Tuesday, 12 July 2022 00:00

የአገር ሰላምና የዜጎች ኑሮ፣ እንደ ነፍስና ስጋ ናቸው።

Written by  ዮሃንስ ሰ
Rate this item
(1 Vote)

 • አንዱ ሲበረታ፣ ሌላው ያንሰራራል። አንዱ ሲታወክ፣ ሌላው ይታመማል።
                        
             ትንሽ የሰከነ አእምሮና የተረጋጋ ኑሮ፣ ትንሽ የአገር ጸጥታና የእፎይታ አየር፣… አይናፍቃችሁም?
ትንሽ እርጋታ፣ እንደገና ተመልሶ ያረጋጋል። አገር በሰላም ከሰነበተና እፎይታ ካገኘ፣ ለዜጎች የኑሮ ተስፋ ይሆናል። የተስፋ ጭላንጭል ይፈጠራል። በዋጋ ንረት የተባባሰውን የኑሮ ምስቅልቅል የማርገብ እድል ያገኛል።
የተጎሳቆለ ኑሮ ካገገመ ደግሞ፣ ተመልሶ አገርን ለማረጋጋ ይጠቅማል። ታዲያ ትንሽ እርጋታ ለማግኘት አትመኙም?
“የማያውቁት ሀገር አይናፍቅም” ካላላችሁ በቀር፤ ለቅጽበት ያህልም ቢሆን፣ ትንሽ እፎይታ ይናፍቃል። ትንፋሽ ለመውሰድ ያህል፣ አንዳንዴ የእፎይታ አየር አያሰኛችሁም? ለአፍታ ትንፋሽ ለመሰብሰብ ያህል፣ የተረጋጋ ኑሮ በምናብ “ውል” የሚላችሁ ይመስለኛል። ግን፣ ላይላችሁም ይችላል።
ግርግር ይለመዳል። በጫጫታ፣ በኳኳታና በጋጋታ መሃል፣ አንድ ሁለት ቀን ከዋልን፣ ግርግሩ “ኖርማል” ውሎ ይሆንብናል። “መረጋጋት” የሚሉት ነገር መኖሩን ሁሉ ልንረሳ እንችላለን። ሳይታወቀን፣ከውካታና ከቱማታ፣ ከሁከትና ከጋጋታ ጋር መላመድ እንጀምራለን።
ውሎና አዳራችን፣ በግርግር ውስጥ ተነክሮ ከሰነበተና ከከረመማ፣እዚያው እንዳያስቀረን ያሰጋል። እያላወሰ የሚያሰምጥ ረግረግ፣ ከያዘ የማይለቅ ሱስ እንዳይሆንብን ያስፈራል።
ለጥቂት ሰዓታት ሞክሩት። ግርግርና ጩኸት ውስጥ ስንገባ፣ ለጊዜው ይረብሸናል። እዚያው ውስጥ ለጥቂት ደቂቃ ከቆየን በኋላ ግን፣ ከረብሻው ጋር እንላመዳለን። ኳኳታውን መስማት፣ ወከባውን ማየት እናቆማለን። ትኩረታችን እየደነዘዘ እንጂ፣ መስማት ማየታችንማ አይቀርም። ውስጣችንም ይመዘግባል። ባይታወቀንም፣ ውስጣችን ይናጣል።
ናላችን እስኪዞር እስኪደነዝዝ፣ ልባችን እስኪጠፋና ትንፋሽ እስኪያጥረን ድረስ ሁለመናችን እንደታወከ የምናውቀው፤ ድንገት ኳኳታው ፀጥ ረጭ ካለ ነው። በውካታውና በሁካታው መሃል፣ ከጣሪያ በላይ በጩኸት እየተነጋገርን እንደነበር የሚታወቀን፣ ጫጫታው ሁሉ የረገበ እንደሆነ ነው።
ድንገተኛው ጸጥታ፤ እንግዳ ነገር ይሆንብናል። እኛም ድምጻችንን እንቀንሳለን። ያለጩኸት እንደማመጣለን፤እንግባባለን።
አካባቢው ሲረጋጋ፣ እኛም እንረጋጋለን።
ሰላም ሰላምን ይወልዳል።
በተቃራኒው ደግሞ፣ ጫጫታ ሲበዛ መደማመጥ ሲጠፋ፣ ከጫጫታው በላይ ለመጮህ እንሞክራለን።
ጫጫታ፣ጩኸትን ይጋብዛል፤ መንጫጫትን ይወልዳል። ውካታና ወከባ እየተለመደ፣ሽኩቻ ወደባሰ ረብሻ፣ ሆታ ወደ ኡኡታ ይጦዛል።
አእምሮም ሆነ ንግግር ሲሳከር፣ ኑሮም ሆነ አገር ሲታወክ፤ ለጊዜው ያስጨንቃል። ሁለመናን ክፉኛ ይረብሻል። ግን፣ የሚላመዱት ነገር ነው። እዚህ ላይ ነው የክፋቱ ክፋት። ሁከት ይለመዳል።
ታዲያ፣ “ይለመዳል” ማለት፣ “ይመቻል” ማለት አይደለም። ሁከት፣ በግልፅም በስውርም፣ እርጋታንና ፀጥታን ያስመኛል። ብናውቀውም ባናውቀውም፣ ትርምስ ያስመርራል። መጥፎ መንፈስንም ያከናንባል። ቢሆንም ግን፣ ይለመዳል።
የደፈረሰ ሃሳብና የተናጋ ኑሮ፣ የተሳከረ መንፈስና የተቃወሰ አገር፣… እንደ “ኖርማል” የመለመድ ባሕርይ አላቸው።
ሁከትን ከመላመዳችን የተነሳ፣ለአፍታ ያህል የእርጋታ ኑሮን ማየት የማንችል ሆኖ ይሰማናል። ለሳምንት ያህል እፎይታን እና የሰላም አየር መመኘት፣ ከአቅም በላይ በከንቱ እንደመመኘት ሊመስል ይችላል።
ድንገት እርጋታ ቢፈጠር እንኳ፣ የእውነት አይመስልም። ግራ በመጋባት፣ ግራ ቀኝ እንመለከታን። በማመንና ባለማመን መሃል ሆነን እንጠይቃለን።
“በሰላም ነው አገር የተረጋጋው?”
“በጤና ነው ጩኸት የቀነሰው?”
“ምን የሚያስደነግጥ ጉዳይ ገጠመው?” እንላለን።
በስድብና በብሽሽቅ፣ በጭቅጭቅና በጫጫታ የተረበሸ አየር፣ በዋጋ ንረትና በኢኮኖሚ ቀውስ የተናጋ ኑሮ፣ በአመጽና በጦርነት፣ በአጸፋ እርምጃና በዘመቻ ቅብብሎሽ ፈተና በዝቶበት የታመሰ አገር፣… ጤና አይሰጥም።
ይባስ ብሎ ደግሞ ከህመም ጋር ያላምዳል። አዎ፣ ወከባውና ሁካታው ያማርራል። ነገር ግን፣ ስናዘወትራቸው አንገረምባቸውም።
ምንም አይነት ሁከት ቢፈጠር፣ “ይሄ ሊሆን አይችልም፣ ይሄ አይደረግም” ብለን አንገረምም። በእርግጥ መደንገጣችን አይቀርም። ምናልባትም ትንሽ ትንሸ ሊገርመን ይችላል እንበል።
ነገር ግን፣ ብንደነግጥና ቢገርመን፣ ለእለቱ ብቻ ነው። ለአንድ ቀን፣ ገና በአዲስነቱ፣ “ጉድ ነው” እንል ይሆናል። በማግስቱ ግን እንለምደዋለን። ሌላ አዲስ የጩኸት ሁካታ፣ ሌላ አዲስ የኳኳታና የጋጋታ ረብሻ ነገ እስኪፈጠር ድረስ፣ ከእስከ ዛሬዎቹ ጋር እንደተዋወቃለን። እንላመዳለን።
መደነቅ እየተውን ማጋነኛና ማዳነቂያ ለመፍጠር ላይ ታች እንድከም እንዴ! የሚደክሙ አሉ።
“የዘወትሮቹና ነባሮቹ ግርግሮች አልበቃ ብለው!” በሚል ስሜት፣ ከተማረርን፣ ገና ግርግርን አልተላመድንም፤ ሙሉ ለሙሉ አልተዋሐደንም ማለት ነው። ሁሉንም ባይሆን ግን፣ ብዙዎቹን ተላምደናል። አዳዲስ የሃሳብ ረብሻዎች መፈጠራቸው፣ ወደ ፊት ያስደንቀን እንደሆነ እንጃ።
“እንዲህ አይነት የሃሳብ ረብሻ፣ ይሄን የመሰለ የሃሳብ ስካር፣ እስከዛሬ የት ተደብቆብን ቆየ?” ብለው በቁጭት የሚረባረቡ ሰዎች እንደሚኖሩ ግን እርግጠኛ ነኝ።
አዲስ የሃሳብ ረብሻ ከዚህም ከዚያም ሲያገኙ፣ እፍ እፍ ብለው ለማራገብ ተፍ ተፍ ይላሉ። ለማራባት ለማዛመት የሚታትሩ ሰዎችም አሉ።
አብዛኛው ሰው ግን፣ የባሰና ተጨማሪ አበሳ የሚመጣ አይመስለውም። በእርግጥ፣ “የባሰ አታምጣ” ማለቱ አይቀርም። ቢሆን ግን፤ የረብሻ አይነቶችን ሁሉ አይቶ የተላመደ ይመስለዋል። ቢመስለው ደግሞ አይገርምም።
በጣም ከመላመዱ የተነሳ፤ የኑሮ መናጋትን ሁሉ “በየአይነቱ ደርሶብን አይተነዋል” የሚል ስሜት ይፈጠርበታል።
“ሌላ ምን አይነት አዲስ ጉስቁልና ይመጣል! ምንስ ያልተናጋ ነገር ቀረና!” ይላል ብዙ ሰው። ሌላ አዲስ መከራ ሲፈጠር፣ ለእለቱ ይገርመዋል፤ ይበረግጋል። ቢሆንም ግን፣ ከወትሮው የተለየ አዲስ ጉድ አይሆንበትም፤አይሆንባቸውም፤ ይለምዱታል።
እንደ ኑሮና እንደ ኢኮኖሚ ሁሉ፤ የአገር ሰላምና እርጋታ ላይም፤ ስጋትና ጉዳት፣ አመፅና ጥቃት እየተደጋገሙ እየተዘወተሩ በጣም ከመለማመዳችን የተነሳ፣ በወጉና በስርዓቱ መነጋገር ሁሉ ያቅተናል። ከየአቅጣጫው የምንወረውራቸው ጩኸቶች፣ የብሽሽቅ እንጂ የቁም ነገር መንፈስ ይርቃቸዋል።
ዋናው ችግርና ጉዳት ላይ ከማተኮር ይልቅ መወዛገቢያነቱ፣ የብሽሽቅ ሰበብነቱ በልጦ ይታየናል። የዛሬ ችግሮችን፤ ለነገ አዳዲስ ችግሮችን ይወልዳሉ።
አገር ድንገት የዕርጋታ አየር ከነፈሰበት ወይም ነገሮች የረገቡና የሠከኑ ከመሰሉ፣… ጥርጣሬ ሊያድርብን ይችላል።
“ምንድነው ነገሩ? ያልሰማሁት ነገር ቢኖር ነው?” ያስብላል።
ትንሽ የሰላም መንፈስና የእርጋታ ስሜት ካየን፣ የተለመደው የሕይወት እንቅስቃሴ በሙሉ ደንዝዞ የቀረ፣ ሞተሩ የተነቀለ፣ ትንፋሹ የተቋረጠ ይመስለናል። የስድብና የብሽሽቅ ጩኸት፣ የስካር ውካታ እና ረብሻ ውስጥ ለቆየ ሰው፤ የጤና ንግግርና የወዳጅ ጭውውት፣ እንደ “ጭርርርርታ” ይሆንበታል።

Read 8078 times