Friday, 08 July 2022 20:34

ይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፡-

Written by 
Rate this item
(0 votes)


ይድረስ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፡-
ከሁሉም በላይ አመራርዎን በየተዋረዱ በጥብቅ ይመርምሩ

ውድ ዶክተር ዐቢይ አህመድ፤ ይህንን ደብዳቤ ወደ እርስዎ ለመጻፍ ብዙ ውጣ ውረድ ሃሳቦች ገጥመውኝ፣ ከአምሥት ጊዜ በላይ እየጀመርኩ ብእሬን አስቀምጫለሁ። በእርግጥ ይህ ጉዳይ እርስዎን ብቻ ይመለከታል ወይ ብዬ ትቼውም ነበር። ነገር ግን ወደ ላይ አንጋጥጬ ባይ ሌላ ሰው አጣሁ፡፡ ለእርስዎ መጻፍ አማራጭ የሌለው አማራጭ ሆነብኝና ልጽፍልዎት ወሰንኩ።

በተደጋጋሚ በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት፣ በኢትዮጵያ ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ ይገባኛል። የኢትዮጵያ ጠላቶች አንዴ በሃይማኖት፣ አንዴ በብሔር፣ አንዴ በጎሣ እያደረጉ ኢትዮጵያን እየዞሯት እንደሆነ ለእርስዎ መንገር ለቀባሪ ከማርዳትም ያነሠ ይሆንብኛል።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ይህቺ መከረኛ ሀገርና መከራ የማይለቀው ሕዝብ፣ በአስቸጋሪ ሰዓት በእጅዎ ላይ ወድቀዋል። እርስዎም እንደ አንድ ዜጋ አብረውን መከራ ከመቀበል ባለፈ ሁሉም ችግር በጫንቃዎት ላይ አርፏል፡፡ የነገሮችን ክብደት የሚያውቀው የተሸከመው ነው።

አንድ ሰው፤ ሰውን ይመርጣል እንጂ ሰውን አይሠራምና በመረጧቸው ተሻሚዎች ሁሉ እርስዎን ለመውቀስ እቸገራለሁ። በእርግጥ አጭር መፍትሄ ጠፍቶ በተደጋጋሚ ንጹሐን ዜጎች ሕጻናትን ጨምሮ የመገደላቸው ምስጢር ሊገለጥልኝ አልቻለም። በእርግጥ የዚህችን ሀገር መጻኢ ዕድል የተሻለ ለማድረግ እየተጉ እንደሆነ ይሰማኛል። ይሁን እንጂ የእርስዎ ማሰብና መውጣት መውረድ ብቻውን ውጤት ሊያመጣ አልቻለም። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ይህንን ስል ምንም ለውጥ አልመጣም ወይም ምንም  ሥራ አልተሠራም እያልኩ አይደለም።

በተለያዩ ቢሮዎች ዜጎችዎ የፈለጉትን አገልግሎት ባለማግኘት እየተቸገሩ ነው። በዚህም የተነሳ አገልግሎትን ሕዝቡ በገንዘብ እየገዛም ነው። ይህም ሕዝቡ የሚሠራውን በጎ ሥራ እንዳያይ አድርጎታል። ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤ ከዚህ ቀደም ርቆ መሄድ አስቸጋሪ የነበረ ሲሆን፣ አሁን ከቤት ወጥቶ ግቢ ውስጥ መዘዋወር አስቸጋሪ ወደ መሆን እየሄደ ነው። ከዚህ ቀደም ጥያቄው በነጻነት የመኖር ነበር፤ አሁን በሕይወት መኖር ራሱ ጥያቄ ውስጥ ገብቷል።

ክቡር ጠ/ሚኒስትር፤ ነገሮች መንገድ ሳይስቱ ወደ መሥመር እንዲመለሱ አሁኑኑ ቢሠራ መልካም ነው። ነገሮች እየሰፉ ሄደው ከወለጋ ወደ ሰሜን ሸዋ ጉጂንና መሠል አካባቢዎችን እያካለለ ነው። ይህ ጉዳይ የእርስዎ ብቻ ሸክም መሆኑ አብቅቶ፣ ሁሉም ከሳሽና ወቃሽ ብቻ ሳይሆን የድርሻውን የሚወጣበት መሥመር ቢበጅ እላለሁ።
ክቡር ጠ/ሚኒስትር፤ ከሁሉም በላይ አመራርዎን በየተዋረዱ በጥብቅ ይመረምሩ ዘንድ ላሳስብዎ እወዳለሁ፡፡
በመጨረሻም ዜጎች ሁሉ -…ነጋዴው፣ መምህሩ፣ ተማሪው፣ ገበሬው፣ ወታደሩ፣ ላብአደሩ፣ ሃኪሙ፣ ጋዜጠኛው ወዘተ... አገርን በማረጋጋትና ሰላም በማስፈን ረገድ የአቅሙንና የድርሻውን የሚወጣበት ምቹ ሁኔታን መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ለመጻፍ የተገደድኩት በሀገሪቱ ላይ ያንዣበበው አደጋ ክፉኛ ቢያሳስበኝ እንደሆነ ይወቁልኝ፡፡
አክባሪዎ
ዘለቀ ረዲ

Read 4107 times