Sunday, 10 July 2022 19:16

“በኢትዮጵያ የመኖር መብት የከፋ አደጋ ውስጥ ወድቋል”

Written by  መታሰቢያ ካሳዬ
Rate this item
(2 votes)

  • በምዕራብ ወለጋ ሴቶች፣ ህጻናትና የአዕምሮ ህሙማንን ጨምሮ በርካታ የአማራ ተወላጆች በግፍ ተጨፍጭፈዋል
   • የትግራይ ሃይሎች በጦርነቱ የማረኳቸው የመከላከያ ሠራዊት አባላት ላይ ስቃይ ፈጽመዋል
                             
          በኢትዮጵያ የመኖር መብት እጅግ የከፋ አደጋ ውስጥ መውደቁንና በርካታ ዜጎች በመንግስት የፀጥታ አካላትና በታጣቂ ሃይሎች መገደላቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ ኮሚሽኑ በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነውንና ከሰኔ ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ሰኔ 2014 ዓ.ም ድረስ ባለው 12 ወራት ውስጥ በአገሪቱ ተፈፀሙ የተባሉ የመብት ጥሰቶችን የሚቃኝ ዓመታዊ ሪፖርት በትናትናው ዕለት ይፋ አድርጓል፡፡
አገሪቱ እጅግ አሳሳቢ በሆነ የሰብአዊ መብት አያያዝ ቀውስ ውስጥ መሆኗን ያመለከተው የኮሚሽኑ ሪፖርት፤ ከሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ ህጻናት፣ ሴቶችና የአዕምሮ ህሙማንን ጨምሮ 749 ሲቪል ሰዎች መገደላቸውን ጠቁሟል፡፡ በተለይ በትግራይ ታጣቂዎች ሆን ተብሎ በተወሰዱ እርምጃዎች 349 ንፁሃን ዜጎች በግፍ  መጨፍጨፋቸውን አመልክቷል፡፡
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተደረጉ ጦርነቶች ሆን ብለው በተወሰዱ እርምጃዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከፍርድ ውጪ ተገድለዋል። ከዚህ በተጨማሪም ኦነግ ሸኔ በተባለውና በፓርላማው በአሸባሪነት በተፈረጀው ቡድን በርካታ ንፁሀን በግፍ መገደላቸውን ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን ጉባ ወረዳ አያሲዲ ቀበሌ፣ 20 የሚደርሱ የመከላከያ ሰራዊት  አባላት በታጣቂዎች መገደላቸውን ያመለከተው የኮሚሽኑ ሪፖርት፣ አንድ ግለሰብ ከእነህይወቱ ከአስክሬኖች ጋር በእሳት እንዲቃጠልና እንዲቀበር መደረጉን ጠቁሟል፡፡
በኮሚሽኑ ሪፖርት ላይ የተገለጸውና ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ተፈጸመ በተባለው የሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀል የትግራይ ታጣቂ ሃይሎች፣ በተማረኩ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ ፣የኤርትራ ሰራዊት የትግራይ ሃይሎች ላይ ማሰቃየትና ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ፈጽመዋል።
ኮሚሽኑ የዘፈቀደ እስርና አፈና በሚመለከት ባወጣው ሪፖርት ላይ እንደገለፀው፤ በኢትዮጵያ ባለፉት 12 ወራት ሰዎች በዘፈቀደና ያለጥፋታቸው መታሰራቸውንና ተገደው እንዲሰወሩ ተደርገዋል። በተለይም በስራ ላይ ከነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ በርካቶች ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ፣ በዘፈቀደና ያለጥፋቸው መታሰራቸውን አመልክቷል። ህወኃት የትግራይ ክልልን ለማስተዳደር ተግባራዊ ያደረገው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሰዎችን መብቶች በከፍተኛ ሁኔታ የገደበና ከኢትዮጵያ ህገ መንግስትና የወንጀል ህግ ጋር የሚጣረስ እንደነበር በሪፖርቱ ገልጿል፡፡
በአገሪቱ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ታግዶ መቆየቱን ያመለከተው የኮሚሽኑ ሪፖርት ፤ ከሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ግንት ወር 2014 ዓ.ም ድረስ ባሉት 11 ወራት 39 ጋዜጠኞች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ከእነዚህም መካከል አስራ አምስቱ በትግራይ ክልል በባለስልጣናቱ የታሰሩ መሆናቸውን አመልክቷል።
በኦሮሚያ ክልል በወለጋ ዞኖች “ኦነግ ሸኔ” የብሔር ማንነትን መሰረት በማድረግ በሚፈፀመው ጥቃት በተለያዩ ጊዜያት በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን በግፍ መጨፍጨፋቸውን ያስታወሰው ሪፖርቱ፤ የተጠቃለለ ቁጥር ገና አለመገኘቱን አስታውቋል። በተለይም በቅርቡ በምሐራብ ወለጋ ዞን በቶሌ ቀበሌና በቄለም ወለጋ የተፈፀመውን ጭፍጨፋ በተመለከተ ኮሚሽኑ ገና በቦታው ተገኝቶ መረጃዎችን አላማጣራቱንና በጥቃቱ የተገደሉ ሰዎችን ትክክለኛ ቁጥር አለማግኘቱን አመልክቷል፡፡
በተለያየ የአገሪቱ ክፍሎች መደበኛ ያልሆኑ የሰዎች የማሰሪያና የማቆያ ቦታዎች መኖራቸውን ያስታወቀው የኢሰመኮ ሪፖርት በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ በአማራ፣ በኦሮሚያና በአፋር ክልልች እንዲሁም በደቡብ ክልል በርከታ ሰዎች “ታጣቂ ሃይሎችን ደግፋችኋል፤ ለእነሱም የተለያየ እገዛ ታደርጋላችሁ” በሚል እየተያዙ መደበኛ ባልሆኑ ማቆያ ቦታዎች ውስጥ እንደሚታሰሩ ገልጿል፡፡ በአንዳንድ የማሰሪያ ቦታዎች በታሳሪዎቸ  ላይ አካላዊ ቅጣት እንደሚፈጸምና ታሳሪዎች በቂና ጥራቱን የጠበቀ ምግብ እንደማያገኙ እንዲሁም የህክምና አገልግሎት እንደማይሰጣቸው ሪፖርቱ አረጋግጧል፡፡
በአጠቃላይ ኮሚሽኑ   ባወጣው በዚሁ ሪፖርት፤ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በአፋር፣ በቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ በጋምቤላ፣ በሶማሌና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ውስጥ በተፈፀሙ ጥቃቶች በርካታ ዜጎች መገደላቸውንና ድርጊቱንም ለማስቆም  በቂ ህጋዊ እርምት እየተወሰደ አለመሆኑን አመልክቷል፡፡
ኢሠመኮ በሪፖርቱ ማጠቃለያም ፤ ከሰኔ ወር 2013 ዓ.ም እስከ ሰኔ ወር 2014 ዓ.ም ኢትዮጵያ በርካታ ፈታኝ ሁኔታዎች ያጋጠመ ሲሆን በተለይም በትግራይ ክልል የተጀመረውና  ተስፋፍቶ የቆየው ግጭት የበርካታ ዜጎችን ህይወት የቀጠፈበት ሲቪል ሰዎች ያለፍርድ የተገደሉበት፣ የዘፈቀደ እስር፣ጠለፋ፣ አስገድዶ መሰወር የጠፈፀመበት ብዙዎች አካል ጉዳተኛ የሆኑበት፣ የህዝብ መገልገያ ተቋማት  የወደሙበት፣ ሴቶች ለከፍተኛ ፆታዊ ጥቃት የጠጋለጡበት፤ አረጋውያ ህጻናትና አካል ጉዳተኞች በተለይም የአዕምሮ ህሙማን የጥቃቱ ኢላማ የተዳረግሁበት፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የህበረተሰብ ክፍል የተፈናቀለበት  ዓመት እንደነበር በዝርዝር አስቃኝቷል።
ኮሚሽኑ በማጠቃለያ ምክረ ሃሳቡም ላይ፤  እጅግ ለከፋው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ምክንያት የሆነው ግጭትና ጦርነት አስቸኳይና ዘላቂ ሰላማዊና ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲሰረው፣ በመንግስትና አገራዊ ምክክር ኮሚሽን አማካኝነት የቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶት በሀገራዊ   የፖለቲካ መፍትሄዎች አስፈላጊ በሆኑ ህገ መንግስታዊና መዋቅራዊ ማሻሻያዎች ላይ ምክክር ተግባራዊ እርምጃዎች  ሊጀመርና መወሰድ እንደሚገባቸው ገልጿል፡፡


Read 10022 times