Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 13 October 2012 10:54

ኪነጥበብና ዘመዶቿ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ጥዋት ተነስቶ መሮጥ ሌላ፤ የኦሎምፒክ ሩጫ ማየት ሌላዜና ከጋዜጣ ማንበብ ሌላ፤ ልብወለድ ድርሰት ማንበብ ሌላ

እንዲያው ስታስቡት፣ “ሕይወት”ን የመሰለ ብርቅ ነገር አለ? ደግሞስ፤ “ብቃት”ን የሚስተካከል ቅድስና ከወዴት ይመጣል! ... ሌላ ሦስተኛ እፁብ ድንቅ ነገር ልጨምር። መቼም፤ ከራዕይ የሚልቅ ውድ ነገር ተፈልጎ አይገኝም። ... የፅሁፌ አጀማመር እንዴት ነው? ግድ የለም አትስጉ። በማብራሪያና በትንታኔ አልጠምዳችሁም። የዲስኩርና የስብከት መግቢያ ከመሰላችሁም፣ ተረጋጉ... ወደዚያ አልገባም። ባለፈው ሳምንት የጀመርኩት ጽሑፍ ላይ አንዳንድ ነጥቦችን ለመጨመር ነበር ያሰብኩት። ግን፣ ራሱን የቻለ ጽሑፍ ቢሆን ይሻላል። የልደት ቀንና የዓመት በዓል ድግስ፤ የፕሪሚዬር ሊግ ውድድርና የልብወለድ መጽሐፍ ዝምድና እንዳላቸው ጠቅሼ አልነበር? ዛሬ ዝምድናቸውን ለማሳየት እሞክራለሁ። ዝምድናቸው፤ የጋብቻ ይሁን የቤተሰብ፤ በአያት ይሁን በአክስት፣ እርግጡን እንለያለን።

ታዲያ፣ ሃረግ እየመዘዝን፣ የዝምድና ቆጠራ ውስጥ የምንገባው፤ ምንነታቸውንና ጥቅማቸውን ለማወቅ ስለሚያግዘን ብቻ ነው። በተለይ “ኪነጥበብ ምንድነው?”፣ “ከኪነጥበብ የምናገኘው ጥቅም (አገልግሎት) ምንድነው?” የሚሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ይረዳናል። ቢሆንም ግን፤ “ሕይወት”፣ “ብቃት” እና “ራዕይ” የሚባሉትን ድንቅ ነገሮች በእንጥልጥል ባልተዋቸው ደስ ይለኛል። ወለል፣ ምሰሶና ጣሪያ እንደማለት ናቸውኮ። የኪነጥበብ ሥራዎች ውስጥ፤ የሞት ሽረት ፍጥጫ የምንመለከተውኮ አለምክንያት አይደለም። ቀልባችሁን የማረከ ማንኛውም ልብወለድ ድርሰት ወይም ፊልም ካለ አስታውሱ። ሦስት ነገሮችን ይይዛል። አንደኛ፣ በታሪኩ ውስጥ የሞት ሽረት አጣብቂኝ ውስጥ የሚገባ ገፀባሕሪ ይኖራል - ከጉዳትና ከሞት ያመልጣል ወይስ አያመልጥም? ሁለተኛ፤ የፍቅርም ሆነ የቢዝነስ አንዳች ትልቅ አላማ (ራዕይ) የያዘ ገፀባህርይ ይኖራል - ይሳካለታል ወይስ አይሳካለትም? ሦስተኛ፤ አንዳች ድንቅ ብቃት የሚያዳብር ገፀባሕርይ ይኖራል - ለስኬት የሚያበቃ ችሎታ (አቅም) አለው ወይስ የለውም? ተመስጠንና ተማርከን የምናነባቸው ልብወለድ ታሪኮች ሁሉ፤ በእነዚህ ሦስት ጥያቄዎች ላይ የሚያጠነጥኑ መሆናቸው የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም። የሰው ልጅ ሲባል፤ ሁለመናው ከሦስቱ ነገሮች የተዋቀረ ነው - ሕይወት፣ ብቃት እና ራዕይ። በቃ! ከእነዚህ ውጭ፣ ሌላ ሌላው ነገር ሁሉ...  ሃተታና ዝርዝር ነው። ሃተታና ዝርዝር ውስጥ፤ ብዙ ብዙ ቁምነገሮች መኖራቸው አይካድም። ግን ያው... ሃተታና ዝርዝር ናቸው። “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” ይባል የለ? በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ፤ “ለህይወት፣ ለብቃትና ለራዕይ” የማይበጅ ማናቸውም ነገር፣ “እንቶፈንቶ” ነው። “ሕይወት፣ ብቃትና ራዕይ” ግን... የሰው ልጅ ዋና “ንጥረነገሮች” ናቸዋ።እንዴት ብለን ብንጠይቅ... ፤ መልስ ለማግኘት ትንታኔና ማብራሪያ፣ መረጃና ማስረጃ መደርደር ይኖርብናል። እውቀት የምናገኘው በዚህ መንገድ ብቻ ነዋ። ለዛሬ ግን፤ አንገባበትም ተባብለናል። ለነገሩ፤ ተንትነንና አውቀን ብንጨርስ እንኳ፤ በቂ አይደለም። ለአመታት ተምረን፣ በተደጋጋሚ ተመርቀን፣ እውቀት አካብተን ስናበቃ፣... ኑሮና ሥራ ላይ ስንዝር መንቀሳቀስ የሚያቅተን ለምን ሆነና! መራመድ ሳንጀምር ገና ስናስበው የሚደክመን፤ በራስ የመተማመን ስሜት ከውስጣችን ተንጠፍጥፎ የሚያልቀው ለምንድነው? እውቀታችን ነፍስ ዘርቶ የሕይወት ኃይል እንዲሆነን አላደረግነውማ። 
የሕይወት ኃይል = እውቀት + መንፈስ እውቀታችን፤ ከመንፈሳችን ጋር ካልተዋሃደ፤ የስሜታችንን ቅኝት ማስተካከል አንችልም። እውቀታችንና መንፈሳችን ለየቅል ሆነዋል ማለት ነው። ሕይወት እጅግ ብርቅ፤ ብቃትም እጅግ ቅዱስ፣ ራዕይም እጅግ ውድ እንደሆኑ ብናውቅ እንኳ፤ በእለት ተእለት ኑሯችን ውስጥ ግን፤ ብዙም ቦታ አንሰጣቸውም። በየእለቱና በየደቂቃው ለብርቅዬዋ ሕይወታችን ቅድሚያ የምንሰጥ ቢሆን ኖሮ፤ በማይረባ ነገር እየተጨቃጨቅን ጊዜያችንን ስናቃጥል አንውልም ነበር። አሁን ግን እንውልበታለን፤ ሕይወታችንንና ጤናችንን እያቃጠልን። ጭቅጭቁ ካለፈ በኋላም ሌሊቱን ጭምር ከአእምሯችን አይወጣም፤ “እንደዚያ ይናገራኛል እንዴ? እንዲህና እንዲያ ብዬ ብመልስለት ኖሮ...” በምናባችን የንትርክ ድራማ ፈጥረን ስንንገበገብ፤ ጨጓራችን ይላጣል። በትርኪምርኪ ጉዳይ ንዴታችን እየጦፈ የደም ግፊታችን ይገነፍላል። በተራ ሽርፍራፊ ጣጣዎች እየተብሰለሰልን፣ ግራ ቀኝ ሳናስተውል፤ ከመኪናው ፊት ዘው ብለን ሕይወታችንን ለአደጋና ለጉዳት እናጋልጣለን። በዝባዝንኬ ውስጥ ራሳችንን እየዘፈቅን፤ ከትምህርታችንና ከሙያችን ተዘናግተን ብቃታችንን እንሸረሽራለን። በማይመለከተን የሰዎች የግል ሕይወት ውስጥ ገብተን ስንፈተፍትና ስናቦካ፤ የራሳችንን ሥራና እቅድ እየረሳን፣ የሩቁ ራዕያችንና አላማችን አስታዋሽ አጥቶ ሲሻግት እናያለን። በዚህም ምክንያት፤ “ሕይወት ትርጉም የለሽ ሆነብኝ” የሚል ጨለማ መንፈስ ይውጠናል። ሕይወትን፣ ብቃትንና ራዕይን ወደ ጎን ገፍተን፤ በእንቶ ፈንቶ ከተጠመድን በኋላ... የሕይወት ጣዕም ሲጠፋብን፤ ከብቃታችን የምናገኘው የማንነት ኩራት ሲርቀን፤ የራዕይ ተስፋ ከውስጣችን ሲሞት... ሰው የመሆን ትርጉምም እልም ብሎ ይከስማል። መንፈሳችን ተሰባብሮ ድቅቅ ይላል። ቅድም እንደጠቀስኩት፤ ከሦስቱ ድንቅ ነገሮች ውጭ፤ ሌላው ሁሉ ከንቱ ነው። እንግዲህ የመጀመሪያው መፍትሄ፤ እውቀት ነው። ከእውቀት ብርሃን እናገኛለን። ግን በቂ አይደለም። የተሰበረውና የደካከመው መንፈሳችንን የሚጠግንና የሚያድስ ተጨማሪ መፍትሄ ያስፈልገናል። ይሄ ነው የሁሉም ሰው መንፈሳዊ ጥማት! እና ታዲያ ምን ተሻለ? “መንፈሳዊ ጥማታችንን የሚያረካ ሁነኛ መፍትሄ፤ ኪነጥበብ ነው” ለማለት እየተንደረደርኩ እንደሆነ ከገመታችሁ... ይሁንላችሁ። ግን፣ ሌሎች መንፈሳዊ ምግቦችም አሉ - ለምሳሌ የልደት ቀን ማክበር፤ የዓመት በዓል ድግስ፤ እንዲሁም ስፖርታዊ ውድድሮችን መከታተል። ኪነጥበብ፤ ከእነዚህ የሚለየው፤ ሁሉንም በአንድነት በመጠቅለል፤ መንፈስን የማደስ ትልቅ ኃይል የያዘ መሆኑ ነው። ኃያልነቱን ብቻ ሳይሆን፤ የመንፈሳዊ አገልግሎቱ ትልቅነት በጨረፍታ ለማየት ከፈለጋችሁ፤ አንድ የተለመደ ፍንጭ ልስጣችሁ?   
ሕመም፣ ጉዳት፣ እንቅፋት የህይወት ብርቅነት፤ የብቃት ቅዱስነት፤ የራዕይ ውድነት.... ለወትሮው ቸል ብንላቸውም፤ አንዳንዴ ግን ልባችን ድረስ ጠልቀው፣ መላ ሰውነታችን ውስጥ ተሰራጭተው ስሜታችንን ይቆጣጠሩታል። ግን አንዳንዴ ብቻ ነው። የሕይወትን ብርቅነት (ለምሳሌ የጤንነትና የሰላም ትልቅነት) በቲዎሪ ብቻ ሳይሆን፤ በእውን የሚጨበጥ የሚዳሰስ ሆኖ ይታየናል - በሕመም ስንጠቃ ወይም በጦርነት ስንታመስ። ህይወታችን ብርቅ መሆኗን ዘንግተን እንቆይና፤ ጤናችንና ሰላማችን ሲቃወስ፤ ወይም የጥፋት አደጋና የሞት ስጋት ሲደቀንብን ፤ ያኔ ... ሕይወት ምንኛ ብርቅ እንደሆነች ከላይ እስከ ታች ከምር ይሰማናል። የእውቀትና የሙያ ብቃት ጎልቶ የሚታየንስ መቼ ነው? በአንዳች ጉዳት ብቃት ጎድሎን፤ መንቀሳቀስና መስራት ሲያቅተን ነዋ። ብቃትን ማዳበር፣ የረዥም ጊዜ ጥረትን ስለሚጠይቅ፤ አንዳንዴ የብቃትን ቅዱስነት ቸል እንል ይሆናል። በስንፍና ሳናጠና እየተኛን ፈተናው ሲከብደን፣ በእንዝላልነት ሳንለማመድ ከርመን ስራው ሲደነጋገርብን፣ በአጠቃላይ ብቃት አጥተን አቅመቢስነት ሲያንዣብብን ግን... በጣሙን ይቆጨናል። ያኔ፣ የብቃት ታላቅነት ገዝፎ ይታየናል። ራዕያችንስ? በአንድ ቀን፣ በአንድ አመት እውን ልናደርገው ስለማንችል፤ ገና ሩቅ ከመሆኑ የተነሳ፤ አንዳንዴ ራዕያችን ደብዘዝ ብሎ ቢታየን አይገርምም። ከአሁኑ ኑሮአችን ጋር ተላምደን፣ የሩቅ ግባችንን ቸል እንለው ይሆናል። ነገር ግን፤ በጉዟችን ላይ ያልተጠበቁ እንቅፋቶችና ፈተናዎች ሲደቀኑብን፤ ራዕያችን ያሳሳናል፤ እፁብ ድንቅነቱ እየታየን ያንገበግበናል።ታዲያ... የሕይወትን ብርቅነት፣ የብቃትን ቅዱስነት፣ የራዕይን ውድነት ለመገንዘብ፤ ...የግድ አደጋ ላይ መውደቅ አለብን? የግድ መታመም፣ መጎዳትና መደናቀፍ ይኖርብናል? በጭራሽ! (የአስተዋይነትና የእውቀት ክብር ጎልቶ እንዲታየን፤ ነፈዝና ቅል ራስ መሆን የለብንም።) እንዲያውም ህመም፣ ጉዳት እና እንቅፋት ሲደጋገም፤ ጭርሱን መንፈሳችን ይጨልማል። ይህን መቋቋም ካልቻልን፤ የሕይወት ጣዕም ይጠፋብንና እንደ እሬት ይመረናል፤ የብቃትን አለኝታነት እንረሳና በአቅመቢስነት እንኮራመታለን፣ የራዕይን አጓጊነት እንዘነጋና፣ “ሰው ከንቱ” ብለን ተስፋ እንቆርጣለን። እዚህ ላይ ነው የኪነጥበብ መንፈሳዊ ፈውስ ብቅ የሚለው። የጥበብን መንፈሳዊነት በሌላ አቅጣጫ እንደገና ለማየት ከፈለግን፤ ኦሎምፒክንና ፕሪሚዬር ሊግን ማንሳት እንችላለን። ስፖርት መስራትና የስፖርት ውድድር መከታተል ለየቅል መሆናቸው አከራካሪ አይመስለኝም - የአንደኛው አገልግሎት ለኑሮ ነው፤ የሌላኛው አገልግሎት ደግሞ ለመንፈስ ነው። ስፖርት የምንሰራበት አላማ ግልፅ ነው። ድሮ ድሮ “የአካል ማጎልመሻ” ይባል አልነበር! አካልን ለማዳበር፣ ስፖርት እንሰራለን። ስፖርት መስራት ያስደስታል፤ አካልን ያዳብራል እንላለን። የስፖርት ውድድሮችን ስንከታተልስ? አገልግሎቱ ምንድነው? ድንቅ ብቃት በማየት መንፈሳችንን ለማደስ አይደለምን? እስቲ የልደት ቀንንና የዓመት በዓል ድግስንም ጨምረን በአጭሩ እንቃኛቸው።
ዋናውን ነገር ለይቶ ማጉላትየልደት ቀን፣ የጋብቻ ቀን፣ የፍቅር ቀን፤ የሽርሽር ቀን ... የአንድ ቀን ሽርጉድ ምን ያደርግልናል? ህይወትና ተፈጥሮ፣ ቤተሰብና ፍቅር የአንድ ቀን ጉዳይ እንዳልሆኑ ጠፍቶን ነው? አይጠፋንም። ነገር ግን  የህይወትንና የፍቅርን ጣፋጭነት፤ የአለምንና የተፈጥሮን ውበት የምናጣጥምበት ፋታ ያስፈልገናል ። የእለት ተእለት ጥቃቅን ጣጣዎች ገለል አድርገን፤ ዋናውን ነገር አጥርተንና አጉልተን ለማየት እድል ይሰጠናል። ከሕይወት በላይ የምናከብረው፣ ከሕይወት በፊት የምናስቀድመው ምን አለ? ምንም ሊኖር አይገባም። እናም ትርኪሚርኪውንና ትልቁን ነገር ቀላቅለን በአንድ አይን በብዥታ ከማየት ተላቅቀን፣ የትልቁን ነገር (የሕይወትን) ብርቅነት ለይተንና አንጥረን፣ አግዝፈንና አጉልተን ስንመለከት መንፈሳችን ይታደሳል። ከሦስቱ የኪነጥበብ መሰረታዊ ባሕርያት መካከልም፤ ዋና ዋና ነገሮችን አንጥሮና አጉልቶ የማውጣት ባሕርይ አንዱ ነው (Selection and Magnification of the Important)
አለምን እንደ አዲስ ማሳመርየአመት በዓል የአንድ ቀን ርችትና ፈንጠዚያ፣ ዝነጣና የተንበሸበሸ ድግስ ምን ይጠቅመናል? ከእለት ተእለት ህይወታችን የተለየ ሳሎኑ ተብረቅርቆ፤ ጓዳው ተሟልቶ፤ በልብስ አምሮ ተውቦ ብርችንችን ያለ የበዓል ድግስ ማዘጋጀት ፋይዳው ምንድነው? ሁሌም ፋሲካ የለም እንደሚባለው፤ ኑሮ የአንድ ቀን እንዳልሆነ ስለማናውቅ ነው? እናውቃለን። ነገር ግን፤ በውጣ ወረድ ከተተበተበው የዛሬ ህይወታችን ለአፍታ አረፍ ብለን፤ ወደፊት የምንመኘውን የተትረፈረፈ የብልፅግናና የደስታ ህይወት፤ ዛሬውኑ በእውን ልናጣጥመው እንጓጓለን። ራዕይን አጉልቶ የማየት የመንፈስ ረሃብ አለብን። የሩቅ ራዕያችንን በጨረፍታ ለአፍታ ያህል፣ ዛሬውኑ በእውን ስናጣጥም መንፈሳችን ይነቃቃል። አለበለዚያ የችግር ኑሮ ይለመዳል፤ የዛሬ ኑሯችን “የእድሜ ልክ ኖርማል ኑሮ” መስሎ ይታየናል። ለብዙ አመታት እስር ቤት ተቆልፎባቸው የቆዩ በርካታ ሰዎች፤ ከእስር ሲወጡ የነፃነት ኑሮ አስቸጋሪ የሚሆንባቸውም በዚሁ ምክንያት ነው። የሚፈልጉትን ምግብ መምረጥ፤ ባሻቸው ሰዓት መተኛትና መነሳት፤ ሌላው ይቅርና ማንንም ሳያስፈቅዱ ወደ መታጠቢያ ቤት መሄድ፤ ከባድ ሸክም ይሆንባቸዋል። የእስር ቤት ኑሮ “ኖርማል” ሆኖባቸዋል፤ ከመንፈሳቸው ጋር ተዋህዷል። አስቸጋሪ ኑሮ ለረዥም ጊዜ እለት በእለት ሲደጋገምም፤ ከመንፈሳችን ጋር ተዋህዶ የአእምሯችንን ቅኝት ያጣምምብናል። ሌላ የተሻለ ህይወትን ማለም ራዕይ መያዝ፤ ለተሻለ ህይወት እድል ሲገኝም የመሞከርና የመጣጣር ዝንባሌያችን ይሞታል። በአጭሩ ራዕያችን ይሞታል። ራዕይ የሞተ እለት፤ እንደ ሰው ሳይሆን እንደእንስሳ ይሆናል - ህይወታችን። የአመት በዓል ድግስ፤ ይህንን ፅልመት ለማጥፋትና፤ ወደፊት የምንመኘውን የብልፅግናና የደስታ ሕይወት ለአንድ ቀን በጨረፍታ እንድናጣጥም፤ በዚህም ራዕያችን ጎልቶ እንዲታየንና መንፈሳችን እንዲታደስ ያደርጋል። ከኪነጥበብ ሦስት ባሕርያት መካከል አንዱ፤ በራዕይ አለምን እንደ አዲስ መፍጠር ወይም ማሳመር ነው (Visionary Recreation of Reality)የሚጨበጥ የሚዳሰስ ማድረግየዛሬዋን ሕይወት አጉልተን ለማየትና ለማጣጣም የልደት ቀንን ካከበርን፤ የወደፊት ራዕያችንን ለማጉላትና ለአፍታ ለማጣጣም የአመት በዓል ድግስን ካዘጋጀን.... ከሁለቱ መሃል አንድ ሌላ ነገር አልጎደለም? የዛሬ ሕይወታችን አለ፤ የወደፊት ራዕያችን አለ። ሁለቱን የሚያገናኝ ድልድይ አያስፈልግም? መቼም፤ ከዛሬ ሕይወታችን ተነስተን የሩቁን ራዕይ እውን የምናደርግበት ደረጃ ላይ መድረስ የምንችለው እንዴት ነው? የመድረስ ብቃት አለን? ይሄውና! ሕይወትንና ራዕይን የሚያገናኝልን ድልድይ... “ብቃት” ነው። የብቃት ቅዱስነት ጎልቶ እንዲታየንና መንፈሳችን እንዲታደስ መፈለግ፤ የጤናማ ሰው ባህርይ ነው።  የስፖርት ውድድሮች አገልግሎትም ይህንን መንፈሳዊ ጥማት ማርካት ነው (ብቃትን በተጨባጭ ማሳየት... በአንዳች መንገድ ብቃትን የተላበሱ ሰዎችን ማሳየት)። ሩጫ ብቃትን ወይም የእግር ኳስ ችሎታን ስናስብ፤ የሰዎች ምስል ድቅን አይልብንም? ሃይሌና ቀነኒሳ፤ ጥሩነሽና ቦልት፤ ሜሲ እና ሮናልዶ... ተጨባጭ የብቃት ተምሳሌቶች ናቸው። በነገራችን ላይ፤ የኪነጥበብ ሦስተኛው ባሕርይ፤ የሚዳሰስና የሚጨበጥ አድርጎ ማሳየት ነው (Concretization)። ኪነጥበብ፤ ስለ ብልህነትና ክህሎት፣ ስለ ቅንነትና ፅናት፤ ስለ ወኔና ፍትህ... በትንታኔ ከመንገር ይልቅ፤ በብልህነትና በሙያ አስደናቂ ደረጃ ላይ የደረሱ ሰዎችን (ገፀ ባህያትን) ቀርፆ ያሳየናል። የቅንነትና የወኔ ድርጊቶችን፣ የፅናትና የፍትህ ውሳኔዎችን በተጨባጭ ያሳየናል።

Read 3615 times Last modified on Saturday, 13 October 2012 11:31