Sunday, 10 July 2022 19:15

መንግስት ለዘር ተኮር ጭፍጨፋዎች የመጨረሻውን መፍትሔ እንዲያበጅ ተቃዋሚዎች አሳሰቡ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(2 votes)

 • የኦሮሞ ህዝብ ከተጠቁ ወገኖች ጎን በመቆም ግድያውን እንዲያወግዝ አብን ጥሪ አቀረበ
                                           
           በተጠና እቅድና ቅንጅት በወለጋ ለሚፈፀሙ ብሔር ተኮር ጭፍጨፋዎችና በዘር ማጥፋት ወንጀሎች መንግስት ትኩረት ሰጥቶ የመጨረሻውን መፍትሄ እንዲያበጅ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሳሰቡ፡፡
የተቀናጀ ተከታታይና ስልታዊ የዘር ማጥፋት ወንጀል በመፈፀምና በማስፈፀም የአማራን ህዝብ ማሸማቀቅ፣ አንገቱን ማስደፋትና ፖለቲካዊ ድል ማግኘት አይቻልም ያለው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)፤ በወለጋ በአማራ ህዝብ ላይ  የሚፈፀመው ጭፍጨፋ በመገናኛ ብዙኃን ጭምር በፕሮፓጋንዳ የታገዘ ነው ብሏል- ግድያውን ባወገዘበት መግለጫው።፡፡
የዘር ፍጅት ፖለቲካ አራማጁና ሽብርተኛው የኦነግ ሸኔ ሠራዊት ከይፋዊና ህቡዕ አጋሮቹ ጋር በመተባበር በአማራ ህዝብ ላይ እየፈፀሙ ያሉትን የዘር ማጥፋት ወንጀል አጠናክረው እንደቀጠሉበት የጠቆመው አብን፤ በአማራ ህዝብ ላይ የተደገሰው ሠፊ ተከታታይና ስልታዊ የዘር ማጥፋት ወንጀል፣ በአጋጣሚና በደም ፍላት እየተፈፀመ ያለ ድንገተኛ ክስተት ሳይሆን፣ ለበርካታ አስርት ዓመታት የታቀደ፣ በተለያየ ቦታና ጊዜም ሰርቶ ማሳያዎች ሲከወኑበት የቆየ ግዙፍ ፕሮጀክት ነው ብሏል፡፡
ይህን የዘር ፍጅት በዘላቂነት ለማስቆም የህገ መንግስትና የትርክት ለውጥ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን  የገለጸው ፓርቲው፤ ህዝብም ጉዳዩን በጥንቃቄና በትዕግስት በመመልከት፣  ለአመጽ ብጥብጥና የበቀል እርምጃ ጥሪ ከሚያደርጉ አካላት ራሱን እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርቧል፡፡
መላው የኦሮሞ ህዝብ፣ የኦሮሞ ወጣቶችና ሃገር ወዳዶች በንፁሃን አማሮች ላይ የተፈፀመውን ጭፍጨፋ በግልፅ እንዲያወግዙና ከተጠቁት ወገኖች ጎን እንዲቆሙ ጥሪ ያቀረበው አብን፤ የምስራቅ፣ ምዕራብና ቄለም ወለጋ ዞኖች ላልተወሰነ ጊዜ  በፌደራሉ መንግስት እንዲተዳደሩ፣ በወለጋ የተፈጸመው ጭፍጨፋ በልዩ አቃቢ ህግ እንዲመረመር፤ የወንጀሉ ፈፃሚዎች ተጣርተው ለህግ እንዲቀርቡ እንዲሁም በቀጣይ ለጥቃት ተጋላጭ ሊሆኑ በሚችሉ አካባቢዎች ቅድመ መከላከል ስራዎች እንዲሰሩ እንዲሁም ዜጎች ተደራጅተው ራሳቸውን ከጥቃት እንዲከላከሉ የሚያስችሉ ተግባራት እንዲከናወኑም ጠይቋል።
መንግስት የህግ የበላይነትን በማስከበር ዜጎችን ከጥቃት የመከላከል ሃላፊነቱን በአግባቡ ባለመወጣቱ በንፁሃን ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች መደጋገማቸውን የገለጸው የኢትዮጵያ ዜጎች  ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) በበኩሉ፤ መንግስት በተለይ በወለጋ አካባቢ ዘላቂ መፍትሔ በሚፈጠርበት አማራጭ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በአስቸኳይ እንዲወያይና የጊዜ ገደብ በማስቀመጥ፣ የተቀናጀና ስር ነቀል የሆነ  የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቂያ የመፍትሄ እርምጃዎች እንዲወሰድ አሳስቧል።
እናት ፓርቲ፣ መኢአድና ኢህአፓ በጋራ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ “ጨፍጫፊው የኦነግ ሸኔ ቡድን ከኦሮሚያ ክልል በተጨማሪ ከአዋሳኝ ክልሎች በዋናነት በአማራ፣ በቤንሻንጉል፣ በጋምቤላና ሲዳማ ክልሎች እየተንቀሳቀሰ፣ የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ አስተጓጉሏል፤ ንፁሃንን በአሰቃቂ ሁኔታ ገድሏል፣ እየገደለም ነው” ብለዋል።
ፓርቲዎቹ በተደጋጋሚ በአማራ ህዝብ ላይ የሚፈጸምን ዘር ተኮር ግድያ ባወገዙበት በዚህ መግለጫቸው፤ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ድርጊቱን እንዲያወግዙና ጥቃቱ በአለማቀፍ ገለልተኛ አካል እንዲጣራ ግፊት እንዲያደርጉ፣ በወለጋ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ፣ ለጥቃት የተጋለጠው ህዝብ እንዲደራጅና ራሱን መከላከልይችል ዘንድ እንዲታጠቅ፣ ከመንግስት አስተዳደር አካላት ጀምሮ በድርጊቱ ተሳታፊ የሆኑ ሁሉ በህግ እንዲጠየቁ አሳስበዋል። የሃይማኖት አባቶች፣ የሃገር ሽማግሌዎች፣ የሲቪክ ማህበራትና ማህበራዊ አንቂዎች ድርጊቱን “የዘር ፍጅት” ብለው በመጥራት በግልጽ እንዲያወግዙ እንዲሁም ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሰኞ ሐምሌ 4 ቀን 2014 ዓ.ም ጥቁር ልብስ በመልበስ ሃዘናቸውን እንዲገልጹ ጥሪ አቅርበዋል።
ከትናንት በስቲያ ሃሙስ በፓርላማ ተገኝነተው በወቅታዊ ጉዳች ላይ ለተነሱ ጠንካራ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ የሰጡት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህድ፤ መንግስት የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ ዋነኛ ሃላፊነቱን አልተወጣም በሚል የሚሰነዘረውን ትችቶች ስህተት ነው ሲሉ ውድቅ አድርገዋል- የመከላከያ አባላትና የፖሊስ ሃይል የዜጎችን ህይወት ለመታደግ በየጊዜው በተለያዩ አካባቢዎች መስዋዕትነት እከፈሉ እንደሚገኝ በመግለጽ።  
ሸኔም ሆነ ሌሎች የንፁሃንን ደም በከንቱ የሚያፈሱ የሽብር ቡድኖችን በጋራ ሆነን ከታገልናቸው መጥፋታው አይቀርም ብለዋል፤ ጠ/ሚኒስትሩ።

Read 9820 times