፣ ዓይኑን ምን እንደጋረደው ግራ ግብት ብሎኛል፡፡ የምን አዚም እንደወደቀባቸው ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ለመሆኑ ኢህአዴግ ውስጥ ሰው የለም እንዴ?…ኧረ ሞልቷል፡፡ እና አፋቸውን ምን ያዘው? አይታወቅም፡፡ ከመካከላቸው እስከዛሬ ለተሰራው ነገር አስተዋጽዖ ያደረገ ሰው የለም?… እስካሁን አልነገሩንም፡፡ በተለይ መለስ ከሞቱ በኋላ፡፡ ድሮ ድሮ ከግለሰቦች ሚና ይልቅ የፓርቲው ሚና እንደሚልቅ ይነግሩን ነበር፡፡ አሁን ግን ሁሉን ነገር ያደረጉት መለስ ብቻ ናቸው እያሉ ጧት-ማታ በየሄዱበት ያወራሉ፡፡

እኛ ደግሞ እነዚህ ሰዎች ምን ሲሰሩ ኖሩ እያልን እንጠይቃለን፡፡ …መንገዱን መለስ፣ባቡሩን መለስ፣ እርሻውን መለስ፣ኢንዱስትሪውን መለስ፣ሌሎቹስ?…ኧረ በፈጠራችሁ! ... ጠቅላይ ሚኒስትሩም ስለራሳቸው ትተው ስለ መለስ ያወራሉ፡፡ መለስ ጥሩ ሰርተዋል ማለት ጥሩ ነው፤ እናንተስ? አሁን የሚመሩን መለስ ናቸው እናንተ? ምነው ኢህአዴጎች አረጃችሁ ልበል?መለስ ጠንካራ መሪ ነበሩ፤ግን በቃ ፈጸሙ፡፡ ታሪክ ይዘክራቸው፡፡ አሁን ተራው የተረኛው ነው፡፡ የዚያኛውን እንዳየነው ሁሉ የዚህኛውንም ማየት እንፈልጋለን፡፡ እንዴት ሃገር በህይወት ያለ መሪውን ትቶ ጧት-ማታ በህይወት ስለሌሉ ሰው ያወራል? ሙሴ ስለሞተ ኢያሱ እያለቀሰ አይቆምም፤ መንገዱን ይቀጥላል፡፡ ትልቁ ጉዳይ የጀመሩትን ዓላማ መፈጸም ነው፡፡ታዲያ አሁን የኛ መንግስት ፋይዳ የሌለው አድናቆት ምን የሚሉት ነው? አቶ ሃይለማሪያምስ እስከ መቼ ራሳቸውን ትተው መለስን እንደ ክርስቶስ ይሰብኩልናል? … ከዚያ ይልቅ የተሰጣቸውን አደራ ቢወጡ አይሻልም? እኔ በግሌ ቀደም ሲል ስለ አሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ባሕርይ በሚገባ የሰማሁት ወሬ አለ፡፡ ስልጣን ከያዙ በኋላ ቢሆን ማጋነን ነው! እል ነበር፡፡ ግን ከዚያ በፊት ደጋግሞ ኢንተርቪው ያደረጋቸው ጋዜጠኛ አንገቱን እየነቀነቀ በጣም፣ እንዲያውም እጅግ በጣም ጥሩ ሰው እንደሆኑ ነግሮኛል፡፡ አንዳችም የባለስልጣንነት ኩራት የለባቸውም፡፡ … ይኸው በቀደምም ገና ሲጀምሩ ህዝብን በማድነቅ አውርተዋል፡፡ አቶ ሃይለማርያም ይልመድብዎ! ህዝብ ያከበሩትን ያከብራል፡፡ተቃዋሚዎችም ለሃገራዊ ጥቅም በሚመች ሁኔታ ብትታገሉ የተሻለ ውጤት ማምጣት የምትችሉ ይመስለኛል፡፡ በመረረ ጥላቻ የተሞላ ትግል የትም አያደርስም፡፡ የፖለቲካ ልዩነትን ከጠላትነት ለይቶ ማየት የሚቻል ይመስለኛል፡፡ እንደ ማህተመ ጋንዲ አይነት ፍቅር ሊኖረን አይቻልም ትላላችሁ? እንደ ሉተር ኪንግ አይነት ትዕግስት መፍጠር አንችልም? መንግስትስ የተሻሉ ፓርቲዎች እንዲቋቋሙ የራሱን ሚና መጫወት አይገባውም? የጎሪጥ መተያየት የሌለበት እንኳ ባይሆን ለአንድ ሃገር የሚሰራ ልብ መፍጠር አይቻልም?ኢህአዴግ ተስፋ ከሚያስቆርጥ ንግግሩ በስተቀር ልማቱን ያለማቋረጡ ደስ ብሎኛል፡፡ አንዳንዱ ተቃዋሚ ለራሱ ከርስ የሚታገል ስለሆነ እርሱ ፎቅ ካልሰራ፣ ዙፋን ላይ ካልተፈናጠጠ፣ ልማት የለም ብሎ ያማርራል፡፡ መንገድ ይሰራ ጥሩ ነው፤ የሃገር መልክ ነው፡፡ ለኢኮኖሚ እድገት ወሳኝ ነው፡፡ መብራት ሃይል ይጨምር፤ ሃብት ነው፡፡የአንዳንዶቻችን ዝንባሌ የራሳችን ስልጣን ብቻ ነው፡፡ እውነት ለመናገር በቅርብ ጊዜ ተቃዋሚ የነበሩ ሰዎች ድንገት የተከረበቱበትን ሁኔታ ሳይ የታዘብኩት ይህንን ነው፡፡ ብዙ ሰዎች የራሳቸውን ጥቅም ካገኙ ትግልም ነጻነትም እንደማይፈልጉ አይቻለሁ፡፡አንድ ጊዜ አብራኝ ሰራተኛ የሆነች አንድ ሴት የነገረችኝ ነገር ሁሌ ግርም ይለኛል፡፡ ልጅቷ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለስልጠና ሄዳ ሳለ የገጠማትን ነው ያወጋችኝ፡፡ ስብሰባው ቦታ አንዳንድ ያልተሟሉ ነገሮች ነበሩና ሰልጣኞቹ ጠየቁ፡፡ ይሄኔ አሰልጣኞቹ ፈረንጆች ነበሩና መላውን ሰልጣኝ ጥቁር ለምን የዚህ ዓይነት የመብት ጥያቄ ትጠይቃላችሁ ብለው እርፍ! ልክ በሚቀጥለው ቀን ተረኛዋ ቅድም የጠቀስኳት ነበረችና ዝክዝክ አድርጋ ተናገረች፡፡ ፈረንጆቹ “እዚህ ኢትዮጵያዊያን ከሌሎቹ ይለያሉ” በማለት “በቃ የጎደለው ነገር ለናንተ ይስተካከላል” ሲሉ ይህቺ ቆፍጣና ግን “ከማንም የተለየ ጥቅም አልፈልግም፤ ከፈለጋችሁ አንድ ላይ አድርጉልን” አለች፡፡ እውነተኛ ትግል ዳቦ እስኪጎርሱ ከሆነ ይደብራል፡፡ ብዙዎቹ የኛ ተቃዋሚዎች የዚህን አይነት መልክ አላቸው፡፡ ሃቀኞቹን ሳይጨምር፡፡ሌላው ኢህአዴግ ያልገባኝ ነገር የመንግስቱ መልክ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ነው…ወይስ ቶታሊታሪያን?…አንዳንድ ባህሪያቱ ወደ ቶታሊታሪያዊነት እያደላ ስለሆነ ያዋጣል ወይ የሚል ጥያቄ አለኝ፡፡ አንድ ፓርቲ፣ በአንድ አይዲዎሎጂ ላይ ተንጠለጠለ፣ በአንድ ሰው የሚመራ ማለት ነው፡፡ በሐይል የሚጠቀም፣ ኢኮኖሚው በአንድ ማዕከላዊ አገዛዝ ስር የሆነና በርሱ ቁጥጥር ስር የሆነ ማለት ነው፡፡ ታዲያ ኢህአዴግ ሃሳቡ ምንድነው?እውነት ለመናገር ኢህአዴግ እልህ መያያዝና አፈና ለቆታል ማለት አይቻልም፡፡ ግን ይህ ነገር እንደማይጠቅም ለኢህአዴግ መንገር የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም በዚህ ተመርሮ ነዋ በረሃ የገባው፡፡ እንዴት በርሱ ላይ ሲደረግ የጠላውን በሌሎች ላይ ያደርጋል!! የሰው ልጅ ነጻነት ያስፈልገዋል፡፡ ልማት ብቻ አይደለም፡፡ ያለ ነጻነት መኖር ደግሞ ከሞት አይተናነስም፡፡ በክፍሌ አቦቸር ግጥም ላሳይ መሰለኝ፡-           ሞት ይቅር ይላሉ- ሞት ቢቀር አልወድም     ከድንጋይ -ቋጥኙ-                   ከሰው ፊት አይከብድም፡፡           ማጣት ክፉ ክፉ፣            ችግር ክፉ ክፉ፣  ተብሎ ይወራል ከባርነት ቀንበር- ከሬት መች ይመራል፡፡ኢህአዴግ በተሻለ ዘመን የተሻለ ስራ መስራት የሚችል ይመስለኛል፡፡ ከዚህም በላይ የህዝቡን ስነ ልቡና ማወቅ አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ በርግጥም ህዝቡ እንኳን ዙፋን ላይ ለተንጠለጠለው መንግስትና ለራሱም ግልጽ አይመስልም፡፡…ግን አንድ ሃገር ለሚመራ መንግስት ከሁሉ በላይ ህዝቡ ምን እንደሚፈልግ ማወቅ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ያለበለዚያ መተላለፍ እንዳይመጣ እሰጋለሁ፡፡ለዚህ ሃሳብ ደጋፊ ከሆነኝ አንድ ዶክተር መምህር የነገሩኝን ገጠመኝ ባወራ ደስ ይለኛል፡፡ አንድ ፕሮጀክት የነበራቸው ሰዎች በደንብ በማያውቁት ክልል ስራ ለመስራት ሄዱ፡፡ ሄደው የሰሩት ስራ ውጤታማም ነበር፡፡ ፕሮጀክቱ የውሃ ቁፋሮ ነበረና በሚገባ ተቆፍሮ ውሃ ወጣ፡፡ ችግሩ የተከሰተው ግን በኋላ ነበር፡፡ ውሃው ለህዝቡ ሲሰጥ ህዝቡ ያንን ውሃ የማይጠጣበትን ምክንያት ተናገረ፡፡ ለካስ እዚያ ስፍራ አያት ቅድመ አያቶቻችን ተቀብረዋል ብለው ያስባሉ!...እናም ድካም፣ገንዘብ፣ሁሉ ከንቱ ቀረ፡፡ ከዚህ ይጠብቀን፡፡ ከዚያ ውጭ አሁን ያለው የልማት እንቅስቃሴ በጀ የሚያሰኝ ነው፡፡ የዐባይ ነገር ደግሞ ከሁሉ የባሰ የቤት ስራችን ነው፡፡ ይሁንና የኑሮ ውድነት አሁንም ትልቁ ጥያቄና ፈተና ነው፡፡ ያም ሆኖ በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ዳቦ ብቻ ለሰው ልጆች ጥያቄ መልስ ይሆናል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ ይልቅ ኢህአዴግ ልማትና ዴሞክራሲው ላይ ቢሰራ የበለጠ ተመራጭና በላጭ የሚያደርገው ይመስለኛል፡፡ ይህቺን ከበረሃ ያመጣትን ቆመጡን ካልተወ ግን ለኛም ለራሱም አይሆን!! ጦር ሜዳ ያልዋለ ስልጣን መያዝ የለበትም ሣይል፣ ስልጣን መስጠቱ በጥሩነት የሚታይ ነው፡፡ በጠመንጃ የተገኘ ስልጣን መልቀቅ ከባድ ነገር ነው፡፡ ይሁንና መንግስት ይህንን ማድረጉ ጥሩና የሚያስመሰግነው ነው (እንደኔ!)

Read 3077 times Last modified on Saturday, 13 October 2012 11:20

Latest from